ያልተላቀቅነው ኤሊኖ እና የመስኖ ልማት ተግባራት

የአለማችን ዋነኛ አጀንዳ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የሁሉንም በር እያንኳኳ የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑ ይታወቃል። ችግሩን የከፋ የሚያደርገውም ሰለባዎቹ የችግሩ ምንጮች ሳይሆኑ ደሀዎቹ መሆናቸው እንደሆነም በርካታ ጥናቶች በአንድነት ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። በእርግጥ የችግሩ ምንጮች ለመፍትሄው ሰለባ ከሆኑቱ በላይ ቢጠበቅባቸውም በሂደት የሁሉም አደጋ በመሆኑ ለማንም ሳይተው የሃገራትንና አህጉራትንም የተጠናከረ ተሳትፎ ጭምር የሚጠይቅ መሆኑ የማያጠራጥር እና አለምን ያስማማ ጭምር ነው።

ለአየር ለውጥ የሚይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት በኩል አርአያ መሆኗ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ የሚነገርላት ሃገራችን ቀድሞ ቢያንስ በየ10 አመቱ ይደርስባት የነበረው የድርቅ አደጋ አሁን በየአመቱም ይጎበኛት ጀምሯል። ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የተከሰተው የኤሊኖ አየር መዛባት ባለፈው አመት አድርሶብን በነበረው አደጋ አሁንም ሊፋታን እንዳልቻለ መረጃዎች እያመላከቱ ነው። የተጀመረውን የተፈጥሮ ሀብትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከመስኖ ልማቱ ጋር አቆራኝተን መስራቱ ላይ ባደረግነው ርብርብ ያገኘነው ውጤት ባይቋቋምልን ኖሮ የዘንድሮው ችግር በዜሮ አባዝቶ ከጫወታ ውጭ ያደርገን እንደነበር ለመገመት አይከብድም።

ከወትሮው በተለየ ስለምን በድጋሜ ለድርቅ ተጋለጥን? አሁንስ ይህንን ድርቅ ለመሸከም የሚያስችል ትከሻ አለን ወይ? መገለጫዎቹስ ምንድናቸው? በዘላቂነትስ ለመቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? በድጋሜ ለጎበኘን ድርቅ ማሳያ የሚሆኑት አካባቢዎችስ የትኞቹ ናቸው? የሚሉተ መሰረታዊ ጥያቄዎች የዚህ ጽሁፍ አቢይ ትኩረት ናቸው።

 

በ2007 ዓ.ም የመኸር ወቅት ላይ በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በብዛት ያጠቃው የምስራቁንና የደቡቡን የአገሪቱ ክፍል ቢሆንም ሰሞኑን ወደ ምስራቅ አማራ እና ደቡባዊና ምስራቃዊ ትግራይ (በአገሪቱ ሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች) ላይ ስለመበርታቱ ከእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ።

 

የሃገሪቱ ኢኮኖሚ የተገነባው በግብርና ላይ በተለይም በአርሶ አደር ማሳ ላይ በሚካሄድ እርሻ ነው።  የአርሷደር ማሳን መሰረት ያደረገው ኢኮኖሚ ደግሞ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እድገት እያስመዘገበ እንደሆነ መንግስትም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይፋ አድርገዋል።  ይህ ዘርፍ ከሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የ70 በመቶ ድርሻ እንዳለው በ2014 የዓለም የእርሻ ድርጅት ባወጣው መረጃ አስታውቋል።  የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ዓመታትን ያሳለፈው ግብርና ግን ዓመታት በተፈራረቁ ቁጥር የሚጋፈጣቸው ፈተናዎች እየበዙበት ይገኛሉ።  ከእነዚህ ፈተናዎቹ መካከል ደግሞ ዋነኛው ድርቅ  ነው።

 

በኤልኒኖ ምክንያት በደረሰው ድርቅ የተነሳ ርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች ላይ የአርሶ አደሩ ምርት እየቀነሰና  የአርብቶ አደሩ የቁም እንስሳት የመሞትና የዋጋ መውረድ እያጋጠማቸው ይገኛል። በእነዚህ አካባቢዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ የተሻለ ምርት ቢገኝም በዚህ ዓመትም ተጨማሪ የርሃብ ስጋት አንዣቧል።  

 

ወርልድ ፕሬስ ዶት ኮም ከተባለ ድረ-ገጽ ላይ የተለያዩ ምሁራን ያስቀመጧቸውን እና   በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚነሳው ድርቅ ምክንያቶች ተብለው ከተመለከቱት ዋነኞቹ እኚህ ሲሆኑ፤  አብዛኛው አርሷደር በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ የግብርና ዘይቤ መከተሉ ቀዳሚው የችግሩ ምክንያት ነው። ዝናብ ላይ መሰረቱን በጣለው እርሻ ላይ ኢኮኖሚዋን የገነባችው ኢትዮጵያ ችግሩ ይበልጥ እንዲጠነክርባት ያደረገው ሌላው ምክንያት ደግሞ “በአነስተኛ የገበሬ ማሳ ላይ የሚካሄድ እርሻ መከተሏ” እንደሆነም ተመልክቷል።  የህዝብ ቁጥሩ በየጊዜው እየጨመረ መሄዱም በምክንያትነት ተቀምጧል። ስለሆነም የአየር መዛባት በገጠመን ቁጥር ኢኮኖሚያችን እንዳይዛባ ፖሊሲውን ተከትለን የተጠናከረ ስራ ማከናወን ይጠበቅብናል ማለት ነው ።

