“ባንኮቻችን ጡንዎቻቸውን እስኪያፈረጥሙ ድረስ በሩን አንከፍተውም”
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ
ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የቱርክና የኢትዮጵያን ግንኙነት "ወደከፍተኛ ደረጃ ያደርሳል" ተብሎ የታመነበትን ጉብኝት ሰሞኑን በቱርክ፣ አንካራ ማካሄዳቸው ይታወቃል። በጉብኝታቸውም ቱርክ በኢትዮጵያ የምታካሂደውን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አጠናክራ እንድትቀጥል መጠየቃቸው፤ ባለሀብቶቹ የሃገራችንን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ፣ በተለይም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ ሃገር እንደሚለውጥ ከተመለከተው በወጪ ንግዱ ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እና ደረጃ ምን እንደሚመስል ለሚቃኘው ለዚህ መጣጥፍ መነሻ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ350 በላይ የቱርክ ኩባንያዎች ሦስት ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ-ነዋይን በማውጣት በሰፋፊ የልማት ዘርፎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ቱርክ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ከምታደርገው ኢንቨስትመንት 50 በመቶ ያህሉን ይሸፍናል። ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ በኢንዱስትሪው በተለይም በማምረቻው ዘርፍ እያደረገች ላለው እንቅስቃሴም የቱርክ ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን እየተነገረ ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 ቱርክ ወደ ኢትዮጵያ የ385 ሚሊዮን ዶላር ግብይት ያደረገች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ወደ ቱርክ የምትልከው የንግድ መጠን ግን 35 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ይህን የንግድ ግንኙነት በማሳደግ በ2020 ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መግባባት ላይ መደረሱን የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት ተከትሎ ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
የሃገሪቱ ባለስልጣናት በአውሮፓና አሜሪካ እያደረጉ የሚገኙት የንግድና ኢንቨስትመንት ቅስቀሳ የሚያሳየን አንዳች ነገር ቢኖር ሃገር ይለውጣል ተብሎ በተያዘው የማኑፋክቸሪንግ እና የወጪ ንግድ ዘርፍ የሃገር ውስጡ ባለሃብቶች ሚና እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ነው።
ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የሃገራችን ከፍተኛ ባለስልጣናት በዚሁ የንግድና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ስራ ተጠምደዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ከወል ስትሪት ጆርናል ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቆይታ የአሜሪካ መንግስት የቻይናን ተሞክሮ በመውሰድ በአገር ውስጥ ሥራ ፈጠራ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ መግለጻቸው ለዚሁ የዲፕሎማሲያዊው ጥረት የተሰጠው ልዩ ትኩረት የት ጋር እንዳለ አመላካች ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ "ቻይና ሞዴል የሆነችው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ለአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደርም ነው፤ ቻይናውያን በአገራቸው እያስፋፉ ያሉት የማምረቻ ዘርፍ ለአሜሪካም ሞዴል ሊሆን ይገባል፡፡" በማለት ለጆርናሉ መናገራቸውን ከዘገባው የተመለከትን ሲሆን፤ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቁልፍ የንግድ አጋርነትንና ሽብርተኛነትን በመዋጋቱ ረገድ ትብብራቸውን ማሳደግ አለባቸው ሲሉ ማሳሰባቸውን ጭምር ከዘገባው ተመልክተናል።
ማየታችን በማምረቻ ዘርፉም ሆነ በወጪ ንግድ እንቅስቃሴው ላይ የሃገር ውስጡ ባለሃብቶች ተስፋ እያስቆረጡ መሆኑን እንድንጠረጥር ገፊ ምክንያት ነው።
የኢትዮጵያ ስፋት፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና ጠንካራ ወታደራዊ አቅም አገሪቱን ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግረዋታል፡፡ አስቀድሞ በድርቅና በእርዳታ ትታወቅ የነበረች አገር ገፅታ አሁን ፍፁም በመለወጡ ምክንያት ሃገራት አይናቸውን ሳያሹ የ”ኑ እና ኢንቨስት አድርጉ” ጥሪዋን እየተቀበሉ ነው፡፡
ለ17 አመታት የቆየው ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ ሸቀጥ የማስገባት እድል ወይም “አጎዋ”ን ለማስቀረት አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የያዙት አቋም በባራክ ኦባማ የአስተዳደር ዘመን በ2015 ታድሷል፤ ስምምነቱም 40 የአፍሪካ አገራት ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የንግድ ልውውጥ እንዲያሳድጉ አግዟቸዋል፡፡ "የአጎዋ ደንብ ለመጪዎቹ አስር አመታት እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ," በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ለጆርናሉ ተናግረው የፕሬዘዳንት ትራምፕ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" መልእክት እውን እንዲሆን የቤጂንግን ሞዴል መከተል ይገባል ማለታቸው የዚሁ የንግድና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አካል ነው፡፡
