የህብረቱ ጉባኤና ሀገራችን ለወጣቶች የሰጠችው ትኩረት

28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የህብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ላይ መካሄዱ ሀገራችን ወደ ቀድሞ አስተማማኝ ሰላሟ በአፋጣኝ መመለሷን የሚያመላክት ነው። ጉባኤው በመዲናችን ሲካሄድ በርካታ ጉዳዩች ተነስተዋል። ከእነዚህ ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሰው የወጣቶች ጉዳይ ነው።

አዎ! የህብረቱ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ያካሄደው ጉባኤ ላይ የቀድሞዋ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ድላሚኒ ዙማ እንደተናገሩት፤ ለወጣቶችና ሕፃናት ትኩረት የማይሰጥ አገር ብሩህ ተስፋ የለውም። አክለውም የስራ ዕድል ካላገኙት አፍሪካውያን 60 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች በመሆናቸው፤ ይህን እምቅ ሃብት በመጠቀም የአህጉሪቱን ህዝቦች ህይወት ወደ ተሻለ ዕድገት ማሸጋገር እንደሚገባ አስረድተዋል።

እርግጥም የጉባኤው ቀዳሚ ጉዳይ ወጣቶች ነበሩ። ወጣቶች የአህጉሪቱ አባል ሀገራት ተስፋዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ አባል ሀገራቱ እናድጋለን ብለው ካሰቡና ከዚህም አኳያ እቅዳቸውን ዕውን ለማደረግ ከሻቱ ለወጣቶች የግድ ቅድሚያ መስጠት ይኖርባቸዋል። ከዚህ አኳያ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ የኢፌዴሪ መንግስት ከሀገራችን የህዝብ ቁጥር ግማሽ ያህል የሚሆኑት ወጣቶች ስራ እንዲያገኙና የሀገሪቱ የልማት ሃይል አንቀሳቃሽ ሆነው የተያዘው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቡን እንዲመታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ የራሱን ዕቅድ ይዞ እንደነበር እናስታውሳለን።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው በወቅቱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለህዝብና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ “…የሀገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት ይሰጠዋል” በማለት ተናግረዋል።

ይህ የመንግስት አቋምም ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት ዕድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መግለፃቸው ይታወሳል።

ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድም የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን ድግ እንደሚልና መንግስትም በያዝነው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን በ10 ቢሊዮን ብር እንደሚጀምር ማስታወቃቸውም አይዘነጋም። የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀየሰው ይህ ኘሮግራም በየጊዜው እየተገመገመ አስፈላጊው የማስተካከያ ርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም ማስታወቃቸው እንዲሁ የሚታወስ ነው።

እርግጥ ይህ የ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቀቃሽ ፈንድ በቅርቡ በመንግስት ከፀደቀ በኋላ ወደ ስራ ለመግባት ተችሏል። በፌዴራል ደረጃ ከተያዘው ከዚህ ተንቀሳቃሽ ፈንድ በተጨማሪ ክልሎች የራሳቸውን በጀት በማከል የወጣቱን የስራ አጥነት ሁኔታ ለመቀነስ ርብርብ እየተደረገ ነው። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ለወጣቶች ስራ ፈጠራ ያግዘው ዘንድ የስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በጀት ማፅደቁን ማስታወስ ይቻላል። ሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በጀት መመደባቸው እንዲሁ።

ታዲያ እነዚህ መንግስታዊ ጥረቶች ሀገራችን የአፍሪካ ህብረት በወጣቶች ላይ ከያዘው አቋም ጋር አንድ የሆነ አስተሳሰብ ቀደም ብላ ማራመዷን የሚያሳይ ይመስለኛል። ህብረቱ በወጣቶች የስራ ፈጠራና ተጠቃሚነት ዙሪያ የያዘው አቋም የሀገራችንን ፕሮግራም የሚያጠናክር መሆኑ ግልፅ ነው። እናም በወጣቶች የስራ ፈጠራና ተጠቃሚነት ዙሪያ የተያዙ አቋሞች ተጠናክረው ለወጣቱ ብሩህ ተስፋ ማምጣት ይኖርባቸዋል።

እርግጥ ወጣቶች የዚህች ሀገር ገንቢዎች ናቸው። ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። በእኔ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ሁለት ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ።

