የሀገራችን ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው፡፡ ይህ ጠላት ለዘመናት አንገታችንን አስደፍቶ የሃፍረት ሻማ እንድንከናነብ ያደረገን መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። እናም ይህን አሳፋሪ ጠላት ታግለን ካሸነፍን፣ ሌሎች ጠላቶቻችንን በቀላሉ ድል እንደምንነሳቸው አያጠያይቅም፡፡ እርግጥ ድህነትን ለመቅረፍ ብሎም ለማጥፋትና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መንግስት ዘርፈ- ብዙ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተግባራትን አከናውኗል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል። እነዚህ ተግባራትም ውጤታማነታቸውን በገሃድ ባስመሰከሩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች የተመሩ በመሆናቸው፤ በመላው ሀገሪቱ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ችለዋል፡፡
በተለይም ካለፉት አራትና አምስት ዓመታት ጀምሮ፣ ለዚያውም የዓለም ኢኮኖሚና የፋይናንስ እንቅስቃሴ ችግር ላይ በነበረበት ወቅት ጭምር ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ሌሎች ተቋማት ጭምር የመስከሩት ሃቅ ነው፡፡ የተገኘው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሁሉንም የሀገሪቱን ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ማንም ሊመሰክር አይችልም፡፡ ለምን ቢባል የችግሩ ባለቤትም ይሁን የመፍትሔው አካል እርሱው ነውና፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሀገርን በማሳደግ ህዝብን ከድህነት ለማላቀቅ የሚያደርገው ሰፊ ርብርብ ለደቂቃ ሳይዘናጋ ወደ ፊት እየገሰገሰ ይገኛል፡፡ እናም እያስመዘገበው ባለው ፈጣን፣ ቀጣይና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገትን ተከትሎ፣ በተለይም ባለፉት ጊዜያት ተከስቶ የነበረውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የተከተለው አቅጣጫ የሀገራችን የልማት እንቅስቃሴ ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል ያደረገ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ይህ አቅምም ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት ገቢራዊ ያደረጋቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ምን ያህል ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
ባለፉት ዓመታት የተገኙትን አቅም መሰረት በማድረግ ለመንግስት ሰራተኛው የደመወዝ ጭማሪ አድርጓል። አንዳንድ ወገኖች ይህ የደመወዝ ጭማሪ የዋጋ ንረትን እንደሚያስከትል ሲናገሩ ይደመጣል። ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ በኢኮኖሚው ውስጥ አዲስ የገንዘብ ዝውውርን ስለሚፈጥር የዋጋ ግሽበት ይፈጥራል የሚል ነው።
ሃቁ ግን የህ አይደለም። መንግስት ለሰራተኛው ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ በገበያው ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። መንግስት በገበያው ውስጥ ተጨማሪ ገንዘብ አያስገባም። የደመወዝ ጭማሪው ገንዘብ መንግስት ከግብር በሚሰበስበው የሚሸፍነው እንጂ አዲስ ገንዘብ ወደ ገበያው ውስጥ በማስገባት የሚፈፅመው አይደለም። ስለሆነም በገበያው የገንዘብ ፍሰት ላይ የሚያመጣው ጫና የለም። እናም በደመወዝ ጭማሪ ምክንያት በገበያውና በሸቀጠች ላይ የሚፈጠር ምንም ዓይነት መዛባት ሊኖር አይችልም።
ይህ ማለት ግን አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴዎች ሁኔታውን ተከትለው የዋጋ ጭማሪ ሊያደርጉ ቢሞክሩ ህብረተሰቡ ዝም ብሎ ሊመለከታቸው ይገባል ማለት አይደለም። ሁሌም ሃላፊነት በጎደላቸው ነጋዴዎች ምክንያት የሚጎዳው ህብረተሰቡ እንደ መሆኑ መጠን ሁኔታውን በቅርበት በመከታተል ችግሩን ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ የመፍትሔ ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይኖርበታል።
በአንፃሩም ህብረተሰቡ ራሱ ትክክለኛ ባልሆነ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ገና ለገና ‘የዋጋ ንረትን ሊፈጠር ይችላል’ በሚል እሳቤ ላይ ተመርኩዞ ሸቀጦችን ያለ አግባብ በማሰባሰብ ተፈጥሮዊውን የገበያ አካሄድ ላይ ያልተገባ ጫና መፍጠር አይኖርበትም። ምክንያቱም መንግስት ልክ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት እሰራለሁ ካለ፤ መያዝ ያከበት ይህንን ትክክለኛ መረጃ እንጂ በጥርጣሬ ላይ የተመረኮዘ መረጃን ስላልሆነ ነው። እርግጥ መንግስት የዋጋ ንረትን እቆጣጠራለሁ ካለ አሊያም የዋጋ ንረት አይከሰትም ካለ ይህንኑ ያደርጋል። ለዚህ አባባሌ ያለፉት ተግባራቱ እማኝ የሚሆኑ ይመስሉኛል።
