ሕገ-መንግሥቱ ለችግሮቻችን ሁሉ ምላሽ ሰጥቷል

በአንድ ወቅት የኃይማኖት አክራሪነት ስለሚያስከትለው ጥፋት በተመለከተ በአዲስ አበባ በተደረገ ውይይት ላይ  አንዲት የአዲስ አበባ ነዋሪ የተናገሩትን ንግግር ልጥቀስና ጽሁፌን ልጀምር። ነዋሪዋ ከደርግ ስርዓት በፊት በአገራችን የነበረውን የኃይማኖት ዕኩልነትና መቻቻል  በተመለከተ የገለጹት “በአጼዎቹ ስርዓት ለእኛ ለሙስሊሞች መቻል እንጂ መቻቻል የሚባል ነገር አልነበረም። ለእኛ ለሙስሊሞች እነዛ ስርዓቶች መልካም አልነበሩም። በኃይማኖታችን ሳቢያ ከፍተኛ መገለል ደርሶብናል።  ይሁንና በአሁኑ መንግስት ይህ ሁኔታ ተቀይሯል።  እውነት እንነጋገር ከተባለ በአሁኑ ሰዓት እንደኢትዮጵያ ያለ የኃይማኖት ነጻነት የተከበረባት አገር ያለ አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረው ነበር። ይህ አባባል ትልቅና እውነት ነው።

 

በአገራችን የመንግስትና የኃይማኖት  አሰራር በህገመንግስት ድንጋጌ የተለያዩባት  አገር ናት። ዛሬ በአገራችን ሁሉም ኃይማኖቶች እና የኃይማኖት ተከታዮች እኩል ናቸው። በህገመንግስታችን  የኃይማኖት ነጻነት መብት በመረጋገጡ  የትኛውም ኃይማኖት ተከታዮቹን  በነጻነት የማስተማር በሰላማዊ መንገድ  ተከታዮቹን  የማብዛት  በተመሳሳይ  ማንኛውም ግለሰብ የመረጠውን ኃይማኖት ሰላማዊ  በሆነ ሁኔታ በነጻነት የማራመድ መብት አለው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስትና ኃይማኖት በአሰራር ፍጹም የተለያዩ ናቸው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  ኃይማኖት የጥንት ነው፣ ይህ መጤ ነው፣ ይህ መጥፎ ነው፣ ይህ እንዲህ ነው፣ ያ እንዲህ ነው በማለት ከመንግስት የሚሰጠውም ድጋፍ ሆነ የሚከለከለው ነገር የለም። የኃይማኖት ነጻነት በተከበረበት አገር የሁሉም ኃይማኖቶች መብት  እኩል ይታያል እንጂ በተከታዮች  መብዛትና ማነስ  ላይ የተመሰረተ  የነጻነት ገደብ  የለም። አንዳንድ ኃይማኖቶች ጥቂት ተከታዮች ስላላቸው የሚያጡት መብት የለም እንዲሁም አንዳንዶቹ ደግሞ በርካታ ተከታዮች ስላሏቸው ከሌላው በተለየ መልኩ የሚያገኙት መብት አይኖርም። ሁሉም ኃይማኖቶች እኩል ናቸው።

 

ሁሉም ሃይማኖቶች ለተከታዮቻቸው ትክክለኛና የጽድቅ መንገዶች ናቸው። እኔ ኃይማኖቴ እንዲነካብኝ  እንደማልፈልገው ሁሉ ሌላውም ኃይማኖቱ እንዲነካበት እንደማይፈልግ ማወቅ ይኖርብናል። አንድ አባባል ከመጸኃፍ ቅዱስ ልጥቀስ “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና (ማቴ. 7፡12)። ይህችን አባባል ልውሰዳት እንጂ በተለያየ አገላለጽ በሁሉም ኃይማኖቶች እንዳለች ለማረጋገጥ ችያለሁ።   በአንተ ላይ እንዲደረግብህ የማትፈልገውን መጥፎ ነገሮች ሁሉ በሌሎች ላይ አታድርግ፤ በተመሳሳይ ለአንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን መልካም ነገሮች ሁሉ ለሌሎችም አድርግ። ይህ ድንቅ ጥቅስ  ነው። ይህ ጥቅስ የአብሮነትንና የመቻቻል መርህን ያጎለብታል።

 

የኢፌዴሪ ህገመንግስት በአገራችን ተዛንፈው የነበሩ  የጭቆና መድረኩች በሙሉ ቀርፏል። መንግስት “ሲኪዩላር” እንዲሆን ህገመንግስቱ ያስገድደዋል። በኢዲሲቷ ኢትዮጵያ ማንም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሃይማኖቱን የማራመድ መብት ተጎናጽፋል። ሕገ-መንግሥቱ ለኃይማኖቶች እኩልነት ጽኑ መሠረት በመፍጠር የመንግስት አሰራርንና የኃይማኖት ጉዳይን  በየፈርጁ እንዲታዩ አድርጓል። ሁሉም ኃይማኖቶች በሕግ ፊት ያላቸውን እኩልነት ያረጋገጠ እንዲሁም መንግሥታዊ የኃይማኖት ወይም ኃይማኖታዊ መንግስት እንዳይኖር አድርጎ መሰረት አስይዟል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በኃይማኖት ነጻነት መጓደል ሳቢያ ለሚነሱ ችግሮች ህገመንግስቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት  ሰጥቶታል። 

 

የኃይማኖቶች ነጻነት በህገ-መንግሥቱ መረጋገጥ መቻሉ ለአገራችን  ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ አንዱ ዋስትና ሆኗል። ዛሬ የግል ፍላጎትን ኃይማኖት ሽፋን  ለማራመድ  የሚደረግ  መሯሯጥ ካልሆነ  በአገራችን  የኃይማኖት  ነጻነት ሙሉ ለሙሉ ተጋግጧል።  በኃይማኖት ነጻነት መጓደል ሳቢያ ሊነሳ የሚችል ምንም ቀዳዳ የለም። በህገመንግስቱ  ማንም የመረጠውን ኃይማኖት የመከተል መብት እንደተጎናጸፈ ሁሉ ኃይማኖት የለሽም የመሆን መብት ህገመንግስታዊ ዋስትና አለው። የእኔ  የኃይማኖት ነጻነት መብት የሚረጋገጠው የሌሎችን የኃይማኖት ነጻነት  መብት ማክበር እስከቻልኩ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው። ይህ የሚያሳየው የኃይማኖት ነጻነት መብት የሚረጋገጠው የሌላውን  ማክበር እስከተቻለ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው።   የአንዱ ወገን መብት የሚከበረው የሌላውን  መብት  ማክበር ሲችል መሆኑን  መገንዘብ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያችን የጋራችን ነች። ሃይማኖታችን ግን የግላችን ነው።  አክራሪነት በዓለም ላይ ያመጣውን ጣጣ ተመልክተናል።

 

ባለፉት ዓመታት በአገራችን አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በጋራ ወይም በተናጥል በኃይማኖት ነጻነት ስም ድብቅ አጀንዳቸውን ለማራመድ ሲነቀሳቀሱ ታይተዋል። አክራሪነት  ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታም ይሁን ለልማታችን የሚበጅ አይደለም። ምክንያቱም  አክራሪነት የመቻቻል  ጥንጣን፤ የአብሮነት ጠንቅ ነው፤ እንዲህ ያለ እኩይ ተግባርን በእንጭጩ ማስቀረት ካልተቻለ አሸባሪነትን ያስከትላል። አክራሪነት በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ ያስከተለውን ጥፋት መመልከቱ የሚከብድ ጉዳይ አይደለም። በእኛም ንጹሃን ዜጎች ላይ በሊቢያ የፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያ የሚረሳ አይደለም። 

