“… የተሸፈነ እማይገለጥ፤ የተደበቀ እማይታወቅ የለም” እንዲል ቅዱስ መፀሐፍ፤ በዘመናት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ምናልባትም ፍቺ የማይገኝለት ዕንቆቅልሽ መስለው ይታዩ የነበሩ ምስጢራዊ ጥያቄዎችን ሁሉ፤ ጊዜ በራሱ በሂደት ሲመልሳቸው ማየት የተለመደነገር ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ዓለም አቀፋዊ የታሪክ ምስክርነት የተሰጠባቸውን መዛግብት ፍለጋ መሔድ ሳያሻን፣ እዚህ በኛው ሀገር ፖለቲከኞች ዘንድ ከጥንት እስከ ዛሬ የሚስተዋለውን እርስ በእርስ የመጠላለፍ ክፉ ልክፍት ማንሳት ብቻ ከላይ የተመለከተውን መለኮታዊ ጥቅስ ግልጽ ለማድረግ የሚረዳ ጉዳይ ይሆናል፡፡
እንግዲያውስ እኔ በዚህ አጭር መጣጥፍ ለማንሳት የፈለግኩት ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይም፤ የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ የሚለውን መሰረተ ሃሳብ ያመነጩት የኢህአዴግ መሪዎች፤ በተለይም ደግሞ ትግርኛ ተናጋሪዎቹ የግንባሩ ታጋዮች ናቸው ከሚል እምነት በሚመነጭ ትምክህተኝነት ተነሳስተው ብቻ የሚቃወሙት ወገኖች ስለመኖራቸው ነውና አሁን በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ አልፈን ለአብነት ያህል እየጠቀስን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ ስለዚህም፤ የፅሁፌ ማጠንጠኛ በሆነው መሰረተ ሃሳብ ዙሪያ እኛ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተሻለ የጋራ ግንዛቤ ላይ የሚደርሰንን ውይይት ለማካሔድ እንድንችል በር የሚከፍት የግል ምልከታዬን ለመሰንዘር እንድገፋፋ ያደረገኝን ተጨባጭ ምክንያት፤ በማስቀደም ነው ሃተታዬን የምጀምረው፡፡
ስለሆነም፤ በኢህአዲግ የሚመራው የኢፌዲሪ መንግስት መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በየራሳቸው ክልላዊ መስተደደር ስር እየተደራጁ የጋራ ጠካታቸው ከሆነው ፈርጀ ብዙ ድህነትና ኋላ ቀርነት ጋር የሞትሽራት ትግል የገጠሙበትን ሀገር አቀፍ የልማት ንቅናቄ፤ በተሻለ የአንድነት መንፈስ አጠናክሮ ለማስቀጠል ይረዳል ብሎ ከማመኑ በመነጨ ቅንነት፤ አጠቃላይ ሂደቱን “የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ” እያለ መጥራት መጀመሩን ተከትሎ፤ ይህን ይበልጥ ለመነቃቃት የሚጠቅም አወንታዊ አንድምታ ያዘለ መሰረተ ሃሳብ ለማጥላላት ሲባል ብቻ የሚደረግ የሚያስመስለው ፕሮፓጋንዳዊ ቅኝት ያለውን “ታላቅ ነበርን፤ ታላቅም እንሆናለን” የተሰኘ የቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ አባባል ማስጮህ የያዙበት አግባብ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች በቅርብ ጊዜው የዘመነ “ነጭ-ሽብር ቀይ-ሽብር” አሳዛኝ ታሪካችን፤ ከተራ የ “እናቸንፋለን” እና “እናሸንፋለን” የሚል የአንድ ፊደል ልዩነት በሚመነጭ ጎራ ለይቶ መፈራረጅ ምክንያት ወደ መረረ የጠላትነት ስሜት እያመራን እርስ በራሳችን ስንጨራረስ የተስተዋልንበትን ታሪካዊ ስህተት የሚያስታውስ አሉታዊ ገፅታው የጎላ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡
ለነገሩ በዛሬዋ ፌዴራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ ውስጥ የንጉሰ ነገስቱን የመከነ ህልም እንደ አዲስ ማስተጋባት በራሱ የሚያስተዛዝብና ጥያቄ የሚያስነሳ ድርጊት አይደል? ስለዚህም እንደእኔ እንደእኔ ከሆነ፤ እንደዚህ ዓይነቱን ሀገራችን ኢትዮጵያ በህዳሴ ጉዞ ላይ ናት የሚለውን የጋራ መግባባት ለማስተባበል ባለመ መትምክሃታዊ ቅኝት የሚገልጽ ተቃውሞ፤ በቸልታ ማለፍ ማለት የወደቀውን ስርዓት በማወደስ ተግባር የተጠመዱት ወገኖች የሚያቀነቅኑት የግዛት አንድነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ልዕልናውን ይዞ እንዲቀጥል መፍቀድ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
