ኢትዮጵያ በአፍሪካ መሪር የነጻነት ትግል ውስጥ ሰፊ የታሪክ አሻራን ያስቀመጠች ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ ሕብረት፣ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጀት ታሪክ ሲነሳ ኢትዮጵያ ሁሌም ቁልፉን ቦታ ትይዛለች፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከታገሉት ሀገሮች አንድዋ ሲመሰረትም ጽህፈት ቤቱን በመዲናዋ ይሆን ዘንድ በመፍቀድ ለአፍሪካ ነጻነት መከበር ታላቅ ሚናን የተጫወተች ሀገር ነች፡፡
የኢትዮጵያው ንጉስ ቀዳማዊ ኀይለስላሴ፣ የጋናው መሪ ክዋሚ ንኩሩማን እና ሌሎችም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመፍጠርና ሕልውናውን አግኝቶ ስራ እንዲጀምር በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚናቸውን ተጫውተዋል፡፡ አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር በወደቁበትና አፓርታይድ በነገሰበትም ዘመን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ታደርግ የነበረውን ተጋድሎ ያላቋረጠች ሀገር ነች፡፡
የኤኤንሲው መሪ ማንዴላ ወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና የወሰዱት በኢትዮጵያ መኮንኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለሞዛምቢክ ነጻነት መሪዎችዋን የዛሬውን አዛውንት ሮበርት ሙጋቤና ሰራዊታቸውን ወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙ ከማድረግም አልፋ አስታጥቃለች፡፡ የደቡብ ሱዳን ንቅናቄ በኮሎኔል ጆን ጋራንግ ይመራ የነበረው በረዥም ግዜ ትግሉ ወደ40ሺ የሚጠጋው ሰራዊታቸው የሰለጠነው በኢትዮጵያ መሬትና በኢትዮጵያ መኮንኖች ነው፡፡
ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ለመውጣት በሚያደርጉት ትግል ሁሉ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፋ ስትታገል ድምጾችዋን ስታሰማ የነበረችና ያለች ሀገር ነች፡፡ አፍሪካውያን መሪዎች ለአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ወደኢትዮጵያ ሲመጡ ሁሌም በደስታ ይሞላሉ፡፡ ለምን ቢባል ኢትዮጵያን እንደቤታቸው፤ እንደራሳቸው ሀገር ስለሚቆጥሩዋት ነው፡፡
አፍሪካ በተፈጥሮ ጸጋዋና ሀብትዋ እጅግ የታደለች በመሆኗ ይህንን ሀብትዋን ለመቀራመት ትላንትም ዛሬም አውሮፓውያን አይናቸውን ተክለው የሚመለከቱዋት ድንቅ አህጉር ነች፡፡ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራቸውም ዛሬም በእርስ በእርስ ጦርነትና ሽኩቻ ውስጥ በመግባት ለውጭ ሀይሎች ሲሳይ ከመሆን አልወጡም፡፡
በአፍሪካ የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች የተከሉት የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲና እርስ በእርስ የማጋጨት የማዋጋት መርዝና ተንኮል ዛሬም ሙሉ በሙሉ ተነቅሎ አልወጣም፡፡ የአፍሪካ ሀገራት በሕብረቱ አማካኝነት በጋራ ጸንተው በመቆም፤ በጋራም በመምከር ከድህነትና ከኃላቀርነት ለመውጣት በአህጉሪትዋ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ወጣት የስራ እድል በስፋት ለመፍጠር የተፈጥሮ ሀብቶችዋን በመጠቀም አህጉሪቱን ለማልማት ሰፊ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የተካሄደው የሕብረቱ 28ኛ ጉባኤ ያተኮረው በአፍረካ ወጣቶች ላይ ነው፡፡ የነገውን ሀላፊነት ተረካቢ ትውልድ አቅም በፈቀደ ሁሉ መረባረብና የስራ ባለቤት የማድረግ ራእይ የሰነቀ ስብሰባ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን በሆነ ልማትና እድገትዋ ሰፊ መሰረተ ልማት በማካሄድዋና ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የገነባችና በመገንባትም ላይ ያለች ሀገር በመሆንዋ ዛሬም ለአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ተምሳሌት በመሆን ተጠቃሽ ሀገር ሆናለች፡፡