አንደኛው በርካታ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ወጣት ይፈጠርና ይህ ስራ አጥ ኃይልም የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ ለሁከትና ብጥብጥ በር የሚከፍት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሀገራት ከወጣቱ ማግኘት የሚገባቸውን የልማት ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይችሉም።

እርግጥ ስራ የሌለው ወጣት ማናቸውንም ጉዳዮች እንደ ስራ ሊመለከት ይችላል—የሁከት ተግባርንም ቢሆን። ይህ ደግሞ የተረጋጋ ሰላምና የልማት ስራ የሚከናወንበትን ሀገር ሊረብሽና ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል። ለዚህ አባባሌ በቅርቡ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የሁከት ተግባር ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል። ወጣቶች በየአካባቢያቸው ካለው የመልካም አስተዳደር ችግር በተጨማሪ በሚፈለገው መጠን ስራ ሳይፈጠርላቸው በመቆየቱ፤ ለሀገራችን የውጭ ጠላቶች ለሚላላኩ የጥፋት ሃይሎች ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ሰለባ ሆነው ነበር።

ይህ ሁኔታም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ የሚዘነጋ አይደለም። እናም አስቀድሞ ወጣቱን በሚፈለገው መጠን በስራ እንዲታቀፍ ማድረግ ቢቻል ኖሮ፤ የተከሰተው ጥፋት ዕውን አይሆንም ነበር—ከሀገራዊ ልማት ተጠቃሚ የሆነ ወጣት በምንም መልኩ የሀገሩን ጥቅም በመፃረር የሌሎች ባዕዳን ሃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን ስለማይችል ነው። እናም የኢፌዴሪ መንግስት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወጣቱን አቅም በፈቀደ መልኩ አደራጅቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ይመስለኛል።

ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራት ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለዚህም ነው— የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለወጣቶች ተጠቃሚነት ትኩረት በመስጠት አባል ሀገራቱ ወጣቱን በስራ ፈጠራ በማነፅ ከአፍላ ጉልበቱ ሊጠቀሙ እንደሚገባ የመከረው። 

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ለወጣቶች የሰጠው ትኩረት የህብረቱን ፍላጎት አስቀድሞ የተገነዘበ ነው ማለት ይቻላል። ግና እዚህ ላይ ‘ወጣቶች ሀገራችን የሰጠቻቸውን ትኩረት እንደምን ሊጠቀሙበት ይገባል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። አዎ! ምንም እንኳን የጥያቄው ምላሽ ሊኖር የሚችለው በወጣቱ ትጋት ውስጥ ቢሆንም፤ እኔም ለመነሻ ይሆኑ ዘንድ ጥቂት ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ለማንሳት እሞክራለሁ።

ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። በእኔ እምነት ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል ይቆጠራል። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት። ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።

በአጭሩ ወጣቱ ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። “ስራ ክቡር ነው” የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ይጠበቅበታል። ያኔ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን ሀገሩን መጥቀሙ አጠያያቂ አይሆንም።

ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ ሊሆን አይገባም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ አዘጋጅተዋል። ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው።

እናም አንድነት ኃይል በመሆኑ፤ በቅድሚያ ተደራጅቶ አዋጪ ስራን መምረጥ፣ የተገኘን ባጀት በስራ ላይ ብቻ ማዋል፣ እንደ አንድ ሆኖ ማሰብ፣ በተመረጠው ስራ ላይ በእኔነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዲሁም ከተጀመረው ስራ የሚገኝ ትሩፋትን በቁጠባና አግባብ በሆነ መንገድ ብቻ መጠቀም ከወጣቱ የሚጠበቁ ተግባሮች ናቸው። ስለሆነም ወጣቱ በመንግስት የተሰጠውን ትኩረት ያህል፤ እርሱም ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን በሚጠቅሙ ስራዎች ላይ በማዋል የነገ “እርሱነቱን” ከወዲሁ ማዘጋጀት ይኖርበታል።

በአጠቃላይ ከመሰንበቻው የተጠናቀቀው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወሰዳቸው አቋሞች፤ ሀገራችን ከምትከተለው የወጣቶች ፖሊሲና ፕሮግራም ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ነው። እናም እንደማንኛውም ሀገር ወጣት፤ የሀገራችን ወጣቶችም ይህን የአህጉሪቱን ብሎም የሀገራችንን ትኩረት በአግባቡ በማጤንና ወደ ተጨባጭ ስራ በመለወጥ ሊጠቀሙበት ይገባል እላለሁ።