የሰላም እጦት የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ከኢራቅ፣ ከሊቢያ፣ ከሶሪያ፣ እንዲሁም ከጎረቤቶቻችን ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ተሞክሮ መገንዘብ ይቻላል። በየሀገራቱ በተፈጠሩ ትርምሶችና ሁከቶች ዜጎች ለዘመናት የለፉበትና የደከሙበትን ሃብትና ንብረት እንዲያጡ፣ ለዓይን ይስቡ የነበሩ ውብና ማራኪ ከተሞቻቸው በቀናት ውስጥ ወደፍርስራሽነት ሲለወጡ ለመመልከትና ውድ የሆነው የሰው ልጅ ህይወትም መና ሆኖ ሲቀር ለመመልከት ግድ ብሏቸዋል።
በየሃገራቱ በተከሰተው መቋጫ የለሽ ቀውስም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ለአስከፊ ረሃብና ስደት፣ ጉስቁልና፣ ለአካል ጉዳትና ሞት ከመዳረግ ባለፈ ሌላ ያስገኘላቸው አንዳች ፋይዳ እንደሌለም አይተናል። እነዚህ ሀገራት በቀላሉ ሊወጡ ከማይችሉበት ዕልቂት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው መንግስቶቻቸው ለተፈጠሩ ችግሮች ፈጥነው ዕልባት ባለመስጠታቸው መሆኑ ይነገራል።
በእኛም ሃገር ከላይ የተመለከቱት ሃገራትን አይነት እንድንሆን የተለያዩና የሰው ህይወትን ጨምሮ በቢሊዮን በሚገመት የንብረት ውድመቶች በሚገለጽ ደረጃዎች ሙከራ ተደርጓል። እነዚህ ሙከራዎች በዚህ ብቻ ሳያበቁ አንፃራዊ ለሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋትም ምክንያት ሆነዋል፡፡ የእኛውን ሃገር ለየት የሚያደርገው ደግሞ በአብዛኛው ሁከቶችና ግጭቶች ላይ ወጣቶች የተሳተፉበት መሆኑ ነው፡፡ በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያ በአሳዛኝ ደረጃ የወጣቶችና ሌሎች ዜጐች፣ እንዲሁም የፀጥታ አስከባሪ ሃይሎቻችን ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ቀላል የማይባል ንብረትም ወድሟል፡፡ በተጨማሪም የዜጐች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ደፋ ቀና ብለው ሰርተው ኑሮአቸውን ለማሸነፍ የሚንቀሳቀሱ ዜጐች ለፈተናዎች ተዳርገዋል፡፡ ይህን የመሰለው ችግር በየአካባቢው እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆኑ ወቅታዊ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ ከተከሰተበት ሁኔታና ከደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት በመነሳት ወጣቶቹ አካባቢ ያልተሰራ እና ይልቁንም ለምሬት ያበቋቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ያሏቸው መሆኑን ለመገመት አይከብድም። ያም ሆነ ይህ ውጫዊ ምክንያቶች ለጥፋት ተልእኮ መሳሪያ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉት በውስጥ ያሉ ችግሮች እስካልተፈቱ ድረስ ብቻ መሆኑ የማያከራክር እውነታ ነው። ከላይ በተመለከቱት ሃገራት የውጭ ሃይሎች እንዳሻቸው ገብተው ለመፈንጨት ያበቃቸው መንግስታቱ የህዝባቸውን የልብ ትርታ በቶሎ አዳምጠው መፍትሄ መስጠት አለመቻላቸው መሆኑ አያጠያይቅም። በእኛም ሃገር የሆነው ሙከራ በቅርጽ ይለያይ እንደሆነ እንጂ በይዘት ተመሳሳይ ነው። በሙከራው ሂደት ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት ጽንፈኞች እና የውጭ ቅጥረኞች ቢሆኑም የሃገሪቱን ህዝብ ከከፊል በላይ የሆነውን ወጣት ታሳቢ ያደረገ የትምህርት ስርአት ቢዘረጋም ተመጣጣኝ የሆነ የስራ እድል አለመመቻቸቱ እና ከተማረው ህዝብ ጋር የሚመጥን የአስተዳደር ስርአት አለመዘርጋት ዋነኛው ምክንያት ነው።
ስለሆነም ልክ ከላይ እንደተመለከቱት ሃገራት ነገሩ ስር ሰዶ ከሚያሳድደን አስቀድሞ ችግሩን በማጤን የልማታችንም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን ማጠንጠኛ ወጣቱ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴና ስርአት እየተዘረጋ መሆኑ ተገቢና እሰየው የሚያስብል ነው።
በያዝነው ዓመት መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ የሚቋቋም መሆኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል። ለፈንዱ ማቋቋሚያም 10 ቢሊዮን ብር መመደቡ በወቅቱ የተመለከተ ሲሆን ገንዘቡ በምን መልኩ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል መመሪያ ከመዘጋጀት ባለፈ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል አሁን ወደመሬት እየወረዱ ነው። ስለሆነም ይህ ፈንድ በራሱ የግጭት መነሻ ለሚሆነው የኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ተጋላጭ እንዳያደርገን ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ መፍጠር የሁሉም ሃላፊነት መሆኑ የማያከራክር እና የዚህ ተረክም መነሻ ምክንያት ነው።
ወደመሬት ወርዶ በወጣቶቻችን ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣና በሃገራችንም የልማት እና የሰላም ግንባታ ላይ ንቁ ተሳታፊ የሚሆን ወጣት ማፍራት ይቻለን ዘንድ ይህን ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ማስተዳደር እና መምራት ያስፈልጋል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንኑ አስር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲያስተዳድር ኃላፊነትን ወስዷል። ገንዘቡ ለክልሎች መሰራጨት የጀመረ ሲሆን ክልሎችም ይህ ተዘዋዋሪ ፈንድ ለወጣቶች በብድር መልኩ ሊቀርብ የሚችልበትን አሰራር በመቀየስ ላይ ናቸው። በፌደራል መንግስት በኩል በየክልሉ ለሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶች የተፈቀደውን ይሄንኑ ተዘዋዋሪ ፈንድ ድርሻ በምን መልኩ መከፋፈል እንዳለበት አሳታፊ የሆነ ውይይት የተደረገበት መሆኑንም የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በየክልሉ ያሉትን የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ለመለየት የምዝገባና የቆጠራ ስራ መካሄዱ ተመልክቷል። ገንዘቡ ለወጣቶች በምን መልኩ መለቀቅ አለበት? ተበዳሪዎችስ መበደር የሚችሉት ምን አይነት ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያሟሉ ነው? የብድሩ ልዩ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎችስ እነማን መሆን አለባቸው? ብድሩ ተዘዋዋሪ ፈንድ እንደመሆኑ መጠን ተመላሽ የሚሆነውስ በምን መልኩ ነው? የሚሉትና በርካታ ጉዳዮች በየክልሉ ውይይት ተደርጎባቸው ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል ስርአት ተዘርግቷል።
የዚህ ብድር ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ወጣት በየትኛው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው? የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ እድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ያሉ የህብረተስብ ክፍሎች ስለመሆናቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃዎች አረጋግጠዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ለብድሩ ብቁ የሚሆኑትም ከዚህ ቀደም በተለያየ የብድር አሰራርና ሂደት ውስጥ የተበላሸ የብድር ታሪክ የሌለባቸው እንደዚሁም ውዝፍ እዳ የሌለባቸው መሆን እንደሚገባቸውም ባለቤት ከሆነው ወጣት ጋር ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ተበዳሪዎች ብድሩን ለመውሰድ መደራጀት የግድ አስፈላጊ መሆኑም በመረጃዎቹ ተመልክቷል። ተበዳሪዎች በሚወስዱት ገንዘብ ላይ የ3 በመቶ ዓመታዊ ወለድ የሚታሰብ መሆኑን ከወዲሁ ተገንዝበው ሊገቡበት ይገባል፤ አንድ ተበዳሪ ጤናማ ባልሆነ ብድር ላይ የ1 ነጥብ 5 በመቶ ብድር ቅጣት እንዲከፍል የሚደረግ መሆኑንም በተመሳሳይ።
በተዘዋዋሪ የብድር ፈንዱ ተጠቃሚነት ዙሪያ ልዩ ተጠቃሚነትን በተመለከተ የሴቶችን እንደዚሁም አካል ጉዳተኞቸንም ጉዳይም በልዩ ሁኔታ ለመመልከት ታስቧል። ፈንዱ በትክክል ለታለመት አላማ እንዲውል በማድረጉ ረገድ በርካታ ባለድርሻ አካላት የድጋፍና የክትትል ስራዎችን የሚሰሩ መሆኑ ቢታወቅም፤ ከእነዚህ አካላት መካከል ከላይ ስለተመለከተው የፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ከክልል ቢሮዎች ጋር በመተባበር በስራ አጥ ወጣቶች ምልመላ፣ ስልጠና በመስጠትና የብድር አሰጣጡ ከጣራ በላይ እንዳይሆን ክትትል በማድረጉ ረገድ የራሱን ሚና መወጣት ይኖርበታል። ወጣቶችንም ሌሎች ባንኮችና አበዳሪ ተቋማት ብድር ከሚሰጡበት የወለድ ምጣኔ በታች ብድር እንዲያገኙ የሚደረግበት አሰራር የተዘረጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፈንዱን በአግባቡ በመጠቀሙ ረገድ ኪራይ ሰብሳቢነት እንደ አንድ ስጋት የሚታይ መሆኑን በመገንዘብ ይህን ችግር ባለድርሻ የሚሆኑ አካላትን ጨምሮ ወጣቶቹ እራሳቸው ከወዲሁ ሊከላከሉና ሊታገሉት ይገባል፡፡