በ28ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ መሪ ቃል ”Harnessing demographic dividend to investment in youth” የሚል ነው። ተሰናባቿ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ ወጣቶቿ ላይ የበለጠ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባት አሳስበዋል።
ተሰናባቿ ሊቀመንበር እንደገለጹት አፍሪካ እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት መካከል ያሉ ለጋ ወጣቶች ቁጥር ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጋ እንደሆነ፤ እንዲሁም አፍሪካ በ2025 እድሜያቸው ከ25 አመት በታች ከሆኑ የአለም ወጣቶች መካከል አንድ ሦስተኛው ለሚሆነው ወጣት መኖሪያ ትሆናለች።
በመጪዎቹ አሥርት ዓመታት ሌሎች ዓለማት በአዛውንቶችና በጡረተኞች ሲጥለቀለቁ አፍሪካ በወጣት ልጆቿ ትደምቃለች ሲሉ ተሰናባቿ ኮሚሽነር ተስፋቸውን ገልጸዋል። ይሁንና ይላሉ ድላሚኒ ዙማ ይህን ታላቅ ሃብት በአግገባብ መያዝ ይኖርበታል። ዙማ አበክረው እንደገለጹት አፍሪካ ወጣቶቿ ተገቢው የሙያ ስልጠናና የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንዲያገኙ፣ ተገቢው ይስራ እድል መመቻቸት ይኖርባታል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነት ቦታ የተረከቡት የጊኒው ፕሬዝዳንትም አፍሪካ ለወጣቶቿ ትክረት ሰጥታ መስራት እንዳለባት አሳስበዋል። የዚህ ዓመት የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ዋና ርዕሰ ጉዳይ ወጣቶች ላይ እንዲያጠነጥን የተደረገበት ምክንያት በሁለት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ተመርኮዞ ነው። የመጀመሪያው የአህጉሪቱ የስነ-ህዝብ አወቃቀር በወጣቶች እየተገነባች በመምጣቷ ሲሆን፤ ሁለተኛው ቁልፍ ጉዳይ “አፍሪካ ከዚህ የሰው ሀብቷ ልታተርፍ ይገባል” የሚል ዓላማ ያነገበ ነበር፡፡
በአህጉሪቱ የወጣቶች ቁጥር መብዛት መንታ ውጤት ያለው ነው። አፍሪካ ይህን ወጣት ኃይል በአግባብ መጠቀም ከቻለች የመቀየር ትልሟ ይሳካል። ካልሆነ ግን አህጉሪቱን ወደ ባሰ ችግር ሊከታት እንደሚችልም በጉባዔው ተወስቷል፡፡
ህብረቱ በስሩ ካቀፋቸው ስምንት ኮሚሽኖች መካከል በአንጻራዊነት ውጤታማ እየተባለ የሚወደሰው ግጭቶችን የመከላከል እና የመፍታት ሚና ያለው የሰላምና የጸጥታ ኮሚሽን ነው፡፡ በጉባዔው ላይ መሪዎቹ የወጣቶችን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ከስምንቱ ኮሚሽኖች፤ የወጣቶችን ጉዳይ እንዲያስተናብር ኃላፊነት የሰጡት የሰዉ ሐይልን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በአንድ አጣምሮ የያዘው ኮሚሽን ላይ ነው። ይሁንና አንዳንዶች የአፍሪካ መሪዎች በጉባዔ ላይ ትላልቅ ውሳኔዎችን ቢያሳልፉም በተግገባር አይተረጉሙትም የሚል ሥጋት አድሮባቸዋል።
የወጣቶችን ጉዳይ በሚመለከት የኢፌዴሪ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት በአጭሩ ለመቃኘት ያክል አንዳንድ ነገሮችን ለማንሳት ወደድኩ። የኢፌዴሪ መንግሥት የወጣቱን በልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅርቡ የገባውን ቃል ጠብቆ አስር ቢሊዮን ብሩን ዝግጁ አአድርጓል። ከዚህ ባሻገር መንግስት ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑባቸውን በርካታ ፕሮጀክቶች ተግብሯል።
ለአብነት ያክል ለዜጎች በተለይ ለወጣቶች የትምህርት እድል ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት አድርገግል። መንግስት በየደረጃው ያለውን የትምህርት ሽፋን ለማሳደግ ጠንክሮ መስራት በመቻሉ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ችሏል። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ዘመን ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ የአንደኛ ደረጃ /ከ1-8/ ንጥር ተሳትፎ መጣኔ በ2002 ከነበረበት 82 በመቶ በ2007 ወደ 96.9 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ተግገባር ነው።
በተመሳሳይ የሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ እርከን /ከ9-10/ ጥቅል ተሳትፎ ወደ 40.5 በመቶ እንዲሁም የመሰናዶ ትምህርት /ከ11-12/ ጥቅል ተሳትፎ ወደ 11.12 በመቶ በማሳደግ ስኬታማ አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በትቁሳቁስ የማሟላት ሥራ እና በአይሲቲ ማስፋፋት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በተመሳሳይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና እና የከፍተኛ ትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም መሠረት በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ወቅት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና የቅበላ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ረገድ አሁን ላይ በፌዴራል መንግሥት ብቻ (በግንባታ ላይ ያሉ አስር አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ሳይጨምር) ከ35 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን በተለያዩ ዘርፎች በማሰልጠን ላይ ናቸው። በሁሉም የቅድመ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች ማለትም በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት እና በርቀት ተሳትፎን በተመለከተ በ2008 ዓ ም 755,244 ማድረስ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ዓመት በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ከአርባ ሺህ በላይ ሰልጣኞች ተመርቀዋል፡፡
በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠና ሥርዓትን ከልማት ተግባር ጋር የተቆራኘ እንዲሆንና ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አብሮ እንዲራመድ የተጀመረውን የዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ቁርኝነት ለመፍጠር ጥረት በመደረግ ላይ ነው። በከፍተኛ ትምህርት ማስፋፋት ረገድ መንግሥት ለወጣቱ ከሰጠው ትኩረት የመጀመሪያውና ትልቁ ነው ቢባል አያንሰውም።
በሌላ በኩል ሥራ ፈጠራን ለማበረታታት መንግሥት ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ሥራ መፍጠር እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግሥት እያደረጋቸው ካሉ በርካታ ስራዎችን መካከል ዘንድሮ ብቻ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ቃል የገባውን የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ የሚያቋቁም አዋጅ፣ ባሳለፍነው ሣምንት ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፀድቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ለወጣቱ የገባውን ቃል ፈጽሟል። ወጣቱም ይህን የመንግሥት ድጋፍ በአግባብ ሊጠቀምበት ይገባል። ፈንዱን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ይሁንና ብድሩን ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ሥራ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሰሩ ተወስኗል። በሁሉም አካባቢ ያሉ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በሌሉበት የአገራችን ክፍሎች የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብድሩን እንዲያቀርቡ ተደንግጓል፡፡
በዚህም መሠረት የንግድ ባንክ ኃላፊነት ለክልሎች የተደለደለውን በመለየት ለሚመለከታቸው አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ማስተላለፍ፣ ተቋማቱ የተላለፈላቸውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ማዋላቸውን መቆጣጠር፣ ስለፈንዱ ገንዘብ አጠቃቀም ዝርዝር መግለጫ የያዘ ሪፖርት በየስድስት ወሩና በየዓመቱ የተመረመረ የፈንዱ ሒሳብን ለገንዘብና ለኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ማቅረብ ይገኙበታል፡፡
ከፈንዱ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት በ18 እና በ34 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ማንኛቸውም ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን አዋጁ ያመለክታል፡፡ ከፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆንም በጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ መደራጀት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ብድሩን ለማግኘት የንብረት ዋስትና የማይጠየቁ መሆኑን ተመልክቷል፡፡ ይሁንና ወጣቶች ከፈንዱ ለሚያገኙት ብድር ኃላፊነት እንዲሰማቸው ግን እርስ በርሳቸው ዋስ እንዲገቡ ይጠየቃል፡፡
የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲን ለማቋቋም በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት ሳይጨምር፣ የቤተሰቡን አባላትና ተቀጣሪ ሠራተኞችን ጨምሮ አምስት ሰዎችን የሚያሰማራና ጠቅላላ የካፒታሉ መጠን ሕንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከሆነ 50 ሺህ ብር፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሆነ ከብር አንድ መቶ ሺህ ያልበለጠ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንዱ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉ ወጣቶች ሊያገኙ የሚችሉት የካፒታልና የሥራ ማስኬጃ ብድር በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሆነ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር፣ በአገልግሎት ከሆነ ደግሞ እስከ 50 ሺህ ብር ነው፡፡