ፖለቲካዊ ነጻነት በተረጋገጠበት የኃይል ትግል ሥፍራ የለውም

በውጭ አገራት የሚኖሩ ጽንፈኛ ተቃዋሚ ሚዲያዎች ባለፈው ዓመት ይኼኔ በተለይ ከኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ እየተቀበሉ የሚሰሩት፤ ኢሣት፣ ኢትዮጵያን ሪቪው፣ ዘሐበሻ፣ መረጃ ዶት ኮም…ፋታ አጥተው ነበር። ፋታ የነሳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በኦሮሚያ ተቀስቅሶ የነበረው አውዳሚ ሁከት ነው። እርግጥ እነዚህ ሚዲያዎች የሁከቱ ባለቤቶችም ነበሩ። ለተቃውሞ መቀስቀስ ዋነኛ ምክንያት ባይሆኑም፣ ተቃውሞው ወደ አውዳሚ ህገ ወጥ ሁከትነት እንዲቀየር በማድረግ ረገድ ቀዳሚ ባለድርሻ ናቸው።

ኦሮሚያ ውስጥ ተቀስቅሶ እያደረ የተለያየ ሰበብ እየፈለገ ወደ አማራና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የተዛመተው ሁከት መነሻው ተገቢ የህዝብ ቅሬታ ነበር። ይህ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የተቀበሉት እውነት ነው። ህዝብ ከልክ ባለፈ የመልካም አስተዳደር መጓደል ተማርሮ ነበር። ከፍርድ ቤቶች ፍትህና ርትዕ ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ከገጠር ወደ ከተማ የፈለሱና በተለያየ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የተመረቁ ተማሪዎች የሥራ እድል በማጣት ወደ ተስፋ መቁረጥ የተሸጋገሩበት ሁኔታ ነበር።

በሌላ በኩል ባለቤትነቱ የህዝብና የመንግሥት የሆነውን መሬት እንደጣቃ እየለኩ የሚቸበችቡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ደላሎች ማንም ከየት አመጣችሁ ብሎ የማይጠይቃቸውን ሃብት እያከማቹ የመንደላቀቅ እድል ያገኙበት ሁኔታ ነበር። በከተሞች ሰዎች በድንገት ሚሊዬነር ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነበር፤ ይህ አሁንም ይታያል። እድሜያቸው ከሃያዎቹ ያልዘለሉ ወጣቶች በሚሊዬን የሚለካ ሃብት ሲያገላብጡ ማየት የአጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን የተለመደ ሆኗል። በመሠረቱ ሃብት ሰዎች ለብዙ ዓመታት ለፍተውና ቆጥበው የሚያከማቹት የተገኘበት መንገድ በግልጽ የሚታይ እንጂ ድንገት እንደ መብረቅ የሚወርድ አይደለም፤ ሎተሪ ለወጣላቸው ካልሆነ በቀር። የከተሞቻችንን ድንገተኛ ባለፀጎች በሎተሪ የከበሩ እንዳንላቸው ብዙዎቹ ሎተሪ ሲደርሳቸው አልታየም፤ አልተሰማምም። በሌላ በኩል በየከተማው ድንገት ሚሊዬነር የሚሆኑት ሰዎች ቁጥር የሎተሪ እጣ ከሚያሸንፉት ቁጥር ይበልጣል። እርግጥ የሎተሪ እድልም ሎተሪው ከሚያስገኘው ገብዘብ በላይ እንደሚሸጥ ይታወቃል። የሎተሪ እጣ ገዥዎቹ ዘርፈው ያከማቹትን ሃብት ህጋዊ አድርገው በይፋ ማንቀሳቀስ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው።

እነዚህ በአንድ በኩል በመልካም አስተዳደር መጓደልና በፍትህ መዛባት፣ በሌላ በኩል በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት ሚዛናዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖር ህዝቡ ላይ መረር ያለ ቅሬታ አሳድሯል። ይህ የመረረ ቅሬታ ሆድ ለባሰው…እንዲሉ ሰበብ ሲያገኝ ድንገት ገንፍሎ ወጣ። ህዳር 2008 ዓ.ም ላይ በኦሮሚያ ጊንጪ ላይ ሁከት የፈነዳው በዚህ አኳኋን ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ ነው። ከዚያ በኋላ ብሶቱ ሁሉም አካባቢ በመኖሩ በቀላሉ ተዛመተ።

