የሀገራችን ፐብሊክ ሰርቪስ ባለፉት 25 ዓመታት በተመዘገቡት ሁለንተናዊ ድሎች ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ነው፤ ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ ይህን አብነታዊ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉ አይቀርም። ፐብሊክ ሰርቫንቱ እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ከተገኙት ልማታዊ ትሩፋቶች የበኩሉን ተጠቃሚነት ማረጋገጡ አይቀርም። ታዲያ ይህ ተጠቃሚነቱ ስር እንዲይዝና እንዲጎለብት ካለፈው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ተግባሩንና ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ይኖርበታል። በመሆኑም መንግስት በህዝቡ ውስጥ የሚነሱትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የገባውን ቃል ዕውን ለማድረግ ተብሊክ ሰርቫንቱ በአስተሳሰብና በተግባር አሰራሩን በማዘመን የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ ይገባል። ለዚህ ደግሞ በሁለንተናዊ መንገድ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ማለፍ እንዳለበት አሌ አይባልም።
ስለሆነም ያለፉትን አሰራሮቹን በመገምገምና የአገልግሎት አሰጣጡን በመዳሰስ ትናንት የነበሩበትን ችግሮች ለማጥራትና የመፍትሔው አካል ለመሆን እንዲሁም የተሟላ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አመለካከት እንዲኖረው ያከናወናቸውና በማከናወን ላይ የሚገኘው የተሃድሶ የግምገማ መድረኮች ወሳኝ ናቸው። ይህም ፐብሊክ ሰርቫንቱ የተጣለበትን ህዝባዊ ኃላፊነት በግልፀኝነትና በተጠያቂነት መፈፀም እንዲችልና በህዝቡ ይቀርቡ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ የሚጫወተው ሚና የላቀ እንዲሆን ያደርገዋል።
የመልካም አስተዳደር ስራዎች ከህዝቡ ጋር በቅርበትና በቀጥታ የሚያገናኙ በመሆናቸውና የህዝቡ የእርካታ መለኪያዎችም ስለሆኑ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዩች ናቸው። ህዝቡ በሚሰጠው እርካታ ተገቢ ያልሆነና ህዝቡን ለምሬት የሚዳርግ ከሆነ ቅሬታ ከመፍጠሩም በላይ፤ የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነትን ያደበዝዛል። መንግስት ለህዝቡ የሚሰጠው አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ እንዳይፈፀምና ህዝብ ከመልካም አስተዳደር ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርጋል።
ይህም መንግስት የሚሰጠው የመልካም አስተዳደር አገልግሎት በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ ያደርጋል። እነዚህ ዕውነታዎችም የህዝቡን አመኔታ በመሸርሸር ለሁከትና ለብጥብጥ መዳረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም። በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ የሚኖር ህዝብ ደግሞ ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ሊያደርግ አይችልም። በመሆኑም ፐብሊክ ሰርቫንቱ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ የመግባቱ ጉዳይ አጠያያቂ ሊሆን አይችልም።
ፐብሊክ ሰርቫንቱ መልካም አስተዳደርን ዕውን ማድረግ ያለበት ዋነኛው ምክንያት ልማትን ለማፋጠንና ዴሞክራሲውን ለማስፋት ነው። ዕውነታውን ከልማት አኳያ ስንመለከተው፤ የኢፌዴሪ መንግስት ባለፉት 25 ዓመታት መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል መቻሉን እንገነዘባለን። በዚህም በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ካለችው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እንዲያሳድጉ አስችሏቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትና የዕድገቱ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ ትግበራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የሀገሪቱ የግብርና መር ፖሊሲ ወደ ኢንዱስትሪ መር በሂደት እንዲሸጋገር እየተደረገ ያለው ጥረትም የሚደነቅ ነው፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት መንግስትና ህዝብ በጋራ በመሆን ባከናወኑት ሰፊ ጥረት እያስመዘገቡ ያሉት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት አሁንም ግለቱን ጠብቆ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በተለይም ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል። በአሁኑ ወቅትም መንግስት የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ለወጣቶች አዘጋጅቷል። ይህን ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀምና የወጣቱን ህይወት በሚቀይር መንገድ መጠቀም እንዲቻል የመልካም አስተዳደር ስራዎች በትክክለኛው መንገድ ገቢራዊ መሆን አለባቸው።
