በፓርቲዎቻችን የጋራ ድርድር መድረክ፤የእስከዛሬው መሪር ምዕራፍ ሊዘጋ ይገባል!!

 

 

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገርና ለመደራደር የሚያስችላቸውን ውይይት መጀመራቸው ሰሞንኛ ዜና ነው፡፡ በተለይ የአገሪቱን ፓርላማ መቀመጫዎች ከአጋሮቹ ጋር መቶ በመቶ ያሸነፈው ኢሕአዴግ ሰላማዊና ሕጋዊ ከሆኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በሚደረገው ውይይትና አካሄድ ላይ የቅድመ ውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ጥሩ እና ሃላፊነቱን ከሚወጣ መንግስት የሚጠበቅ ውሳኔ ነው፡፡ ይህ ሊሆን ከቻለባቸው ምክንያቶች መካከልም አሸናፊው ሁሉንም ጠቅልሎ ተሸናፊው ደግሞ በዜሮ የሚወጣባትና በዚህ የተነሳ ግጭት ተቀስቅሶ ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለጉዳት መዳረጉ በተደጋጋሚ መታየቱ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ግምታችንን ለማጠንከርም  የቅርብ የሆነ አስረጅ እዚህ ጋር መጥቀስና ማስታወስ ይገባል።

ይህም አስረጅ ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ሙሉ ቀን ተሰይሞ የዋለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የቀትር በኋላው ፕሮግራም ነው። በወቅቱ የነበረው አጀንዳ ስለሃገሪቱ የመድበለ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ በሆነውና የምርጫ ስርአትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የሰጡት ማብራሪያ ነው።

‹‹የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት የሚባለው በዓለም ላይ ካሉት ሦስት የዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓቶች አንዱ ነው፡፡ አገራችን በመረጠችው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይህን የምርጫ ሥርዓት ላለፉት አምስት ምርጫዎች ስንጠቀም ቆይተናል፡፡ በዚህ ሥርዓት የአብዛኛው መራጭ ሕዝብ ውክልና ሲኖረው አነስተኛ ድርሻ ያለው ሕዝብ በምክር ቤት ውክልና የለውም ማለት ነው፤›› በማለት ያስረዱት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ይህንን ሥርዓት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በጥናት ሲመረምረው መቆየቱን ጭምር ለተከበረው ምክር ቤት መናገራቸው ግምታችንን አጥብቀው ከሚያጠናክሩልን አበይት ነጥቦች የመጀመሪያውና ዋነኛው ነው፡፡ ‹‹ይህንን ከግምት በማስገባት የአገራችንን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ውክልና በማረጋገጥ፣ እንዲሁም የመድበለ-ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴን በተሻለ ለማሳደግ የተዳቀለ የምርጫ ሥርዓትን በመተግበር የምክር ቤት ውክልናን ማሳደግ አለብን፤›› ሲሉ የመንግስታቸውን አቋም ማሳወቃቸውም በተመሳሳይ፡፡ በዚህ አግባብ፣ በየወቅቱ (ምርጫ በመጣ ቁጥር) እንደአሸን በፈሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን አማካኝነት ተበጣጥሰው ሜዳ ይቀሩ የነበሩ ድምጾች ዋጋ ስለሚኖራቸው ምክር ቤቱ ተገቢና ለሃገር ጠቃሚ የመሟገቻ መድረክ እንደሚሆን አያጠያይቅም።

ክቡር ጠ/ሚኒስትራችን “ሌሎች የምርጫ ሥርዓቶች” በማለት ከጠቀሷቸው የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት እና የአብላጫ ድምፅ ውክልናን ከአገራችን ነባራዊ/ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የተዳቀለ የምርጫ ሥርዓትን ዕውን ማድረግ ነው። ይህም የገዢው ፓርቲ የቤት ስራ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚዎቹንም ፖለቲካዊ ተሳትፎ የግድ የሚልና ለድርድር ልባቸውን እና ቤታቸውን ክፍት እንዲያደርጉ የሚያጠይቅ ነው።    

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በአገሪቱ ማጎልበት የመንግሥት አቅጣጫ  ሲሆን፣ በተጨማሪም በሕጋዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመደራደር ሕጎችን የማሻሻልና ካስፈለገም የሕገመንግሥት ማሻሻያዎችን በመቀበል የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት መንግስት እንደሚሠራ ሲያረጋግጡ በሃገሪቱ የፖለቲካ ስርአት ላይ ያገባናል የሚሉ ተቃዋሚዎችም እንደተለመደው በጭፍን ከመቃወምና ስልጣን ከመጋራት አባዜ ተላቀው በዚህ መንገድ ተወዳድረው ማሸነፍ ስለሚያስችላቸው ፖሊሲ ቢያስቡ ጠቃሚም ተገቢም መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሚቻለው የዴሞክራሲን መሠረታዊ መርሆዎች ማሟላት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አራቱ የዴሞክራሲ ምሰሶዎች ማለትም ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሚዲያው በሚገባ የሚናበቡበትና እርስ በርስም ቁጥጥር የሚደራረጉበት ሥርዓት እንዲኖር መንግስትና ገዢው ፓርቲ አቋም መያዛቸው ተገቢና ምናልባትም የዘገየ ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል።  እንዲህ ያለ ስርዓት ሲገነባ የሕዝብ ከፍተኛ ተሳትፎና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር በማስፈን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ስለሚቻል የብልሹ አሰራሮች ቀዳዳዎች ሁሉ ይደፈናሉ፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ተቀዳሚው አጀንዳ ይሆናል፡፡  

ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም የሚቀድም ነገር የለም፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመወያየትና ለመደራደር ሲቀመጡ፣ የድርድሩ የመጨረሻ ግብ የሕዝብ ተጠቃሚነት ሊሆን የሚገባው እንደሆነ የማያጠያይቅና ከላይ የተመለከተው እና ከጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ ተቀንጭቦ የቀረበው አስረጅ የሚያረጋግጠው ነው፡፡ አሁን  ለድርድሩ ተዘጋጅተናል ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ የድርድር ነጥቦችን ማዘጋጀታቸው እየተደመጠ ነው፡፡ በእርግጥም ለውይይትም ሆነ ለድርድር የተዘጋጀ አካል የራሱን አጀንዳ መቅረፁ ተገቢ ነው፡፡ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ዋነኛ ገጽታ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት መደራደር መቻል ሲሆን፣ ለዚህም ዝግጅት ማድረጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች የመደራደሪያ አጀንዳቸውን ሲቀርፁ ግን ከላይ በተመለከተው አግባብ ሕዝብን ማዕከል ስለማድረጋቸው ደግመው ደጋግመው ማረጋገጥ ቢኖርባቸውም ግና ድርድሩ ሳይጀመር አንዳንዶቹ ፓርቲዎች አሁንም በተለመደው የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ለመጓዝ ፍንጭ እያሳዩ  ነው።

ምንም እንኳን ፓርቲያቸው ያገዳቸው መሆኑ ቢታወቅምና የመታገዳቸው ምክንያትም የፖለቲካ ውስልትና እንደሆነ የተለያዩ ሚዲያዎች አስቀድመው የዘገቡት ቢሆንም አሁንም የሙጥኝ ያሉትን ስልጣን አላስነካ ያሉ የሚመስሉት የሰማያዊው ፓርቲ “ለቀመንበር” ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተናገሩት ለፍንጫችን የመጀመሪያው አስረጅ ነው።

“ለቀመንበሩ”፤

ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታወቀው ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል እጅግ ምስቅልቅሉ የወጣ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በመንግስት አቅም ማስተዳደር ባለመቻሉም፣ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ነች ተብሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሞተዋል፤ 10 ሺዎች የሚገመቱ ታስረዋል። ከእነዚህ ውስጥ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎችም ይገኙበታል፡፡ [• • •]    በህዝቡ ሰላማዊ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ሲጠየቁ የነበሩትም፣ ከኢህአዴግ አቅም በላይ የሆኑ ናቸው፡፡ እኛም የምንጠይቀው የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ ነው። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ችግር ከኢህአዴግ አቅም በላይ ነው

