አርብቶ አደሩ ባህሉንና ልምዱን እንዲለዋወጥ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል!

 

  • የአርብቶ አደሩ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን!'' 

          የዘንድሮው የአርብቶ አደር ቀን መሪ ቃል

 

የኢፌሬሪ መንግስት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ልማትን ማረጋገጥ የስርዓቱ ብቻ ሳይሆን የአረጊቱም የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን በመገንዘብ እነዚህን ሁለት ነገሮች ለማሳከት ጠንክሮ በመስራት ላይ ይገኛል።  በመሆኑም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት አገሪቱ በየዘርፉ  በርካታ ለወጦችን ማስመዝገብ ችላለች።  በፖለቲካው መስክ አገራችን ህገመንግስታዊ አገር ለመሆን በቅታለች፤ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተረጋግጧል፣ በመረጧቸው ተወካዮቻቸው መተዳደር፣ ባህላቸውን ማሳደግ ችለዋል፣ አገራችን በአለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሰሚነትም እጅጉን ከፍ ብሏል፣ የአገሪቱ ገጽታም  መሻሻል አሳይቷል።

 

በኤኮኖሚ ረገድም በእነዚህ ዓመታት አገሪቱ ባለሁለት አሃዝ የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች። አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 800 ዶላር አካባቢ ደርሷል። በማህበራዊ ዘርፎችም  ትምህርት፣ ጤና፣ መሰረተ ልማቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍተዋል። መንግስት ፍትሃዊ ልማትን ለማረጋገጥ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲነግስ የከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ ሆነዋል።  

 

የዛሬ ርዕሰ ጉዳዬ የፌዴራል ስርዓቱ ለአገራችን ያስገኘውን ጥቅም  ለማብራራት አይደለም። ይልቁንም ዛሬ ለማንሳት የፈለኩት በአገሪቱ ፍትሃዊ ልማትን እውን ለማድረግና በተለይ ደግሞ ባለፉት ስርዓታት ትኩረት ተነፍሯቸው የነበሩ  አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች  አገራችን እያስመዘገበች ካለችው ዕድገት እንደሌላው አካባቢዎችን ፍተሃዊ  ተጠቃሚ   እንዲሆኑ  መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት  ለማንሳት ነው።

 

 

መንግስት ለአርብቶ አደሩ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ማህበራዊና መገልገያዎችንና መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋተ ላይ ነው።  አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የኢፌሬሪ መንግስት የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፎ በመስራት ላይ ይገኛል። የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በንጽጽር ሲታዩ በሁሉም መልክ ተጠቃሚነታቸው ይቀንሳል። በመሆኑም መንግስት  ለእነዚህ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ባለፉት  ሁለት አስርት አመታት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

 

መንግስት የአርብቶ አደሩን ችግሮች ለመቅረፍ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን ነድፎ በመተግበር ላይ ነው።  ለአብነት ከአጭር ጊዜ አኳያ  የአርብቶ አደሩን ነበራዊ ሁኔታ በመረዳት በዚያ አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ከአርብቶ አደሩ ጋር ተንቀሳቃሽ እንዲሆኑ ተደርጓል። አርብቶ አደሩ አንድን ሰፈር ለቆ ወደ ሌላ ሰፈር በሚጓዝበት ወቅት የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም የሰው ሃይላቸውንና ቁሳቁሳቸውን ይዘው በመንቀሳቀስ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተደርገው ተዋቅረዋል። ንጽህ  የመጠጥ ውሃ ለሰው እንዲሁም  ለእንሰሳት የሚያገለግሉ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ይገኝበታል።  ይሁንና ይህ የመፍትሄ የአርብቶ አደሩን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚችልና የልማት ተጠቃሚነቱን ሙሉበሙሉ ሊያረጋግጥ የሚችል አይደለም።

 

የአርብቶ አደሩን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ  ጋር በመነጋገር የመንደር ማሰባሰብ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። የአርብቶ አደሩ ህይወት በዘላቂነት መቀየር የሚቻለው ዘለማዳዊው  የአኗኗሩ ዘዴ  መቀየር ሲቻል  ብቻ  በመሆኑ መንግስት ከአርብቶ አደሩ ጋር በመነጋገር  በመንደር የማሰባሰብ ስራን በማከናወን ላይ ነው። በመሆኑም  አሁን ላይ  በርካታ የአርብቶ አደር የነበሩ ማህበረሰቦች  በፍቃደኝነት  በመንደር በመሰባሰባቸው የመሰረተ ልማትና መሃበራዊ  መገልገያዎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። አርብቶ አደሩ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ የመኖር ልምድን ባሳደገ ቁጥር የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነቱ ያድጋል፤  አካባቢው ይጠበቃል፣  ከዚህም ባሻገር    በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩት በሃብት ሽሚያ ሳቢያ የሚነሱ  ግጭቶች ይወገዳሉ።

