“ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በምታደርገው መዋቅራዊ ሽግግር ውስጥ የህብረት ስራ ማህበራት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል”
-የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለፁት ከመሰንበቻው የህብረት ስራ ማህበራት አራተኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል ሲከፈት ባሰሙት ንግግር ነው። ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ከሶስት መቶ በላይ የህብረት ስራ ማህበራትና የግብአት አቅራቢ ተቋማት በኤግዚቪሽኑ ላይ ተገኝተዋል። በባዛሩ ላይ የግብርና ምርቶች፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ የዕደ ጥበብ እና ሌሎች የስራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የህብረት ስራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን አቅርበዋል። እርግጥ እነዚህ ማህበራት ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ መንግስት ዘርፈ ብዙ ዕገዛ አድርጓል።
ገና ከምስረታቸው ጀምሮ መንግስት ለማህበራቱ የሚያስፈልጋቸውን ዕገዛ ሁሉ ገቢራዊ አድርጓል። እንደሚታወቀው ተመሳሳይ ፍላጎት ባላቸው ሰዎች መካከል በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ህብረት በመፍጠር ገንዘብን፣ ዕውቀትን፣ ንብረትንና ጉሌበትን በማስተባበር የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህላዊና ሌሎች የጋራ ፍላጎቶችን በማሟላት እርስ በርስ መደጋገፍንና ቁጠባን የሚፈጥሩ የህብረት ስራ ማህበራትን ማቋቋምና መምራት ያስፈልጋል።
ማህበራቱ በገጠርና በከተማ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ በአባላት ምርት ላይ እሴት በመጨመር፣ የገበያ ትስስርን በመፍጠር፣ አላስፈሊላጊ የገበያ ሰንሰለትን በማሳጠር እና የዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር በሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
በተለይም ማህበራቱ የሚከተሏቸውን መሠረታዊ መርሆዎችና ልዩ ባህሪ እንደጠበቁ ሆነው ሀገራችን እየተከተለች ባለችው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት (በተመረጡ ዘርፎች የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያለው) ውስጥ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ተገቢ ነው። እርግጥ ማህበራቱ የአባላቶቻቸውን መብትና ጥቅም የሚያረጋግጡ፣ አባላቱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመሯቸውና የሚቆጣጠሯቸው ናቸው። ዓላማቸውንም ለማሳካት የኅብረት ሥራ ማህበራት የሚደራጁበትንና የሚመሩበትን ህግ በማውጣት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 55 (1) መሰረት በአዋጅ እንዲተዳደሩ ተደርጓል። በዚህ አንቀፅ መሰረት ስልጣን የተሰጠው የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አዋጅ አውጥቶ ማህበራቱ በአግባቡ እንዲደራጁ አድርጓል።
አዋጁ እንደሚያስረዳው ማህበራቱ የሚከተሉት ዓላማዎች አሏቸው። እነርሱም አባላት በተናጠል በመስራት ሊወጧቸው የማይችሏቸውን የኢኮኖሚ ችግሮችን በተባበረ ጥረት መወጣት፣ መቋቋምና መፍታት፣ አባላት ያሏቸውን ዕውቀት፣ ሃብትና ጉልበት በማቀናጀት የተሻለ ውጤት ማግኘት፣ በአባላት ዘንድ በራስ መተማመንን ማጎልበት፣ ለማምረት የሚያስፈልገውን ወጪና የአገልግሎት ዋጋን በመቀነስ አባላት የሚፈልጉትን ግብአት ወይም አገልግሎት በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኙ ማድረግና ምርታቸው ወይም አገልግሎታቸው የተሻለ የገበያ ዋጋ እንዱያገኝ ማስቻል እንዲሁም የቴክኒክ ዕውቀትንና የስራ ፈጠራን በስራ ላይ በማዋል የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች እንዲስፋፉ ማድረግ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም በአባላት መካከል የቁጠባ ባህል እንዲዳብር እና እንዲስፋፋ ማድረግ፣ ለአባላት የብድር አገልግሎትን በመስጠት ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የአባላት የብድር የሕይወት መድን ዋስትና መስጠት፣ አባላቱ በግላቸው ቢሰሩ ኖሮ ለደርስባቸው የሚችለውን ጉዳትና ኪሣራ በጋራ በማካፈል የእያንዳንዱ ሰው ጉዳትና ኪሳራ መቀነስ እንዲሁም አባላትን በማስተማርና በማሰልጠን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅማቸውንና ባህላቸውን ማጎልበት ሌሎች ተደማሪ ዓላማዎች ናቸው።
እነዚህን ዓላማዎች በመፈፀምና በማድፈፀም ረገድ መንግስት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አድርጓል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤትም ቀደም ሲል በመግቢያዬ ላይ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የተናገሩትን በመግለፅ የጠቀስኩት ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሽግግር ሁነኛ መገለጫ ነው።