የሚል ሃሳብ ይዘው ወደውይይቱ የሚቀርቡ መሆኑን አድምቀው ገልጸዋል። እንደ አዲስ አድማስ ሀቲት ከሆነ ይህን ብቻም አይደለም ወደ ውይይቱ ይዘው የሚቀርቡት፤ እውቁ ዜመኛ “አለ ገና” እንዳለው፣ ገና ሌላም ብዙ ነገር አላቸው –

 [• • • ] የሽግግር መንግስት ሊሆን ይችላል፣ ስልጣን መጋራት ሊሆን ይችላል፣ አስቸኳይ ምርጫ ማድረግ ሊሆን ይችላል፣ የህገ መንግስት ማሻሻል ማድረግ ሊሆን ይችላል። [• • •]    ኢህአዴግ በአገሪቱ ችግሮች ላይ በግልፅ ተወያይቶ፣ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ወደፊት ሊያራምድ ይችላል ወይ በሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡

የሚለውን ሀሳብ ነው።

በእርግጥ ከየትም ይምጡ ከማንም ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ እስከሆኑ ድረስ አማራጭ የፖለቲካ ድምፆች መደመጥ አለባቸው፡፡ ለአገራቸው ዘለቄታዊ ህልውናና ለዴሞክራሲ ግንባታ ራዕይ ያላቸው ዜጎች በአደባባይ በነፃነት እንዲታዩ፣ ለሕዝብና ለአገር የሚጠቅሙ የታፈኑ ሐሳቦች ያላንዳች መሰናክል እንዲንሸራሸሩ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ የነገሠበት ሥርዓት እንዲፈጠር፣ በሕግ የበላይነት ብቻ የምትተማመን አገር እንድትኖር፣ ወዘተ አማራጭ ድምፆች የሚሰሙበት መድረክ መመቻቸት አለባቸው፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩት መሠረታዊ መብቶች በተግባር ተከብረው ዜጎች ለአገራቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ተቃዋሚዎቹ ከልብ መነሳት አለባቸው ሲባል (ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ምናልባት በድርድሩ ሊሻሻል የሚችሉባቸው እድሎች ቢኖሩም) ህገ መንግስቱ ባልተሻሻለበት አግባብ የአስቸኳይ ምርጫ እና የጥምር መንግስት ጥያቄን ወደመድረኩ ይዞ ለመቅረብ ተዘጋጅቻለሁ ማለት ህዝብን ያላስቀደመና ከላይ ከተመለከቱት መርሆዎች ውጪ ነው፡፡

ይህ ማለት ግን ህዝብን ያስቀደመ አጀንዳ ይዘው ለመቅረብ ዝግጁ የሆኑ ፓርቲዎች የሉም ማለት አይደለም። በአዲስ አድማስ ዘገባ መሰረት ለዚህ አስረጅ የሚሆነን ደግሞ የኢዴፓው ተወካይ የሰጡት አስተያየት ነው።

ከዚህ ቀደም /ሚኒስትሩ የጋራ /ቤት አባል ፓርቲዎችን ሰብስበው ቃል በገቡት መሰረት፣ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ መልካም ነው። የህግ አወጣጥ አፈፃፀም ችግሮችን በተመለከተ፣ የማያሰሩና ችግር ያለባቸው እየተባሉ በኢህአዴግም በኩል የሚገለፁ የፖለቲካ አቅጣጫዎች አሉ። እዚህ ላይ ሰፊ መግባባት የሚደረስበት ውይይት እንዲካሄድ እንሻለን፡፡ አሁንም ትልቁ የዲሞክራሲያዊ ሂደት ግዙፍ ተቋም ነው ተብሎ የሚታወቀው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ይህ ምርጫ ቦርድ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በሰጡት አቅጣጫና /ሚኒስትሩም ለወደፊት በውይይት የምናዳብረው ይሆናል ብለው ቃል በገቡት መሰረት፣ እየጠየቅናቸው ያሉት የምርጫ ህግ ክፍተቶች የሚሟሉበት ሁኔታ በዚህ ውይይት መፈጠር አለበት፡፡ የምርጫ ቦርድ አወቃቀርና የምርጫ ስርአቱ የሚሻሻልበት መንገድ መፈጠር ስላለበት፣ አንዱ የድርድር አጀንዳ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡

