∙∙∙ የጋራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንጂ ትምክህትና ጥበት እንዲፈነጩበት አይደለም

በአገራችን ዴሞክራሲ በትግል እውን ከሆነ በኋላ የዜጎችና የማህበረሰቦች መብቶች ሳይነጣጠሉ ተከብረዋል፡፡ ከግለሰብ እስከ ቡድን መብት ድረስ ያሉ መብቶች እውቅና ተሰጥቷቸው የህግ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በህገ መንግስታችን ሃሳብን የመግለፅ፣ የመቃወምም ሆነ የመደገፍ፣ የመደራጀት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ በህይወት የመኖር፣ ከአካላዊ ጉዳት የመጠበቅ ወዘተ… ግለሰባዊ መብቶች ተከብረዋል፡፡ 

“የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በተራዘመ ትግል ዕውን ባደረጉት ዴሞክራሲያዊ መድረክ እየተረቀቀ ያለውን ሕገ-መንግስት የመተርጎም ስልጣን የራሳቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እንጂ ለማንም የሚተውት ጉዳይ አይደለም” የሚለው አስተሳሰብ የበላይነትን መያዙም በግዴታ ተጭኖ የነበረው አንድነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገርሰሱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ “ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ለዳኞች መተው አለበት” ብለው ቢሞግቱም ጥያቄው የሕግ ጉዳይ ሳይሆን የአትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አብረው ለመኖር የገቡት ቃል ኪዳን፣ እምነትና ፖለቲካዊ ጉዳይ በመሆኑ ይህ አቋም አሸናፊ ሆኖ መውጣት ችሏል፡፡

በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ ሆኖ ፀድቋል። 

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሀገራቸው ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውና እኩልነታቸው መረጋጡ በመላ ሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር ሰላምን ከማስፈኑም ባሻገር ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ግንባታ መሰረት ጥሏል፡፡ ከዚያ ባሻገር አልፎ አልፎ በአጎራባች ክልሎች መካከል ለሚነሱ ግጭቶች ምክንያቱ ጥበት ወይም ትምክህት አልያም ደግሞ ጥበትና ትምክህት በአንድ ላይ ሆነው በሚፈጥሩት ጸረ ዴሞክራሲያዊ አጀንዳ የሚፈጠር ነው።ፌደራላዊ ስርአቱ ዋነኛ የሆነውን የመልማትና የመጠቀም በጥቅሉ የጋራ ኢኮኖሚ የመገንባት ጥያቄን ከላይ በተመለከተው መልኩ እየመለሰ ነውና።

በቡድን መልክ የሚገለፁ ማህበረሰቦችም የተሟላ እኩልነት ተጎናፅፈዋል፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ሴቶች፣ ሠራተኞች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና የመሳሰሉ ማህበረሰቦች  የቡድን መብቶቻቸውን የተጎናጸፉ መሆኑም እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣይነት ህልውናዋ ተረጋግጦ ልትቀጥል የምትችለው ዜጎቿንና ህዝቦቿን አክብራ ስትይዝ ብቻ እንደሆነ በማመን ተግባራዊ የተደረገው ዴሞክራሲ አገሪቱን ለፅኑ ህዝባዊ አንድነት አብቅቷታል፡፡ስለሆነም በሃይማኖትም ሆነ በብሔር፣ በፆታም ሆነ በሌላ መልክ የሚካሄዱ  ግጭቶች መነሻቸው ትምክህትና ጥበት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ብዙኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዳደር መቻሏ፤ ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ የፈጠረውን የእርስ በርስ መተማመን ለመናድ የሚደረግ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴ ምንጩ ትምክህት ወይም ጥበት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊወስዱ እንደማይችሉ በተግባር በታየበት አግባብ የድንበር ጉዳይን የግጭት ምክንያት ነው ማለት ውሃ አያነሳም። በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ መንገድ ከፍቷል። መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን ደግሞ በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ በማሰብ የሚሰጣቸው እገዛዎች፣ በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ አዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓቸዋል፡፡