በመሆኑም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ሀገራችን ወደ ኢንዱስትሪ መር ልማት ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት የህብረት ስራ ማህበራቱ የበኩላቸውን ድርሻ ይጫወታሉ። በመሆኑም የህብረት ስራ ማህበራቱ ጠቀሜታ መታየት ያለበት ከዚህ አኳያ ይመስለኛል።
እርግጥ የዕቅዱ ትኩረት ግብርና የልማታችንና ፈጣን ዕድገታችን የማይተካ አስተዋፅኦ የሚያደርግና የዘመናዊ አምራች ዘርፍ ዕድገት ዋና ምንጭ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በመሆኑም ለውጥ ማምጣት የጀመሩትን የስትራቴጂክ የምግብ ሰብሎች ምርታማነትና ጥራት የበለጠ ከማሳደግ በሻገር የላቀ ዋጋ የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ የልማት ቀጣናን ማዕከል ያደረገ ርብርብ በማድረግ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም ራሱን የቻለ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ራእይ መቀመጡና ላለፉት 1ዐ ዓመታት በተከታታይ የተመዘገበውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠልና የመካከለኛ ገቢ ራዕዩን ለማሣካት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚመዘገበው እመርታና ከዚሁ ጋር በኢኮኖሚው አወቃቀር ላይ የሚጠበቀው ለውጥ በቀጣዩ አምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ዘመን ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑ፣
የኢኮኖሚው የማምረት አቅም ላይ ለመድረስ ቅልጥፍና መጨመርና የአምራች ዘርፎች (ማኑፋክቸሪንግና ግብርና) በሚመረቱ ምርቶች ለጥራት፣ ለምርታማነት እና ተወዳዳሪነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራና ይህንንም ለማስፈፀም ቀደም ብሎ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተጀመረው ካይዘን በስፋትና በጥልቀት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ የቤንች ማርኬንግ እንቅስቃሴም እንደሚስፋፋ ግልፅ ግቦች ተቀምጠዋል።
በመሆኑም እነዚህን ግቦች ለማስፈፀም የህብረት ስራ ማህበራት የድርሻቸውን ይወጣሉ። በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ለሚኖራቸው ጉልህ ድርሻ በቁጠባና በኢንቨስትመንት ረገድ ድርሻቸው የጎላ ሊሆን ይችላል። እንደሚታወቀው በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዘመን በማኑፋክቸሪንግና በግብርና፣ በመሠረተ-ልማት፣ በማህበራዊ ልማት ዘርፎችና በሌሎች መስኮች የሚከናወኑ የግልና የመንግስት ኢንቨስትመንቶች ፈጣን ዕድገትን በማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ይጠበቃል፡፡
ስለሆነም በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ እስካሁን የተመዘገበውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መጣኔ ጠብቆ ለመሄድ ታቅዷል፡፡ ለዚህ ከፍተኛ ግምት ላለው ኢንቨስትመንት መሸፈኛ የሚያስፈልገው ፋይናንስ በአብዛኛው ከሀገር ውስጥ ለማሰባሰብ ካልተቻለ ደግሞ የፈጣን ዕድገቱ ዘላቂነት አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም፡፡ እናም በኢንቨስትመንትና በሀገር ውስጥ ቁጠባ መካከል ያለው ሚዛን ለማመጣጠን የአገር ውስጥ ቁጠባ በተጀመረው አቅጣጫ ማሳደግ ይገባል።
የሀገር ውስጥ ቁጠባን ለማሳደግ በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በርካታ እርምጃዎች ተወስደው ውጤት ማስገኘት ጀምረዋል፡፡ በሚቀጥለው የዕቅድ ዘመንም የተወሰዱት እርምጃዎችን አሟልቶ በመተግበር ከጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ ቢያንስ ሁለት-ሦስተኛውን በአገር ውስጥ ቁጠባ ለመሸፈን እንዲቻል በዕቅድ ዘመኑ የአገር ውስጥ ቁጠባ መጣኔውን ወደ 29 ነጥብ 6 በመቶ ለማድረስ ግብ ተይዟል።
የግለሰቦችና የንግድ ድርጅቶች ቁጠባ በማሳደግ ረገድ ዋናው ጉዳይ እነዚህን አካላት የማስተማርና የማነሳሳት ተግባር ነው፡፡ ይህን በመከወን ረገድም የህብረት ስራ ማህበራት የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ። በመሆኑም ሊበረታቱና ሊጠናከሩ ይገባል። እርግጥም በአሁኑ ወቅት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እያደገ መሆኑና የቁጠባ ባህላችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ፣ የህብረት ስራ ማህበራቱ ከዚህ አኳያ ሊጫወቱት የሚገባውን ሚና ማጠናከር ይገባል። እናም ህብረት ስራ ማህበራት ሊጠነክሩና ሊበረታቱ ይገባል—ወደ ኢንዱስትሪ መር ዕድገት ሊያሸጋግሩን የሚችሉ የልማት ሃይሎች ናቸውና።