ዋስትና ላለው ሠላምና መረጋጋት ህዝቡ ዘብ ይቁም

ካለፈው ዓመት መግቢያ ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው ሁከት ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በተደጋጋሚ ሲነገር እንደቆየው፣ በመንግሥት አፈጻፀም በኩል የነበሩ ችግሮች ለሁከቱ መቀስቀስ አመቺ ሁኔታን ፈጥረዋል። የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የፍትህ መዛነፍ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛባት፣ በተለይም በከተሞች አካባቢ የሥራ አጥነት መስፋፋት በርካታ ወጣቶች በሥርዓቱ ላይ ቅሬታ እንዲያድርባቸው ማድረጉም ይታወቃል። ለሁከቱ መቀስቀስ አመቺ ሁኔታ የፈጠሩት እነዚህ ሁኔታዎች ነበሩ።

በመንግሥት የአፈጻፀም ችግር የተፈጠረው የህዝብ በተለይም የወጣቱ ማህበረሰብ የታመቀ ቅሬታ አመቺ አጋጣሚ ሲያገኝ በድንገት ወደ አደባባይ ተቃውሞነት ተዛመተ። የተከማቸው ቅሬታ በአደባባይ ተቃውሞነት መገለጹ ብዙም የሚያስገርም አይደለም። በተለይ ወጣቶች ገንፍለው አደባባይ መውጣታቸውን እንደ ትልቅ ጥፋት መቁጠር የአስፈፃሚውን ችግር መሸሸግ ስለሚመስለኝ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም። ምንም እንኳን ቅሬታዎች በሰላማዊ መንገድ ሊቀርቡ የሚችሉበት በህግ የተቀመጠ ስርዓት ቢኖርም፣ በየደረጃው ያሉ ለመልካም አስተዳዳር መጓደል ምክንያት የሆኑ አስፈጻሚዎች ወጣቶች ቅሬታቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚገልጹበት እድል ይሰጧቸው ነበር ብሎ ማሰብ ስህተትነቱ ያይላል። እናም ወጣቶች ገንፍለው ለተቃውሞ አደባባይ መወጣታቸውን እንደ ስህተት ከማሰብ ይልቅ፣ ለዚህ ያበቃቸውን ቅሬታ የፈጠረውን አስፈፃሚ መውቀስና ተጠያቂ ማድረግ የበልጥ ወደፊት ያራምዳል።

መንግስትም ይህን እውነታ ተቀብሏል። የሁከቱ መሰረታዊ ምክንያት በመንግስት አፈጻጸም ላይ የነበሩ ድክመቶች መሆናቸውን ተቀብሎ፤ እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ መጀመሩ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። በተለያዩ የኦሮሚያና የአማራ አካባቢዎች ገንፍሎ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጣው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ጋር በተያያዘ የነበረው ችግር፤ የወጣቶችን ቅሬታና ተገቢ ተቃውሞ፣ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት፣ መብትና ነጻነት ያላገናዘበ ቡድናዊ ዓላማ ባላቸው እና/ወይም የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪዎች ተጠልፎ ወደ አውዳሚ ሁከትነት የተለወጠ መሆኑ ነው። በየአካባቢው የነበረው የወጣቶች ተቃውሞ ተጠልፎ ወደ ሁከትነት ተለውጦ የህዝቡን ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን፣ የዜጎችንና የውጭ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንቶችን፣ መንግስታዊ ተቋማትን፣ ፍርደቤቶችን፣ . . .አወደመ። ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ በውጭ ሃገር የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በማህበራዊ ሚዲያ የሚያስተላልፉትን መልዕክት የሚቀበሉ ወጣቶች በሁከቱ የሚወድመውን የህዝብ ሃብት ለመከላከል የተሰማሩ የሰላም አስከባሪ ሃይል አባላት ላይ የሃይል እርምጃ ይወስዱ ነበር፤ በድንጋይ፣ አልፎ…አልፎም በጦር መሳሪያ። ወጣቶቹ ህይወታቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ከሰላም አሰከባሪ ሃይል አባላት ላይ የጦር መሳሪያ ለመንጠቅ ግብ ግብ የሚገጥሙበት ሁኔታ የተለመደ ነበር። መንገዶቸ ተዘገተው ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ተገትቶ ነበር። በተለይ ኑሯቸው በዕለት ስራ በሚያገኙት ገቢ ላይ የተመሰረተ ከተሜዎች የሚበሉትን ያጡበት ሁኔታ ነበር። ኑሯቸውን ለማሻሻል ከዕለት ገቢያቸው ላይ በእቁብ የቁጠባ ስርአት ገንዘብ የወሰዱ በጥቃቅን ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እዳቸውን መክፈል አቅቷቸው የተሳቀቁበት ሁኔታ ነበር።

በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች በብሔራዊ ማንነታቸው ተለይተው ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል፤ ንብረታቸው በእሳት ወድሟል። በኦሮሚያ ደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን አመያ አካባቢ የነበረውን ልብ ይሏል። የሃይማኖት ተቋማትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ተዘርፈዋል፤ በእሳት ወድመዋል። ሰዎች በአደባባይ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ሁነቶች ላይ መሳተፍ አስፈርቷቸው ነበር። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መላክ ፈርተው ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የግል ኮሌጆች ለማስተማር የተገደዱበት ሁኔታ ነበር።

ይህ አውዳሚ ሁከቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀለለ ከመምጣት ይልቅ መልኩን እየቀያየረ ማንኛውንም አመቺ አጋጣሚ በመጠቀም በየአካባቢው እየፈነዳና እየተቀጣጠለ ተዛመተ። በተለይ በቢሾፍቱ አርሰዲ ሃይቅ የኢሬቻ በአል አከባባር ስነስርአትን ለሁከት ለመጠቀም ከተደረገውና ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ከሆነው ሙከራ በኋላ ሁኔታዎች መልኩን ቀየረ። በተለያዩ የአሮሚያ አካባቢዎች የተደራጁና የታጠቁ ቡድኖች ለቁጥጥር አዳጋች በሆነ አኳኋን የህዝብና የመንግስትን ሃብት የማውደም መጠነ ሰፊ  እንቅስቃሴ አድርገዋል።

ይህን አውዳሚ ሁከት በተለመደው ህግ የማስከበር ስርአት መቆጣጠር የማይቻል ሆነ። በመሆኑም በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 93 መሰረት ለስድስት ወራት ስራ ላይ የሚውል የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ታወጀ። የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን አዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ አስጸደቀ። አዋጁ በህገመንግስቱ መሰረት የተወሰኑ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ገደቦች ስለሚጥል እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለሚያስፈጽመው ኮማንድ ፓስት አባላት የተለየ ስልጣን ስለሚሰጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጻጸሙን የሚከታተል መርማሪ ቦርድ ሰይሟል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በህገመንግስቱ መሰረት – በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለጽ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብአዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል፤ ማንኛውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢሰብአዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሃሳብ መስጠት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ አስተያየት የመሰጠት ሃላፊነቶች አሉት።

በዚህ መሰረት ለስድስት ወራት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ከመስከረም 28 ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመውና ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቶች የተጣሉበት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ሰሞኑን መጋቢት 19፣ 2009 ዓ/ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል። ቦርዱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፤ ከኦሮሚያ፣ ከአማራና ከደቡብ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 2ዐ ሺህ 659 ሰዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው እንዲለቀቁ መደረጋቸውን አስታውቋል። 457 ተጠርጣሪዎች በዕድሜና በጤና ምክንያት ምክር ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውን፣ 4 ሺህ 996 ተጠርጣሪዎች ደግሞ ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም ቦርዱ አሰታውቋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ስም ዝርዝር  እንዲታረሙ በተደረገበት ማዕከል ተለይቶ በክልል መስተዳድሮች አማካኝነት በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ እንዲታወቅ በመደረጉ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ቦታ እንዲያውቁ መደረጉንም አመልክቷል። በሁከትና ብጥብጥ የተሳተፉ ከ20 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን ከማሰር ይልቅ በተሃድሶ ስልጠና ታርመው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉ ለሰላምና መረጋጋቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ያስታወቀው ቦርዱ፣ በተሃድሶ ወደየመኖሪያ አካባቢያቸው የተመለሱት ታራሚዎች አይደገምም በሚል መፈክር ያወደሟቸውን ተቋማት መልሰው በመገንባት ላይ እንደሚገኙም አመልክቷል።

ቦርዱ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም በተመለከተ 174 አቤቱታዎችን መቀበሉን፣ ከእነዚህ መሃከል 54 የሚሆኑት ጥቆማዎች ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎባቸው አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት መተላለፋቸውን አስታውቋል። 12ዐ አቤቱታዎችና ጥቆማዎች ደግሞ ቦርዱ ለክትትልና ቁጥጥር ስራው  በግብአትነት እንደተጠቀመባቸው አመልክቷል።

ከአንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ “አባሎቻችን የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አባል በመሆናቸው ብቻ ተይዘው እንግልት ደርሶባቸዋል” የሚል አቤቱታ ቀርቦለት እንደነበረ ያመለከተው ቦርዱ፣ ይህን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ያቀረቡትን አቤቱታ በመያዝ እስረኞች በሚገኙበት ስፍራ ተገኝቶ የማጣራት ስራ ማከናወኑን አስታውቋል። በምርመራና ማጣራት ስራው በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል ተብለው ተጠርጥረው ከታሰሩ በስተቀር የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆናቸው የታሰሩ እንደሌሉ ማረጋገጡንም አስታውቋል። “በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል” በሚል ተጠርጥረው የታሰሩትም የደረሰባቸው ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እንደሌለ መረጋገጡን ገልጿል።

