ለህዝባዊ ጀግኖች የተበረከተ ሽልማት

 

ከመሰንበቻው የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊት ቀንን “በህዝባዊ መሰረት የተገነባው ጀግንነታችን እየታደሰ ይኖራል" በሚል መሪ ቃል ለአምሰተኛ ጊዜ በሰራዊቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ አክብሯል—የካቲት 9 ቀን 2009 ዓ.ም። በሀገር አቀፍ ደረጃ በየሁለት ዓመቱ እንዲሁም በሰራዊቱ ክፍሎች ውስጥ ደግሞ በየዓመቱ የሚከበረውና “ከሁሉም በፊት ለህዝብና ለሀገር” በሚል እሴቱ የሚታወቀው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን፤ በዚህ ዕለት የሰራዊቱ ህዝባዊነት፣ ፅናት፣ ጀግንነትና ለሀገር ሲባል የተከናወኑ ልማታዊ ተግባራት የሚታሰቡበትና የሚገለፁበት ዕለት ነው።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አኩሪ ታሪኩ ተጠብቆ እንዲቀጥልና ታሪኩን ለአዲሱ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ይህን ዕለት ማክበር ታላቅ ጠቀሜታ እንዳለው ስለታመነበት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ የካቲት 7 እንዲከበር በኢፌዴሪ መንግስት ተወስኗል። በዚህ ውሳኔ መሰረትም የሰራዊቱን ህዝባዊነት፣ የድልና የሰላም ሃይልነት እንዲሁም የልማት አጋርነትን በሚያሳይ መልኩ ላለፉት አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃና በሰራዊቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ዕለቱ እየተከበረ ዛሬ ላይ ደርሷል።

ከሰሞኑም ከሰራዊቱ ክፍሎች ውስጥ ከተከናወኑት የአከባበር ስነ ስርዓቶች በተጨማሪ፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ ከተማ በ13ኛ ክፍለ ጦር ስር ለምትገኘው 4ኛ ሬጅመንት የኢፌዴሪ መንግስት የሁለተኛ ደረጃ አድዋ ሜዳይ ሽልማት አበርክቶላታል። በሽልማቱ ስነ ስርዓት ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ “…አምስተኛውን የሰራዊት ቀን ስናከብር በአሸባሪው አልሸባብ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረስ ከቻሉ ብሔራዊ ጀግኖቻችን ጋር በመሆኑ በዓሉን ልዩ አድርጎታል” ማለታቸው የሰራዊታችንን ህዝባዊ ጀግንነት የሚያሳይ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከዛሬ ዘጠኝ ወር በፊት በአሸባሪው አልሸባብ ላይ የተጎናፀፈው አስደናቂ ድል የፕሬዚዳንቱን አባባል የሚያጎላ ነው። ይኸውም በወቅቱ አሸባሪው አልሸባብ ሶማሊያ በሚገኘው፣ በሂራን ዞን ሀልገን ከተማንና አካባቢውን በተቆጣጠረው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት 4ኛ ሬጅመንት ላይ በአራት አቅጣጫዎች ለማጥቃት ባደረገው ሙከራ፤ ሰራዊቱ በወሰደው የአፀፋ ርምጃ አምስት ከፍተኛ አመራሮቹንና አንድ አፍጋኒስታዊ አሸባሪውን ጨምሮ 245 የሽብር ቡድኑ አባላት ለህልፈተ-ህይወት እንዲዳረጉ አድርጓል።

በዚያን ሰሞን ሬጅመንቷ የሽብር ቡድኑን እግር በእግር እየተከተለች ዱካውን በማደን በሰነዘረችው ጥቃት የአሸባሪዎችን ቁጥር ወደ 305 ከፍ ማድረጓ አይዘነጋም። ይህ የሬጅመንቷ ድል አድራጊነት የሰራዊታችንን የድል ሃይልነት የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፤ ለህዝቦች ነፃነት ሀገራችን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ጭምር ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ሰላምና መረጋጋት የሰጠችው ትኩረት ምን ያህል በቁርጠኝነት የታጀበ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ሰራዊቷም የሰላም ሃይል መሆኑንም የሚያሳይም ጭምር።  

እንደሚታወቀው ሰራዊታችን በአፍሪካ ህብረት ጠያቂነት በሶማሊያ ከአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ቦማሊያ (አሚሶም) ጋር መቀላለቀሉ ይታወሳል—በ2006 ዓ.ም። በወቅቱም የተሰጠው ግዳጅ በአሚሶም ተልዕኮ ስር ቀጣና ሶስትና አራት የተባሉ ቦታዎችን በመረከብ ከአሸባሪው አልሸባብ ነፃ አድርጓቸዋል።

