መንግሥት በቀየሳቸው የልማት አቅጣጫዎች ሀገሪቱ በእጅጉ በመለወጥ ላይ እንደምትገኝ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ህገ-መንግሥታችንም ልማት የመብት ጉዳይ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የልማት ዋነኛው ዓላማም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ነው፡፡ ይህም በህገ-መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡
መንግሥት ልማትን በተለይም ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ መረባረብ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ህገ-መንግሥቱ ለ17 ዓመታት ሰፍኖ የነበረውን የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት በመቀየር፣ በተመረጠ አኳኋን የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያለበት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንዲመራ ማድረግ ብሎም የተፋጠነ ዕድገትን በማረጋገጥ ሀገሪቱ ከነበረችበት የከፋ ድህነትና ኋላ ቀርነት ችግር ማላቀቅን ዓላማው አድርጓል፡፡
እንደሚታወቀው የገበያ መር ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተከትሎ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተነድፎ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህም በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ለልማታዊ የግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን መንግስት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡
ባለፉት ሥርዓቶች የወጡና የግሉን ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚገቱ ህጎችና ደንቦች በአሁኑ ወቅት ተወግደዋል፡፡ በዚህም ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ በመለወጥ መንግሥት በየጊዜው የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ በየጊዜው ከታዩ ልምዶች ትምህርት በመውሰድ ጥንካሬዎቹን የማጎልበት ድክመቶቹን የማረም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩም መምጣታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
በህገ መንግሥቱ የሚፈለገው ዓይነት ፈጣን ዕድገት ደግሞ ልቅ በሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ብቻ ሊረጋገጥ የማይችል በመሆኑ ካለፈው ትምህርት መውሰዱ ተገቢ ይሆናል።
ልቅ የሆነ የገበያ ሥርዓት ዘላቂና ሰፊ መሰረት ያለው ዕድገት የማምጣት አቅም እንደሌለው እና ይልቁንም የህዝብንና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሰማሩ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም በሂደት መንግሥት የማይተካ ልማታዊ ሚና የሚጫወትበት የነፃ ገበያ ሥርዓት መከተል እንደሚገባ ታምኖበት በመስራት ላይ ይገኛል።
መንግሥት የግሉና የመንግሥት የዘርፎች ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች እየተከተለ ነው።
ይህም መንግስት ታዲያ እዚህ ላይ የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል የሚካሄድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል።
ይህ ሁኔታም እንደ መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን የግሉ ባለሃብት በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል።
እርግጥ ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።
አሁንም ግን ከዕድገት ደረጃችን ጋር ተያይዞ ከሚኖረው የገበያ ጉድለት እና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዞ ሊከሰትና ፈጣን ዕድገቱን ሊያስተጓጉል የሚችለው አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። አደጋውን ለማስቀረት አስቀድሞ የተለየና መፍትሔም የተቀመጠለት ጉዳይ ሆኗል።
በመሆኑም የመሬትና የባንክ አስተዳደር ሥርዓቶቹ እንደታቀደው ልማትን በሚያፋጥንና የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተሟላ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው መንግሥት በጽኑ ያምናል። ማመን ብቻም ሳይሆን፣ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱም ፍትሃዊ ውድድርን የሚያሰፍንና ህጋዊ ያልሆነ ጥቅምን የሚዘጋ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ማከናወኑንም ቀጥሏል። በዚህም የመንግሥት ተሳትፎ የባለሃብቱን ልማታዊ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ መሆኑም በገሃድ እየታየ ነው።
በተለይም ባለፉት 25 ዓመታት መንግሥት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥበብ በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ሂደት ውስጥ ውስን ሃብቱን መሰረታዊ ችግሮችን በሚፈቱ የልማት ሥራዎች ላይ አውሏል። የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እና የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትንና ማህበራዊ ልማትን ማረጋገጥ ችሏል።
ከዚህ ጎን ለጎንም መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተውባቸዋል።
ባለፈው የበጀት ዓመት የተመዘገበው አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገት መመዝገቡ ለሀገራችን መፃዒ ዕድል ትልቅ ብስራት ነው። በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከበፊቱ የተሻለ ጥረት ለማድረግ የሚመለከተው አካል ሁሉ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ይገኛል።
ከዚህ አኳያ የመንግሥት ደጋፊ ተቋማት አቅም ለማሳደግ የፋብሪካዎች የቴክኖሎጂና የማኔጅመንት አቅም ካደገ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ልማትን በማስፋፋት የተፋጠነ ልማትን ለማረጋገጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ይገኛል። በመሆኑም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዋና ዋና ዘርፎች፣ በተለይም በግብርና ልማት እንዲሁም በኢንዱስትሪ መር አቅጣጫን በቀዳሚነት የገቢ ምርት መተካት ላይ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው።
ምንም እንኳን ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ በኢንቨስትመንቱ ላይ ጉዳት ቢደርስም መንግስት ተገቢውን ካሳ በመክፈል ጭምር ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል። በተፈጠረው ሁከት ችግር ደርሶባቸው የነበሩ ባለሃብቶችን በብድር መልክ እንደ አዲስ ከማቋቋም አንስቶ ከውጭ የሚያስገቧቸውን ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲያስገቡ በመፍቀድ ጭምር መንግስት ተገቢውን ድጋፍ አድርጎላቸዋል።
ይህም መንግስት ለሀገራችን ኢንቨስተሮች ሙሉ ዋስተና የሚሰጭ ከመሆኑም በላይ፤ ማንኛውም ባለሃብት እዚህ ሀገር ውስጭ ለሚያፈሰው መውዓለ ነዋይ መንግስት ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታም በሀገራችን ውስጥ የተጀመረው የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዳይስተጓጎል አድርጎታል።