እንደሚታወቀው ሀገራችን በተመረጠ ሁኔታ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ባለበት የነጻ ገበያ ሥርዓት መመራት ከጀመረች የ25 ዓመታት ዕድሜን አስቆጥራለች፡፡ ይህም በሀገር ውስጥ ፈጣን፣ ዘላቂ፣ ተወዳዳሪና ከተጽዕኖ የፀዳ የንግድ ሥርዓት እንዲሰፍን ያስቻለ ነው፡፡ የገበያ ስርዓቱ ሸማቹም ሆነ አምራቹ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የንግድ ልውውጡን እንዲያካሄድ ሙሉ ነፃነት የሰጠ ከመሆኑም ባሻገር፤ ልማታዊ ባለሃብት በጥራትና በብዛት እንዲፈጠርም የማይተካ ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ነው፡፡
እርግጥ መንግስት የነፃ ገበያ ሥርዓቱን ከመዘርጋት ጀምሮ ስር እንዲሰድ በማድረግ በኩል የአንበሳውን ድርሻ ይዞ ችግሩን በቁርጠኝነት ተወጥቷል፡፡ ሆኖም በውስጥና በውጭ ጉዳዩች ሳቢያ በተለያዩ ወቅቶች የዋጋ ንረቶች ቢከሰቱም ጉዳዩን በቁጥጥር ስር ማዋል ችሏል፡፡ ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት ምክንያት ሊሆኑ ችለው ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ ሀገራዊ መሰረት የነበራቸው ምርቶች ላይ ተንተርሶ የተፈጠረው የገበያ ዋጋ መናር ክስተት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
በተለይም የሀገራችን የግብርና ምርቶች በከፍተኛ መጠን እያደጉ በነበሩበት ወቅት በከተሞች ውስጥ ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር ተያይዞ የተከሰተ ነበር፡፡ አዎ! የህብረተሰቡ ገቢ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ለመሰረታዊ ሸቀጦች ያለው ፍላጎት አብሮ ሊጨምር መቻሉ ነባራዊ ዕውነት ነው። የግብርና ምርት አቅርቦት በእጅጉ አድጎ በነበረበት በዚያ ወቅት የሸቀጦች ፍላጎት አብሮ በማደጉ ምክንያት ዋጋው ከተገመተው በላይ በላቀ ደረጃና ፍጥነት ሊጨምር ችሎ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
እርግጥም ባለፉት ዓመታት ለታየው የዋጋ ንረት አንዱ ምንጭ የእህል ዋጋ ያለማቋረጥ መጨመር ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ለገበያው የሚቀርበው ትርፍ ምርት ኢኮኖሚው በሚፈልገው ልክ አለማደጉን ተከትሎ እንዲሁም የገበያው ተዋንያን የእህል ዋጋ እንዲጨምር ለማድረግና ይጨምራል ከሚለው ግምት በመነሳት የሚያቀርቡትን መጠን መቀነሳቸው ብሎም ዋጋውን በቀጣይነት በመጨመራቸው ነው፡፡
ተግባሩ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ነጋዴው ድረስ ባሉ ተዋንያን አማካኝነት የተፈፀመ ሲሆን፤ የግብይት ሥርዓቱ ቅልጥፍና የጎደለውና ለውድድር በበቂ መጠን ያልተረጋጋጠ መሆኑን የሚያሳይ ጭምርም ነበር፡፡ የገበያ ሥርዓቱ ለሀገራችን አዲስ እንደመሆኑ መጠን ለዋጋ ንረቱ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
አንድን ምርት ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ በርካታ የግብይት ሰንሰለቶችን ማለፉ የግድ በመሆኑ፤ እነዚህ ሰንሰለቶች በየምዕራፉ ተገቢ ያልሆነ ወጪን ማስከተላቸውና ይህም በሸቀጦች የመሸጫ ዋጋ ላይ የሚንፀባረቅበት ሁኔታ እንዲከሰት አድርጓል፡፡ይህ ብቻ አይደለም። የምርት መጠን ማነስም ሌላኛው የዋጋ ንረቱ ምክንያት ነበር፡፡ ወደ ገበያ የሚወጣው የምርት መጠን ከህብረተሰቡ ፍላጎት አኳያ ያነሰ መሆኑ የእህል ዋጋው ጭማሪ እንዲያሳይ ማድረጉ አይታበይም፡፡ ሆኖም እነዚህን ዕውነታዎች ዛሬ ላይ ሆነን ስናያቸው፤ ለዚህ የሚያበቃን ነገር የለም። ምክንያቱም አሁን ያለው የምርት ሁኔታ አጥጋቢና የህብረተሰቡን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ስለሆነ ነው።
እንደሚታወቀው ዘንድሮ ከ320 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት እንደሚሰበሰብ ተገልጿል። ይህ ከፍተኛ የሆነ ምርትም ለእጥረት ሊያጋልጠን አይችልም። እርግጥ ምርቱ ለአርሶ አደሩ የዋጋ መውደቅና እህልን በመጋዘን የማከማቸት ችግር ሊያጋጥም የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ ነው። ሆኖም ይህን ተግዳሮት ለመቅረፍ መንግስት ቃል ገብቶ እየሰራ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ካለፉት የመንግስት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተሞክሮ እንደምንረዳው ትርፍ ምርትን ለእርዳታ እህል ማዋል ይቻላል። ታዲያ በአሁኑ ወቅት የታየው ምርታማነት ድርቅና ውርጭ ባለበት ወቅት ጭምር መሆኑ የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምን ያህል ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል።
በጥቅሉ ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ አንድም መንግስት ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚያስገባው ገንዘብ ባለመኖሩ፣ ሁለትም በአሁኑ ወቅት ትርፍ የሆነ ምርት በመገኘቱ ምንም ዓይነት የዋጋ ንረት ሊኖር አይችልም።
ስለሆነም ህብረተሰቡ ይህን ዕውነታ በመረዳት ጭማሪውን ምክንያት በማድረግ ሊፈጠሩ ከሚችሉ የተሳሳቱ መረጃዎች ራሱን ማቀብ ይኖርበታል። ምናልባትም ‘የዋጋ ንረት ይከሰታል’ በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ህብረተሰቡን ለማደናገር የሚሹ ኃላፊነት የጎደላቸው ነጋዴዎች ካሉም ለሚመለከተው አካል በመጠቆም የመብቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል።