የከበደ አደራ፤ የዘመኑ ጥያቄ እና ፍላጎት ከወጣቶቻችን አንፃር

የዓድዋ ድል የቀደሙ አያት ቅድመ-አያቶቻችን በዓድዋ ተራሮች እና ሸለቆዎች በመዝመት እና በፋሺስት እና ወራሪው የኢጣሊያን ዘመናዊ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ታላቅ ድል የተቀዳጁበት አንጸባራቂ እና ሕያው የመላ ጥቁር ሕዝቦች ድል ነው፡፡ ቀደምት አባቶች ለወጣቱ ትውልድ የተዉት ሀገርህን ነቅተህ ጠብቃት፤ አልማ፣ አሳድጋት የሚል የከበደ አደራ ነው፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ በዘመኑ ኃያል ከሚባሉት ሀገሮች ተርታ የምትገኝ፣ ሠራዊቷም ዘመኑ የፈቀደውን የጦር መሣሪያ የታጠቀ፣ የተደራጀ እና ከፍተኛ ወታደራዊ ዕውቀት በነበራቸው ጄኔራሎች የሚመራ የነበረ ሲሆን፤ በጦርነቱ ታንኮች፣ መድፎችን እና አውሮፕላኖችን ሳይቀር አሰልፋ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ጀግኖች ግን ጦር፣ ጋሻ እና ጎራዴ፣ ጥቂት ጠመንጃዎች እና መትረየሶች፣ አነስተኛ መድፎችን በመታጠቅ፤ ከሁሉም በላይ በልብ የተጻፈ ታላቅ የሀገር ፍቅር፣ ወኔ እና ጀግንነትን በመያዝ ነበር ፋሺሽቱን የተጋጠሙት።

በዚህ ያልተመጣጠነ ዓቅም ኢትዮጵያውያን ያንን የደረጀ የአውሮፓ ሠራዊት በጦር ሜዳ ገጥመው ማሸነፍ ይችላሉ ብሎ ያሰበም የገመተም የውጭ ኃይል አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ጀግኖች ግን ዓለም ራሱን እስኪጠራጠር እና ማመንም እስኪሳነው ድረስ  ያንን ዘመናዊ የተባለ ሠራዊት ገጥመው ድል አደረጉት፡፡ ታላላቅ የተባሉት የኢጣሊያ ጄኔራሎችም ተሸንፈው ተማረኩ፡፡ በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሠራዊት ኢትዮጵያ በተባለች የጥቁሮች ምድር በጦር ሜዳ ድል ተነሳ፤ በወቅቱ የነበሩት መገናኛ ብዙኅን እንደዘገቡትም “አይቀጡ ቅጣትን ተቀጣ”፡፡

ከዓድዋው ጦርነት በፊት በዓለም ላይ የነጮቹ ወራሪ ሠራዊት በየትኛውም ለወረራ በተሰማራበት ሀገር ተሸንፎ አያውቅም፡፡ ይህ ሁሉ ታሪክ የጣሊያንን ውድቀት ባረጋገጠ መልኩ ዓድዋ ላይ ድል ተደረገ፤ ተደረገናም ያ የነጮች የተኮፈሰ ታሪክ ተቀየረ፡፡ ድሉ በመላው ዓለም በሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ከአጥናፍ አጥናፍ ተስተጋባ፡፡ በባርነት እና በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ሲማቅቁ የነበሩ ሕዝቦች የዓድዋን ድል በመከተል ነጻነታቸውን ይጎናፀፉ ዘንድ ተጋድሎአቸውን አጋጋሙት፡፡ በታላቅ መስዋዕትነት እና ተጋድሎ ነጻነታቸውን ማወጅ እንዳለባቸውም ከዓድዋው ድል ተማሩ፡፡

ከዓድዋ ድል በኋላም በርካታ የዓለማችን ቅኝ ተገዢ ሀገራት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎን በማድረግ እና መስዋዕትነትን በመክፈል ነጻነታቸውን ማስከበር ቻሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ዓድዋ በተባለ ስፍራ የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት በጥቁር ሕዝቦች ጀግንነት ያውም በጦር ሜዳ ድል መደረጉ በተምሳሌነቱ የሚጠቀስ የሚወደስ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች መነጋገሪያ እና አርማም ሆነ፡፡