የሚለው የፓርቲው አቋም የመጀመሪያውና ገንቢው ሃሳብና ስለአጀንዳችን ሊጠቀስ የሚገባው የፓርቲው ዝግጁነት ነው። ሌላም አለ፤ እነሰማያዊ ህዝብን ማእከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ሊማሩበት የሚገባ አቢይ ነጥብ።

 [• • •] ሌላው ሀገሪቱ አሁን የምትተዳደርበት ስርአትና የክልል አወቃቀሮች ሂደት የፌዴራሊዝምን እውነተኛ ገፅታ የያዙ ባለመሆኑ፣ ፌደራሊዝሙ ምን መምሰል እንዳለበት መወያየት አለብን፡፡ ራሱን የቻለ የህገ መንግስት ድንጋጌዎች እንዳሉ ሆነው፣ የክልል ቅራኔ እያመጡ ያሉ የድንበር አከላለሎች በሙሉ ሊፈቱበት የሚችል፣ አንድ ወጥ የሆነ መላ ሊዘየድ ይገባል። •••• የተቃዋሞ ጎራው በራሱ አንድ እንደ /ቤት ያለ አካል መስርቶ፣ ህዝብን ማንቃት ይኖርበታል። የራሱን አቅጣጫዎች ጥርት አድርጎ ይዞ መቅረብ ስላለበትም፣ ይሄን የተቃውሞ ጎራው ቢያስብበት ጥሩ ነው፡፡ ከድርድሩና ውይይቱ የምንጠብቀው ውጤት የዴሞክራሲ ተቋማትን መጎልበትና ነፃና ገለልተኛ ሆነው ህዝብን ማገልገልን ነው፡፡ ህብረተሰቡም ሆነ መንግስት አሊያም የተቃውሞው ጎራ ከፅንፈኝነት አመለካከት ይልቅ የሠከነ ውይይት አድርጎ፣ ስልጣን በሠላም የሚሸጋገርበትን መንገድ መፍጠር ለሃገሪቱ ትልቅ ጥቅም ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ እኛ ከዚህ ድርድር እንዲመጣ የምንፈልገው፣ ህብረተሰቡን በነፃነትና ገለልተኝነት የሚያገለግሉ የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማት እንዲፈጠሩ ነው፡፡

ሰላማዊው የፖለቲካ ፉክክር  ልክ እንደኢዴፓ ከላይ በተመለከተው መልኩ በፍትሐዊነት ሲከናወን ዴሞክራሲ የምር ሥርዓት ይሆናል፡፡ ዴሞክራሲ ልክ እንደሰማያዊው ተወካይ አስተሳሰብ ሲስተናገድ ደግሞ ጥፋት ይሆናል። ከላይ የተመለከተው የኢዴፓ አቋም እና ዝግጁነት የሕግ የበላይነትን በትክክል ተቀብሎ ለማስፈን የሚተጋ ፓርቲ መሆኑን ሲያሳይ፤ በአንጻሩ የሰማያዊው ደግሞ በቂምና በጥላቻ አረንቋ ውስጥ የሚዳክረውን የአገሪቱ ፖለቲካ ወደባሰ አዘቅት ለመጨመር የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑን የሚያረጋግጥ እና ድርድሩን ለማጨንገፍ የታለመ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ፖለቲካው አሁን ካለበት አሳዛኝና አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ ወጥቶ ቂምና ጥላቻ እንዲወገዱ፣ የፉክክር ስሜቱና ግለቱ ከሕገወጥነትና ከፅንፈኝነት ተላቆ የሕዝብ ፈቃድ የሚፈጸምበት እንዲሆን መድረኩ አማራጭ ሐሳብ ያላቸውን ያላንዳች ገደብ ማስተናገድ ባለበት ልክ ሌላ ሴራ ካሴሩት ጋር ደግሞ ውሳኔው የገዢው ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እና ህዝብን ያስቀደሙ ተደራዳሪ ፓርቲዎች በሙሉ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከፅንፈኝነትና ከጭፍን ጥላቻ ህዝቡም ሆነ ሃገሪቱ ያተረፉት ነገር እንደሌለ በተደጋጋሚ ታይተዋልና ይብቃችሁ ሊባሉ ይገባል፡፡ ዴሞክራሲም በዚህ አሳዛኝ መንገድ ተገንብቶ አያውቅም፡፡ የእስካሁኑን አሳዛኝ ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ መውሰድ ይጀመር፡፡ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ሳይቀሩ በኃላፊነት ስሜት በመነሳት ለሕዝብ ፈቃድ የሚገዛ ዓውድ እንዲፈጠር መትጋት አለባቸው፡፡

ዴሞክራሲ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገነባ ሥርዓት እንደመሆኑ መጠን፣ በትንሹም ቢሆን የተቃና ጉዞ  እንዲኖር መስዕዋትነት መክፈል እንጂ በውሃ ቀጠነ አተካሮ አያስፈልገንም፡፡ ተቃዋሚዎቹ ከገዥው ፓርቲ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነትም ሆነ እርስ በርሳቸው ከመጠላለፍ አባዜ በመላቀቅ ለሒደቱ ማማር የበኩላቸውን ያደርጉ ዘንድ እንጂ ዛሬም እንደተለመደው ገዢው ፓርቲን በማጣጣል ከህዝብ አተርፋለሁ ብሎ ማሰብ ጊዜውን አለመረዳት፤ ይልቁንም ሊመሩት የሚከጅሉትን ህዝብ አለማወቅ ይሆናል፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድሩ ወቅት ከይስሙላና ከታይታ አቀራረቦች መታቀብ አለባቸው፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት መደራደር ልዩነቶችን እያጋነኑ በተራ ምክንያቶች ከመፋረስ ያድናል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ቂሞችን፣ ጥላቻዎችን፣ በክፉ መፈላለግና ሌሎች አላስፈላጊ ድርጊቶችን አስወግዶ በቀና መንፈስ መነጋገር ሕዝብን ማክበር ነው፡፡   

የተበላባቸው ድክመቶችን አስወግዶ ሕዝብ በሚፈልገው ቁመና ላይ መገኘትና አማራጭ ድምፅ መሆን የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ ያለበለዚያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራን ለሚችሉት መተው ነው፡፡ ይህ ሕዝብ የሚፈልገው ብቁ አመራርን ብቻ ነው፡፡ በተለይ በግራም ሆነ በቀኝ የተሠለፉ የፖለቲካ ኃይሎች ይህ ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ አለባቸው፡፡ ይህ የተከበረ ሕዝብ የሚፈልገው አገሩ ሰላም እንድትሆንለት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊት እንድትሆን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲከበርባት ነው፡፡ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖርባት ነው፡፡ ፍትሕ በተግባር የተረጋገጠባትና ዜጎቿ በነፃነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ጦር አውርድ የሚሉ፣ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚሻረኩ፣ ሥልጣንን ሙጥኝ ብለው አገር የሚዘርፉ፣ ልዩነቶቹን እያጋነኑ የሚከፋፍሉትንና አገርን ለጥፋት የሚዳርጉትን አንቅሮ ተፍቷቸዋልና ይህንን ታሳቢ ያደረገ የድርድር ዝግጅት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፤ የፖለቲካ ትርፍ የሚሸመተውም በዚሁ መንገድ ብቻ ነው።