 

 

በመንደር መሰባሰብ መሰረተ ልማትን በአግገባቡ ተጠቃሚ ማደረግ ከማስቻሉም በላይ ለአካባቢው ሰላም መጠበቅ ትልቅ ድርሻ  ያበረክታል። ምክንያቱም አርብቶ አደሩ ለውሃና ለግጦሽ የሚያደርገውን እሽቅድድም ያስወግድለታል። በመንደር መሰባሰብ ዘመናዊ የመስኖ ልማትን፣ ዘመናዊ የእርሻና ልማትና የእንስሳት እርባታ ዘዴዎችን ለማስፋፋት  እንዲሁም ምርቱን በቀላሉ ማሳደግ እንዲችል ያደርገዋል። በአንዳንድ አርብቶ አደር አካባቢዎች ትርፍ ምርት ማግኘት በመቻላው ለገበያ በማቅረብ ላይ ናቸው።

 

የመንግስት  የትኩረት አቅጣጫ አርብቶ አደሩ በአካባቢው የሚገኙ  የገጸና የከርሰ ምድር ውሃዎችን በስፋት በማልማት የመስኖ በስፋት ማከናወን ነው። ይህ ተግባር  አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል  አርብቶ አደርነት ማሸጋገር  ያስችላል። የመስኖ ልማት ስራዎችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የተሻሉ የእንሰሳት ዝርያዎችን ለአርብቶ አደሩ በማከፋፈል  ጥቂት እንሰሶችን በማርባት  የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር በስፋት በመስራት ላይ ነው።  

መንግስት ለአርብቶ አደሩ ዕውቅና እንዲያገኝ እንዲሁም አርብቶ አደሩ ልምድ እንዲለዋወጥ ለማስቻል በየዓመቱ የአርብቶ አደሮች ቀን እንዲከበር አድርጓል። በመሆኑም  የዘንድሮው የአርብቶ አደሮች ቀን    “የአርብቶ አደሩ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን'' በሚል  መሪ ቃል በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ በጅግጅ  ለ16ኛ  ጊዜ በመከበር ላይ ነው።   አርብቶ አደሩ ባለፉት ስርዓቶች ፖለቲካዊ ፣  ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተጠቃሚ አልነበሩም። በመሆኑም አርብቶ አደር አካባቢዎች በአብዛኛው  ከአገራዊ ጉዳዮች ተገለው ነበር።

የኢፌዴሪ መንግስት ከተመሰረተ ጀምሮ በአገራችን ተጨባጭ ለውጦች መመዝገብ ችለዋል።  የፌዴራል ስርዓቱ አርብቶ አደሩ ራሱን በራሱ ማስተዳደር  እንዲችል እድል ከመፍጠሩም ባሻገር በመዓከላዊ  መንግስቱም በቂ ውክልና እንዲኖራቸው አድርጓል።  በኢኮኖሚውም ረገድ መንግስት አገሪቱ   እያስመዘገበችው ከለው ፈጣን ልማት  አርብቶ አደር አካባቢዎችም ፍተሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው።

የአርብቶ አደሮችን  ቀን በዓል ክፍለ አህጉራዊ ገጽታ እንዲኖረው ለማድረግ  የኢፌዴሪ መንግስት ከኢጋድ አባል አገራት ጋር በቅርበት በመስራት ላይ ነው። በሁሉም የኢጋድ አባል አገራት በሚባል መልኩ፣ አርብቶ አደሮች ይገኛሉ። በአገራችን ወደ 15 ሚሊዮን የሚደርሰው ህዝባችን አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። አርብቶ አደሮች በስፋት የሚገኙትም  ሰሜን ምስራቅ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ አካባቢዎች ነው።

 

የኢትዮጵያ መንግስት የኢጋድ አገሮች አርብቶ አደር ህዝቦች ልምድ እንዲለዋወጡ  ለማድረግ  እንዲሁም በቀጣይ  የአባል አገሮች  አርብቶ አደሮች በዓሉን   በጋራ ማክበር እንዲችሉ የኢጋድ ተወካይ በዘንድሮው የአርብቶ አደሮች  ቀን በዓል  ላይ ጅግጅጋ  እንዲገኙ ተደርጓል።  የአርብቶ አደር ቀን መከበሩ ዋንኛ አላማ የአርብቶ አደሩን የልማት  ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተሞክሮዎችን መለዋወጥ የሚችሉበትን መድረክ ለመፍጠር እንዲሁም   ለውጦችንና ክፍተቶችን ለመፈተሽ ከማስቻሉም በላይ አርብቶ አደሮች እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁና ባህላቸውንና ልማዳቸውን እንዲያስተዋውቁ ትልቅ ዕድል ይፈጥሯል። ከዚህም በተጨማሪ የአርበቶ አደሩን አንድነት ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳለው መገመት ይቻላል።