የህግ የበላይነትን ማክበር ለአንድ ማህበረሰብ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ህግ ከሰዎች የበላይ ሆኖ ካልተከበበረ ሰብዓዊም ይሁን ዴሞክራሲያዊ መብቶች እውን ሊሆኑ አይችሉም። በዚያ ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ከልካይ እንዳሻቸው የሚንቀሳቀሱት ጉልበተኞች ይሆናሉ። እነዚህ ጉልበተኞችም ለፈለጉት መብት ይሰጣሉ፤ ደስ ላላቸው ደግሞ መብትን ይነፍጋሉ።
ሆኖም በህግ ካልተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ እንደሚሆንበት ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል።
ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው። ይህም የህገ መንግስቱን አንቀፅ (56) ተገልጿል። በዚህ አንቀፅ መሰረት በምክር ቤተ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅት የፌዴራሉን መንግስት የህግ አስፈፃሚ አካል እንደሚያደራጁና እንደሚመሩ ተገልጿል።
ይህም የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ህገ ወጥ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ከህገ መንግስቱ አኳያ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉ ማናቸውም የፖለቲካ አሊያም የሽብር ድርጅቶች ህገ ወጥ ናቸው።
ከእነርሱም ጋር የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት ወይም የእነርሱን አጀንዳ በማራመድ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች የህግ የበላይነትን መፃረር እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህ ሃይሎች ከህግ የበላይነት ጋር ሆድና ጀርባ በመሆናቸው ነው።
ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ውስጥ በአሸባሪነት የተሰየሙትን ኦነግንና ግንቦት ሰባት የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን ከደገፈ ወይም የእነርሱን ዓላማ ለማሳካት በተለያዩ መንገዶች ከተንቀሳቀሰ ከህግ የበላይነት ጋር እየተጋጨ መሆኑን ግንዛቤ ሊይዝ ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ የሽብር ቡድኖች ህገ መንግስቱን ተፃርረው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው ነው። እናም እነርሱን አለመደገፍ የህግ የበላይነትን ማክበር ሲሆን፣ የእነርሱን ህገ ወጥ ዓላማ በማናቸውም መንገድ መደገፍ ደግሞ የህግ የበላይነትን መፃረር መሆኑን መረዳት ይገባል።
የህግ የበላይነት ልዕልና ሊጠበቅ ይገባል። የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል።
ይህም ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። በመሆኑም ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር በሀግ አስፈፃሚው አካል በሚፈፀምበት ወቅት የተለየ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም።
ለዚህ ፅሑፍ አንባቢያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ከሰሞኑ ክስተት አንድ ዕውነታን ላንሳ። ይኸውም በህገ መንግስቱ መሰረት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው። እንደሚታወቀው አዋጁ ተፈፃሚ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ክልከላዎቹን ጥሰው በሚገኙ ሰዎችና ድርጅቶች ላይ ተገቢውን የአስቸኳይ ጊዜ ርምጃ መውሰድ ተገቢ መሆኑ ተገልጿል።
ይህም የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ በማሰብ የተደረገ ነው። ይሁንና አዋጁ ለሁሉም የሚሰራ መሆኑ ተዘንግቶ አንዳንድ ወገኖች አዋጁን የተላለፉ እንደ ዶክተር መረራ ጉዲና ዓይነት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሆን ተብሎ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት የተደረገ ሲያስመስሉ ይስተዋላሉ።
ነገር ግን ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በአንድ ሀገር ውስጥ የሚወጣ ማንኛውም አዋጅ ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት መሆኑ ነው። ለነገሩ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ አዋጁን በመተላለፍ ዶክተር መራራ ጉዲና በህግ ጥላ ስር ዋሉ እንጂ፤ ሌላ ሰው ቢታሰር ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ ነገር አይነሳም ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን አዋጁ ለሁሉም የወጣ ከመሆኑም በላይ የህግ የበላይነትን ልዕልናን ለማስከበር ሲባል አዋጁን የተላለፉ ግለሰቦችን በህግ አግባብ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢና ትክክል ይመስለኛል።
በእኔ እምነት የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር ነው። ምክንያቱም ህገ መንግሰቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ አስፈፃሚውም አካል ሆነ ማንኛውም ዜጋ መፍቀድ ያለበት አይመስለኝም።
የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ ነውና። የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። እናም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ገቢራዊ ለማድረግ የህግ የበላይነት በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል።
የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።
እርግጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው። ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚኖርባት ይመስለኛል።
የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሰላምን እንጎናፀፋለን። ሰላምን ስንጎናፀፍ ደግሞ የምናውዳቸውን የልማትና የዴሞፐክራሲ ስራዎችን ዕውን እናደርጋለን። ህጎች ለአንዱ የሚሰሩ ለሌላው ደግሞ የማይሰሩ ለሆኑ አይችሉም። ሁላችንም በህግ ፊት እኩል እንስተናገዳለን። የህግ የበላይነት ሲኖር ሁላችንም ከሚገኘው ሀገራዊ ጥቅም ተካፋዩች እንሆናለን። የህግ የበላይነት በህገ መንግስቱ ላይ የተረጋገጠ ብቻ ሳይሆን፤ ለአገራችን ጠቃሚነቱ ታምኖበት እንዲተገበር ምክንያት የሚሆን ይመስለኛል።
የህግ የበላይነትን ማክበር ህገ መንግስቱን ማክበር ነው። ህገ መንግስቱ ማክበር ደግሞ አገራችን ለተለመችው ዕድገት ተገቢውን መደላድል ፈጥሮ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ነው። ስለሆነም ህግና ስርዓትን የበላይ አድርጎ መመልከት ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የሚያፀና ነው። ይህም ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ስለሆነ እርሱን አክብሮ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው።