ከዘመቻ ርብርብ ወደዘላቂ መፍትሄ

ኢትዮጵያ ዘንድሮም በአየር ንብረት መዛባት በተፈጠረ ድርቅ ተጽእኖ ስር ወድቃለች። የድርቁ ተጽእኖ ያረፈው በኦሮሚያ ቦረና፣ ጉጂና ምስራቅ ሃረርጌ ዞኖች፤ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ደቡብ ኦሞ ዞን ሰገን ወረዳዎች፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ ዘጠኝ ዞኖች፤ እንዲሁም በተለያያ የአፋር ክልል አካባቢዎች ላይ ነው። እነዚህ አካባቢዎች በአብዛኛው ቆላማና የአርብቶ አደር መኖሪያ አካባቢዎች ናቸው። በዚህ የድርቅ ተጽእኖ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ተዳርጓል። ባለፈው ዓመት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ ለድርቅ ተጽእኖ ተጋልጦ እንደነበረ ይታወሳል።

ይህ ባለፈው ዓመት አገሪቱን የመታት ድርቅ በሃምሳ ዓመታት ካጋጠማት ሁሉ የከፋ ነበር። ያም ሆኖ፤ የአንድም ሰው ህይወት ሳይጠፋ፣ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሳይፈናቀሉ፣ የትምህርት ሂደት ሳይስተጓጎል ድርቁን መከላከል ተችሏል። ድርቁን በመከላከል ረገድ የኢፌደሪ መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ መያዙ ይታወቃል። ባለፈው ዓመት ከውጭ ከመጣ የእህል እርዳታ ቀረጢት መሳ ለመሳ የኢፌዴሪ መንግስት አርማ ያለባቸው  ቀረጢቶች ተሰልፈው እንደነበረ ይታወሳል። ይህ በኢትዮጵያ የድርቅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው። መንግስት ድርቁን ለመከላከል የ16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት መድቦ እንደነበረም ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በተለያየ ጊዜ ማለትም በ1985/86፣ በ1994፣ በ2003 ዓ/ም የተለያየ የተጽእኖ ደረጃ ባላቸው ድርቆች ተመትታለች። እነዚህ ከ1983 ዓ/ም በኋላ ያጋጠሙ ድርቆች እንደ1965/66 እና 1976/77 ዓ/ም ድርቆች ሁሉ ወደችጋርነት ተለውጠው ለሰው ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ምክንያት አልሆኑም። ተጽእኖውን የመከላከሉ ስራ በተለይ የ1985/86 እና የ1994 ዓ/ም በውጭ እርዳታ የተከናወነ ነበር። መንግስት በወቅቱ የድርቁን ተጽእኖ ይፋ አውጥቶ እርዳታ በመጠየቅ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳይደርስ መከላከል ችሏል።

የ2008ቱና የዘንድሮውን ተጽእኖ በመከላከል ረገድ ግን መንግስት የአንበሳውን ድርሻ ለመያዝ በቅቷል። ልክ እንደቀደሙት የድርቅ ተጽእኖዎች ሁሉ ችግሩን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቢያሳውቅም፣ እርዳታ እስኪደርስ እጁን አጣጥፎ አልጠበቀም። ከራሱ የመጠባባቂያ የእህል ክምችት በማውጣት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አቅርቧል።

ይህ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም። አገሪቱ ባለፉት 13 ዓመታት ባስመዘገበችው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት የተገነባ አቅም ነው። የአምናው ድርቅ ሲጀምር አገሪቱ 450 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጠባባቂያ የእህል ክምችት ነበራት። ይህ የእህል ክምችት በጎደለበት መጠን እየተተካ ሳይጎድል እንዲቀጥል ማድረግ የተቻለበት ሁኔታም ነበር።