በኩል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጆርናሉ ይህን መልእክት ሲያስተላልፉ መነሻቸው ለሁለት አስርት አመታት የተመዘገበው ተከታታይ ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገትና ቀጣይነቱ የአገሪቱን በራስ የመተማመን ደረጃ ከፍ ያደረገው መሆኑን መገመት አይከብድም፡፡
የአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን በሪፖርቱ መጥቀሱም አይዘነጋም፡፡
መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረትና በርካታ ማበረታቻዎች ሌላኛው የውጭ ባለሃብቶች አይናቸውን ሳያሹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያደረገ ምክንያት ነው፤ ቀደም ባሉት ስርአቶች የመንግስት የነበሩት ተቋማት ወደግል ይዞታ እንዲዛወሩ መደረጉም እንደዛው።
ከ200 የበለጡ የመንግስት የንግድ ድርጅቶች ባለፉት ሀያ አምስት አመታት ለባለሐብቶች ተላልፈዋል፡፡ ኬኬአር ኤንድ ኩባንያው በአበባ ምርት፣ የቱርክ፣ የቻይና እና የአሜሪካ ኩባንያዎች በጨርቃ ጨርቅና ጫማ ማምረት ዘርፍ በመሰማራት በሺ ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ያስገኙ መሆኑም ሌላኛው እና ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ስለመሆናችን ጥቂቶቹ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በ2011 ሶስት የመንግስት ቢራ ፋብሪካዎች ለዲያጆና ሔኒከን ኢንተርናሽናል በግማሽ ቢሊዮን ዶላር የተሸጡ ሲሆን ባለፈው አመት የጃፓኑ ሲጋራ አምራች ኩባንያ በ510 ሚሊዮን ዶላር ከመንግስትን የትንባሆ ማምረቻ የ40 በመቶ ድርሻ ገዝቷል፡፡
መንግስት ከነዚህ ዘርፎች በሚያገኘው ትርፍ በመታገዝ የባቡር መስመር ዝርጋታንና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ያካሂደበታል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሐብቶች ክፍት ቢሆን በአገሪቱ ያሉትን ባንኮች ይውጧቸውና እስከዛሬ ለምቶ ያየነውን ጨምሮ ወደፊትም በሚሆነው ላይ ሁሉ ጋሬጣ መሆናቸው አያጠያይቅምና ጉዳዩ በዚህ መልኩ ሊሰላና ከነጻ ገበያ መርሆ ጋር የሚያጣርሰው አንዳችም ነገር እንደሌለ ለይቶ መገንዘብ ተገቢ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የሚያከናውናቸው የገዘፉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የኢትዮጵያ የእድገት ስትራቴጂ ዋነኛ መሰረት ሆነው ይቀጥላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም "ባንኮቻችን ጡንቻቸውን እስኪያፈረጥሙ ድረስ በሩን አንከፍተውም፡፡" ሲሉ ለጆርናሉ ማረጋገጣቸው ስለዚሁ እና ስለሃገራችን ልማት ጠቃሚ የሆነውን መንገድ ለማጠየቅና በማንም የማንጠመዘዝበት ደረጃ ላይ ስለደረስን መሆኑ አያጠያይቅም።
የእንግሊዝ የታዳሽ ኃይል ኩባንያዎች ከ850 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የገናሌ ዳዋ ቁጥር 6 የኃይል ማመንጫና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ሊገነቡ እንደሆነ መሰማቱም የዚሁና የደረስንበትን ደረጃ የሚያጠይቅ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኩባንያዎቹ 250 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን ገናሌ ዳዋና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ያከናውናሉ። የመስኖ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች 27 ሺህ ሄክታር መሬትን ለማልማት የሚያስችል እንደሆነም የኩባንያዎቹ የስራ ሃላፊዎች ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኩባንያዎቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት በገናሌ ዳዋ 6 የኃይል ማመንጫ ግንባታ በማህበራዊና አካባቢያዊ ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተጽዕኖ የዳሰሳ ጥናት ያካሄዱ ሲሆን፤ ለሁለቱም ፕሮጀክቶች ግንባታ ከ850 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ እንደተመደበ እና ለ55 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንደሆነም መረጃዎቹ ገልጸዋል።
በዚሁ ልክ ደግሞ በወጪ ንግድ ዘርፍ ያለው አፈጻጸም የማያመረቃ በመሆኑ የውጮቹን ባለሃብቶች መጋበዝ ተገቢ ይሆናል። ምክንያቱም አገሪቱ የወጪ ንግድ በአማካይ በ36.3 በመቶ እንደሚያድግ የሚያመላክት ግብ ከተጣለ ሁለት ዓመታት ቢያልፉም እስካሁን ጠብ ያለ ነገር ያልታየ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ግብ በአምስት ዓመቱ የዕትእ ዕቅድ ዘመን ውስጥ ይሳካል ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን፣ በ2007 በጀት ዓመት የተገኘውን 3.01 ቢሊዮን ዶላር ታሳቢ በማድረግ ከ2008 በጀት ዓመት ጀምሮ ከጠቅላላው የአገሪቱ የወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ የተቀመጠው ትንበያ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በተግባር እንደታየው ግን በ2008 በጀት ዓመት የተመዘገበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከተተነበየው ከ1.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዝቅ ያለ ነው፡፡
