ብቁ የሕዝብ አገልጋይ መፍጠር

የመንግስት ሰራተኛው በጥልቅ ተሀድሶው ውስጥ መሳተፉ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ የመንግስት ሰራተኛው የሀገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ ስራዎች በመሉ በጫንቃው የተሸከመና በመንግስት የሚነደፉትን ፖሊሲዎችና አቢይ ሀገራዊ እቅዶች በመፈጸምና በማስፈጸም በኩል ግንባር ቀደም ፈጻሚና ተዋናይ ነው፡፡

በሀገሪቱ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥና አፈጻጸም ዙሪያ በግልጽ በታዩ፣ ሕዝብን ባስከፉና ባስመረሩ አሰራሮች ሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ችግሮችን በተመለከተ ከመንግስት ሰራተኛው ጋር የፊት ለፊት ውይይት መደረጉ  የመፍትሄው አካል ተደርጎ መወሰዱ በተገቢነቱ  ይበረታታል፡፡

የተፈጠረውን ችግር በተጨባጭ ማሳየት ሁሉም የየበኩሉን ኃላፊነት ወስዶ የድርሻውን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ ወሳኝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሁሉም መስክ ከታች እስከ ላይ የተከሰቱት የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች ሀላፊዎችን ብቻ ሳይሆን ከስራቸው ያሉትን፣ በግንባር ቀድምነት የሚያሳትፉት የመንግስት ሰራተኞች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሙስና በባህርይው አንድ ሰው ብቻውን የሚሰራውና የሚፈጽመው አይደለም፡፡ የተቀናጀ የቡድን ስራ ነው፡፡ በየመስኩ በቢሮም ሆነ ከቢሮ ውጭ ያሉ ተሳታፊዎችን፣ አጋሮችን፣ ተባባሪዎችን፣ አስተላላፊ ደላላዎችን፣ ጉቦ ሰጪና ተቀባዮችን ይፈልጋል፡፡ አንድ ሀላፊ ተባባሪዎች ሳይኖሩት ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ ብቻውን ሊገባ አይችልም፡፡ በዚህም መልኩ ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ድረስ በተለያዩ አመታት በበርካታ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ከሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ደረጃቸው ቢለያይም እርምጃ (የተጠበቀውን ለውጥ ባያመጣም) ሲወሰድ ቆይቶአል፡፡

አንዱ ከስራ ሲቀነስ ሌላው ወደ ሕግ ሲቀርብ ሌላው ዝቅ ብሎ እንደጥፋቱ መጠን እንዲሰራ ቢደረግም ችግሩን ስርነቀል በሆነ ሁኔታ መፍታት አልተቻለም፡፡ በሌላው ላይ የተወሰደውን እርምጃ እያዩ፣ ሌሎች በስራው ላይ የሚሰማሩት አዳዲስ ሰዎች ተመልሰው እዛው ጥፋት ላይ ተዘፍቀው በተደጋጋሚ ታይቶአል፡፡ ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር ችግሩ ከጥቅም ጋር የተያያዘ መሆኑንና ከፍተኛ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ካልመጣ በስተቀር በተለመደው አካሄድ መሰረታዊ የሚባል ለውጥ ማምጣት የማይቻል መሆኑን ነው።

በዚህ ረገድ ውጤታማ ስራ ለመስራት ጥልቅ ተሀድሶውን በመንግስት ሰራተኛው ውስጥ ማካሄድና ማስረጽ ተገቢና ትክክለኛ አካሄድ ነው፡፡ ራሱን፣ አሰራሩን፣ ሕዝባዊ አገልግሎት አሰጣጡን በሰፊው እንዲፈትሽ፣ ስህተቱን በጥልቀት እንዲመለከት፣ ችግሩ ተመልሶም  እንዳይደገም ለማድረግ የሚያስችለውን እውቀት እንዲጨብጥ ያደርገዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን  በመፍታት ለሀገሪቱ ልማትና እድገትም ከፍተኛውን ድርሻ በመወጣት በኩል  የመንግስት ሠራተኛው የተቀናጀ ርብርብ በእጅጉ መሰረታዊ ነው፡፡ በአዲስ አበባና በክልሎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመንግስት ሠራተኞች የተሀድሶ ግምገማ ንቅናቄ መድረኮችን አካሂደዋል፤ በመካሄድም ላይ ይገኛሉ፡፡ ተሀድሶው አንድ ግዜ ብቻም ሳይሆን ምን ተሰራ? ካለፈው የተሻለ ምን ለውጥ ተገኘ? የቀድሞው ስህተቶች ታርመዋል፣ ተሻሽለዋል? ወይንስ በተለየ መልኩ ቀጥለዋል? እና የመሳሰሉትን በመፈተሽ በዘለቄታነት መሄድ አለበት፡፡

በተሀድሶው ውይይት ሕዝቡን ለምሬት የዳረጉ እየዳረጉም ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት  የሚያስችሉ ሀሳቦች በስፋት ተንሸራሽረዋል፡፡ ሠራተኛው በሀገሪቱ ለተመዘገቡ ለውጦችና ውጤቶች የጎላ አሻራ ቢኖረውም በሚስተዋሉ የብልሹ አሠራርና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራትና አመለካከቶች የራሱ ድርሻ  እንዳለው በግልጽ የተነገሩባቸው መድረኮች ናቸው፡፡