ባሳለፍነው አመት ገጥሞን የነበረው ድርቅ  ቀድሞ ከነበሩት እና ቢያንስ በየ10 አመቱ ከገጠሙን ሁሉ የከፋ የነበረ ቢሆንም በራሳችን አቅም ልንቋቋመው ችለናል። ያም ሆኖ ግን የአለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ዛሬም ጫናውን አራግፎብናል። የተሻለ የመኸር ምርት እንደሚሰበሰብ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅትም እርዳታን ተስፋ ያደረጉ ነፍሶች በርከት እንደሚሉ ከላይ የተመለከቱት አስረጂዎች እየነገሩን ነው ።

ህዝቡን ከድህነት የሚያላቅቅ፣ በሂደትም የበለፀገ ሀገር ለመገንባት የሚያስችልና የግብርና ልማትን የሚያፋጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ በሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ተግባራዊ ማድረግ መቻላችን ለመቋቋማችን ዋነኛ ምክንያት ነው። መንግስት ለግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎች እና ለገጠሩ ህብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መገኘቱም ሌላኛውና ሊጠቀስ የሚገባው ምክንያት ነው። ያለንን የልማት አቅም ማለትም ሰፊ ጉልበት፣ መሬት፣ ውሃ እና ውሱን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም ያስቻለን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂውም በተመሳሳይ።

ግብርናችን በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ ሀገር እየተገነባ የመጣበት እውነታ ቢኖርም፤ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ያለና አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑን ታሳቢ ያደረገ እና ይልቁንም ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችንን የሚጨምር የመስኖና የተፋሰስ ልማት ዝግጅትም ከወዲሁ አስፈላጊ መሆኑን ከዚህና በድጋሚ ከጎበኘን አደጋ በላይ አመላካች መጠበቅ አያስፈልገንም፡፡ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ዕድገት እየተመዘገበ ቢሆንም የተሟላ አቅም ከመገንባት አኳያ ግን ገና የሚቀረን ስለመሆኑም ከዚህ በላይ አጋጣሚ እስኪፈጠር መጠበቅ አያሻም ።   

የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተነድፎ ወደ ተግባር ሲገባ የተለያዩ መነሻዎች የነበሩት ቢሆንም ዋናው አጀንዳ ግን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ መመዝገብ የጀመረውን የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፤ በዚህም የአርብቶ አደሩን አካባቢ መደገፍ የሚያስችል አቅም ጭምር በመገንባት የአርሶ አደሩንም ሆነ መላውን ህዝብ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ማሻጋገር ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በአርብቶ አደር አካባቢዎች የድርቅ ስጋትን ለመቀነስ ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ቢሆንም በዘላቂነት ከድርቅ አደጋ ነጻ የሆነ ቀጠና መፍጠር አልተቻለም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በመስኖ የበቆሎና የሰሊጥ ምርትን ጨምሮ የተለያዩ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ በርካታ መረጃዎች ቢያመላክቱም ዛሬም ከተመጽዋጭነት መላቀቅ ያልቻለ አካባቢ ሆኗል። ከሰሞኑ በተከበረው የአርብቶ አደሮች በአል ላይም የተንጸባረቀው ይኸው ነው።

በበአሉ ላይ እንደተነገረው በቦረና፣ ጉጂና ሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋለውን የድርቅ ስጋት ለማስወገድ  እንደተደረገው ሁሉ በሌሎችም የአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ተመሳሳይ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል። ለእንስሳት በቂ መኖ ማቅረብ እንዲቻል በቂ መኖ ከማይገኝባቸው አካባቢዎች መኖ ወዳለው ቦታ ማንቀሳቀስ እና ዳግም የገጠመንን   የድርቅ አደጋ በቁጥጥር ስር ማዋል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል።  እየፈረጠመ በሚገኘው አቅማችን እና ፖሊሲያችን ታግዘን ታዳጊ ክልሎች በልዩ ድጋፍ አማካኝነት ልማታቸውን በፍጥነት ማመጣጠን የሚችሉበትን ስርአት መዘርጋትም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ።  

ዛሬ ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት ላይ የሚገኘውና መስኖን መሰረት ባደረገው የግብርና ስራ ኢትዮጵያ በግብርና ምርቶች በዓይነት፣ በጥራት እና በመጠን ተወዳዳሪ ሆና በዓለም የግብርና ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖራት በማስቻል ውጤታማ ሂደት ላይ  የመገኘታችንን ተሞክሮም ማስፋትና ማጥለቅ ይጠበቅብናል ።

አርሶ አደሮች ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻል፣ በእንስሳት ዘርፍ ያለውን የምርምር ስራዎች ማጠናከር እና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ሁለንተናዊ የግብርና ምርምር ስራዎች ማከናወን ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ያስችለናል።

ዝናብ አጠርና እርጥበታማ በሆኑ አካባቢዎችም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎችን በጊዚያዊነት መከላከል እንዲቻልም የተጀመረውን ልማታዊ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማጠናከር ያስፈልጋል ።  

በግብርናው ሴክተር የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ በዕቅድ ዘመኑ ከተወሰዱ መፍትሄዎች አኳያ በግብርናው ሴክተር ያለውን የሰው ኃይል በአመለካከትና በክሂሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራዎችን በመስራት የሰው ኃይሉን ምርታማነት የማሳደግ፣ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር ማስተሳሰር፣ አደረጃጀቶቹን የማጠናከርና የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅ እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋትን ሥራ አሁንም ሙጥኝ ማለት ለበለጠ ውጤት የሚያበቃን መሆኑን ለአፍትም መዘንጋት አይገባም።