የሰላም አምባሳደር ሆኖ ወደ ጎረቤት ሶማሊያ የአሚሶምን ግዳጅ ተቀብሎ ሲንቀሳቀስ የተሰጡትን ተልዕኮዎች ገቢራዊ አድርጓል። እነርሱም በተረከባቸው ቀጣናዎች ያለውን ሰላም አስተማማኝ የማድረግ፣ ከአሚሶም እና በእርሱ ሰር ካሉ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ጋር በመጣመር በሶማሊያ የመሸጉ ሽብርተኞችን መደምሰስና ማጥፋት እንዲሁም ከህዝቡ ጋር በመሆን የተረጋጋ የመስተዳድር መዋቅሮችን እንዲፈጠሩ መስራት ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎቹ እንዳደረገው ሁሉ፤ በሶማሊያም ህዝቡ ራሱን የሚያስተዳድርበትንና የፀጥታ መዋቅሩን በባለቤትነት የሚመራበትን ሁኔታ የመፍጠር፣ የሶማሊያ መንግስትን የፀጥታ ኃይል የተሻለ ብቃት እንዲኖረው ለማድረግ የማሰልጠን፣ የማስታጠቅ፣ የማደራጀት፣ የራሱንም አቅም እንዲገነባ የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል። አጥጋቢ ውጤትም አግኝቷል። በእኔ እምነት ሶማሊያ ዛሬ ለመሰረተችው አዲስ ህዝባዊ መንግስት የሰራዊታችን ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ምክንያቱም መከላከያ ሰራዊታችን በተሰጠው ቀጣና ውስጥ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የማቀላጠፍና በዚህም ለዕርዳታ ሰጪዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የዕለት ደራሽም ሆነ ሌሎች ሰብዓዊ ተግባሮች በተገቢው ሁኔታ እንዲደርሱ የማድረግ፣ መንግስታችን በሚደግፈው ውስን ሀብትም ጉልበቱንና ዕውቀቱን በማስተባበር አንዳንድ ማህበራዊ ተቋማትን ለአካባቢውን ህብረተሰብ የመገንባት ተልዕኮን ከመወጣት ባሻገር፤ ከሰላም ወዳዱ ከሶማሊያ ህዝብ ጎን በመሆን በአውደ ውጊያ አልሸባብን ድል በመንሳት የተጎናፀፋቸው ውጤቶች ዛሬ በዚያች ሀገር አንፃራዊ ሰላም በማስፈንና አዲስ መንግስት በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመረጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ በመምጣቱ ነው።

የአሚሶምንና ወንድም የሆነውን የሶማሊያ ህዝብን እንዲሁም የሀገሪቱን ፌዴራላዊ መንግስት ጥሪን ተቀብሎ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ በሶስት ዞኖች ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፤ ላለፉት ስምንትና ዘጠኝ ዓመታት በአሸባሪው አልሸባብ የተያዙን ባይደዋን፣ አወደሌን፣ ሂርኩትን፣ ቡራካባን፣ ዲንሱርን፣ ገብረሃሬን፣ ዋጅድን፣ ጎፍጎይድን፣ ቀንሳ ሃደሬን…ወዘተ. አካባቢዎች ከአልሸባብ በመንጠቅ በአካባቢዎቹ የሰላም አየር እንዲነፍስባቸው ማድረግ ችሏል።

በአልሸባብ ቁጥጥር ስር የነበሩት የበለደወይኒ እና የኪስማዩ ወደብ አካባቢዎችም በመከላከያ ሰራዊታችን ቁጥጥር ስር ወድቀዋል። እነዚህ ዕውነታዎችም ሰራዊታችን በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታን አጎናፅፈውታል። አሸባሪው አልሸባብ እነዚህን አካባቢዎች በመነጠቁም ለከፍተኛ ውድቀት ተዳርጓል። ከተጠናከረ መደበኛ ሰራዊትነት (Conventional Army) ወደ አጥፍቶ ጠፊ ሽምቅ ተዋጊነት ዝቅ እንዲልና በቀቢፀ ተስፋ እንዲወራጭ አድርጎታል።

የእነዚህ ድሎቹ ውጤት ህዝባዊነቱ ናቸው። ርግጥ ሰራዊቱ ለዚህ ድል የበቃው ከሌሎች ሀገሮች የላቀ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ስለታጠቀ አይደለም— ዋነኛ ትጥቁ ህዝባዊነቱ ስለሆነ እንጂ። አዎ! የሰራዊታችን ዋናው ትጥቅ የየትኛውንም ሀገር ህዝብን እንደ ህዝብ ማክበሩና እነርሱም እርሱን ከምግባሩ በመነሳት ስለሚያከብሩት ተልዕኮው እንዲያሳካ ሁሌም ከጎኑ ስለሚሰለፉ ነው።