በውጭ አገር ያሉ የጽንፈኛ ተቃዋሚ ሚዲያዎች ይኼኔ ነበር የተነሱት – የሁከት ፊት አውራሪና አጋፋሪ ሆነው። የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስትርም ሥራ አገኘ። ለእነ ኢሣት፤ ዘሐበሻ፣ ኢትዮጵያን ሪቪውና መረጃ ዶት ኮም ወዘተ…የሁከት ቅስቀሳ አቅጣጫ በመስጠት ሥራ ተጠመደ። ባለቤትነቱ የአሜሪካ መንግሥት የሆነውና በኢትዮጵያውያን የሚዘጋጀው ቪኦኤም በቀጥታ ከኤርትራ መንግሥት አቅጣጫ ባይቀበልም፣ ጋዜጠኞቹ በስሜት ከሚደግፏቸው ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች በኩል ወላፈኑ ይደርሳቸው እንደነበረ በወቅቱ ሲያስተላልፏቸው የነበሩት መረጃዎችና መረጃዎቹ ሲቀርቡበት የነበረው ስሜት አዘል ቃና አስረጂ ነው። ጃዋር መሐመድ የሚመራው ኦሮሞ ሚዲያ ኔት ደግሞ የሁከቱ ፊት አውራሪ ሆነ።

የኦሮሞ ሚዲያ ኔቱ ጃዋር መሐመድ በተለይ በፌስ ቡክ ገጹ በቀጥታ ሁከት ያዛል፤ ወጣቶች አደባባይ ወጥተው አውዳሚ ሁከት እንዲያካሂዱ፣ ንብረት እንዲያወድሙ፣ ገበያ እንዲያተራምሱ፣ መንገድ እንዲዘጉ፣ ከፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች መሳሣሪያ እንዲነጠቁ፣ የተወሰኑ ሰዎችን እንዲደበድቡ፣ ቤታቸውን እንዲያቃጠሉ፣ እንዲያስፈራሩ ወዘተ…። ሁከቱ የሚያስከተለውን አደገኛ ውጤት በወጉ የማይረዱ ለጋ ወጣቶች ትዕዛዙን ተቀብለው አደባባይ ወጥተው ራሳቸውን እስከ ሞት ለሚደርስ አደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ በአድማ የወንጀል ድርጊት ይፈጽማሉ። በዚህ መካከል ከአዋኪዎቹም ከፀጥታ አስከባሪውም ወገን ሰዎች ይሞታሉ፣ ይቆስላሉ። እነ ኢሣት፣ ዘሐበሻ፣ መረጃ ዶት ኮም ደግሞ ይህን የሟቾች ዜና በብዙ እጥፍ እያባዙ ውዥንብር እየነዙ ሁከት ያጋፍራሉ።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ነን የሚሉ ሥውር ርዕዮተ ዓለማዊ አጀንዳ ያላቸው ሂዩማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ ቡድኖች ደግሞ በራሳቸው አንድም ማጣራት ሳያካሂዱ የሁከት ፊት አውራሪና አጋፋሪ ሚዲያዎችን ወሬ ተቀበለው "በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፀመ" የሚል ሪፖርት ያወጣሉ። ሳይመቻቸው ህጋዊና ሠላማዊ መንገድን፣ አመቺ አጋጣሚ ሲያገኙ ደግሞ ህገ ወጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማራመድ ሥልት የሚከተሉ አንዳንድ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችም ከጽንፈኛ ሚዲያዎቹና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ከሚሉ ቡደኖች ጋር የፈጠራ የሟቾች፣ የቁስለኞች፣ የታሳሪዎች ቁጥር…እየተመጋጋቡ ውዥንብሩን አጋጋሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች ይህን ያህል ሰው ተገደለ ብለው ያልተረጋጋጠና የተጋነነ መረጃ ያቀብሉና፣ ይህን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮቹና ጽንፈኛ ሚዲያዎቹ ሲያወሩ ተመልሰው እነዚህን ተቋማት በአስረጂነት እየጠቀሱ መንግሥት ማብጠልጠልን ተያያዙት።

እያደረ ይኼው ሁከት ወደ አማራ ክልል ተዛመተ፤ የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘትን መነሻ በማደረግ። ቀጥሎ በተለይ በሰሜን ጎንደር ከተማ ዞን አካባቢ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ የሚል አጀንዳ ይዞ ብቅ አለ። ይህ ሰሜን ጎንደርን መነሻው ያደረገ ሁከት ወደ ደቡብ ጎንደርና የጎጃም ዞኖችም ተዛምቶ እንደነበረ ይታወሣል። ሁከቱ ሰበብ እየፈለገ መፈንዳቱን ቀጠለ። በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኮንሶ ዞን ሆኖ የመዋቀር ጥያቄ በሚል ሰበብ ድንገት ፈነዳ። በመቀጠል በዲላ ከተማ በጌዲዮ ብሄረሰብና በከተማዋ  በሚኖሩ የሌላ ብሄር አባላት መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ተደረገ።

ሁከቱ ዞሮ መስከረም 2009 ዓ.ም ላይ ወደ ኦሮሚያ ተመለሰ። በጃዋር፣ በኤርትራ መንግሥትና በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝብ ተቀናቃኞች የሚመሩ ሚዲያዎች ባስተላለፉት ትዕዛዝ መሠረት በቢሾፈቱ ከተማ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁከት ቀሰቀሱ። በዚህ ሁከት ላይ በተፈጠረው መገፋፋት ሰዎች በአካባቢው የነበረ ገደል ውስጥ ወድቀው ህይወታቸው አለፈ። ይህ እንደተፈጠረ የሟቾችን አስከሬን ፎቶ ግራፍ በፌስ ቡክ በመቀባበል በፀጥታ አስከባሪ ኃይል በጥይት ተደብድበው፣ ከሄሊኮፕተር በተተኮሰ ጥይት ተመትተው የተገደሉ አስመሰለው በማውራት በመላው ኦሮሚያ ሁከት ቀሰቀሱ። በየከተማው ተደራጅተው የተዘጋጁ የሁከት አስፈጻሚዎች ባልተለመደ ሁኔታ የበረታ የኃይል ሁከት ቀስቅሰው በመቶ ሚሊዬን የሚቆጠር የመንግሥትና የግለሰቦችን ንብረት፣ የንጹህ መጠጥ ውኃና የኤሌትሪክ ማከፋፈያ ማዕከላትን፣ ማህበራዊ ተቋማትን…አወደሙ። እዚህ ጋር ሲደርስ ህዝብ የሁከቱን መድረሻ በሚገባ ተገነዘበ። ምንም እንኳን መንግሥት ላይ ቅሬታ ቢኖርበትም መፍትሄው በሁከት መንገድ የሚገኝ እንዳልሆነ ተገነዘበ። ይኼኔ የመንግሥት ያለህ የሚል ድምጽ ማሰማት ጀመረ። እስካሁንም በሥራ ላይ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው ይህን በአገሪቱ ጠላቶች የሚመራ አውዳሚ ሁከት በመመከት በህዝቡ ጥያቄ መሠረት ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን ነው። እነሆ አሁን ሠላምና መረጋገት ሰፍኗል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ በማደረግ ሠላምና መረጋጋቱን በማስፈን ረገድ ህዝብ ቀዳሚውን ድርሻ ይዟል። ሠላምና መረጋጋት የሰፈነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳይሆን በህዝቡ ነው። አዋጁ ህዝቡ ሠላሙን እንዲጠብቅ አመቺ ሁኔታ ነው የፈጠረው። ህዝቡ የሁከቱን መሪዎች አጋልጦ በመስጠት፣ በሁከቱ የወደሙ እንደ ትምህርት ቤት ያሉ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ወዘተ…ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ውዥንብር ውስጥ ገብተው ሁከቱ ውስጥ የተሳተፉ ወጣቶች ህዝብ ፊት ቀርበው ይቅርታ የጠየቁባቸው አካባቢዎች አሉ። በጉልበታቸው ያወደሙትንም ንብረት መልሰው የገነቡበት ሁኔታም እንደነበረ ይታወሣል። ይህ እንዲሆን ያደረገው የሁከቱን አካሄድ የተረዳና ሠላሙን ለመጠበቅ  የቆረጠ ህዝብ ነው። ከዚህ በተጓዳኝ መንግሥት ለሁከቱ መንገድ የቀደዱትን የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር እንዲሁም የወጣቶችን ሥራ አጥነት የሚያቃልሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመረ። ይህን የሚያደርገው ከህዝብ ጋር እየተወያያ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች በአጠቃላይ በህዝቡ በተለይ ደግሞ በወጣቱ ዘንድ ተስፋ አሳደሩ። ይህ ተስፋ የሁከትን መንገድ እያጠበበው ሄዷል። 

