ኃይማኖት በመንግሥት መንግሥትም በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በግልፅ ደንግጓል፡፡ የመንግስት አሰራርና ሃይማኖታዊ ስርዓት የተለያዩ መሆናቸውን በህገመንግስቱ አንቀጽ 11 ላይ ሃይማኖታዊ መንግስትም ሆነ መንግስታዊ ሃይማኖት በኢትዮጵያ እንደማይኖር ተደንግጓል። ሴኩዩራሊዝም የአገራችን መርህ ነው። ይሁንና አንዳንድ ሃይሎች ፖለቲካንና ሃይማኖትን ሆን ብለው በመደበላለቅ የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም አልተሳካላቸውም።
አክራሪው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች የኃይማኖት ልዩነትን ለፖለቲካ ፍላጎት ማሳኪያ ለማድረግ ሲሯሯጡ ቆይተዋል። አቶ ጃዋር በዚህ ረገድ ዋንኛ ተዋናኝ ናቸው። አክራሪው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች አገራችንን ለማወክ በርካታ ካርዶችን ይጠቀማሉ። ጃዋርና ተከታዮቹ አንዱ በር ሲዘጋባቸው ሌላውን ሲያንኳኩ ነበር። አቶ ጃዋርና ተከታዮቹ የብሄር ካርዳቸው ለሁከት ማነሳሻነት አልሳካ ሲላቸው የሃይማኖት ካርዳቸውን ለመጠቀም ቢሞክሩም ይህም ሲነቃባቸው እንደገና ወደ ብሄር ካባቸው ተመልሰዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ እምነቶች አገር ናት። የኢትዮጵያ ህዝቦች ከብዙዎቹ የዓለማችን ህዝቦች ቀድመው የክርስትናንም ይሁን የእስልምና እምነቶችን ከመቀበላቸውም ባሻገር ምዕመኑ ለዘመናት አብረው ተቻችለው መኖር የቻሉባት አገር ናት። በርካታ የዓለማችን አገሮች አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ብሄር፣ አንድ ቋንቋ ኖሯቸው ለበርካታ ግጭቶች ተጋልጠው ስናይ በአገራችን ያለውን ልዩነት አቻችለን በሰላም መኖር የቻሉትን የአገራችን ህዝቦች የእውነተኛ ሃይማኖተኛ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኛ ይህን መልካም የህዝቦች ግንኙነት ለማሻከርና ግጭት ለመፍጠርና ድብቅ ፖለቲካዊ ፍላጎቱን ለማሳካት ጥረት ሲያደርግ ነበር። አልተሳካለትም እንጂ።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሃይማኖት ነጻነት በአገራችን ተረጋግገጧል። ማንም ሃይማኖቱን በነጻነት ማራመድ የሚችልበት ሁኔታ በመመቻቸቱ ምዕመናን የአምልዕኮ ሥርዓቶቻቸውንና አስተምህሮዎቻቸውን ያለምንም ተጽዕኖ በነጻነት ማካሄድ ችለዋል። በአገራችን የኃይማኖት ነጻነት በዚህ መልክ ተረጋግጦ ባለበት በአሁኑ ወቅት በኃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች አሁንም የኃይማኖት ነጻነት የለም በማለት ሁከት ለመፍጠር ይሯሯጣሉ። ኃይማኖትን ለፖለቲካ ፍላጎት ለመጠቀም መንቀሳቀስ ከትርፉ ይልቅ ጉዳቱ ያየለ መሆኑን አክራሪው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች በአግባብ የተረዱት አይመስልም። አክራሪነት ሰደድ እሳት ነው። መነሻው እንጂ መድረሻውን መገመት አይቻልም።
ድብቅ አጀንዳ ያነገቡ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ዓላማቸውን ለማራመድ ሃይማኖት እንደ ሽፋን መጠቀም ምርጫቸው የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ህዝብ ለሃይማኖቱ ቀናዒ መሆኑን ስለሚያውቁ፤ ልናሳስተው እንችላለን በሚል የተሳሳተ ስሌት ነው። ይሁንና አሁን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንም እንደፈለገው የሚዘውረው ህዝብ እንዳልሆነ በተግባር አሳይቷል። ምክንያታዊ ህብረተሰብ በመገንባት ላይ ነው። ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ይህ መንገድም ዝግ መሆኑን አሁን ላይ በመረዳት ላይ ያሉ ይመስለኛል።
