ኢትዮጵያ የ100 ሚሊዮን ህዝቦች መኖሪያ አገር ነች። ከዚህ በህዝብ ቁጥሯ ከአፍሪካ በ2ኛ ደረጃ ከሚስቀምጣት ህዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ወጣት ነው። የኢትዮጵያ የወጣቶች ቁጥር ከ52 የአፍሪካ አገራት የህዝብ ቁጥር ይበልጣል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ቁጥር በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ በ7ኛ ደረጃ ላይ ከምትገኘው ጎረቤታችን ኬንያ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ይበልጣል። የኬንያ ህዝብ በዛት 45 ሚሊዮን ነው።
ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የአንድ አገር ጉልበት ነው። ከፍተኛ የማምረት፣ አዲስ እውቀት የመቀበልና ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ የመጓዝ አቅም ያለው የህብረተሰብ ክፍል ነው። ወጣት ጉልበት የአንድን አገር ሰላምና መረጋጋት የሚያስጠብቅ የጸጥታና የመከላከያ ኃይል የሚገነባ የህብረተሰብ ክፍል ነው። በመሆኑም የአንድ አገር እድገትና ደህንነት ደረጃ ባላት የወጣቶች ቁጥር ሊሰፈር ይችላል። ይህ የሚሆነው ግን ወጣቱን በተገቢው መንገድ ማስተማር፣ ማሰልጠን፣ ስራ ላይ እንዲሰማራ ማድረግ፣ የአመለካከትና የፍላጎት መብትና ነጻነቶቹን ማረጋገጥ ሲቻል፣ ወጣቱ በአገሩ የመኖር ዋስትናው ሲረጋገጥና መጪ ህይወቱ በተስፋ ሲሞላ ብቻ ነው።
ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል በአግባቡ ማስተማር፣ ማሰልጠን፣ በስራ ላይ ማሰማራት ካልተቻለ ብሩህ አዕምሮና የተሟላ ጉልበት ያለው አምራች ዜጋ የአገር እዳ ይሆናል። ይህ ሁኔታ በማሽቆልቆል ላይ ያለ አገር ማሳያ ተደረጎም ሊወሰድ ይችላል። የሚንቀለቀል ስሜት ያለው ወጣት አስከፊና ተስፋ ቢስ የኑሮ ሁኔታን በጸጋ መቀበል አይችልም። በከፍተኛ ቁጣ ይቃወማል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተስፋ ያሳጣውን ሁኔታ ወይም ስርአት ለመለወጥ ይነሳል። ይህ የወጣትነት ነባራዊ ባህሪ ነው። ወጣቶቹን የዘነጋ የመንግስት ስርአት በእሳት እንደሚጫወት ይቆጠራል። በመሆኑም ለአገር ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ኪነጥበባዊ . . . እድገትና ደህንነት ወሳኝ የሆነውን ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ከስራ ውጭ ማድረግ እድገትን ከማሽመድመዱ ባሻገር የአገርን ሰላምና መረጋጋት ያናጋል። መድረሻው ምንም ይሁን ምን የስርአት ለውጥ መምጣቱ አይቀሬ እንዲሆን የሚያደርግ ነባራዊ ሁኔታም ይፈጥራል።
የ50 ሚሊዮን ወጣቶች ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ ለዚህ አፍላ የህብረተሰብ ክፍል ልዩ ትኩረት ሰጥታለች። የማምረት አቅም ያለው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ለመፍጠር የትምህርት እድል አስፋፍታለች። በአሁኑ ጊዜ ዕድሜአቸው የደረሱ ህጻናት የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት እድል አግኝተዋል። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትና የቴክኒክና ሞያ ስልጠና እድል አግኝተዋል። ከግማሽ ሚሊዮን የማያንሱ ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የመከታታል እድል አግኝተዋል። ይህ አምራች ወጣት የህብረተሰብ ክፍል የመፍጠር መሰረታዊውና ቀዳሚው ተግባር ነው። ወጣቱን ለአምራች ዜግነት ማብቃት በራሱ ግን በቂ አይደለም። በተጨባጭ በምርት ስራ ላይ እንዲሰማራ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ችግሮች አሉ።
ከአስር ዓመት በፊት በ1998 ዓ/ም ወጣቶችን የማምረት ስራ ላይ በማሳተፍ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት አንቀሳቃሽና የእድገቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ ተቀርጾ ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህም በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶች በመንግስት በሚደረግላቸው የፋይናንስ፣ የመስሪያ ቦታ፣ የሞያ፣ የገበያ ትስስር ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ይህ ፓኬጅ እየከረመ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም። ይህን ሁኔታ የኢፌዴሪ መንግስት ተገንዝቧል። የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ይህን አስመልክተው በ5ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የስራ ዘመን መከፈቻ የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤
መንግስት የወጣቱን ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደተንቀሳቀሰ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ ከ3ኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ ተቀርፆ በተካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩም ይታመናል። ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው መፍትሄም ሆነ በዚህ ላይ በመመስረት የተከናወነው ስራ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጐት ጋር ፈፅሞ የሚመጣጠን እንዳልሆነ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና ተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአፈፃፀም ብቃት መጓደልና በስነ ምግባር ጉድለቶች ሲደነቃቀፉ የወጣቱ ትውልድ ቅሬታ እንደሚባባስ ታይቷል። በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች በመሰረቱ ከኢኮኖሚ ፍላጐትና ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮች የራሱን የወጣቱን ትውልድ በቀጥታና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን በሚያሳትፍ አቅጣጫ መፍታት ጊዜ የማይሰጥ ተደርጐ ሊወሰድ ይገባዋል።
ብለው ነበር።
በዚህ መሰረት ከአስር ዓመት በፊት በተዘጋጀው የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። ጉዳዩን በባለቤትነት የያዘው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ባለፈው ወር መግቢያ ላይ እንዳስታወቀው፣ የወጣቶች የልማትና የእድገት ፓኬጅ ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ለማሻሻል የተከለሰው የወጣቶች የልማትና የእድገት ፓኬጅ በየጊዜው የሚነሱ የወጣቶችን ጥያቄዎች በሚመልስ መልኩ የተቀረፀ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በፓኬጁ መሰረት መንግስት ከክትትልና ድጋፍ ሚናው በተጨማሪ የወጣቶችን ጉዳይ የሚከታተል አደረጃጀት በየደረጃው ባሉ እርከኖች ያቋቁማል።
በፓኬጁ ዙሪያም ለወጣቶች ግንዛቤ ለመፍጠር ባለፈው ወር የአስራ አምስት ቀን ስልጠና ተሰጥቷል። ሁሉንም ወጣቶች ፍትሀዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ትክክለኛ የስራ አጥ ቁጥር የመለየት ስራ እየተከናወነ ይገኛል። ስራ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ቢያንስ አምስት ሆነው በመደራጀት በየአካባቢያቸው ባሉ አዋጭ የሥራ መስኮች ላይ እንዲሰማሩ እንደሚደረግ፣ በግብርና ስራ የመሬት አቅርቦት እጥረት ስላለ በገጠር ያሉ ወጣቶች የመሬት ይዞታ በማይፈጁ እንደ ዶሮ፣ ከብትና ንብ ማርባት ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ እንደሚደረግም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ወጣቶች በማደግ ላይ በሚገኘው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ በመሳተፍ የአገሪቱ እድገት ሞተር ሆነው ከእድገቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የሚጠይቀው ፖሊሲና ፓኬጅ ብቻ አይደለም። በተለይ በስራ ፈጠራ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እጃቸውን ሸበቦ የያዘውን የካፒታል እጥረት መፍታት ይሻል። መንግስት ለዚህም መፍትሄ አበጅቷል። ይህን ለስራ ፈጣሪ ወጣቶች የሚደረግ የፋይናንስ አቅርቦት በተመለከተ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በምክር ቤቶች የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ ባደረጉት የመንግስትን ዓመታዊ የስራ ክንውን አመልካች ንግግራቸው ገልጸውታል። ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር የሚከተለውን ብለው ነበር።
. . . ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት እድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል። ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን የግድ ይላል። በዚህ መሰረት፣ መንግስት በያዝነው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን ይጀምራል። ለዚህም ሲባል ለፈንዱ ማቋቋሚያ አሥር ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን የወጣቶችን ተሳትፎና ቁጥጥር በሚያረጋግጥ ተዘዋዋሪ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። ለወጣቶች የስራ መነሻ ይሆን ዘንድ ከተመደበው ፈንድ ጐን ለጐን የስራ ፈጠራው የሚያተኩርባቸው መስኮች ተለይተውና ከወጣቶች ጋር ተመክሮባቸው መግባባት ላይ እንዲደረስባቸው ይደረጋል።
በዚህ መሰረት፤ የህዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት የ10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ አጽድቋል። በአዋጁ መሰረት በስራ ፈጠራ ፈንዱ ተጠቃሚ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ18 እስከ 34 አመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። አዋጁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈንዱን በፌዴራል መንግስት ስም እንዲያስተዳድር ሃላፊነት ሰጥቷል። በአዋጁ መሰረትም ብድሩ በአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት አማካኝነት የሚፈጸም ይሆናል። ተቋማቱ በማይገኙበት ሁኔታ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቋማቱን ተክቶ እንዲሰራ ይደረጋል። ከዚህ ባለፈም ፈንዱን በዝርዝር እየመረመረ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት የሚያቀርብ ይሆናል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችም በየደረጃው ማስተግበር የሚያስችል ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ለዚህ አገልግሎት በቀጣይ 6 ወራት በስራ ላይ የሚውል በጀትም ተመድቧል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ለፌዴራል መንግስት የ18 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ሲያጸድቅ፣ ከዚህ ውስጥ 5 ቢሊዮን ብር ለወጣቶች የስራ አድል ፈጠራ ተንቀሳቃሽ ፈንድ እንዲውል መወሰኑ ይታወሳል።
ከላይ እንደተመለከተው፤ አገሪቱ አምራች የሆነውን የወጣት ሃይሏን በመጠቀም የኢኮኖሚውን እድገት ለማስቀጠል፣ ወጣቱንም ከእድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ተጨባጭ እርምጃዎች ወስዳለች። አሁን የሚጠበቀው በወጣቱ በኩል ያለ የስራ ተነሳሸነት ነው። ወጣቱ ስራ ሳይንቅ የሚችለውንና አዋጭ የሆነውን፣ አገሩን ጠቅሞ ራሱን መለወጥ የሚችልበትንና፣ ከራርሞ የሚወደውን ስራ መስራት የሚያስችል አቅም የሚፈጥርለትን ማንኛውንም ስራ ለመሰራት መዘጋጀት አለበት። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ያለውን ነባር ስራ ላይ ያለውን የጥላቻ/የንቀት አመለካከት መስበር ይሻል። የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ወጣት፣ አጠቃላይ ህብረተሰቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወዘተ. ያለፉ ስርአቶች ውርዴ የሆነውን ስራ የመናቅ አመለካከት በመስበር ወጣቱ በተገኘው የስራ መስክ እንዲሰማራ ለማነሳሳትና ለማበረታታት መትጋት አለባቸው።