ምንም እንኳን ቡድኖቹ የመሰላቸውን ሀሳብ በሰላማዊ መንገድ እንዳይገልፁ ማገድ ሕገ መንግስታችን ላይ የተደነገገውን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መጣስ እንደሚሆንና መደረግ እንደሌለበት ቢገባኝም፤ ግን ደግሞ ማራመድ የያዙት አቋም ምን ማለት እንደሆነ ህዝቡ እንዲገነዘበው የማድረግ ሃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅብን መዘንጋት አይኖርበትም፡፡፡፡ ደግሞስ ይህ የምንገኝበት ወቅት በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የአስተሳሰብ ልዕልና መቀዳጀትን ግድ የሚል ወሳኝ ምዕራፍ የመሆኑ ጉዳይ እንደምን ሊረሳ ይችላል? ስለዚህም በኔ እምነት፤ የሰላማዊ ትግሉ የስበት ማዕከል ተደርጎ መወሰድ የሚኖርበት ቁልፍ ነጥብ፤ የህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነውን ብዝሃነታችንን በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል ጤናማ የአስተሳሰብ ምህዳር እንዲጠፋ ለማድረግ ያለመ ዕክል እየፈጠሩብን ያሉትን የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝት ፅንፈኛ አመለካከቶች በመድፈቅ ላይ ነው ባይ ነኝ፡፡
ይህን የምልበት ምክንያትም፤ በተለይ ከላይ የተመለከተውን “ታላቅ ነበርን፤ ታላቅም እንሆናለን” የሚል የአፄ ኃይለ ስላሴ ጥቅስ እንደወቅታዊ መሪ ሃሳብ የመቁጠር አዝማሚያን በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሲጥሩ የሚስተዋሉት ወገኖች፤ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ በሚለው አገር አቀፍ አጀንዳችን ዙሪያ ሊፈጠር የሚገባው የጋራ ግንዛቤ እንዳይፈጠር ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለምና ነው፡፡ ከዚሁ የትምክህት ሃይሎችን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በማቀንቀን የሚታወቁት የመዲናችን አንዳንድ ቡድኖች፤ በየኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያው ሲያስጮሁት ከሚደመጠው መሪ ሃሳብ መረዳት የሚቻለው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ፤ እነርሱና ደጋፊዎቻቸው ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ሂደቱን እንደማይቀበሉት ብቻ አይደለም፡፡
ይልቅስ አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ “በአንድ ወይም በሌላ መልኩ” ቀልብሰው ወደ ወደቀው የአፄውያኑ የጨፍልቀህ ግዛ ስርዓት ሊመልሱንም ጭምር ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያስረዳ ጉዳይ ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ስለዚህም ነው ቡድኖቹ ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ ድረስ እጅጉን በተጠና መልኩ ተቀናጅተው በከፈቱብን የአስተሳሰብ ጦርነት አማካኝነት በዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የህዳሴ መንፈስ ለማደብዘዝ ሲረባረቡ የሚታዩት፡፡
ጉዳዩን ይበልጥ አሳዛኝም አሳሳቢም እንዲሆን እያደረገው ያለው፤ደግሞ ፅንፈኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች የየራሳቸውን የትምህክትና የጠባብ ብሔርተኝት አባዜ የተጠናወተው አመለካከት በማስረፅ የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ለማምከን የሚሞክሩበት አደገኛ ዘረኝነታቸው ነው፡፡ ማለትም፤ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ አጠቃላይ ቁመና የትግራይ ተወላጆችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል የተቀረፀ እንጂ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ህዝብ የሚመለከት እንዳልሆነ አስመስለው ለማቅረብ ሲሉ የሚፈፅሙትን እጅግ በጣም አስነዋሪ ፖለቲካዊ ደባ ስንታዘብ ብዙ የሚያስደነግጥ ገፅታ እንዳለው መገንዘብ አያዳግትምና ነው፡፡ ይህን ጥሬ ሀቅ የሚጠራጠር ሰው ካለ በተለይም በምዕራቡ ዓለም ሀገራት እየኖሩ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሹት ፅንፈኛ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አቋም አራማጅ ቡድኖች በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩትን አስነዋሪ ዘረኝነት የማያውቅ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሌላው ቀርቶ፤ መላው