በተለይ ያልተሰሩ ተግባራትን እንደተሰሩ (የሀሰት ሪፖርት) የማቅረብ፣ ተልዕኮን ማዝረክረክ፣ የጠራ ግንዛቤ ያለመያዝ፣ ተገልጋዩን ሕብረተሰብ ማስቆጣት፣ ማማረር የአቅምና ከሥነ-ምግባር የሚመነጩ ክፍተቶች በሰራተኛው  ውስጥ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮች ሲሆኑ፤ ክፍተቶቹ የለውጥ ሥራዎች በአግባቡ እንዳይተገበሩ ከማድረግ በተጨማሪ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲባባሱ ከፍተኛውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡

የተጀመረው የጥልቅ ተድሀሶ  መድረክ ለሠራተኛው የጠራ ግንዛቤ በማስጨበጥና አቅም በመገንባት በየደረጃው ሕዝቡ ላቀረባቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡

ለተያዙት መሠረታዊ ሀገራዊ የልማትና የእድገት ግቦችና አላማዎች ስኬታማነት ሰራተኛው የድርሻውን እንዲወጣ ኃላፊነቱን በማሳወቅና በማሳሰብ ረገድ የጥልቅ ተሃድሶው መድረክ ወሳኝ ሁኖ በየዘርፉ ቀጥሎአል፡፡ ውይይቱ በአመራሩም ሆነ በሠራተኛው ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ክፍተቶችን በሰፊው የዳሰሰ፣ ችግሮችን ነቅሶ ያወጣና መፍትሄዎችንም በግልጽ ያስቀመጠ በመሆኑ የበለጠና የተሻለ ስራ ለመስራት መደላድል ፈጥሮአል የሚል ሰፊ እምነት አሳድሮአል፡፡ ውይይቱ መልካም አስተዳደርና  የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን በመፍታት ረገድ መነሻውን አካሄዱን በየስራ መስኩ በስፋት የሚስተዋሉትን ችግሮች ሕብረተሰቡን ለቅሬታና ለብሶት የዳረገው ምን እንደሆነ በመንግስት ሰራተኛው በኩል በግልጽ የሚታዩትን ችግሮች በስፋት ለመዳሰስና ለመመልከት ያስቻለ ነው፡፡

እንደየስራ ዘርፉ ባህርይ ቢለያይም ሁሉም ከሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚገናኙ መስሪያ ቤቶች መሰረታዊ የሆኑ የየራሳቸው ችግሮች ያሉዋቸው መሆኑን ሰራተኛው በተለያዩ መድረኮቹ ገልጾአል፡፡ የሕዝብ ቅሬታና መከፋት የተከሰተው እጅግ ብዙ በሆኑ የአገልግሎት ተቋማት ሲሆን በነዚህ ቦታዎች ውስጥ የሚሰራው ደግሞ የመንግስት ሰራተኛው ነው፡፡

ተሀድሶው ይህንን በአደባባይ የወጣና የሚታይ ግዙፍ ችግር ለመቅረፍ በሚቻልበት ደረጃ ነው ከሰራተኛው ጋር ግልጽ ወይይት የተደረገው፡፡ የተለያዩ፣  ከዝቅተኛው እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት ድረስ ያሉት ሃላፊዎች በሰራተኛው ፊት ቀርበው በራሳቸው ላይ ግለሂስ አድርገዋል፡፡ ሂደቱም አዲስ ጅምር በብዙ መልኩ በህዝብ ዘንድ የጎላ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት ፈጥሯል፡፡ ሀላፊዎችም ሆኑ ሰራተኞች ለሚፈፅሟቸው ስራዎች በቀጥታ በሕዝቡ (በሰራተኛው ፊት ቀርበው የማስረዳት ግዴታ ስላለባቸው ይህም ሀላፊነትንና ተጠያቂነትን በአደባባይ የሚያስከትል ስለሆነ በዚህ መልኩ መወቀስ የራሱ ከፍተኛ የስነልቦና ችግርም ስላለው እንዲጠነቀቁና ስራቸውን በሀላፊነት እንዲሰሩ  ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ጅምር መልካም ቢሆንም በሀሰት የመወንጀል፣ የስም ማጥፋት፣ የመጠቃቃት ሁኔታ እንዳይፈጥር ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የሚገልጹም በርካቶች ናቸው፡፡

ከሕዝብ ጋር ለሚደረጉት የቀጥታ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መፍትሄ ለማስገኘት የሚደረገው ጥረት በአንድ ግዜ ባይሆንም ደረጃ በደረጃ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፡፡ ተከታታይ የሆኑ ክትትሎችና የቁጥጥር ስርአት መዘርጋቱ ደግሞ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡

ጠንካራ የሆነ የቁጥጥርና የክትትል ስርአት መዘርጋቱ ተጠቃሚ የሚያደርገው ሕዝብና መንግስትን ነው፡፡ አዳዲስ የአሰራር ስርአቶችን ቀድሞ ከተለመደው ውጪ መዘርጋት ወሳኝ ሁኖ የመጣበት ወቅትም ላይ ነን፡፡ በመሆኑም በመንግስት ሰራተኛው በኩል የጥልቅ ተሀድሶው ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት ሊያገኝ ይገባል።