የታላቁ ግድባችን የሂሳብ ቀመሮች

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ እንዲጀመር የመሠረት ድንጋይ በይፋ የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ቀናት ብቻ ይቀራሉ፡፡ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ አቅም በአፍሪካ ትልቁ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ 10 ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች መካከል አንዱ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከራሷ በሚፈልቀው የዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የቆየውን የግብፅ ብቸኛ ተጠቃሚነትንና ኃያልነትን የሰበረመሆኑ ክንውኑ ታሪካዊ ነው፡፡ ይህ አገራዊ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የውኃ ሀብታቸው ያለ ጥቅም ለዘመናት ሲፈስ እያዩ ምንም ማድረግ ላልቻሉ የናይል ወንዝ ተጋሪ አገሮችም ጭምር ነው።

 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጅምሩ አንስቶ ኅብረተሰቡን ያስተሳሰረ ነው። አሁንም በፋይናንስ ድጋፍም ሆነ በመንፈስ በአንድነት አስተሳስሮን በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። የፀጥታ ችግሮችና ፈተናዎች በነበሩባቸው አካባቢዎችም ጭምር በኅብረተሰቡ  ቀዳሚ ሥፍራ የተሰጠው፣ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ኃያል ሥፍራን የያዘ ፕሮጀክት እንደሆነ እያየን ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ነው ከሚያስብሉት ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያሳረፈበት ስለሆነ ነው።

 

ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ላይ በዋና ኮንትራክተርነት እንዲሳተፍ መንግሥት ሲወስን ብዙዎች ተጠራጥረውትና ምን ሲደረግ ብለው የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከታሰበው በላይ ውጤት በማሳየት አገራዊ አቅም ሆኖ ወጥቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ሥራዎች ግማሽ የሚሆነውን የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች ኃላፊነት ወስዶ በብቃት እያከናወነ ነው። ይህንን ስራ የውጭ ኩባንያዎች ኃላፊነቱን ወስደው ቢሆን ኖሮ ይደርስብን የነበረን ዲፕሎማሲያዊ ጫና መገመት አይከብድም። በራሳችን አቅም ወደስራው መግባታችን ያስወገደልን ዲፕሎማሲያዊ  ጫናውን ብቻ አይደለም። ግንባታው የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገልን እና እንደሚያደርግልን አያጠያይቅም፡፡ ይህን ለማጠየቅ  ተመሳሳይ ጫና በጊቤ ሦስት ላይ ገጥሞን እንደነበር ማስታወሱ ይበቃል፡፡  

ታላቁ የህዳሴ ግድብ  ለውጭ ተፅዕኖ ተጋላጭ ያልሆነው በራሳችን አቅም እየተሰራ ስለሆነ ጭምር ነው። እንኳንስ ለውጭ ኮንትራክተር ጠቅልለን ሰጥተነው ይቅርና በከፊል የሰጠነው እና ሲቪል ኮንትራቱን የወሰደው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ለቆ እንዲወጣ ጫና ደርሶበታል፡፡  ነገር ግን ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ ብዙ ዓመታት የቆየ በመሆኑና ኢትዮጵያን በደንብ ስለሚያውቅ ጫናውን ተቋቁሞ አብሮን ተሰለፈ እንጂ ሌላ ኩባንያ ቢሆን ኖሮ ምን ይፈጠር እንደነበር ለመገመት አይከብድም፡፡ ስለዚህ የአደጋ ተጋላጭነቱን የቀነስንበት አንዱ መንገድ የራሳችንን አቅም በማስገባት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ የፋይናንስ ጫናም ቀንሰናል፡፡ የቴክኖሎጂ አቅምም ፈጥረናል፡፡ አንድ አገር ቀጣይ ዕድገትን የሚያረጋግጠው አስተማማኝ የሆነ የቴክኖሎጂ አቅም ሲኖረው ነው፡፡ ነፃ ነን ማለት የሚቻለው በራስ መሥራት ሲቻል ነው፡፡

