ሀገራችን ከድህነትና ከኋላቀርነት ታሪኳ ለመውጣት በሚያስችል ዘላቂ የልማት አቅጣጫ ላይ መሆኗን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጭምር የተስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በጎ ገፅታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተለይም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በስር ነቀል በሆነ የስርዓት ለውጥ ላይ ያላቸው አቋም ጤናማነት የጎደለውና አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ ምንም ዓይነት የሚበጅ ጎን እንደሌለው አድርገው እንደሚቆጥሩ ጎልቶ የሚንፀባረቅበት መሆኑ የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡
ሀገራችን ለምትመራበት ፌዴራላዊ ሕገ መንግስት ተገቢ ዕውቅና መስጠትን እንደውርደት ከመቁጠር የሚመነጭ የሚመስለውን ግትር አቋም በማራመድ በሚታወቁት የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካ ሃይሎች መካከል የሚስተዋለው ቅጥ ያጣ ፍጥጫ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፤ እኛ ኢትዮጵያ ህዝቦች ጎራ ለይተን እርስ በእርሳችን የጎሪጥ ወደምንተያይበት አደገኛ አዝማሚያ እንድናመራ የሚያደርግ አሉታዊ ስሜት እየተፈጠረ የመጣበት እውነታ ስለመኖሩም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ስለሆነም፤ የዚችን ሀገር ስር ከሰደደው ድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በሚያስችላት የእድገት ጎዳና ላይ ናት ተብሎ እንዲታመን ያደረጉትን በጎ ገፅታዎች ሁሉ ከማጎልበት ይልቅ፤ መክነው እንዲቀሩ ለማድረግ ያለመ እኩይ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች፤ ምናልባትም አዲሱን ታሪክ ምዕራፍ የሚቀለብስ አደጋ ያስከትሉብን ይሆናል የሚል ስጋት እንዲሰማን የሚያደርግ ተፅእኖ አሳድረውብናል፡፡
በዚህ መጣጥፍ ለመዳሰስ የምፈልገው ኢህአዴግና 21 በሕጋዊ መንገድ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጀመሩት ውይይት ሀገራችን የለውጥ ጉዞ ላልተጠበቀ የቅልበሳ አደጋ ተጋልጦ ዳግም ወደ ትናንቱ አብሮ የመውደቅ ታሪካችን እንመለስ ይሆን? የሚለውን የዜጎቻችን ስጋት አዘል ጥያቄ ሊመልስ የሚችል የጋራ መግባባትን መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው የፅሁፌ ትኩረት ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና 21 ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች፤ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ዘለቄታዊ ዕጣፈንታ ለመቃናት ሲሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብዬ የማስበውን መሰረታዊ ነጥብ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡
እንደኔ ፅኑ እምነት ከሆነ፤ የሀገራችን የፖለቲካ ሃይሎች እንቅስቃሴ የጋራ ቤታችን ናት የምንላትን ኢትዮጵያንና መላውን ህዝቦቿን ወደተሻለ የዕድገትና የብልፅግና አቅጣጫ የሚወስድ ቅኝት ይኖረው ዘንድ ግድ ነው፡፡ ስለሆነም፤ የአሁኑ የኢህአዴግና የተቀናቃኞቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት፤ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ጎልቶ ማንፀባረቅ የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነትን በጠየቀው የዘመናት ትግል የተቀዳጁትን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት እንደተራ ነገር ቆጥረው ለመገርሰስ ሲሞክሩ የሚስተዋሉ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኛ አስተሳሰብን የሚያቀነቅኑት ቡድኖችን አደብ የሚያስገዛ ሀገራዊ መግባባት ላይ የመድረስ ጉዳይ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ይህን ስል ተቃዋሚዎቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች ወክለው ከኢህአዴግ ጋር ለመወያየትና ለመደራደር የሚቀርቡ ወገኖች ለሀገራችን ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣፈንታ አይበጅም ብለው የሚያምኑበት የፌደራላዊ ስርዓቱ ደካማ ጎን ካለ መተቸት አይጠበቅባቸውም ለማለት አይደለም ፡፡ እኔ እንደዜግነቴ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሁለትዮሽ ውይይትና ድርድር መድረክ ላይ የሚሳተፉትን ወገኖች አደራ ለማለት የፈለግኩት ቁልፍ ጉዳይ ቢኖር፤ ያሻቸውን የመከራከሪያ ነጥብ የሚያነሱበት አግባብ በሕገ መንግስታዊ ማዕቀፍ ውስጥ የሚቀርብ መሆን አለበት፡፡ እንጂ ተደራዳሪዎቹ የየራሳቸውን አቋም በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳይኖራቸው ማለቴ አይደለም፡፡
ይህንን ያልኩበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ፤ በተለይም የለየለትን ትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ጽንፈኛ አመለካከት የሙጥኝ በማለት የሚታወቁ አንዳንድ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካ ሊቃን ብዙውን ጊዜ የሚያራምዱት አቋም፣ ለሕገመንግስታዊ ስርዓቱ ተገቢ ዕውቅና ከመንፈግ የሚጀምር በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም እንደኔ እንደኔ በአሁኑ የፓርቲዎች የውይይትና ድርድር መድረክ ላይ የየራሳቸውን ፓርቲ ወክለው የሚቀርቡት ወገኖች እስከዛሬ ድረስ ከምናውቀው ስርዓቱን አላስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ ከማቅረብ የተለመደ ግትርነት ይልቅ፤ ዘመኑ የሚጠይቀውን ስልጡን ፖለቲካዊ አቋም በሚያንፀባርቅ የሕግ የበላይነት ጥላ ስር የሚካሔድን ሰላማዊ ትግል ሊያሳዩን እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡
ከዚህ መሠረተ ሃሳብ አኳያ አንድ የቅርብ ጊዜ ክስተትን አብነት መጠቀስ እውዳለሁ፡፡ እንግዲያውስ በእኛ የዘመን ቆጠራ ቀመር፤ ባለፈው 2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የቱርኩን ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣሔር ኤርዶጋንን ከስልጣናቸው ለማስወገድ የሚፈልጉ ሃይሎች ያደረጉትን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ለመቃወም አደባባይ ከወጡት ብዙ ሺ ቱርካውያን መካከል አንዷ የነበረችው ለአልጄዚራው ዘጋቢ የሰጠችውን አስተያየት እንመልከት፡፡
ጋዜጠኛው “የፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ደጋፊ በመሆንሽ ነው አይደል አንቺ ድርጊቱን ለማውገዝ ሰልፍ የወጣሽው የኔ እመቤት?” ሲል ጠይቋት ቱርካዊቷ ወይዘሮ የሰጠችውን ምላሽ በተለይም እንደኛ አገር ላለው የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ትምህርት ሰጭ መልዕክት ያዘለ ሆኖ አግኝቸዋለሁና ነው፡፡ እንዴት? ለምትሉኝም ከብዙ በጥቂቱ እጠቅሳለሁ…
“ኧረ እኔ ፕሬዝዳንቱን በጣም የምጠላው ተቃዋሚ ነኝ” ስትል የመለሰችው ሴትዮዋ፤ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን ለማውገዝ ሰልፍ የወጣችበትን ምክንያት ስታስረዳም “ግን ደግሞ የምጠላውን ፕሬዝዳንት ከስልጣን እንዲወርድ አድርጌ በምትኩ የምወደውን ሌላ መሪ እንድመርጥ ዕድል የማገኘው የሀገሬ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ሲኖር ብቻ እንደሆነ ስለምገነዘብ የወታደሮቹን ድርጊት ለመቃወም ነው” ነበር ያለችው፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ገዢውን ፓርቲ የጎዱ እየመሰላቸው፤ መላ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነትን በጠየቀ የዘመናት ትግል የተቀዳጁትን ሕገ መንግስታዊ የቃል ኪዳን ሰነድ እንደተራ ነገር ሊቆጥሩት ሲቃጣቸው የሚስተዋሉበትን አግባብ አቁመው፤ ከየትኛውም ዓይነት የቅልበሳ አደጋ በመከላከል ረገድ የየራሳቸውን ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው የሚያጠያይቅ ጉዳይ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል ባይ ነኝ ፡፡ ኢህአዴግን ህዝባዊ ድጋፍ በማሳጣት እነርሱ በምርጫ አሸንፈው ሀገር ለመምራት የሚያስችላቸውን ፖለቲካዊ ስልጣን መያዝ ካለባቸውም፤ ገዢው ፓርቲ ሕገመንግስቱ ላይ የተደነገጉ የቡድንና እንዲሁም የግለሰብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን አክብሮ በማስከበር ረገድ የሚያሳየውን ድክመት እንደዋነኛ የትግል ሜዳ ተጠቅመው መሆን አለበት፡፡ እንጂ ስርዓቱን እንደስርዓት ለመናድ ያለመ ሴራ በመዶለት ላይ ከተጠመዱት የቀለም አብዮት ናፋቂ ቡድኖች ጋር በመሆን ለውጥ ለማምጣት መሞከር አደገኛ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡
ኢህአዴግ መንግስትም ሰላማዊ ትግል እናካሂዳለን በሚል ሽፋን ለነ ኦ.ነ.ግ እና ግንቦት ሰባት የሽብር ተግባር በጉዳይ አስፈፃሚነት እየሰሩ ያሉትን ቡድኖች በመለየት፤ በትክክለኛው ሕገ መንግስታዊ የሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አለበት፡፡ ከዚህም ሌላ የሀገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት አጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ የየራሳቸውን በጎ አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ከሚገኙት ሃይሎች በቅጡ ለይቶ ለህዝብ ግልጽ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ይህን ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ የሚሆነውም በሁለት መሰረታዊ ምክንቶች ነው፡፡
የመጀመሪያው ምክንያት፤ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን “በአንድ ወይም በሌላ መልኩ” በሀይል በመገርስስ ስልጣን የመጨበጥ ብርቱ ፍላጎት ያላቸው የቀለም አብዮት ናፋቂ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሪ ተዋንያኖች የትኞቹ ናቸው? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ፤ መላው ሰላም ወዳድ ህዝብ የማያሻማ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማድረግ ስለሚጠበቅብን እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል፡፡ እንዲሁም ሁለተኛው መሠረታዊ ነጥብ ደግሞ፤ በተለይም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተፈቃቅደው ተፈቃቅረውና እርስ በእርሳቸው ተከባብረው የሚኖሩበትን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ከመገንባት በስተቀር ሌላ ለኢትዮጵያውያን ዘለቄታዊ ዕጣ ፈንታ የሚበጅ የጋራ መፍትሔ ሊኖር እንደማይችል የሚያምኑትን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በፅንፈኖቹ ቡድኖች አሉታዊ ተጽዕኖ ሳቢያ እየደረሰባቸው ካለው ፈርጀ ብዙ ኪሳራ የሚታደግ ድጋፍ ለመስጠት እንዲያመችም ጭምር ነው፡፡ በዚህም ሆን ተብሎ በሚፈጠር ብዥታ ውስጥ ለማምታታት የሚሞከርበትን አዝማሚያ ማጥራት እጅጉን አንገብጋቢ ሀገራዊ አጀንዳ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚያስገድድ ተጨባጭ ችግር ተጋርጦበናል የሚል እምነት አለኝ ፡፡
ስለዚህም ኢህአዴግና በሰላማዊ ትግል አስፈላጊነት ከልባቸው የሚያምኑት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን በተጀመረው የውይይትና የድርድር መርሐ ግብር የተለየ የኃላፊነት ስሜትን በሚጠይቅ የሰከነ መንፈስ ተነጋግረውና ተደማምጠው የጋራ አቋም ሊይዙባቸው ይገባል ተብሎ የሚጠበቁ አንኳር አንኳር ነጥቦችን አንስቼ በመጠቆም ይኖርብኛል፡፡ በዚህ መሠረት ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን አጠቃላይ እውነታ ከጭፍን የጥላቻ ፖለቲካ በፀዳ ስሜት ለሚታዘብ ሰው ሁሉ፤ የሚገለፅለት ጥሬ ሀቅ ቢኖር፤ ፀንፈኛ አቋም የሚያራምዱት ተቃዋሚ ቡድኖች፤ በኢትዮጵያውያን ህዝቦች ዘመናትን ያስቆጠረ የጋራ ታሪክ እምብዛም ያልተለመደ አስነዋሪ ዘረኝነታቸውን በፈጠጠና ባገጠጠ መልኩ ያጧጧፉበት እጅግ በጣም አሳሳቢ ወቅት ላይ ስለመድረሳችን ነው፡፡
በተለይም ደግሞ ለራሳቸው በበለፀጉት የምዕራቡ ዓለም ሀገራት እየኖሩ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ህዝቦች በብሔርና በሃይማኖት ልዩነታችን ምክንያት አቃቅረው፣ የዚችን ሀገር የሩዋንዳ ዕጣ እንዲገጥማት ለማድረግ ያለመ የሚመስል እጅግ መርዘኛ ፕሮፖጋንዳቸውን በማዛመት እኩይ ተግባር ላይ መጠመድን እንደጠቃሚ ሙያ የቆጠሩት የጥፋት ቡድኖች፤ ምን እየደገሱልን እንደሆነ መላው ሰላም ወዳድ ህብረተሰብ የሚረዳበትን የተሻለ ግንዛቤ የመፍጠር ጉዳይ የጋራ ትኩረት እንደሚፈልግ የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡ ይህን ስልም ከሁሉም የውይይቱ መድረክ ተሳታፊ ፓርቲዎች በሚጠበቅ የመተማመን መንፈስ ሀገራዊ የደህንነት ስጋት ተደርጎ የሚወሰዱ የጋራ ፈተናዎቻችን ዙሪያ የመፍትሔ ሃሳብ ማስቀመጥ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ ይመስለኛል፡፡
አለበለዚያ ግን ጥረታችንን ሁሉ የእንቧይ ላይ ካብ ከመሆን ያለፈ ተጨባጭ ውጤት እንዳያመጣ ለማድረግ የሚሹት የጥፋት ኃይሎች የሚያሴሩት ሴራና የሚፈፅሙት ፈርጀ ብዙ ደባ በሚያስከትለው አደጋ ምክንያት የሚደርሰው ጉዳት ለኢህአዴግ አባላት ብቻ የሚተው ተደርጎ መወሰድ እንደማይችል ከወዲሁ ሊጤን ይገባል፡፡ ጉዳዩ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዘመናት ትግል የተቀዳጁትን ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞ የማስቀጠል ወይም አለማስቀጠል ጥያቄ እንጂ ለተወሰኑ ወገኖች ፍላጎት መሳካት ሲባል ብቻ የሚደረግ አይደለም የሚለው ነጥብ ላይ ልናሰምርበት ይገባል ማለቴ ነው፡፡