ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አገራትን ለመቀላቀል የሚያስችላትን በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በስፋት በማከናውን ላይ ትገኛለች። ለአረንጓዴ ልማት ስኬት ኢትዮጵያ የሃይል ፍጆታዋን ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ የሃይል ለማድረግ እንዲሁም ከታዳሽ ሃይል የሚመነጭ ሃይልን በተመጣጣኝ ዋጋ ለጎረቤት አገራት በመሸጥ የገቢ ምንጯን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ ነች። በአማካይ በዓመት ከ10 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ ያለው የአገራችን ኢኮኖሚ ቀጣይነቱን ለማረጋገገጥና የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ የአገራችን የሃይል አቅርቦቱም በየዓመቱ ቢያንስ ከ20 በመቶ ማደግ ግድ ይለዋል። ለዚህም ነው መንግስት በየዓመቱ በርካታ የሃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ላይ የሚገኘው። የኢትይጵያ የሃይል አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ የሃይል ምንጭ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት አገራችን ከታዳሽ የሀይል ምንጮች ብቻ በመቶ ሺዎች ሜጋ ዋት የሚቆጠር ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ዕምቅ አቅም አላት። ከዚህም ውስጥ ከውሃ ወይም ሀይድሮ ብቻ ከ45 ሺህ ሜጋዋት በላይ ማመንጨት ትችላለች። በዓለም ላይ ሃይል ለማመንጨት እንደውሃ ቀላልና ርካሽ የለም።
ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ የሃይል አማራጭ በሙሉ ማመንጭት ብትችልና ከአገር ውስጥ ፍጆታዋ የተረፈውን ወደ ውጭ ብትልክ በዓመት 50 ሚልዮን ቶን ለአየር ንብረት ብክነት የሆነውን ጋዞችን መቀነስ ትችላለች። ይህን ታሳቢ በማድረግ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቋቋም የሚያስችል የአረንጓዴ ልማት ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ በመቅረጽ በመተግበር ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የሃይል ፍላጎቷን ከታዳሽ ሀይል በተለይም ከውሃና ከንፋስ በማመንጨት ረገድ በተነጻጻሪ ከሌሎች ሀገራት ቀዳሚ ሆናለች። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ የገነባቻቸውን በርካታ የሃይል ማመንጫዎች ሁሉም ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆኑ ናቸው። ባለፉት አስር ዓመታት መንግስት እድሳት ካደረገባቸው የሃይል ማመንጫዎች ባሻገር አዳዲስ ከገነባቸው የሃይል ማመንጫዎች ቢያንስ ከአራት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ማመንጨት ችሏል። የጊቤ (አንድ፣ ሁለትና ሶስት)፣ ተከዜ፣ ጣና በለስ፣ አሻጎዳ፣ አይሻ ተጠቃሽ ናቸው። በግንባታ ላይ የሚገኙት ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ፣ ኮይሻ፣ ገናሌ ዳዋ ተጠቃሾች ናቸው። ሁሉም የሃይል ማመንጫዎች ከታዳሽ የሃይል ምንጭ የሚቀርቡ መሆናቸው አገሪቱ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠችውን ትኩረት ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከታዳሽ ሃይል ማመንጨት ጥረቷ ባሻገር ለአረንጓዴው ልማት ስትራቴጂ ስኬት ሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነች። የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ፣ ኢትዮጵያ ያቀደችውን የተለጠጠ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካትና የሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ ድርቅን መከላከል ትኩረት ያደረገ ነው። ኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ማከናወን በመቻሏ በርካታ ለውጮችን ማስመዝገብ ችላለች።
ኢትዮጵያ አሁን እያስመዘገበች ያለችው የኢኮኖሚ ዕድገት በነዳጅ ሃይል የሚመነጭ ቢሆን 2022 ዓ.ም ወደ አየር የምትለቀው የሙቀት አማቂ ጋዞች 400 ሚልዮን ቶን እንደሚደርስ የዘርፉ ባለሙያዎች ይተነብያሉ። ከዚህ ባሻገር አገሪቱ ነዳጅ አምራች ባለመሆኗ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማጋለጥ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ይገታል፤ ይህ ሲሆን ደግሞ ዜጎች የሃይል ፍላጎታቸውን ደን በመጨፍጨፍ ለማሟላት ስለሚገደዱ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ ይከሰታል። ይህ ደግሞ ለአካባቢ ብክለት ዋንኛ ምክንያት ይሆናል።
ከታዳሽ ሀይል በተለይም ከውሃ ሀይልን በማመንጨት በተነጻጻሪ ከሁሉም የሃይል ማመንጫዎች እጅግ አዋጭ ነው። በዚህ ዘርፍ አገራችን በተፈጥሮ የታደለች በመሆኗ በቀጣይ ከፍተኛ ገቢ ልታገኝ ትችላለች። ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ቀድማ አረንጓዴ ልማትን መተግበር በመጀመር ተምሳሌት ልትሆን የምትችል አገር ነች።
የኢፌዴሪ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ማሳደግና ማዘመን የአረንጓዴ ልማት የስትራቴጂ አካል አድርጎ በመውሰድ ላይ ይገኛል። ግብርና በኢትዮጵያ የአብዛኛው ዜጎች መተዳደሪያ መሆኑና ዋንኛው የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ የሚመጣ ለውጥ ሁሉን አቀፍ ነው። መንግስት ለዚህም ነው ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት የሰጠው። መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በተለምዶ እንደሚደረገው የተገኘው መሬትን ማረስ እንደማይገባና አርሶ አደሩ ከመሬት ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ በባለሙያዎች እንዲታገዝ በመደረግ ላይ ነው።
በአርብቶ አደሩም አካባቢዎች የተጀመሩ መልካም ነገሮች እንዳሉ ማየት ይቻላል። አርብቶ አደሩ በጥቂት እንሰሶች የተሻለ ውጤት ማግኘት የሚያስችሉ የእንሰሳት ዝርያዎችን እያገኘ ነው። ከዚህም ባሻገር አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲሸጋገር የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
ከዚህም ባሻገር የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል አነስተኛ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ስራዎችም በመተግበር ላይ ናቸው። እነዚህ ተግባራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለአካባቢ ጥበቃ ያላቸው አስተዋጽዖ እጅግ ከፍተኛ ነው።
ለአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው ስኬት መንግስት እያከናወነው ያለው ሌላው ተግባር የደን ሃብትን መጠበቅና ማልማት ነው። የኢትዮጵያ የድን ሽፋን ከአስርት ዓመታት በፊት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ (ከሶስት በመቶ አካባቢ) ደርሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይሁንና መንግስት የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ በተካሄዱ የተፋሰስ ልማትና በየዓመቱ በሚተከሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በአጭር ጊዜ የአገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 15 በመቶ እድገት አሳየቷል።
አንዳንድ ባለሙያዎች አሁን ላይ የአገሪቱ የደን ሽፋን ከተጠቀሰው አሃዝ እንደሚልቅ ይናገራሉ። አርሶና አርብቶ አደሮች የተፋሰስ ልማት ስራዎች የሚያስገኙትን ጥቅም በተግባር መረዳት በመቻላቸው በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶና አርብቶ አደሮች በተፋሰስ ልማት ስራዎች ያለማንም ጎትጓች በነጻ በመሳተፍ ላይ ናቸው።
አርሶና አርብቶ አደሮች ባለሙያዎች በሰጧቸው ምክር የተጎዱ አካባቢዎችን ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረጋቸው በርካተ አካባቢዎች በቀላሉ ማገገም ችለዋል። እንዲሁም ከእነዚህ ማገገም ከቻሉ አካባቢዎች አርሶና አርብቶ አደሩ ለእንሰሳቱ የተሻለ መኖ ማግኘት ችለዋል።
ከዚህም ባሻገር በተፋሰስ ልማት ያገገሙ አካባቢዎች ለግብርናው ምርት መጨመር ትልቅ አስተዋጽዖ ከማበርከቱም በላይ ለዜጎች ከፍተኛ የስራ ዕድል በመፍጠር ላይ ነው። የተፋሰስ ልማት ባገገሙ አካባቢዎች ወጣቶች አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት እንዲሁም ንብ በማነብ የገቢ ምንጫቸውን ማሳደግ ችለዋል። የተፋሰስ ልማት ስራዎቻችን የአካባቢን ደህንነት ከማስጠበቃቸው ባሻገር የአገሪቱንም ኢኮኖሚ ማሳደግ የሚያስችሉ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መሰረት ያደረገው የታዳሽ የሃይል አቅርቦቷ የራሷን ፍላጎት ካሟላች ብኋላ ለአከባቢው አገራት ትርፍ የኤሌክትሪክ ሀይልን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ የምትሆንበትን አሰራርን በመከተል ላይ ነች። እስከሰሁንም ጅቡቲና ሱዳን ተጠቃሚ ሆነዋል። ኬንያም በቅርቡ ተጠቃሚ የምትሆንበት መሰረተ ልማት ተዘርግቷል። ኢትዮጵያ ታዳሽ ሀይል ለአከባቢው አገራት በማቅረብ የአካባቢውን አገራት በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስተሳሰርና የቀጠናውን ሰላም ዘለቄታ ለማረጋገገጥ በመስራት ላይ ነች።
የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን የሚያስፈልገው የመነሻ መዋዕለ-ንዋይ በጣም ከፍተኛ ቢሆንም ኢትዮጵያ ለዘርፉ ልማት ትኩረት በመስጠቷ ብድርና ዕርዳታ ያልተገኘባቸውን ፕሮጀክቶች በራሷ አቅም በመገንባት ላይ ነች። ኢትዮጵያ በቀጣይ 20 ዓመታት ለኃይል ማመንጫ መሰረተ ልማቶችን ብቻ ለመገንባት 38 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልጋት የአለም ባንክ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። መንግስት ይህን ዘርፍ ለማልማት ቁርጠኛ አቋም ያለው በመሆኑ ብድር ለሚገኝላቸው ፕሮጀክቶችን በብድር ካልሆነም በራስ አቅም በማልማት ላይ ይገኛል።
የአገራችን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ድርቅን ለመቋቋም ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ ነች። አለማችን ለአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመጋለጧ ለድርቅና ጎርፍ በመጋለጥ ላይ ነች። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የሚችል ዕድገት በመገንባት ላይ ነች።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ባለፈው አመት አገራችን በ50 ዓመት ታሪክ ተከስቶ የማያውቅ ድርቅን በአብዛኛው በራሷ አቅም መቋቋም ችላለች። ዘንድሮም በመጠኑ አነስተኛ ቢሆንም በአገራችን በርካታ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቷል። መንግስት በራሱ አቅም ለዜጎች ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ለመፍጠር ያላትን ውጥን ላማሳካት፤ የአረንጓዴ ልማት ወሳኝ ሚና እንዳለው በመረዳት ከማንኛውም አገር ቀድማ በመተግበር ላይ ትገኛለች። አገራችን የአረንጓዴ ልማትን ከኢኮኖሚ ዕድገቷ ጋር ማስተሳሰር ችላለች።
በአረንጓዴ ልማት አገራችን ጥሩ ሞዴል ወይም ተምሳሌት ልትሆን የምትችል አገር ናት። በመሆኑም የአገራችንን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ሌሎች አገራትም ተግባራዊ በማድረግ ዓለማችንን ከጥፋት መታደግ ይኖርባቸዋል።