የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት በአገራችን የሥልጣን ብቸኛ ምንጭ የህዝብ ድምጽ መሆኑን ደንግጓል። ወደ ሥልጣን የሚመጣም ሆነ ከሥልጣን የሚወርድ ፓርቲ በህዝብ ይሁንታ ብቻ ነው። ሥልጣንን ፍለጋ የሠላማዊ ዜጎችን ህይወትና ደህንነት ሥጋት ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ለአመጽ መቀስቀስ፣ ድንጋይ መወርወር ወይም ማስወርወር፣ የልማት ተቋማትን ማፈራረስ…ዛሬ ታሪክ ሆኖ እንዲቀር የብዙዎች ፍላጎትና እምነት ነው፡፡ በእርግጥም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ይህ የሚታሰብ ነገር አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ዛሬ የልማትና የዴሞክራሲ ጎዳና የአገሪቱ ችግሮች ሁሉ ቁልፍ መሆናቸውን ተረድተው እነዚህን ለማሳካት ርብርብ ላይ ናቸው።
የሠላማዊ ዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል፣ ንብረት ማውደም፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና መቃቃር ማንገስን፣ የግለሰቦችን ክብርና ዝና በማጉደፍ ማብጠልጠልን የመሰሉ እኩይ ተግባራት ለአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጠንቅ ነው። ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ደግሞ ይህን የጥፋት መንገድ የመታገያ መስመራቸው አድርገውታል። አገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን የምትከተል አገር ናት። በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየአምስት ዓመቱ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ወቅት ሥልጣን ለመያዝ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ፤ ነገር ግን ይህን ዕድል የፈጠረላቸውን ህገ መንግሥት ከምርጫ በኋላ ሲያከብሩትም ሆነ ሲያስከብሩት ብዙም አይስተዋልም።
ፓርቲዎች ሠላማዊ ምርጫ እንዲያካሂዱ ያደረገው ህገ መንግስሥቱ ነው። አገራችን ባለፉት 15 ዓመታት ገደማ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው ይህ ህገ መንግሥት በፈጠረው ሥርዓት ነው። በአጭሩ ይህ ህገ መንግሥት የአገራችን ዙሪያ ገባዋ ነው። ይሁን እንጂ ቀላል የማይባሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ያስገኘላቸውን መልካም ነገሮች ከማጣጣም ባለፈ ይህን ሥርዓት የፈጠረውን ህገ መንግሥት ከማክበርና ማስከበር ላይ የሚስተዋሉ እጥረቶች አሉባቸው።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ለዘመናት ምላሽ ላላገኘው የሰብዓዊ መብቶች መከበር ጥያቄ፤ የህዝብ ሉዓላዊነት እና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማንነትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ፤ አንገብጋቢ ለሆነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ፤ በህዝብ ሰፊ ተሣትፎ እና በዴሞክራሲያዊ አካሄድ የፀደቀ ህገ መንግሥት ነው። ይህ ሰነድ የህዝቦች አብሮነት እስትንፋስ ነው። ህገ መንግሥቱ ለዘመናት መልስ ያላገኙ ቁልፍ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ምላሽ እንዲያገኙ አድርጓል።
በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአገራችን መሠረታዊ ግብ እና ራዕይ የሚገለፅበት የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ህግ ሲሆን፤ ሁሉም የመንግሥት አካል ሥልጣንና ኃላፊነት ምንጩ እና መሠረቱ ይኸው ሰነድ ነው፡፡ የማንኛውም የመንግሥት አካል ውሣኔ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከህገ መንግሥቱ የሚመነጩና ከህገ መንግሥቱ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፡፡ በአገራችን የሚወጡ ማናቸውም ህጎች ህገ መንግሥታዊ መሠረት ያላቸውና ህገ መንግሥቱን የማይቃረኑ መሆን ይገባቸዋል፡፡ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥትም፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስለ አገራቸው ያላቸውን የጋራ አንድነት የሚያመላክት ሰነድ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለአገራቸው ያላቸውን ራዕይ በህገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ እንዲህ ሲል ሰፍሯል “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡ በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሠላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነጻ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤ … አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤ በትግላችንና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሠላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ፤ ይህ ሕገ መንግሥት ከዚህ በላይ ለገለጽናቸው ዓላማዎችና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት በሕገ መንግሥት ጉባዔ ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 1987 አጽድቀነዋል፡፡” ይላል።