እናም ሠራዊታችን በፅኑ ህዝባዊ መሰረት የተገነባ የሰላም ሃይል ስለሆነ፤ ትጥቁም ሆነ ስንቁ የማይነጥፈው ህዝባዊ ወገንተኝነቱ እና የግዳጅ አፈጻጸም ብቃቱ ብሎም ዲሲፕሊኑ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። ለዚህም ነው—ሶማሊያን ጨምሮ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ግዳጆች ሁሉ ህዝባዊ ጀግንነቱን የሚያስመሰክረው። በ13ኛ ክፍለ ጦር ስር የምትገኘው 4ኛ ሬጅመንት የዚህ ህዝባዊ ጀግንነት ሁነኛ ማሳያ ናት።

ሬጅመንቷ በአልሸባብ ላይ የተጎናፀፈችው ህዝባዊ ድል የሁሉም ሰራዊት ክፍሎች መገለጫ ነው። እናም በእኔ እምነት ሬጅመንቷ በመንግስት የተሰጣት የሁለተኛ ደረጃ አድዋ ሜዳይ ሽልማት በግዳጅ አፈፃፀሟ ላሳየችው ፅናትና ብቃት ብሎም አብነታዊ ጀግንነት ይሁን እንጂ፤ የሁሉም የሰራዊታችን ክፍሎችን የሚወክል ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል። ምክንያቱም ሌሎች የሰራዊቱ ክፍሎችም በታሪክ አጋጣሚ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ስፍራው ቢያቀኑ የሚፈፅሙት ተመሳሳይ ህዘባዊ ድል ስለሆነ ነው። ይህም ሁሉም የሰራዊታችን ክፍሎች በአንድ ዓይነት ህዝባዊ አመለካከት የሚመሩና በሚሰማሩባቸው ተግባሮችም አንድ ዓይነት ድሎችን የሚጎናፀፉ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በአሚሶም ስርም ይሁን ከአሚሶም ውጭ በሶማሊያ እያከናወነ ያለው የህዝቦችን ሰላም የማረጋገጥ ተግባር፤ ሀገራችንና ህዝቦቿ ለጎረቤቶቻቸው ያላቸውን ቀናዒ ፍላጎት የሚያሳይ ነው። ሶማሊያ ሰላም ካልሆነች ቀጣናው የአሸባሪዊች መፈንጫ ይሆናል። የቀንዱ ሀገራትም በሽብርተኞች ይታመሳሉ። ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ማድረግ አይችሉም። ቀጣናዊ ትብብርንም ማጎልበት አይቻልም። ታዲያ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጎረቤት ሀገራት ደግሞ የችግሩ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ ይሆናሉ። በዚህም ሳቢያ ሀገራቱ በውስጣቸው ያሰቡት ሰላምና ዴሞክራሲን የማረጋገጥ ብሎም የቀንዱ ሀገራት ከሰላም ማግኘት የሚገባቸው ልማታዊ ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ይፈጥራል። ይህን ሁኔታ ለመቀየርም ሰላም አዋኪ ሃይሎችን አደብ ማስገዛት ብሎም የቀጣናው ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ ይገባል።

ኢትዮጵያ ይህን ቀጣናዊ ሰላም ዕውን ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ይዛለች። ይህ አቋሟም ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ያለና ነገም የሚቀጥል ነው። ሶማሊያ ሙሉ ለሙሉ ከአሸባሪዎች ነፃ እስከምትሆን ድረስ ሰላም ወዳድ አቋሟ አይቀየርም። የሶማሊያ ህዝብ ወደ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለሚያደርገው ሽግግር እንደ መንገስትም ሆነ እንደ ህዝብ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የምታደርግ ይመስለኛል። ይህ የሀገራችን አቋምም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለሬጅመንቷ የሜዳሊያ ሽልማቱን ሲሰጡ “…የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አለም አቀፍ ተቀባይነቱ እያደገ መምጣቱ፣ የሀገሪቱን የሰላም ወዳድነትና ለሰው ልጆች ነፃነት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል” በማለት በማያሻማ ሁኔታ ገልፀውታል። እናም ሽልማቱ ለህዝባዊ ጀግኖች የተበረከተ የሀገራችን ቁርጠኛ አቋም መገለጫ ነው ማለት ይቻላል።