ሽብርተኝነት ዘርን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ ዕድሜን፣ ሃይማኖትን… ወዘተ ሳይለይ ሁሉንም የሰው ዘር ያለ ሃጢያቱ የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት ነው። አክራሪነት የሚለው ቃል የሚሰጠን መሠረታዊ ፍቺ ከሃይማኖት አጥባቂነት ወይም የሃይማኖት ህግጋትን ከመጠበቅ በእጅጉ የተለየ ነው። አንድ ግለሰብ “ሃይማኖቱን አጠበቀ” ያልን እንደሆነ ሃይማኖቱን በጥብቅ አመነበት፣ ሌሎች ሰዎችንም ሃይማኖታዊ ህጉ በፈቀደው መሰረት እንዲከተሉ አደረገ የሚል ሲሆን በሌላ በኩል የሃይማኖት አክራሪነት የራስን ሃይማኖት በሃይል በሌሎች ላይ መጫን፣ ሌሎች እምነቶች ሊኖሩ አይገባም የሚል ነው። አክራሪነት የእኔን እምነት ብቻ መከተል ይኖርበታል የሚል ጤነኛ ያልሆነ አስተሳሰብን የሚያራምድ ነው፡ የራስን እምነትና ፍላጎት በሌላው ላይ በኃይል ለመጫን ንፁሃን ዜጎችን በዘግናኝ ሁኔታ ያለ አንዳች ርህራሄ በጅምላ እስከመጨረስ የሚያደርስ መሆኑ ነው። እዚህ ላይ ‘አክራሪነትን’ እና ‘አጥባቂነትን’ ለይተን መመልከት ይኖርብናል።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ጸረሰላም ሃይሎች ሃይማኖታዊ ፖለቲካቸው አልሳካ ሲላቸው አክራሪ የብሄር ፖለቲካቸው ይህ ደግሞ አላስኬድ ሲላቸው ሌሎች የጥፋት መንገዶችን ማማተራቸው መቼም የሚቆም አይሆንም። ይሁንና የእነዚህ ሃይሎች የመጨረሻ ግብ የግል ፖለቲካዊ ስልጣን ፍለጋ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ኃይማኖት አክራሪነት ከሽብርተኝነት ተግባራት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።
አክራሪነት እኔ ከያዝኩት እምነት ሌላ እምነት የለም የሚል የተዛነፈ አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ (አክራሪነት) ሜታሞርፈሳይዝ ሲያደርግ ወደ አሸባሪነት ይቀየራል። አሸባሪነት ዘርን፣ ቀለምን፣ ሃይማኖትን፣ እድሜን፣ ወዘተ ሳይለይ በጅምላ የሚበላ ሰይጣናዊ ድርጊት ነው። የሽብር ድርጊት ዜጎች በሠላም ውለው እንዳይገቡ የሚያደርግ ህዝብን በማስፈራራትና በስጋት ውስጥ በመክተት ለጥፋት ተባባሪ ያደርጋል።
በዓለማችን በተለያዩ አገራት እየታየ ያለው የአሸባሪዎች ድርጊትም ከዚህ የተለየ አይደለም። ይህ አስተሳሰብ በመሠረቱ ፀረ ሕዝብ የሆነ አስተሳሰብ ነው። ይህንን ተግባር ከኃይማኖት ጋር አስተሳስሮ በኃይማኖት ሽፋን ለመፈፀም የሚደረገው ጥረት ደግሞ ሌላው አሳዛኝ ገጽታው ነው። በአለም ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የሽብር ድርጊቶች ሁሉ በሃይማኖት ሽፈን የሚካሄዱ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያነገቡ ናቸው። እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የተለያዩ ኃይማኖት አማኞች ባሉባቸው አገራት አክራሪነት እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ምክንያቱም አክራሪነት አክራሪነት ብዝሃነትን አይቀበልም። እኔ ያልኩት ብቻ ትክክል ስለሆነ ሁሉም እኔ የያዝኩትን ይያዝ የሚል አካሄድ አለው።
ሃይማኖትም የህዝቦች የማንነት መገለጫ በመሆኑ መንግስት ሁሉንም ሃይማኖቶች ተከባብረው እና ተቻችለው እንዲኖሩ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። መንግስትና ኃይማኖት አንዱ በአንዱ አሰራር ጣልቃ አይገባቡም ቢባልም ፍጹም የማይገናኙ ሁለቱ የዓለም ዋልታዎች ናቸው ማለት ግን አይቻልም። ምክንያቱም መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ግዴታ አለበት። በዚህ አሰራሩ ከሃይማኖት ጋር መገናኘቱ ትላንትም ነበር፤ ዛሬም አለ፤ ነገም መኖሩ የግድ ነው። የህግ የበላይነት በመንግስት በለስልጣን፣ በሃይማኖት መሪዎች፣ በባለሃብት፣ ወይም በሌላ ግለሰብ ሊጣስ አይችልም። አገራችን ህገመንግስታዊ አገር ናት። ሁላችንም ምክንያታዊ ልንሆን ይገባል። የህግ የበላይነት የሚረጋገጠው በመንግስት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የህብረተሰብ ጥረት ነው።