ድሉ የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ድል ተደርጎ ተወሰደ፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የነጻነት አርማ አድርገው ተቀበሉት፡፡ በርካታ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማዎቻቸውን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለሞች ዓይነት እንዲሆንም አደረጉት፡፡ ስለዚህ የዓድዋ ድልን መላው የአፍሪካ ሕዝቦች የራሳቸው አድርገው የወሰዱት፤ እጅግ የሚኮሩበት ታላቅ ድልም ሆነ፡፡ የድሉ ዜና ከኢትዮጵያ ተራሮች እና ሸንተረሮች፤ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ሰማይም ሞላ፡፡

ይህ ድል አፍሪካውያን እና በሌሎችም ዓለማት የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ለነጻነታቸው እንዲታገሉ መነሳሳትን የፈጠረ ሲሆን፤ በሂደትም ለነጻነት ያበቃቸው የዓድዋ ድል በኩር ተምሳሌትነት ነው፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ተተኪ ወጣት ትውልድ የቀደሙት አያቶቹ እና አባቶቹ በታላቅ ብሔራዊ ፍቅር እና ጀግንነት ተጋድሎ አድርገው በወራሪው ጠላት ላይ የተቀዳጁትን በጀግንነት የተሞላ ድል አድራጊነት ጠብቀው ያቆዩለትን የከበደ የአገር አደራ ለመወጣት ይበልጥ መትጋት፣ በቁርጠኝነት ሀገሩን በማልማት እና ከድህነት በማውጣት አዲስ ድል እና ታሪክ ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ የወቅቱ ጠላት ድህነት ነውና!!

ያ በዓድዋ ተራሮች፣ ሸንተረሮች እና ሸለቆዎች በወራሪ የቅኝ ገዢ ሠራዊት ላይ የተገኘ እና በዓለም ታሪክ የተመዘገበ አንፀባራቂ ድል፤ ዛሬ ደግሞ በተጀመረው ሀገርን የማልማት እና የማሳደግ ድህነትን እና ኋላቀርነትን ለማጥፋት እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ ትንቅንቅ እና ትግል በድል አድራጊነት በመወጣት አዲስ ታሪክ፣ አዲስ ጀግንነት፣ አዲስ የዓድዋ ድልን በተለየ መልኩ መፈጸም ያለብን ስለመሆኑ አባቶች ለዛሬው ትውልድ የአስረከቡት ታላቅ አደራ ነው፡፡

እኛ ሀገርህን ከወራሪ ጠብቀን በደም እና አጥንታችን ዛሬ የምትኮራበትን ነጻነት አስረክበንህ አልፈናል፡፡ አንተስ የዛሬው የእኛ ተተኪ የሆንከው ትውልድ ኢትዮጵያን ትላንት ከነበረችበት ተረክበህ የት አደረስካት? ለሚለው የሕሊና እና የመንፈስ ጥያቄ የዛሬው ትውልድ ምላሽ በተግባር ሀገሩን በልማት፣ በማሳደግ፣ አንድነትዋን፣ ክብርዋን እና ነጻነትዋን በመጠበቅ፣ የውጭ ጠላቶቿን ከፋፋይ ሴራ በማክሸፍ እና እንደአባቶቹ በጋራ እና በሕብረት ጸንቶ በመቆም ሀገሩን በመጠበቅ የሚሰጥ መልስ ነው የሚሆነው፡፡

በዓድዋ ጦርነት ተገኘው ድል የታላቅ ኢትዮጵያዊነት፣ የአንድነት ጽናት እና ጀግንነት፣ በፍቅር ለሀገር መስዋዕት እና ቤዛ የመሆን ታላቅ ተምሳሌት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ልጆች በፍፁም በአንድነት ለሀገራቸው ቆመው፣ ተዋግተው፣ ሞተው እና ገለው ዘላቂ የሀገራቸውን ሕልውና ያስጠበቁበት፣ እንዲሁም  ሉዓላዊ ድንበሯን ያስከበሩበት ታላቅ ድል ነው፡፡

አንፀባራቂው የዓድዋ ድል በዓል በመላው ዓለም ዘንድ ልዩ እና ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ የአንድነት፣ የታላቅ ጀግንነት፣ የኅብረ ብሔራዊነት፣ የማንነታችን ልዩ መለያ ስለሆነ በተምሳሌትነቱ ዘመናትን የሚሻገር፣ ለቀጣይ ትውልዶችም አያት/ቅድመ-አያቶቻቸው እና አባቶቻቸው ለሀገራቸው ነጻነት እና ክብር የተፋለሙበት፣ ዓለምን ባስደመመ መልኩ በድል አድራጊነት የደመደሙት ጦርነት ስለሆነ፣  ክብራቸው እና ኩራታቸው በመሆኑ ሊማሩበት የሚገባ፣ ለታላቅ ሀገራዊ ግንባታም እንዲሰለፉ የሚያበቃቸው ነው፡፡

ወጣቱ በዚህ ወቅት ከፊቱ የተደቀነ ጦርነት ባይኖርም ለዘመናት በሀገሩ ተንሰራፍቶ የኖረውን ድህነት እና ኋላቀርነት  ለማንበረከክ  ከአያቶቹ የተማረውን የአንድነት እና አልበገርም ባይነት መንፈስ ለሀገራቸው የነበራቸውን የጸና ፍቅር እና እምነት በማያወላውል ሁኔታ ያሳዩበት በመሆኑ ወጣቱ ሀገሩን በመለወጥ በማልማት እና በማሳደግ ረገድ ብዙ ሊማርበት ይገባል፡፡ እናት-አባቶቻችን በአልገዛም ባይነት  የኢጣሊያ ጦርን በዓድዋ ተራሮች ላይ ድል አድርገው ብቻ ሳይሆን፤ አሳፍረው መመለሳቸው  በአሁኑ ወቅት ለተለያዩ  የውጭ የባዕዳን የባሕል ወረራ እየተጋለጡ  ላሉ የዚህ ትውልድ አባላት ማንነታቸውን እና ራሳቸውን እንዲያውቁ ትልቅ ትምህርት ሊሆናቸው  ይገባል፡፡ 

የቀደሙት አባቶቻችን የጀግንነት መንፈስ ዛሬም ነገም በደማችን ውስጥ አለ፤ ይኖራልም፡፡ የዛሬው ወጣት ትውልድ ተላቅ ሀገራዊ አደራ እና ኃላፊነት ተሸካሚ በመሆኑ ሰፊ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ሀገሩን ለመለወጥ እና ለማልማት መትጋት ይገባዋል፡፡ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመረውን  ሁሉን አቀፍ ንቁ ተሳትፎ ይበልጥ በማጠናከር የአባቶቹን የአገርን ዳር ድንበር የማስከበር አኩሪ ታሪክ በልማቱ ዘንድ በመድገም ቃላቸውን፣ የከበደውን አደራ  ለመወጣት ያስችለዋል፡፡

የዓድዋ ድል ለጥቁር አፍሪካውያን የነጻነት ጮራ የፈነጠቀ ብዙ ሀገራትን ለትግል እና ድል ያነሳሳ፣ ከፍተኛ የሞራል ስንቅም የሆናቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ላይ ድል የተቀዳጁበት የዓድዋ ጦርነት በዓለም አዲስ ታሪክ እንዲመዘገብ ያደረገ፣ የነጮችን የበላይነት ሕልም የሰበረ እና የጥቁሮችን እኩልነት ያበሰረ ነው፡፡ የዓድዋ ድል በነጭ  ቅኝ ገዥዎች ላይ የተመዘገበ አኩሪ  ድል ሆኖ  በዓለም የታሪክ መዝገብ ላይ በደማቁ የሠፈረ የመጀመሪያው ታላቅ የጥቁር ሕዝቦች ተጋድሎ እና ድል ነው፡፡ የፀረ- ቅኝ ግዛት ትግሉ በያለበት እንደ ሰደድ እሳት እንዲቀጣጠል ያደረገ፤ ለዛሬው ዘመን ነጻነት ይበቁ ዘንድም ጎህ የቀደደ ድል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በአንድነት በመቆም ከዳር እስከ ዳር በመነሳት ለአገር ክብር እና ነጻነት ታላቅ የሕይወት  መስዋትዕነት  ከፍለው መላውን ዓለም ያስደመሙበት በደማቸው ታክ የጻፉበት አኩሪ ድል እና ተጋድሎ ነው፡፡ ዓድዋ እና የዓድዋ ድል ሲነሳ ይህ ምን ግዜም ተደጋግሞ ሊነገር፣ ሊተረክ፣ ሊዘመር . . . የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

የዓድዋ ድል የአሁኑ ትውልድ ከቀደሙት አባቶቹ ብዙ ጉዳዮችን የሚማርበት፣ ለጋራ ሀገር ያለልዩነት መቆምን ያጸና ድል ነው፡፡ የዘመነች እና ከድህነት የወጣች ያደገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትውልዱ የአባቶቹን የጀግንነት መንፈስ ተቀብሎ በታላቅ ወኔ እና ሥነ ምግባር ለመወጣት ራሱን ማብቃት፣ ጠንክሮ መሥራት እና መለወጥ እንዳለበት የከበደ አደራን በትከሻው ላይ የሚጥል ነው የዓድዋ ተጋድሎ እና ድል፡፡

ዛሬም በሀገራችን በብዙ መስኮች እየተመዘገቡ ያሉት የልማት እና የዕድገት ውጤቶች እና ድሎች፤ ሀገራዊ ታላላቅ ግንባታዎች ተተኪው ትውልድ የአባቶቹን አደራ በመወጣት ላይ እንዳለ የሚያሳዩ ሕያው ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ ከብዙዎቹ ትልቁ እና አንዱ የሆነው በዓባይ ወንዝ ላይ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ  በራስ ሀገራዊ ዓቅም፣ ገንዘብ፣ ጉልበት እና ዕውቀት፣ እንዲሁም በሕዝቡ ታላቅ ተሳትፎ እና ባለቤትነት የመገንባቱ ሥራ አንዱ ማሳያ እና ማረጋገጫ ነው፡፡

 በዘመኑ ከዓለም ኃያላን አገራት ጎራ ትመደብ የነበረችውን፣ ወራሪዋን ፋሽስት ኢጣሊያ እና ለቅኝ ገዢነት የዘመተውን ሠራዊትዋን በታላቅ ጀግንነት በዓድዋ ጦርነት ገጥማ እና መክታ ድል የመታች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር  ኢትዮጵያ ነች። ለዚህ አኩሪ ድል ያበቋት ልጆችዋ ናቸው፡፡ ይህም መቸም ሆነ የት፣ ሁሌም ለፃፍ፣ ለዘመርለት እና ሊተረክለት የሚገባ ህያው ገድል ነው።

የዛሬውም ሆነ መጪው ትውልድ ይህንን የገዘፈ ኢትዮጵያዊ ኩራት እና ጀግንነት ሊጠብቀው፣ ሊኮራበት፣ ሀገሩን የበለጠ ለማልማት እና ለማሳደግ ከቆራጥነታቸው እና ከብርታታቸው ሳያቅማማ ሊማርበት ይገባል፡፡

የዓድዋ ድል ሁሌም ሲከበር እና ሲዘከር ይኖራል፡፡ በዓድዋ ድል  የተገኘውን የአንድነት ጽናት እና ብርታት ተጋድሎ መሠረት በማስፋት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ማኅበራዊ ልማትን በማረጋገጥ ድሕነት እና ኋላቀርነትን ከምድራችን ነቅለን ለማጥፋት ትውልዳዊ ርብርብ ያስፈልገናል፡፡ ሀገራችንን ለማዳከም እና ለማጥፋት በተለያዩ አቅጣጫዎች እያደቡ ያሉትን የውጭ ኃይሎች እና ሴራቸውን ትውልዱ ነቅቶ በመጠበቅ፣ ሀገሩን በማልማት፤ ከጠላት በመከላከል ወዘተ ታላቅ፣ አባቶቹን እና እናቶቹ የተጣለበትን የከበደ አደራ በተግባር ሊወጣ ይገባዋል፡፡ ወጣቶቻችን ሊመልሱት የሚገባው የዘመኑ ጥያቄም ይሄው ነው።