በአገራችን እየተገነባ ያለው የፌዴራል ስርአት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት እንጂ ድንበር ለይቶ የሚያጋጭ አይደለም። በአገራችን እየተገነባ ባለው የፌዴራል ስርአት በክልሎች መካከል መነጣጠልና መለያየት ሳይሆን ጠንካራ ትብብርና መደጋገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጎለበተ መጥቷል። ከዚያ ባሻገር አልፎ አልፎ የምንሰማቸው የግጭት ምክንያቶች የሚሆኑት ትምክህትና ጥበት ናቸው።  

የድንበር ጉዳይን ከፊት አስቀድመው ለሚነሱ ግጭቶች አንዳንዶች ምክንያቱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ በራሱ የግጭት መንስዔ ስለሆነ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። ያም ሆኖ ግን ፌዴራላዊ ስርአቱ በመሰረታዊ ባህሪው የማህበረሰቦችን ማንነት ማክበር በመሆኑ ችግር ፈች እንጅ ችግር ፈጣሪ ወይም አባባሽ ሊሆን አይችልም። አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሃገራችን በዘመናዊ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ምዕተ ዓመት የሞላው ረዥም የሰላም ዘመን እንድትኖር፣  ህዝቦቿ ለሃያ አምስት ዓመታት በሰላም፣ በፍቅርና በመካባበር እንዲኖሩ ያስቻለ ነው።

አገራችን ባፀደቀችውና በምትመራበት ህገ-መንግስት ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓትን የመረጠች መሆኑ እሙን ነው፡፡ የመረጥነው ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት ለአንዴና ለሁልጊዜ ረግቶ የሚቀመጥ ሳይሆን ከአገሪቱ የእድገት ደረጃ ጋር ተገናዝቦ ሁሌም ቢሆን በታዳጊነት መገንባትና እየዳበረ መጓዝ ያለበት መሆኑም በተመሳሳይ። ከዚህ በመነሳት በአገራችን  ብዝሃነት ያሉዋቸው ማህበረሰቦች እንደሚገኙና እነዚህም የየራሳቸው ልዩ ልዩ ፍላጐቶች ያሏቸው መሆኑን በመገንዘብ የተለያዩ ጥቅሞችን በማቻቻልና በማጣጣም ልትመራ የሚገባት እንደሆነ ታምኖበት በዚሁ ቅኝት እየተራመደች እንጂ ለግጭት ከሚጋብዝ ቅኝት ከተገላገለች ቆይታለች።   

በእርግጥ በጥቅሞች መካከል የሚከሰቱ ልዩነቶች ሁሉ በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲገለፁ ማድረግ፣ አገራችን በተረጋጋ መንገድ ለመቀጠል እንድትችል የሚያደርጋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ  ታምኖበት ፍላጐቶች በነፃነት እየተገለጹ ባለበት ሁኔታ የሚመጡ ግጭቶች መነሻቸው ትምክህትና ጥበት ከመሆበን አያልፍም፡፡

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሀገራቸው ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውና እኩልነታቸው መረጋጡ በመላ ሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር ሰላምን ከማስፈኑም ባሻገር ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ግንባታ መሰረት የመጣሉን እውነታ የሚቀበል ህብረተሰብ ቀድሞ ነገር ድንበርን የግጭቱ ምክንያት አያደርግም፡፡ በየክልሎቹ የሚከናወነው የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ፈጣንና በየደረጃው ያለውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንጂ ለግጭት አይደለም። በህዝቡ ፍላጎት ልክ ባይሆንም በገጠር ሁሉን አቀፍ የመንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም /URRAP/ መሰረት ወረዳን ከወረዳ፣ ቀበሌን ከወረዳና፣ ወረዳን ከዞን ማእከላት የሚያስተሳስሩ የገጠር መንገዶች ግንበታ የተከናውነው የጋራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንጂ ትምክህትና ጥበት እንዲፈነጩበት አይደለም።

መንግስት ለመሰረተ ልማት ግንባታና መስፋፋት በሰጠው ትኩረት በየክልሎች በሚገኙ  የከተማና የገጠር አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የኤለክተሪክ፣ የቴሌኮም፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በስፋት በመዘርጋት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ተመጣጣኝና ተቀራራቢ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ያስቻለው ይኸው የፌደራላዊ ስርአት እንጂ ሌላ አይደለም።