ብዙዎች የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ልምድና ተሞክሮ በመነሳት የእድገትና የልማት አቅጣጫዋን በፋና ወጊነት በመከተል በየሀገራቸው ስርነቀል የኢኮኖሚ እድገት ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ሰሞኑን በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ሙሳ ፋቂ መሃማት ሕብረቱን ለቀጣይ አራት አመታት በሊቀመንበርነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡ ጋናዊው ክዌሲ ቋርቴይ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል፡፡ የ56 አመቱ ሙሳ መሃማት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2005 የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሰው ናቸው፡፡ ዶክተር ኒኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንን ላለፉት አራት አመታት በሊቀመንበርነት መምራታቸው ይታወቃል፡፡
በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 28ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ የተሻለች አህጉር ለመፍጠር የሚያግዙ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ በተጠናቀቀው ጉባኤ ኢትዮጵያ አቋሟን ያሳየችበትና ራሷን ያስተዋወቀችበት ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለመገናኛ ብዙህን በላኩት መግለጫ አፍሪካ የበለፀገች፣ ለሕዝቦቿ የምትመች እንድትሆን የሚያስቸሉ ውሳኔዎች ሲተላለፉ ኢትዮጵያ ከአባል ሀገሮች ጋር ጥረት አድርጋለች፡፡ በጉባኤው የሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ወደ ሕብረቱ የመመለስ ጥያቄ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀ መንበር፤ የስምንት የተለያዩ ኮሚሽነሮች ምርጫዎች፤ ሕብረቱን ለአንድ ዓመት የሚመራውን መሪ መምረጥ፤ የሕብረቱ አዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርን በተመለከተ የቀረቡ አጀንዳዎች ውሳኔዎች ማግኘታቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረጓ በተጨማሪ ከነዚህ ታሪካዊ ውሳኔዎች ጀርባ የራሷን ሚና ለመወጣት ችላለች፡፡ ከመሪዎቹ ስብሰባ በተጓዳኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ ከሩዋንዳው ፖል ካጋሜ፣ ከደቡብ ሱዳኑ ሳልቫኬር፣ ከመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሪየዝና ሌሎች በርካታ አገሮች መሪዎች ጋር መወያየታቸው ታውቆአል፡፡
በጉባኤው የስንብት ንግግር ያደረጉት የቀድሞ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ዶክተር ድላሚኒ ዙማ ቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሙሳ ማሕማት የአፍሪካን የአንድነት ተልዕኮና የተቀመጡ ግቦችን እንዲያሳኩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዶክተር ድላሚኒ ዙማ በአፍሪካ በጠመንጃ የሚካሄድ ተኩስን በሙሉ በማስቆም ሰላማዊና የበለጸገች አፍሪካን እውን ማድረግ የሕብረቱ ዋነኛ ራዕይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የአፍሪካውያን ድምጽ በዓለም እንዲስተጋባ ለማድረግ አፍሪካውያን በማንም ሳይከፋፈሉ በአንድነት መንቀሳቀስ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሙሳ ማሕመት የአፍሪካን ብዝሀነት ማዕከል በማድረግ ማገልገል ቀላል ባይሆንም ፈተናዎቹን መጋፈጥ አያስፈራኝም፤ የአፍሪካን ራዕይ የማሳካውም ከሌሎች ጋር በመተባባር ነው ብለዋል፡፡ የ2063 የልማት ግቦችን ለማሳካት የአፍሪካውያን ወጣቶች፣ ምሁራንና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ያለው ግጭት በተለይም ሴቶችን ለችግር እያጋለጣቸው በመሆኑ ጉዳዩ እደሚያሳስበው የአፍሪካ ሕብረት ገልጾአል፡፡ ግጭቱ ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ በርካታ ደቡብ ሱዳናውያን እንዲሰደዱ ምክንያት እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ሕብረቱ በተለይም ግጭት ባለባቸው የአፍሪካ አገሮች ያሉ ሴቶችን ሊያጋጥማቸው ከሚችሉ ችግሮች ለመታደግ የሚያስችል ቅስቀሳ ለ16 ቀናት እንደተደረገ የሕብረቱ የሴቶችና ልማት ዳይሬክተር ማዋካባ ዊለር ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሯ ባለፉት አራት ዓመታት የአፍሪካ ሴቶችን በትምህርት በማሳተፍ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ውጤት ቢመዘገብም ችግሮቹ አሁንም እንደቀጠሉ ተናግረዋል፡፡ የሲቪል ማሕበረሰቡ የሴቶችን ድምጽ እንዲሰማና ምላሽ እንዲሰጥ ዳይሬክተሯ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት በዚህ ረገድ እያበረከተው ያለው አስተዋፅኦ ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