ከዚህም ባሻገር የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት “የግለሰቦች መብትና ነፃነት የተረጋገጠባትና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዘቦች የራሰን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በተሟላ ሁኔታ የተከበረባት የበለፀገች ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያን በጋራ መመሥረት” መሆኑን፤ በቅርቡ የህገ መንግሥት ጉባዔ አባላት ካደረጉት ውይይት እና ምክክር፤ ከህገ መንግሥቱ መግቢያ እና ከሌሎች ዝርዝር ድንጋጌዎች ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡
የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በተሟላ ሁኔታ የተከበረባት የበለፀገች ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ መፈቃቀድና በህግ የበላይነት የተመሠረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመመሥረት ቃል የገቡት፤ የቃል ኪዳናቸው ማሰሪያና የጋራ መተዳደሪያቸው የሆነውን የኢፌዲዴሪ ህገ መንግሥት በማፅደቅ ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ የሉአዓላዊነታቸው መገለጫ ነው፡፡ ስለሆነም ህገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማክበር ልዩነቶች በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሥርዓት በህገ መንግሥቱ በበቂ ሁኔታ ዘርግተዋል፡፡
በህገ መንግሥቱ የማንነት ጥያቄዎችን ጥሩ አድርጎ መልሷል። “ጥሩ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ..ወዘተ ሆኜ፤ ጥሩ ኢትዮጵያዊ መሆን እችላለሁ” የሚል አቋም የሚያራምዱ ወገኖችን፤ በዘረኝነት እና በጠባብነት፣ በፀረ- አንድነት ዓላማ አራማጅነት ሊፈረጁ አይገባም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ የድሮው እኔ አውቅልሃለው አካሄድ ከእንግዲህ አይሰራም። ማንነትን አሽቀንጥሮ እንዲጣልና በደምሳሳው ኢትዮጵያዊ ነህ የሚለው የድሮ አስትተሳሰብ ለአገራችን አንድነት የሚበጅ አይደለም። ማንነትን የሚደፈጥጥ በደምሳሳው ኢትዮጵያን ነህ የሚባለው የግዴታ አንድነት አገራችንን ለጦርነት፣ ለድህነትና ለኋላ ቀርነት የዳረጉ ነበሩ፡፡ በመጨረሻም፣ አቋማቸው የከሰረ አቋም መሆኑ በተጨባጭ ተረጋገጠ፡፡ ይህ ህገ መንግሥት፤ የቡድን እና የግለሰብ መብቶች እና ነፃነቶች እንዲከበሩ፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ዕድል እንዲጎናፀፉ ያደረገ ህገ መንግሥት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መክረው እና ዘክረው ባፀደቁት፤ የጋራ ራዕይ እና አገራዊ ግባቸውን በገለፁበት ህገ መንግሥት በግልፅ የሰፈረውን በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነትን የሚጎዳ ተግባርና አመለካከት በብሔረሰብ መብት ተሸፍኖ ሲመጣ አለሳልሶ ለመያዝ ሲሞክር ይታያል፡፡ የጥበት ኃይሎች ፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ቀዳዳ የሚያገኙበት ዕድል እንዳይፈጠር ለመጠንቀቅ ሲል የአንድነትን አስፈላጊነት አበክሮ ሲገልፅ አይታይም፡፡ ነገር ግን፤ ኢሕአዴግ ለአንድነት የታገለ ድርጅት መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
የህዝቦችን ጥያቄ አንግበው የታገሉት እና ደርግን የደመሰሱት ኃይሎች፤ ሥርዓቱን ወደ መቃብር ከሸኙ በኋላ፤ የአገሪቱን የመበታተን ዓላማ ቢኖራቸው ያን ለማድረግ የሚከለክላቸው ኃይል አልነበረም፡፡ የመለያየት ግብን ለማሳካት ተጨማሪ ሥራ ከማይጠይቅ ደረጃ ደርሰው ነበር፡፡ የአንድነትን መፈክር አንግቦ ጦርነት የከፈተው ኃይል ከተሸነፈ በኋላ፤ የመገንጠል ዓላማ የነበረው ማንኛውም ኃይል እንደ ኤርትራ የፍላጎቱን ለማድረግ ይችል ነበር፡፡ ሁሉም በትጥቅ ትግል ያገኘውን ድል እያጣጣመ በየፊናው ጎጆ ሊወጣ ይችል ነበር፡፡ ሆኖም፤ ያ አልተደረገም፡፡
‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና የልማት ጥረታችንን በፍጥነት ውጤታማ ካላደረግን አደጋ ይፈጠራል›› የሚል ግንዛቤ ይዘው፤ ፈጣን ዕድገት ለማረጋገጥ ያለ ዕረፍት በጥድፊያ እየተረባረቡ የሚገኙ የልማት ኃይሎች፤ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲመለከቱ ዕረፍት ሊነሳቸው ይችላል፡፡ ሆኖም፤ የጀመርነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥራ፤ የአዲስ ባህል ግንባታ ሥራ እንደ መሆኑ መጠን፤ ረዘም ያለ ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ መሆኑ እና አሁን ያለችው ኢትዮጵያ የሽግግር ዘመን ኢትዮጵያ እንደ መሆኗ፤ በመነሻ የተጠቀሰውን ብርሃን እና ጨለማን ያዳበለ ሁኔታ ይዛ መታየቷ አይቀርም፡፡ ስለሆነም፤ በሂደት የሚታዩ መሰል ችግሮችን በማስተዋል እየፈቱ መጓዝ ግድ ይሆናል፡፡ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን ለአደጋ የሚያጋልጡ የአመለካከት ችግሮችን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ የችግሮቹን መሠረታዊ ባህርይ እና አንደምታ በትክክል ተገንዝቦ የሚፈጥሩትን አደጋ ለማስወገድ ወይም ለመቀነስ የሚያስችሉ ተጨባጭ እና ትክክለኛ ሥልቶችን በመቀየስ፤ በዚሁ ላይ ህዝቡ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