ሰላም የሁሉም ጉዳዩች ማጠንጠኛ ቋጠሮ ነው። ያለ ሰላም ምንም ነገር ማከናወን አይቻልም። ሰላም ከሌለ የህግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም። መብት አይከበርም። መብት ሰጪና ነሺዎች ጥቂቶች ይሆናሉ። ጉልበት ያለው የህግ አስፈፃሚ ይሆናል። በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይም በህግና በስርዓት ሳይሆን በጉልበተኞች የሚወሰን ይሆናል። ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም። ህግ የበላይነቱን ስለሚነጠቅም በእነዚህ ሃይሎች እጅ ይወድቅና ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል።
ይህን የሰላም እጦት ፈተና የትኛውም ሀገር ህዝብ ይገነዘበዋል። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም ሀገር ህዝብ በሚገባ ያውቃል። አንድ ሀገር ሰላምን ለማስፈን ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አዋጆችን ሊያወጣ ይችላል። አዋጁ ግን በህዝቡ ይሁንታ ሊደገፍ ካልቻለ ተፈፃሚነቱ አጠራጣሪ ይሆናል። ርግጥም ህዝቡ ያልደገፈው አዋጅ የታለመለትን ግብ ሊመታ አይችልም። ይህም የሰላም ዋነኛው ምሶሶና ማገር የዚያች ሀገር ህዝብ እንጂ አዋጅ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ነው። ለዚህም ነው የፅሑፌን ርዕስ ‘ሰላም በህዝብ ፍላጎት እንጂ በአዋጅ አይጠበቅም!’ ያልኩት።
እንደ እውነቱ ከሆነ ከሀገራችን ህዝብ በላይ የሰላምን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ላለፉት 25 ዓመታት በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ ያውቃልና። እናም ስለ ሰላም ሲነሳ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እማኝ ሊሆን የሚችለው የሀገራችን ሀዝብ ይመስለኛል።
ርግጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ሃይሎችና በሀገራችን የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። ሁከቱን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል። ይህ አዋጅም በወቅቱ ሰላሙን ተነጥቆ በነበረው የየአካባቢዎቹ ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ ያለው ስለነበረ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ተችሏል።
በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። የሁከቱ ተሳታፊ የነበሩ ወገኖችም የተሃድሶ ትምህርት ወስደው በሁለት ዙሮች ተመርቀዋል። በሁከቱ ወቅት የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ቃል በመግባትም ወደየመጡበት አካባቢዎች ተመልሰዋል። በቅድሚያ እነዚህን አጥፊ ዜጎች በመጠቆምና ለእርምት ወደ ተሃድሶ ማዕከሎች እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የህዝቡ የማይተካ ሚና እዚህ ላይ ሊደነቅ የሚገባው ይመስለኛል። ይህም ማንኛውም አዋጅ ያለ ህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው።
እንደሚታወቀው በቅርቡ የጦላይ፣ የይርጋለምና ብርሸለቆ የተሃድሶ ማዕከላት በሁለተኛው ዙር ያስተማሯቸውን በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉና የተሃድሶ ስልጠናን የተከታተሉ 11 ሺህ 352 ሰዎች ሰልጣኞችን አስመርቀዋል። ርግጥ ሰልጣኞቹ በሁከቱ ወቅት ቀደም ሲል ያቀረቡት ጥያቄዎች ተገቢ ቢሆኑም፣ ጥያቄዎቹን ለማስፈፀም የተከተሏቸው መንገዶች ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጋጩ ነበሩ። ይህን ከፍተት ለመሙላትም በስልጠና ቆይታቸው ወቅት በህገ መንግስት፣ በኢትዮጵያ ታሪክና ህዳሴ እንዲሁም ‘አይደገምም’ በሚሉ ሰነዶች ዙሪያ ትምህርት ትምህርት እንዲወስዱ ተደርጓል። በመጀመሪያው ዙርም ዘጠኝ ሺህ 800 ሰዎች ተመሳሳይ የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።
በእኔ እምነት ለዚህ ውጤት መገኘቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ ህዝቡ ነው። ህዝቡ በማንኛውም መስፈርት ሰላሙን ተፃርሮ ሊቆም አይችልም። በመሆኑም ለሰላሙ እውን መሆን አጥፊዎችን በማጋለጥና በመገምገም የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል። ወደ ቀያቸው ሲመለሱም ዕውቀት ገብይተው መመለሳቸውን ስለሚገነዘብም ድጋፍና ክትትል ማድረጉ አይቀርም። ይህም ህዝቡ ለሰላሙ ምን ያህል ቀናዒ መሆኑን የሚያሳይ ተግባር ይመስለኛል።
ተመራቂዎቹም የህዝቡን ሁለንተናዊ ድጋፍ በማገዝ ረገድ ለሀገራቸው ሰላምና መረጋጋት የበኩላቸውን ዕገዛ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። ይህን ለመከወንም በሁለቱም ዙሮች የተመረቁ ሰልጣኞቹ ከጥፋት ድርጊት ራሳቸውን በማራቅ የልማት ሐዋርያ ሊሆኑ ይገባቸዋል።