እርግጥ ከወጣቶቹ ተጠቃሚነት በተጨማሪ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ በገጠርም ሆነ በከተማ የምታከናውነው የልማት ርብርብ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እንዲቀየር ማድረጉ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ እናም አብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚተትኑት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቱ በዚሁ ከቀጠለ፤ ሀገሪቱ ባስቀመጠችው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ጎራ ለመሰለፍ ያስችላታል፡፡ እናም ይህ የሀገራችን ራዕይ ዕውን እንዲሆን ፐብሊክ ሰርቫንቱ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል። ተግባሩን ለማከናወንም ይህን ዕውነታ ተገንዝቦ ስራውን በአግባቡ እንዲፈፅም ያደርገዋል። በመሆኑም ፐብሊክ ሰርቫንቱ በታድሶ የግምገማ መድረኮች ውስጥ አልፎ የአፈጻፀም ደረጃውን በመለየት የታያዙትን ሀገራዊ ትልሞች ዕውን ለማድረግ ከእርሱ የሚጠበቅበትን ሚና መለየት ይኖርበታል።
ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አኳያም ፐብሊክ ሰርቫንቱ እዚህ ሀገር ውስጥ ባለፉት 25 ዓመታት የተከናወኑትን ተግባራት በነጠረ ሁኔታ ከማወቅ ባሻገር፤ስሜቱንና ዕምነቱን በግልፅ በማውጣት ሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ላለው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ በተዘጋጁት መድረኮች ላይ ማንኛውም ፐብሊክ ሰርቫንት ያለ አንዳች መሸማቀቅ የፈለገውንና ያሻውን ሃሳብ አንሸራሽሯል፤ በማነሸራሸር ላይም ይገኛል። ይህም እዚህ ሀገር ውስጥ በመገንባት ላይ ያለው ስርዓት ዴሞክራሲያዊና ሰኣታፊ መሆኑን በግልፅ እንዲያየው ተደርጓል። ወደ ስራው በሚሰማራበት ውቅትም ይህን ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም የሚመለከታቸውን ህፀፆች እንዲቀርፍና ጠንካራዎችንም እንዲያጎለብት የሚያስችለው ይመስለኛል።
እርግጥ መድረኩን በተመለከተ አንዳንድ ወገኖች “የይስሙላ ነው” ሲሉ ይደመጣሉ። ሆኖም መድረኮቹ የይስሙላ አለመሆናቸውን ራሱ ሲቪል ሰርቫንቱ ባንሸራሸራቸው ሃሳቦችና እየተወሰዱ ካሉት ተጨባጭ ሁኔታ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል። መድረኮቹ በፐብሊክ ሰርቫንቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በግልፅነትና በአሳታፊነት መንፈስ ያዩ ናቸው። ይህ በመሆኑም በሰራተኛው ውስጥ የቀሩ ሃሳቦች አሉ ለማለት አይቻልም። ሁሉም የመሰለውን ነገር አፍረጥርጦ አውጥቷል። እያንዳንዱ ሲቪል ሰርቫንት በሌላው ላይ ሂስ በመስጠት ገንቢ ተግባራትን ከውኗል። ይህ ተጨባጭ ማሳያም መድረኮቹ ቀጣይ ስራዎችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን ማሳየታቸውን እንጂ የመድረኮቹን “ይስሙላነት” የሚያመላክቱ አይደሉም።
በተካሄዱት ጥልቅ የተሃድሶ መድረኮች አማካኝነት በተሰብሳቢዎቹ አማካኝነት በተገኙት ግብዓቶች ሳቢያ በየደረጃው የተወሰዱት ርምጃዎችም የመድረከፖቹን ቁርጠኝነት አመላካቾች ናቸው። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ የመንግስት ስራ ፈፃሚዎች ላይ የተወሰዱት የአስተዳደራዊና ህጋዊ ርምጃዎችም የዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅዎች ይመስሉኛል። ለምሳሌ ያህል የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በቅርቡ በከፍተኛ የመንግስት ስራ አመራሮች ላይ የወሰደው አስተዳደራዊና ህጋዊ ርምጃዎች ተጠቃሽ ነው። ምን ይህ ብቻ! በአማራ ክልል ከ193 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች የተሳተፉበት ጥልቅ ተሃድሶና የተገኘው አዎንታወ ውጤት ሌላኛው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። እነዚህ ጉዳዩችም ዴሞክራሲን በመገንባት ላይ የሚገኝ ሀገር መልካም አስተዳደን ከማስፈን አኳያ የሚከተለውን ግልፅ የሆነ መርህ የሚያሳይ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።
ያም ሆነ ይህ ግን በማንኛውም ዴሞክራሲን የህልውና ጉዳይ አድርጎ በሚንቀሳቀስ ሀገር ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ቁልፍ ነው። እርግጥ መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሠረት ነው። ስለሆነም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ መረባረብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም።
ታዲያ ይህን ዕውነታ በውል የተገነዘበው የኢትዮጵያ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስትም ሃሳቡን ወደ ድርጊት ለመለወጥ በጥረት የታገዙ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ከጀመረ 25 ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት በርካታ ተግባራቶች ዕውን ቢሆኑም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም።
በተለይም በፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ አሰራር አልተፈጠረም። በመሆኑም ይህን የአገልጋይነት መንፈስ ለመፍጠርና በመንግስት ስልጣን ያለመገልገል አመለካከትን በተጨባጭ ሁኔታ ለማስያዝ የፐብሊክ ሰርቫንቱ በተሃድሶ ውስጥ ማለፍ የግድ ይሆናል።
ይህም ልማትን ለማፋጠንና ዴሞክራሲን በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር መደላድልን ይፈጥራል። ልማት ከተፋጠነና ዴሞክራሲው እንዲጎመራ የሚያስችል ምህዳርን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረም እንደ ሀገር የምናስበውን ራዕይ ለማሳካት እንችላለን። ስለሆነም የፐብሊክ ሰርቫንቱ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ማለፍ ዕውነታ ከዚህ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳይ አኳያ መታየት ይኖርበታል።