ስለዚህ መያዝ የሚገባው ቁም ነገር በዚህ ፈታኝ ፕሮጀክት የአገር ውስጥ ኩባንያ አስገብተን ግድቡን እየገነባን፣ አቅማችንን መገንባታችንን የተመለከተው እንጂ ጀማሪ እንደመሆናችን የሚያጋጥሙን መንገራገጮች ሊሆኑ አይገባም፡፡ የገነባነውን አቅም ብዙ ርቀት ሳንጓዝ ግና በግንባታው የመጀመሪያ ዓመት ላይ ለማየት ችለናል፡፡ 5ሺ 200 ሜጋ ዋት የነበረው የግድቡ የማመንጨት አቅም ወደ 6ሺ ሜጋ ዋት የተሸጋገረው በኮርፖሬሽኑ ነው፡፡ አሁን ደግሞ አጠቃላይ የግድቡ የማመንጨት አቅም ወደ 6ሺ 450 ሜጋ ዋት አድጓል፡፡ ይህም የሆነው በዚሁ ኮርፖሬሽን በኩል በተገነባ አቅም ነው። ስለዚህ ኮርፖሬሽኑ መማር ብቻ ሳይሆን እየተማረና እየሠራ ተጨማሪ የማመንጨት አቅም እንዲኖርም አስችሎናል። ይህንን ውጤት ሲያስመዘግብ ተጨማሪ ኃይል እንጂ ተጨማሪ ወጪ አልወጣም፡፡  

የማመንጨት አቅሙ ከ5ሺ 200 ሜጋ ዋት ወደ 6ሺ ሜጋ ዋት እንዲያድግ ሲደረግ፣ በሲቪል ሥራው ዲዛይን ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ የነበሩት 15 ተርባይኖች ወደ 16 ስላደጉ የግድቡ ዲዛይን መሻሻሉ፤ በዚህ ምክንያትም ጊዜ መውሰዱ የሚጠበቅ ነው፡፡ አንድ ተጨማሪ ተርባይን እንዲይዝ ለማድረግ የግድቡ ጎን እንዲሰፋ መደረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ተራራ መግፋት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም የጊዜ ጉዳይ ሲሰላ እንዚህንም ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።  

ከጊዜ ጋር ተያይዞ ሊታሰብ የሚገባው ሌላኛው ቁምነገር ኃይል የማንጨት ሥራ ከታችኛው አገሮች ጋር በመመካከር የሚከናወን መሆኑን የተመለከተው ነው፡፡ ምክንያቱም ስምምነት አለን፡፡ ግድቡን በስንት ዓመት በውኃ እንሙላው በሚለው ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ የተጀመሩ እና በሒደት ላይ የሚገኙ ጥናቶች መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡  

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት አሁን ከግንባታ ጋር ተያያዥ የሚሆኑ ፈተናዎችን በሙሉ ያለፈ ለመሆኑ ቦታው ላይ ተገኝቶ የተመለከተ ሁሉ የሚመሰክረው ነው። ከጊዜ ጋር ተያይዞ ጥያቄ ስናነሳ እና ሊያወናብዱን የሚሹ ሃይሎች ጊዜን መነሻ አድርገው ቢሞግቱን መዘንጋት የሌለብን ከታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ጋር ስምምነት የሚጠይቀው አጠቃላይ ግድቡን በውኃ የመሙላት ሒደት ዋነኛው ፈተና መሆኑን ነው፡፡ በስንት ዓመታት ውስጥ ቢሞላ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት አያደርስም የሚለው በባለሙያዎች የተደገፈ ስምምነት ያስፈልገዋል፡፡ ጥናቱን እንዲያከናውኑ የተቀጠሩት ሁለት ገለልተኛ አማካሪ ኩባንያዎች ጥናታቸውን ለመጀመር በአሁኑ ወቅት ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ አጠቃላይ  ተርባይኖቹን (16ቱን) ሥራ ለማስጀመር የሚያስፈልገው ውኃ ትልቅ ሐይቅ እንደ ማለት ሲሆን፤ ከግብፅ የአስዋን ግድብ የሚበልጥ ነው፡፡ ጥንቃቄና ተነጋግሮ መግባባት የሚያስፈልገው ሥራ ነው፡፡ ሁለቱ ተርባይኖች ቅድሚያ ኃይል እንደሚያመነጩ የሚያስፈልገውን ውኃ በተመለከተ ግን ብዙ ችግርና ጫና የሚፈጥር አይደለም፡፡  