ኢትዮጵያውያን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ አንድ ህብረተሰብ፤ ያለ የሌለ አቅማችንን አስተባብረን የምንገነባውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለማውደም ያለመ ጥቃት የመፈፀም እኩይ ተልዕኮ የተሰጣቸው የሻዕቢያ መንግስት ቅጥረኞች፤ ከሰሞኑ ያልተሳካ ሙከራ ያደረጉበትን የሽብር ተግባር የሚያደንቁ የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንዳሉ ነው ምንጮች የሚያመለክቱት፡፡ እንጂ በውጭ የሚኖሩት ፅንፈኛ ተቃዋሚ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኛ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ቡድኖችማ “ቱ.ፍ! ይሄ በዓባይ ወንዝ ላይ የተጀመረ ግድብ ከተገነባ ሞተናላ!” እንደማለት የሚቆጠር መገበዝ በፈጠረው ተራ እልህ የመጋባት ስሜት ተነሳስተው ከግብፃውያን ቢጤዎቻቸው ጋር እየተመሳጠሩ ታሪክ ይቅር የማይለውን የሀገር ክህደት ተግባር ወደመፈፀምና ማስፈፀም ከገቡ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
ደግነቱ ግን፤ የታላቁን የዓባይ ወንዝ የውሃ ሀብታችንን ገድበን ትርጉም ላለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የማዋል አለማዋሉ ጉዳይ፤ የሚወሰነው ካረጀ ካፈጀው መሳፍንታዊ የፖለቲካ አስተሳሰባቸው ጋር ወደ ከርሰ መቃብር መውረድን የመረጡ በሚመስሉት ስልጣን ናፋቂ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሆኑ ቀርቶ፤ በመላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም፤ አስመራ ላይ ከትመው የኢሳያስ ግፈኛ አገዛዝ ከኤርትራ ህዝብ ጉረሮ እየቀማ በሚሰፍርላቸው ቀለብ አማካኝነት ኢትዮጵያን እንደሀገር ለማተራመስና የህዳሴ ጉዞዋን አምክኖ ለማስቀረት ያለመ ስትራቴጂ ነድፈው፤ የሚንቀሳቀሱት ቡድኖች ያልደገሱልን የጥፋት ድግስ ያለመኖሩን ያህል፤ አንዱም እንኳን ግቡን ሳይመታ እነሆ ታላቁ የህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድባችን ግንባታው እየተገባደደ ስለመሆኑ ወዳጅም ጠላትም የተረዳው ሀቅ ይመስላል፡፡
ኧረ እንዲያውም ረቡዕ የካቲት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ የታመነ ምንጭ ጠቅሶ ከፃፈው ዜና እንደተረዳሁት ከሆነስ፤ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሂደት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት ተግባሩን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊጀምር ይችላል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ታዲያ ዛሬም ድረስ በዘመነ መሳፍንቱ ጨለምተኛ አስተሳሰብ ዕርስ በርስ ተጠላልፈን እንድንወድቅ ሊያደርጉን እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩትን የለሊት ወፎች (ፅንፈኞቹን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ማለቴ እንደሆነ ልብ ይሏል?) ምን ይውጣቸው ይሆን!? መቸስ እነርሱ የህልውናቸው መሰረት አድርገው የሚወስዱት የፈርጀ ብዙ ድህነትን ድቅድቅ ጨለማ እንደሆነ ቢታወቅም ቅሉ፤ በህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያ ህዝቦች ያላሰለሰ ጥረት ምክንያት እነሆ ታላቁ የብርሃን ምፅአት ተቃርቧልና ወየውላቸው!!
ለማንኛውም ግን ሀገራችን ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ በስተጀርባ እየሆነ ስላለው ነገር ከሞላ ጎደል ለማየት የሞከርንበትን ፅሁፍ ከማጠቃለሌ በፊት አንድ ነጥብ ላይ ሊሰመርበት እንደሚገባ ልጠቁም፡፡ እርሱም፤ በተለይ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፅንፈኛ አመለካትን የሚያቀነቅኑት ወገኖች በስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ሂደቱ ላይ እየፈጠሩ ያሉትን አሉታዊ ተፅእኖ ትርጉም ባለው መልኩ ለመመከት የሚያስችል ሀገር አቀፋዊ የአስተሳሰብ ትግል ማፋፋም ግድ ይላል የሚል ነው፡፡ በተረፈ የሰማነውን ሁሉ ወደቁም ነገር የምንለውጥ የተግባር ሰዎች ያደርገን ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡ መዓሰላማት!