ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ለድርድር አቅርባ የማታውቅ የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ሀገር ናት። ከባርነት፣ ከጭቆና እና ከቅኝ ተገዢነት ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ላደረጉ በርካታ የዓለማችን ህዝቦች አርአያና ምሳሌያቸው እስከ መሆንም ደርሳለች። ፈለጓን የተከተሉ በርካታ አፍሪካውያንም ባስመዘገቡት ድል ባለውለታነታቸውን በብዙ መንገድ ገልጸውላታል። የሰንደቆቻቸው ቀለማት በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት እንዲደምቅ ማድረጋቸውም አንዱ ማሳያ ነው።
ይህን መሰል የኩራትና የክብር መገለጫ ያላት ሀገር፤ በሌላ ገጽታዋ በጥቁር ቀለም የተከተበ ታሪክም አላት- ስሟን ከረሃብና ከድህነት ጋር ደጋግሞ የሚያስነሳ አሳፋሪ ጠባሳ። ዛሬ ግን የሀገሪቱ መንግሥትና መላው ህዝብ ይህን ጠባሳ በመፋቅ ታሪክን ለመለወጥ በጋራ እየሰሩ ነው።
የሀገራችን ህዝቦች ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ረሃብና ጦርነት ሲነሱ የኢትዮጵያን ስም አብሮ መነሳቱ ማብቃት አለበት ብለው ከቆረጡ 26 ዓመታት ሊሆናቸው ነው። ለዚህ ሁሉ አስከፊ ሁኔታ የዳረገን ዋነኛ ጠላታችን ማነው? ብለው ጠይቀው ትክክለኛውን ምላሽም አግኝተዋል። ጎረቤቶቻቸውን፣ በተለይም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ ለማድረግ በእኩልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ፖሊሲን ቀርፀውም እየተንቀሳቀሱ ነው።
‘ድህነትን እንዴት እናስወግዳለን?’ ብለው መክረው መፍትሔ ካበጁም ቆይተዋል። በሁሉም መስክ ፈጣን ልማትን ሊያመጡላቸው የሚችሉ አቅጣጫዎችን የሚከተል ብቸኛ አማራጫቸውን ገቢራዊ ከማድረግ ባሻገር፤ በትግበራ ሂደቱም ላይ የጋራ መግባባትን ፈጥረዋል። ዕድገትን እያስመዘገቡ ካሉ የዓለማችን ሀገራትና ህዝቦች በጥቁር ቀለም የተጻፈውን መጥፎ ታሪካቸውን በጥረታቸውና በስኬታቸው እንደሚቀይሩ ርግጠኞች የሆኑበትን ምዕራፍ በር እያንኳኩ ነው።
የሀገሪቱ የለውጥና የዕድገት ግስጋሴ ዘላቂና ፈጣን እንዲሆንም የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለሁለት ጊዜ ነድፈዋል። አንደኛውን የልማት ትልም በአጥጋቢ ሁኔታ አገባደዋል። ወደ ሁለተኛው የዕድገት ዕቅድ ከተሸጋገሩም ዓመት ከመንፈቅን ተሻግረዋል። በተለይም እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር የዕድገት ውጥኖችን ማሳካት የሚችሉት ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም እንደሆነ በማመን ዓባይ ወንዝን ለልማታቸው አጭተውታል።
በዚህ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገራችንን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት የሟማላት አቅም ያለው ነው። ይህም ጥረት የዚህ ወንዝ ትሩፋት ተቋዳሽ የሆኑና የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑም የሀገሪቱንና የህዝቦቿን ከሌሎች ጋር ተባብሮ የማደግ ፍላጎትን በግልጽ አሳይቷል። በሌላ በኩልም ‘ዋነኛውና ብቸኛው ጠላቴ ድህነት ብቻ ነው’ ብሎ ለተነሳና ከድህነት ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ለገጠመ ህዝብ ቁርጠኝነቱና ተነሳሽነቱ ምን ያህል የጠነከረ ለመሆኑም ማሳያ ይመስለኛል።
በተለይም የተፋሰሱን ሀገራት በማይጎዳ መንገድ ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት የማልማትና የመጠቀም መብትን በሚያረጋግጥ ሁኔታ ሥራው መጀመሩ መላው የሀገሪቱን ህዝቦች በጋራ መነሳታቸውን የሚያረጋግጥ ብሩህ ተስፋን ሆኗል። መላው የሀገራችን ህዝች በዚህ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኙትና የራሳቸውን አሻራ የሚያሳርፉበት ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመሩ ስድስት ዓመት ሊሆን በጣት ብቻ የሚቆጠሩ ቀናት ይቀሩታል።
የግድቡ ስድስተኛ ዓመት ሲከበር “ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የሀገራችን ህብረ ዜማ! የህዳሴያችን ማማ!” በሚል መሪ ቃል ይዘከራል—በመጪው ሚያዚያ 23 ቀን 2009 ዓ.ም። ይህ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ሃብት የሆነው ግድብ፤ የሀገራችን ዜጎች ላለፉት ስድስት ዓመታት በህብረ ዜማቸው ያለፉባቸውን የመተባበርና የመደጋገፍ መንገዶችን የሚያሳይ ነው። ህዝቦች ከተባበሩና ከተደጋገፉ የማይወጡት ዳገት፣ የማይወርዱት ቁልቁለትና የማያከናውኑት ልማታዊ ተግባር የሌለ መሆኑን ከታላቁ የህዳሴ ግድብ በላይ ማሳያ ሊኖር የሚችል አይመስለኝም።
የግድቡ ግንባታ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ አቅሙ እየጨመረና እየጎለበተ የሚሄድ ነው። በታለቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት “በእኛው አቅም ራሳችን እንገነባዋን” በሚል መንፈስ የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ መሰረት ተቀምጦለት፣ የሚያመነጨው አቅም 5250 ሜጋ ዋት መሆኑ ሲነገር፤ የሀገራችን ህዝቦች ከዳር እስከ ዳር ድረስ የተሰማቸውን ስሜትና ግድቡን በቁርጠኝነት ለመገንባት ያሳዩትን ተነሳሽነት የሚዘነጋው ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም። ህዝቡ በወቅቱ ከመንግስት ጎን በመቆም የተጠየቀውን ሁሉ ነገር ለመፈፀም ቃል ከመግባት ባሻገር፤ ግድቡ የሚገነባበት ጉባ ወረዳ ድረስ በመሄድ ግንባታውን ለ24 ሰዓት እያከናወኑ ያሉትን የልማት አርበኞች አበረታትቷል።
በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች የዕለት ጉርሱን ከመቀነስ ጀምሮ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ ከፍ ሲልም ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ፍፃሜ ያለውን የማያወላውል አቋም አረጋግጧል። ይህ አቋሙም ላለፉት ስድስት ዓመታት ያህል ላፍታም አልተቋረጠም። ግድቡን ለመገንባት በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ሁሉ የበኩላቸውን ዕገዛ እያደረጉ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
የዓባይ ወንዝን የተፈጥሮ ፍሰት እንዲቀየር ሲደረግ ይህ ህዝብ ሙሉ ድጋፉን ቦታው ድረስ በመገኘት ሰጥቷል። ማንኛውም ግድብ ሲገነባ ወደ ግድቡ የሚገባውን ውሃ የመስቀየስ ተግባር ስለሚከናወንና በግድብ ግንባታ ስራ ሂደት እንደ አንድ ወሳኝ ስራ የሚቆጠረውና የወንዙን ተፈጥሯዊ ፍሰት የማስቀየር ስራ መሆኑን በመገንዘብም፤ ለቅየሳውስራ ሙሉ ድጋፍ ሰጥቷል። ይህ ሁኔታም ህዝቡ ከግንባታው ጅማሮ በየመሃከሉ በሚደረጉ ማስተካከያዎች ህዝቡ ሁሌም ከፊት እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው።
ህዝቡ ምንግዜም ቢሆን ከግድቡ ባለመለየት ባደረገው ሁለንተናዊ ርብርብ፤ የግድቡ ሃይል የማመንጨት አቅም በሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ እመርታ ወደ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት ከፍ ብሏል። የሚመነጨው ሃይል ለምን ዓይነት ሀገራዊ ጠቀሜታ እንደሚውል ስለሚያውቅም የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ በማጠናከር ከግድቡ አካባቢ አልራቀም። በዚህ ወቅት የግድቡ ሃይል የማመንጨት አቅም በ750 ሜጋ ዋት ያህል ሲያድግና ስድስት ሺህ ሲደርስ በቅድሚያ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ህዝቡ ነው። ህዝቡ ግንባታውን በቅርበት በመከታተልና ከእርሱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ከጅምሩ በገባው ቃል መሰረት ተግባራዊ በማድረጉ ይህ ውጤት ሊገኝ ችሏል።
በቅርቡ ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የቦርድ አባል ዶክተር ደብረፅዩን ገብረሚካኤል ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት የግድቡ ሃይል የማመንጨት አቅም ስድስት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ማጋ ዋት መድረሱን ተናግረዋል። ይህም ግድቡ አሁን ባለበት ሁኔታ በህዝቦች ያላሰለሰ ጥረት በፊት ከነበረው ጋር የተከዜን ያህል ሃይል የማመንጨት አቅም መጎናፀፉን ያሳያል። የውጤቱ መገኘት ህዝቡ ለግድቡ በሚያደርገው ድጋፍ የሀገራችን ቴክኖሎጂ እያደገና እየጎለበተ እንዲሄድ አድርጎታል። ይህ በመሆኑም ግድቡ ከራሳችን አልፎ ለታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት በቂ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያገኙ የሚያደርግ ይሆናል።
የግድቡ ሃይል የማመንጨት አቅሙ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ግብፅን ጨምሮ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የሚሆኑት ሀገራችን በምትከተለው በዓባይ ወንዝ ዙሪያ የሚገኙ የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ እንዲጠቀሙ ካላት ፍትሐዊ እሳቤ በመነሳት ነው። ይህ እሳቤም ኢትየጵያና ህዝቦቿ የእነርሱ ተጠቃሚነት ከተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ስለሚገነዘቡ ነው። እናም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ግድቡ የማመንጨት አቅሙ በጨመረ ቁጥር ተጠቃሚዎቹ እነርሱ መሆናቸውን በመገንዘብ ከሀገራችንንና ከህዝቦቿ ጋር በቀናነት መንፈስ መተባበር አለባቸው።
በአጠቃላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስድስተኛ ዓመቱን ለማክበር ዋዜማ ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፤ ህዝቡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ያደረጋቸውን ተግባራት ፍሬ የሚያይበት ወቅት ነው። ህዝቡ በአዲሷ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ልማታዊ አሻራ ለማሳረፍ እየሰራ በመሆኑም፤ ነገም ግንባታው ተጠናቅቆ ለማየት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው። እናም ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥልበት ዕለት ይሆናል፤ ስድስተኛው ዓመት የግድቡ የተጀመረበት ዝክረ በዓል።