በዓለማችን ረጅም በተባለው የዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ከመወሰናችንና ግንባታው ከመጀመሩ በፊት ከፍተኛ ቁጭት የነበረን መሆኑ ይታወቃል። እኛ በዓባይ ወንዝ ለዘመናት የነበረን ቁጭት ተወግዶ ግንባታውን በመጀመር የግንባታው ሂደት መፋጠኑ ኢትዮጵያውያን እንደ አገር በአንድ ላይ ለአንድ ዓላማ የመቆማችንን፤ ለወደፊትም ይህን መንገድ የመከተላችን ዓቢይ ማሳያ እንደሆነም ይታመናል።  ስለሆነም ሁሉንም ነገር ስናሰላ ብዙ ውጣ ውረድ የነበረበትን ሂደት በማስታወስ ሊሆን ይገባዋል። በተለይም የዓባይን ወንዝ ለመገደብ ለግንባታ የሚሆን ገንዘብ በብድርም ሆነ በእርዳታ እንዳናገኝ በርካታ ተጽዕኖዎች እንዳጋጠመን አይካድም። ለእነዚህ ተጽዕኖዎች ሳንበረከክ አባይን ለመገድብ ስንነሳ እና ከግድቡ መጀመር ቀጥሎም ቢሆን ከተፋሰሱ አገራት ጋር በትብብርና በመግባባት መንፈስ ለመስራት ከፍተኛ ጥረት መደረጉ በበጎ ጎኑና በአርአያነቱ የሚጠቀስ የሂሳብ ቀመራችን ሊሆን ግድ ይለናል። ያጋጠሙንን አንዳንድ መሰናክሎችና ተግዳሮቶች ለመበጣጠስ ከተካሄዱት ፖለቲካዊና፣ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጋር የሕዝባችን ቁርጠኝነት ለውጤታማነታችን የላቀ ድርሻ ነበረው። በተለይም የግብፅ አለመረጋጋትን ተከትሎ የፕሬዚዳንት የሙርሲ ወደ ስልጣን መምጣት እና ከሙርሲ መንግሥት ምስረታ በኋላ በግንባታው መጀመር የተለያዩ ተቃውሞዎች እንደነበሩ ይታወቃል። አንዳንዶቹ በአገራችን ላይ ስጋት በማሳደር ጫና ለመፍጠርም የታለሙ የነበሩ እንደሀነ እና እንዴት ማቀዝቀዝ እንደቻልን መዘንጋት አይገባም ። 

ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች ዓይንና ጆሮ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ወረዳ ከዘለቀ ቆይቷል። በአሁኑ ሰአት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት ደረጃ አበረታች ከመሆኑም በተጨማሪ የግንባታው ሂደት በመፋጠን ላይ ነው። መላ ሕዝባችንን በተሳትፎው እንደጀመረው ለመጨረስ በተለያዩ መንገዶች ድጋፉን በማጠናከር የድርሻውን እየተወጣ ነው። ይህ የባንዲራ ፕሮጀክት ፍፃሜው ሩቅ እንደማይሆን ሁሉ ያንን ለማየት የማይጓጓ የለም። ግድቡ ሲጠናቀቅም አካባቢው የሚኖረው ገፅታና ማራኪነት ከወዲሁ ተስፋ ሰጭ ከመሆኑ በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎችም ለበርካታ ዜጎች የሰራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በአካባቢው በግድቡ ምክንያት በሚፈጠረው ኃይቅ ለአሳ እርባታና ለከፍተኛ የምርምር ስራ አመቺ መሆኑና በተፈጥሮ ለበርካታ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል ይሆናል። በዚህም ተስፋችን እውን ሆኖ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍጻሜ የተሻለች ኢትዮጵያን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከፍታው 145 ሜትር፣ የጎኑ ርዝመት 1.8 ኪ.ሜ. ሲደርስ የሚከማቸው የውሃ መጠን የጣና ሀይቅን ሁለት እጥፍ ይሆናል። ግድቡ ሲጠናቀቅ 1ሺ 680 ስኩየር ኪ.ሜ. የሚሸፍን ወደ 74 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር የውሃ መጠን ይኖረዋል። ከግድቡ ወደ ኋላ ሜዳማ ስፍራውን አልፎ በርቀት የሚታዩት አነስተኛ ተራራማ ስፍራዎች ጭምር ወደ 246 ኪ.ሜ. ወደ ኋላ በሚሞላ የውሃ ሀይቅ ተሞልተው ደሴት ይሆናሉ። በግድቡ ምክንያት የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ከፍተኛ የዓሳ ሀብት የሚመረትበት ከመሆኑ በተጨማሪ ለአካባቢው ስነምሀዳር ጠቀሜታ ያላቸው ሌሎች በየብስና ውሃ ነዋሪ የሆኑ እንስሳት እፅዋትና አእዋፍ መኖሪያም ይሆናል። እንዲሁም ከመዝናኛነቱም ባለፈ ለሳይንሳዊ የምርምር ሥራ ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚኖረው ይጠበቃል። በዚህም አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን እንደሚችል ተረጋግጧልና ሂሳብ ስናሰላ እነዚህነ እና መሰል ጉዳዮችን ታሳቢ ልናደርግ ይገባል።