ከዚህ ባሻገርም የሀገራቸውን ሰላም የማስጠበቅ የዜግነት ኃላፊነት አለባቸው። እያንዳንዷ የሰላም ቀን በራሳቸውና በህዝባቸው ላይ የምታመጣውን ለውጥ በመገንዘብም የየቀያቸው ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን የተማሩትን ትምህርት በተግባር ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል። ይህን ሲያደርጉም የበደሉትን ህዝብ ይክሳሉ፤ የየአካባቢያቸውን ሰላም በአስተማማኝ መሰረት ላይ በማኖርም የራሳቸውንና የህዝባቸውን ተጠቃሚነት ይበልጥ ያረጋግጣሉ።
ተመራቂዎቹ የህዝቡ አካል ናቸው። በየተሃድሶው በወሰዷቸው ስልጠናዎች ከዚህ ቀደም የነበሩባቸውን ክፍተቶች ሞልተዋል። በተለይም ጥያቄዎችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ከማቅረብ አኳያ ህገ መንግስታዊ ዕውቀትን ገብይተዋል። በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ያላቸው ግንዛቤም ጎልብቷል። እንዲሁም ሀገራችን እስካሁን የነበረችበት አጠቃላይ ሂደትና በቀጣይስ ስላላት መንገድ በቂ ግንዛቤ ይዘዋል።
ሰልጣኞቹ ምንም እንኳን ከግንዛቤ እጥረት አሊያም አለማወቅ ባለፉት ጊዜያት የፈጠሯቸው ችግሮች ቢኖሩም፤ ባገኙት የተደራጀ እውቀት ችግሮቹን ‘አይደገምም፣ የበደልነውን ህዝብ እንክሳለን’ ማለታቸው እንደ ህዝብ ለሰላም ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው። ይህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ዕገዛ ማድረጉ የሚካድ አይመስለኝም።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊቀጥልም ሆነ ላይቀጥል ይችላል። አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት የሆኑት ጉዳዩች ሙሉ ለሙሉ ሲቀሩ አዋጁ የማይቀጥልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፤ ሁኔታዎቹ ካልተቀየሩም ሊቀጥል ይችላል። ያም ሆነ ይህ ግን አሁን ባለው ሁኔታ አዋጁ ቀሪ ጊዜያት አሉት። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም አዋጁ የታሰበውን ዓላማ ሙሉ ለሙሉ እንዲያሳካ ተመራቂዎቹ እንደ ህዝቡ አካል የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል። በዚህም አዋጁን እንዲተገበር ራሳቸውን ተገዥ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የአዋጁ አካል በመሆን ጭምርም በቀሪዎቹ ጊዜያት ጉልህ ተሳትፎ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው ተመራቂዎቹ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው። በአሁኑ ወቅት መንግስት ስራ ፈጠራን በማጎልበት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የ10 ቢሊዮን ብር በጀት ይዟል። ክልሎችም ከየራሳቸው በጀት ተጨማሪ በጀት እየያዙ ነው። ለምሳሌ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በመመደብ ለወጣቶች ስራ ከመፍጠር ባሻገር፤ የተለያዩ የማዕድን ቦታዎችን ወደ ወጣቶች በማዛወር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
ታዲያ ይህን መሰሉን መንግስታዊ ቁርጠኝነት ወጣቶች በተገቢው መንገድ ሊጠቀሙበት ይገባል። ማንኛውም ስራ የሚከናወነው በሰላም ማዕቀፍ ውስጥ በመሆኑም ወጣቶች ስለ ሰለማቸው አጥብቀው ማሰብ ይኖርባቸዋል።
በፅሑፌ ርዕስ ላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የትኛውም ሰላም በህዝብ ፍላጎት እንጂ በአዋጅ ስለማይጠበቅ ተመራቂዎቹ ስለ ሰላም ቢደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የሀገራችንንና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ የውጭ ሃይሎችና የውስጥ ተላላኪዎቻቸው የፈፀሙት ፀረ-ሰላም ድርጊት የት ድረስ እንደ ዘለቀ ተመራቂዎቹ የሚያውቁት እውነታ ነው። ስለሆነም ሁሌም ከማንኛውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የማየት፣ ህጋዊ አካሄዶችን በማጤንና አሉታዊና አዎንታዊ ጎኑን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሳኔ መስጠት ይኖርባቸዋል።
የተመራቂዎቹ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆኑን በማጤን ሁሌም ከሰላም ወዳድ ሃይሎች ጋር መቆም ይኖርባቸዋል። ርግጥ ተመራቂዎቹ የሰላምን ጠቀሜታ በስልጠና ቆይታቸው ውስጥ ከምንግዜውም በላይ በመገንዘባቸው ለሰላም ዘብ እንደሚቆሙ አያጠራጥርም። ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን የሀገራችንን ሰላም መሆን የማይፈልጉ የውስጥ ሆነ የውጭ ሃይሎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ማናቸውንም ተግባሮቻቸውን ከቀሰሙት ዕውቀት አንፃር እየመዘኑ መፈፀም እንደሚኖርባቸው እዚህ ላይ ማስታወስ አስፈላጊ ይመስለኛል።