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን መጨረሻ (2007 ዓ.ም.) ወቅት፣ ከወጪ ንግድ 6.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ሲጠበቅ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በ2002 ዓ.ም. የተገኘውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር መነሻ በማድረግ የተሰላው ይህ ዕቅድ በ2007 ዓ.ም. ያስገኘው ውጤት ግን ከግማሽ በላይ ያነሰ ሆኖ ነው፡፡
በመጀመሪያው የዕቅዱ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በዓመት በአማካይ የተገኘው ገቢ 3.1 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ለወጪ ንግድ ከሚቀርቡ ሸቀጦች መካከል ከቡና 783.3 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቅባት እህሎች 481 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጥራጥሬ 200.3 ሚሊዮን ዶላር ማግኘትን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ ይሁንና ከቡና የገቢ ዕቅድ ውስጥ 61 በመቶ፣ ከቅባት እህሎች 64 በመቶ፣ ከጥራጥሬ 42.4 በመቶ ብቻ ውጤት ተገኝቶ ዕቅዱ ተደምድሟል፡፡ ከ2008 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ ዕቅዱ ማጠቃለያ 2012 ድረስ የተቀመጠውም የወጪ ንግድ ገቢ ትንበያ አገሪቱ በዘርፉ እመርታ የምታሳይበት ይሆናል ቢባልም ከጅምሩ ዕቅዱና ክንውኑ ሳይገናኙ ቀርተዋል፡፡ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ (በ2012 ዓ.ም.) የወጪ ንግድ አጠቃላይ ገቢ 13.9 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ተገምቷል፡፡ እንደትንበያው ከሆነ በ2009 ዓ.ም. 6.7 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2010 ዓ.ም. 8.7 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2011 ዓ.ም 11.03 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2012 ደግሞ 13.9 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ታሳቢ ቢደረግም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ያለውና እስከ 2009 ዓ.ም. አጋማሽ የታየው አፈጻጸም በዕቅዱ መሠረት ገቢው እያደገደ እንዳልሆነ ነው፡፡
መንፈቅ ዓመቱን ካገባደደው የ2009 በጀት ዓመት፣ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ቢጠበቅም ባለፉት አምስት ወራት የተገኘው ግን 1.57 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በአምስቱ ወራቶች ውስጥ ይገኛል የተባለው ገቢ እርግጥ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ በአምስቱ ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ በዕቅድ ከተያዘው ግብ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑ ብቻም ሳይሆን ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር በንፅፅር ሲታይ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ የታየበት በመሆኑ፣ አሁንም የታሰበውን ያህል ገቢ ማስገኘት ያልቻለ ዘርፍ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በሁለቱም የዕቅድ ዘመኖች ውስጥ ዋና የወጪ ንግድ ገቢ ምህዋር የሆኑት የግብርና ምርቶች ናቸው፡፡ ከግብርና ምርቶች ውስጥ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቀንድ ከብትና የጫት ምርቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ምርቶች የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ70 እስከ 80 በመቶ በላይ ድርሻን ይዟል፡፡
የ2009 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ መረጃ እንደሚጠቁመው እነዚህ ምርቶች ቀዳሚ የወጪ ንግድ ገቢ ማስገኛ ቢሆኑም፣ በአፈጻጸም ደረጃ ከዕቅድ በታች እየተመዘገበባቸው በመሆኑ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ይገኛል ተብሎ የታቀደውን 4.8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የማይቻል እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉና በቆዳና በቆዳ ውጤቶች በጨርቃጨርቅና መሰል የማምረቻ ዘርፎችን ጨምሮ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ከዚህ የበለጠ ግብዣና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ የመንግስት ቁልፍ ተግባር ሆኖ ሊቀጥል ይገባል።