የዘንድሮው ድርቅ ተጽእኖ ያረፈባቸው ዜጎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ የቀነሰ ቢሆንም፤ ባህሪው ግን የተለየ ነው። ይህም በቆላማ የአርብቶ አደር መኖሪያ አካባቢ የተከሰተ ከመሆኑ የመነጨ ነው። አርብቶ አደሩ በእንስሳት ርባታ ላይ ጥገኛ ነው። የምግብ ፍጆታውን የሚያሟላው በየዕለቱ ከእንስሳቱ በሚያገኘው ወተት፣ ቅቤ፣ ትኩስ ደምና መሰል የእንስሳ ተዋጽኦ ነው። ድርቁ የእንስሳት መኖ ሲያጠፋው የዕለት የምግብ ፍጆታውን ማሟላት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የእንስሳት ተዋጽኦዎች በየእለቱ የሚገኙ በመሆኑ የድርቁ ተጽእኖ ፋታ የሚሰጥ አይደለም። ይህ የዘንድሮው ድርቅ አንዱ ልዩ ባህሪ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፤ ለአርብቶ አደሩ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ከማቅረብ ጎን ለጎን ለእንስሳቱም መኖ ማቅረብ ግድ ይላል። መኖ የማቅረብ ስራ ግን ለሰው የምግብ እርዳታ እንደማቅረብ ቀላል አይደለም። በቅድሚያ ለሁሉም የአርብቶ አደር እንስሳት የሚበቃ መቂ መኖ በአገሪቱ ማግኘት አዳጋች ነው። ለእንስሳት የሚሆን ሳር ከውጭ አገር ገዝቶ ማጓጓዝም የማይሆን ነገር ነው። ከዚህ በተጨማሪ፤ የእንስሳት መኖ በተለይ ሳር ቦታ ስለሚይዝ የማጓጓዙ ተግባር ውድ ነው። ለምሳሌ፤- በቀን አራት ከብቶችን የሚመግብ አንድ አራተኛ ሜትር ኩብ ሳር አንድ ኩንታል እህል ከሚይዘው ቦታ በላይ ቦታ ይይዛል። ይህን ያህል ይዘት ያለው መኖ ደግሞ ለአራት ከብቶች የአንድ ቀን ፍጆታ ብቻ ነው የሚውለው። ከዚህ አኳያ በአማካይ በአባወራ እስከሃምሳ ከበቶች ላሉት የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ለሁሉም እንስሳት የሚበቃ መኖ በየእለቱ፤ ምናልባትም አንድ ዓመት ለሚሞላ ጊዜ ማቅረብ የማይቻል ነው። መኖው እንደልብ ቢገኝና በቂ የማጓጓዝ አቅም ቢኖር እንኳን   አንድ ከብት በዚህ አኳኋን ለወራት መመገብ ከከብቱ ዋጋ በላይ ወጪ ያስወጣል። ሰለዚህ አዋጭ አይደለም።

ያም ሆኖ ግን፤ ቢያንስ ለዘር የሚሆኑ ከብቶችን ለማትረፍ መኖ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። ይሁን እንጂ፤ ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ለሁሉም እንስሳት መኖ ማቅረብ ስለማይቻል እንስሳት የሚሞቱበት ሁኔታ ይታያል። በጉጂ ዞን ብቻ ከሃያአራት ሺህ በላይ ከብቶች መሞታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በቦረና ያለው ሁኔታ ደግሞ ከጉጂ ዞንም የከፋ ነው። በዘህም የተነሳ አርብቶ አደሩ በእንስሳት ሞት ምክንያት የሚደርስበትን ጉዳት ለመቀነስ ከብቶቹን ለገበያ እንዲያቀርብ ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እንስሳቱን አርዶ ቋንጣውን ለመከላከያ ሰራዊትና ለዩኒቨርሲቲዎች እንዲያቀርብ የማድረግ ውጥንም አለ። ይህም ቢሆን ግን በከብቶች ሞት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት በጉልህ መቀነስ የሚችል አይደለም።

በድርቁ ምክንያት የሚሞቱትን እንስሳት ለማዳን የሚደረገው ጥረት አስቸጋሪ ቢሆንም በገንዘብ የማይተመነው ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት በድርቁ ሳቢያ እንዳይጎዳ የመከላከሉ ስራ ግን በአስተማማኝ ሁኔታ ውጤታማ ነው። ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የከፋ ድርቅ በመከላከል የተገኘው ውጤት ይህንኑ መድገም እንደሚቻል ያረጋግጣል። በዘንድሮው ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚውል 141 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ከመጠባበቂያ ምግብ ክምችት በማውጣት ወደ አካባቢዎቹ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል። በአንዳንድ አካባቢዎች በቂ እርዳታ እየደረሰ አይደለም የሚል ቅሬታ ቢሰማም አጠቃላይ የእርዳታ አሰጣጥ ሂደቱ ግን በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንደማይደርስ የሚያረጋግጥ ነው። የመንግስት የመጠባበቂያ እህል ክምችት አምና ከነበረበት 450 ሺህ ሜትሪክ ቶን ወደ 670 ሜትሪከ ቶን ማደጉም የእርዳታ አቅርቦት እጠረት እንደማይፈጠር ያረጋግጣል። በእርዳታ አቅርቦት ላይ የሚሰማው ቅሬታ ከአቅርቦት እጥረት የመነጨ ሳይሆን አስተዳደራዊ ነው።

በእርዳታ አቅርቦት ላይ በተለየ በመዘግየት ረገድ የሚሰማውን ቅሬታ ለማቃለል የአሰራር ስርአት ተዘርግቷል። ይህም የእርዳታ ስርጭት ስርአቱን መቆጣጣር የሚያስችል አሰራር ነው። የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ኮሚሽን እንዳስታወቀው ለድርቅ ለተጋለጡ ዜጎች በሚቀርብ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ላይ አልፎ አልፎ መዘግየቶች ይስተዋላሉ። ይህን ችግር ለመፍታት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚቀርበውን እርዳታ የሚቆጣጠር ብሄራዊ ኮማንድ ፖስት ሊቋቋም ነው። ኮማንድ ፖስቱ በፌዴራልና በክልል መንግስታት የሚሰጠውን እርዳታ የሚከታተልና በታችኛው አመራር ዘንድ የሚስተዋሉ የአፈጻጸም ክፍተቶችን በማስተካከል እርዳታው ለሚመለከተው አካል እንዲደርስ የማድረጉን ስራ የማገዝ ተልዕኮ ያለው ነው። ብሄራዊ ኮማንድ ፖስቱ ከክልልና ከሚመለከታቸው የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚዋቀር ነው። ይህ በተለይ ከአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አቅርቦት መዘግየት ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ቅሬታ መፍትሄ ማበጀት ያስችላል።

እንግዲህ ድርቅ በአመዛኙ የተፈጥሮ ክስተት በመሆኑ ከነአካቴው ማስቀረት አይቻልም። እናም ኢትዮጵያ ለወደፊትም በድርቅ መመታቷ አይቀርም። የቅርብ ጊዜ ሁኔታዎች እንደሚያመለክቱት በፊት በየአስር አመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን ድግግሞሹ እየጨመረ መጥቷል። በመሆኑም ድርቅን እንደድንገተኛ ችግር ሲደርስ ብቻ በዘመቻ ለመከላከል ከመራሯጥ ይልቅ፣ አይቀሬ መሆኑን አስቀድሞ ተገንዝቦ ተጽእኖ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። እርግጥ የአገሪቱን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደመስኖ ልማት ለማሸጋጋር እየተደረገ ያለው ጥረት፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ መሪነቱን ድርሻ ከግብርና ወደኢንዱስትሪ ለማሸጋጋር የተነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የድርቅን ተጽእኖ በዘላቂነት የመከላከል ስትራቴጂ ተደረጎ ሊወሰድ ይችላል።

ይሁን እንጂ፤ የህዝቡን አኗኗር መሰረት ያደረጉ በአጭር ግዜ ውስጥ ሊተገበሩ የሚችሉ ስራዎችንም መስራት ያስፈልጋል። ለምሳሌ፤- በቆላማና የአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የድርቅን ተጽእኖ በዘላቂነት ለመከላከል አርብቶ አደሩ ለእንስሳቱ ሳርና ውሃ ፍለጋ ከስፍራ ስፍራ የሚዟዟረውን የኑሮ ዘይቤ ቀይሮ አንድ ቦታ ረግቶ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም ውሃን ማእከል ያደረገ ስራ ነው። አርብቶ አደሩ አንድ ቦታ ረግቶ ሲኖር የግብርና ስራንም ስለሚለማመድ የድርቅን ተጽእኖ የመቋቋም አቅሙ ይጠናከራል። እርግጥ በዚህ ረገድ ባለፉት አምስት ዓመታት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸው ይታወቃል።

የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስቴር በቅርቡ እንዳስታወቀው፣ የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስና የምግብ ዋስትናውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በአገር አቀፍ ደረጃ የ5 ዓመት ፕሮግራም ተዘጋጅቷል። በዚህ ፕሮግራም ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎ ድርቅን ለመቋቋምና ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የአፋር፣ የደቡብና የኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደር ማህበረሰቦችን  የእንስሳት ሃብት በማልማት ከገበያ ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚ ለማድረግ የውሃ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ሽፋን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በዚህ ረገድ እስካሁን አበረታች ውጤት መገኘቱንም ገልጿል። በአሁኑ ጊዜ የመጠጥ ውሃ ሽፋን በኦሮሚያ አርብቶ አደር አካባቢ 68 በመቶ፣ በአፋር 63 በመቶ፣  በኢትዮጵያ ሱማሌ 62 በመቶ፣ በደቡብ 51 በመቶ መድረሱንም አመልክቷል። የእንስሳትን ጤና ሽፋን በተመለከተም በኦሮሚያ አርብቶ አደር አካባቢ 81 በመቶ፣ በደቡብ አርብቶ አደር አካባቢ 72 በመቶ፣ በአፋር 67 በመቶ፣ በኢትዮጵያ ሱማሌ 63 በመቶ ደርሷል።

በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግስት ድርቅ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የአስቸኳይ ጊዜ ምግብና ተያያዥ እርዳታ በማቅረብ ተጽእኖውን የመቋቋም አቅሙ ባለፉት ዓመታት በተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ምክንያት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል። እስካሁን ያለው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታም የእድገቱን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ድርቅ ወደችጋርነት ተለውጦ የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፍበት ሁኔታ ወደታሪክነት ተቀይሯል ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ፤ ድርቅ ሲከሰት ተጽእኖውን እንደድንገተኛ አደጋ በዘመቻ ለመከላከል የሚደረገውን ርብርብ አስቀርቶ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ የማድረግ ስራ ብዙ ይቀረዋል። አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ትራንስፎርም ከማድረግ ጎን ለጎን ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የመስኖ ልማትን ማስፋት፣ በቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ውሃን ማእከል ያደረጉ የልማት ስራዎች ማከናወን ወዘተ. በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉልህ ውጤት ማሳየት በሚችሉበት ሁኔታ መከናወን የሚገባቸው መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።