 

የእምነት ጉዳይ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው  መሆኑን አክራሪዎች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ለግል ፍላጎታቸው ማሳኪያ ኃይማኖትን እንደሽፋን መጠቀምን ይመርጣሉ።   አክራሪዎች ኃይማኖተኞች አይደሉም። ለኃይማኖትም ቍብ የላቸውም። ለሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አይገዳቸውም። ይልቁንም  በየትኛውም መንገድ ይሁን በማንኛውም ሁኔታ  ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት  ወደ ኋላ አይሉም። አክራሪዎች በንጹሃን ደም ተረማምደው ወደ ስልጣን ኮርቻ መሰቀል እንጂ ለአገርና ለህዝብ አይጨነቁም።    

 

አክራሪዎች የኃይማኖት አብሮነት፣ የኃይማኖት መቻቻል የሚባል ነገር እንዲኖር አይፈልጉም። እነዚህ ነገሮች የሚዳብሩ ከሆነ አክራሪዎች ህልማቸው ሊሳካ እንደማይችል ያውቁታል። በመሆኑም አክራሪዎች የኃይማኖት አብሮነትንና መቻቻልን የሚሸረሽሩ፣ በአንድ ኃይማኖት ውስጥ ሳይቀር  ተከታዮችን እርስ በርስ በመከፋፈልና እንዳይተማመኑ በማድረግ፤   የኃይማኖት መሪዎችን  ስም በማጥፋት  ከተከታዮቻቸው ጋር እንዳይስማሙና እንዳይተማመኑ የማድረግ  የተለያዩ  የፈጠራ ውንጀላዎችን  ያናፍሳሉ።

 

የኃይማኖት አብሮነት ማለት የሌላውን ኃይማኖት ልዩነት መቀበል ወይም  ሰዎች የመረጡትን ኃይማኖት እንዲከተሉ መፍቀድ ማለት ነው። የኃይማኖት አብሮነት እና መቻቻል ከግለሰብና ከቤተሰብ የሚጀምር ጉዳይ ሲሆን ማንም  የራሱን እምነት መምረጥ እንደቻለ ሁሉ የሌላውንም የመምረጥ መብት የሚያከብርበት፣ የራሱን እምነት በፍቅርና በሰላም  ለሌላው የሚያካፍልበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ቤተሰቦች የተለያየ እምነት እየተከተሉ በአንድ ቤት የሚኖሩበት፣ የሚበሉበትና የሚጠጡበት   አገር ናት።

 

እነዚህንና ሌሎችንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ለተመለከተው፣ በህብረተሰቡ መካከል ያለው የኃይማኖት አብሮነት እና ትብብር በአገራችን ምን ያህል ስር የሰደደ  እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ አገራችን የያዘችው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና  የልማት ስራዎች  ቀጣይነት ለማረጋገጥ  ሰላማችንን ሊያውኩ የሚችሉ ቀዳዳዎችን መድፈን  የሁላችንም ስራ መሆን ይኖርበታል።  ከእነዚህ ነገሮች መካከል  አንዱ  ደግሞ  በየቤተእምነቱ  ያሉ አክራሪዎችን  ማጋለጥና ማውገዝ የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ መሆን መቻል አለበት።

 

እያንዳንዳችን ለኃይማኖት አብሮነት እና ትብብር ዘብ መቆም ይኖርብናል፡፡ የኃይማኖት አብሮነት እና ትብብር ካለ ዘላቂ  ሰላም ይኖራል፡፡ ዘላቂ ሰላም  ለልማታችን ቁልፍ ሚና አለው፤ ባለፉት 14  ዓመታት አገራችን ባለሁለት አኃዝ ዕድገት  ማስመዝገብ የቻለችው ሰላም በማግኘታችን  ብቻ ነው። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ሰላምን ማስፈን ትልቅ ስራ፣ የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል። ይሁንና ሰላምን ማወክ አንድ አካል ብቻውን ይፈጽመዋል። በመሆኑም ይህን ተግባር የሚፈጥሙ አካላትን ህዝብና መንግስት በጥብቅ መካታተል ይኖርባቸዋል።   

 

ሁላችንም በየቤተዕምነታችን የሚታዩ  አክራሪነትንና ጽንፈኝነት መገለጫ የሆኑ ድርጊቶችን መዋጋት ይኖርብናል።  ከዚህ  ባሻገር የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ የሆነውን  ድህነትን መዋጋት የሁላችንም ቀዳሚው ስራችን መሆን ይኖርበታል።  ልማትን አጠናክሮ መቀጠል፣ ሕገ-መንግሥታዊና በሰላም አብሮ ተቻችሎ የመኖር ባህላችንን ማጎልበት፣ የኃይማኖት ተቋማት ሚዛናዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት ተከታዮቻቸውን ማስተማር ይኖርባቸዋል።  አክራሪው ኃይል ኃይማኖታዊ ይሁንታን እንዳያገኝ የሃይማኖት መሪዎች  በተከታዮች ላይ የጠራ አመለካከት ለማስያዝ መንቀሳቀስ፣ የኃይማኖት ተቋማት መቻቻልንና አብሮነትን መስበክ፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንዲሁም መንግስትም  የተጣለበትን የህግ ማስከበር ስራ  አጠናክሮ በመስራት አክራሪነትንና ጽንፈኝነት ቦታ እንዳይኖራቸው ማድረግ ይኖርበታል።

 

አክራሪዎች የረጅም ጊዜ  እቅድ አዘጋጅተው ራሳቸውን  የኃይማኖት ተቆርቋሪ የኃይማኖት ደቀመዝሙር አድርገው  በማቅረብ የግል ፍላጎታቸውን ለማሳከት  ኃይማኖትን እንደሽፋን ይጠቀማሉ። አክራሪነት  በኃይማኖት ሽፋን የሚፈፀም ፖለቲካዊ ቁማር ነው። የመንግስት አሰራርና ኃይማኖት ለየቅል ይሁኑ እንጂ አይነኬ አይደሉም። መንግስት የህግ የበላይነት የማስከበር ህገመንግስታዊ ግዴታ አለበት። የህግ የበላይነት ማስከበር የማይችል መንግስት፣  መንግስት ሊሆን አይችልም። አገርም እንደአገር ልትቀጥል አትችልም። መንግስት የህግ የበላይነት የማስከበር ሂደቱ ከጣልቃ ገብነት ሊወሰድ አይገባም።  ሁሉም ዜጋ  የህግ የበላይነት እንዲከበር የበኩሉን  አስተዋጽዖ ማድረግ ይኖርበታል።   ይህን  የአክራሪዎች  መሰሪ  አካሄድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊያውቀውና ሊያወግዘው ይገባል።  

 

በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት በመንግሥት እና በኃይማኖቶች እንዲሁም በተለያዩ ኃይማኖቶች መካከልም ትክክለኛ ግንኙነት  እንዲጠናከር እንዲሁም መተማመን  እንዲጎለብት ያደረገ ሰነድ ነው። እንደኢትዮጵያ የኃይማኖት አብሮነትና የኃይማኖት መቻቻል ያለባት አገር ያለ አይመስለኝም።  ይህ ታላቅ ኩራት ነው። ይሁንና አክራሪዎች ይህን ድንቅ ባህላችንን ለመሸርሸር  ሲሯሯጡ ቆይተዋል። ይሁንና እስካሁን አልተሳካላቸውም። ነገም ይህን እኩይ ተግባራቸውን ሊቀጥሉበት ይችላሉ። በመሆኑም  እንዲህ ያሉ ተግባራትን ሁላችንም ልንታገሳቸው አይገባም።