ከዚህ ጎን ለጎን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በየአካባቢው ተቀስቅሶ የነበረው ሁከት ውስጥ የጎላ ድርሻ የነበራቸው ሃያ ሺህ ገደማ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሠላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። በሁከት ውስጥ ሆን ብለው ወጤቱን እያወቁ የገቡና የመሪነት ድርሻ የነበራቸው እንዲሁም ከባድ ወንጀል የፈፀሙ ሁለት ሺህ ገደማ ሰዎች ደግሞ ክስ እንዲመሠረትባቸው ተወስኗል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየአካባቢው ተበትኖ የነበረ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያም እንዲሰበሰብ ተደርጓል።

እነዚህ ሁኔታዎች በመላ አገሪቱ በውዥንብር ምክንያት ተቀስቅሶ የነበረውን አውዳሚ ሁከትና ግርግር በመቀልበስ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አድርገዋል። እስካሁን ያለው ሁኔታ ሠላምና መረጋጋቱ ዘላቂ ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ነው። ይህ በመላ አገሪቱ የሰፈነ ሠላምና መረጋጋት በሁከት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንንዳለን ብለው አስበው የነበሩ ጽንፈኛ ተቃዋሚዎችንና የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎችን ተስፋ አስቆርጧል። በዚህ ምክንያት ሰሞኑን ሚዲያዎቻቸው ስለ የትጥቅ ትግል እያወሩ ይገኛሉ። የትጥቅ ትግሉስ ሊሳካላቸው ይችል ይሆን? አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት የትጥቅ ትግል በማካሄድ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን እንረዳለን።

አንድን ሥርዓት በትጥቅ ትግል መለወጥ ይህን አማራጭ የግድ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ይፈልጋል። የትጥቅ ትግል ህዝብን ወደ ሥልጣን ማምጣት የሚያስችሉ ሌሎች አማራጮች ሁሉ ሲታጡ የሚገባበት የመጨረሻ አማራጭ ነው። ህዝብ የትጥቅ ትግል ወደማካሄድ እንዲሄድ በቅድሚያ ሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አማራጮች ሁሉ የተዘጉ መሆን አለባቸው። ለምሣሌ በዘውዳዊውና በወታደራዊው ደርግ የመንግሥት ሥርዓቶች፣ ሥርዓቶቹ ከሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ውጭ የሆነ ማንኛውንም አመለካካት ማራመድ አይቻልም ነበር። ዜጎች በግልም ሆነ በአመለካካት ከሚመስሏቸው ጋር በፖለቲካ ፓርቲ ተደራጅተው አመለካከታቸውን ለህዝብ መግለጽ፣ ማራመድ፣ በአመለካከታቸው ለመንግሥት ሥልጣን የመወዳደር፣ በህዝብ ድምጽ በሚገኝ ውክልና ሥልጣን የመረከብ በህግ የተረጋገጠ መብትና ነጻነት የላቸውም። በማንኛውም መንገድ ይህን ማድረግ፣ ለማድረግ መሞከር እንደወንጀል ያስቀጣል።

በዚህ ሁኔታ የህዝብን ፍላጎት የሚወክሉ አመለካከቶች፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልማት አማራጭ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎችን የያዙ ዜጎች ወደ ሥልጣን መምጣት የሚያስችላቸው ብቸኛ አማራጭ የኃይል ትግል /የትጥቅ ትግል/ ይሆናል። ወታደራዊውን ደርግ በኃይል የመለወጥ ትግል አስፈላጊ የነበረውና በመጨረሻም ሥርዓቱ በትጥቅ ትግል የተወገደው በዚህ ምክንያት ነው። ይህ ነባራዊ ሁኔታ ሳይሟላ ህዝብ በትጥቅ ትግል የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ከሚካሄድ እንቅስቃሴ ጋር አይተባበርም። ይህ ነባራዊ ሁኔታ ሳይሟላ የትጥቅ ትግል አማራጮችን የሚይዙ ቡድኖች ቢነሱ እንኳን ከጥቂት ተከታዮች አልፈው የሥርዓት ለውጥ ማምጣት በሚያስችል መጠን ህዝባዊ ሊሆኑ አይችሉም። ፖለቲካዊ ነጻነቶች በህገ መንግሥት በተረጋገጠበት አገር የኃይል ወይም የትጥቅ ትግል አማራጭ ሥፍራ የለውም።