ከፖለቲካ ድርጅቶች ከቀረቡ አቤቱታዎች በተጨማሪ “ተጠርጣሪዎች አመቺ ባለሆኑ ጠባብ ክፍሎች ታጉረዋል፣ የመጠየቂያ ጊዜ አልተሰጠም፣ የእስረኞች ለፍርድ  ሳይቀርቡ ለወራት እንዲቆዩ ተደርጓል፣ በዋስትና የተለቀቁ ሰዎች መልሰው ታስረዋል” የሚሉ አቤቱታዎችና ጥያቄዎች ለኮማንድ ፖስቱ ቀርበው መፍትሄ እንደተሰጣቸው አስታውቋል። ተጠርጣሪዎች በሚያዙበትና በምርመራ ወቅት ከህግ ውጭ የሆነ አሰራር በፈጸሙ አካላት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም ገልጿል።

በሌላ በኩል ፀረ ሠላም ኃይሎች አሁንም “በህቡዕ በመንቀሳቀስ ችግር ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ኮማንድ ፖስቱ በትኩረት ይከታተል” የሚሉ ጥቆማዎች እንደቀረቡለትና በዚህ መሰረት ቦርዱ ኮማንዱ ፖስቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን አስታውቋል። ህዝቡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካለው ጠቀሜታ አንጻር፣ እንዲቀጥል ፍላጎት ማሳየቱንም ጠቁሟል። ይህን ተከትሎ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ሐሙስ መጋቢት 21፣ 2009 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአራት ወራት እንዲራዘም የሚጠይቅ ረቂቅ ለህዝብ ተወካዮች ጥያቄ አቅርበው አዋጁ ተራዝሟል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስከ ሐምሌ 28፣ 2009 ዓ/ም ስራ ላይ ይውላል ማለት ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ያስፈለገበትን ምክንያቶች ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። እነዚህ ምክንያቶች፤ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመጠቀም የሚፈልጉ ፀረ ሰላም ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ በሁከት እና ብጥብጡ ቀንደኛ መሪዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቢያዙም እስካሁንም ያልተያዙ መኖራቸው፣ በወረቀት ፅሁፎችን በመበተን አሁንም ሰላምና መረጋጋትን ለማደፍረስ የሚጥሩ ወገኖች አልፎ አልፎ መታየታቸው እንደሆኑ ነው አቶ ሲራጅ ያስረዱት። በተጨማሪም ያሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋቱ የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉም የአዋጁን መራዘም አስፈላጊ የሚያደርገው መሆኑን አመልክተዋል። በመላ ሀገሪቱ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ህዝቡ የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን አዋጁ ይራዘም የሚል አስተያየት እንዳለው በመረጋገጡንም በምክንያትነት አንስተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም በሙሉ ድምፅ ወስኗል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተራዘመባቸው ጊዜያት አፈፃፀሙ የዜጎችን ሰብአዊ መብት በጠበቀ መልኩ እንዲሆንም አሳስቧል። በድንበር አካባቢዎች ኮማንድ ፖስቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰላም እና መረጋጋትን የበለጠ እንዲያሰፍንም አሳስቧል። በጽሑፉ መግቢያ ላይ እንደተመለከትነው ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን ተገቢ ቅሬታ ለመግለጽ ያነሳውን ተቃውሞ በመጥለፍ በተለመደው ህግ የማስከበር ስርአት መቆጣጠር ያልተቻለ፣ ህዝቡ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት ያደረሰና ስጋት ላይ የጣለ ሁከት ተቀስቅሶ ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈለገው ይህን ለመከላከል ነበር። የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ አሁን እንደምንመለከተው በመላ ሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ የተለመደው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ቀጥሏል። ይሁን እንጂ ሠላምና መረጋጋቱ ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ እንዳልተረጋገጠ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው ኮማንድ ፖስት አስታውቋል። ህዝቡም በሚኖረበት አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከማንም በላይ ሰለሚያውቅ አዋጁ እንዲራዘም ጠይቋል። የአዋጁ መድረሻ ሠላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሠላማዊ ማድረግና ለዘላቂነቱ ዋስትና መስጠት በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው እንዲራዘም መደረጉ ተገቢ እርምጃ ነው።

ይሁን እንጂ የአንድ አገር ሠላም ሁሌ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታና በልዩ የሰላምና መረጋጋት ጥበቃ የሚረጋገጥ አለመሆኑ መታወቅ አለበት። የሰላም እጦት ዋነኛ ተጎጂ ህዝቡ የሆነውን ያህል፣ ሰላምና መረጋጋትን በማስከበር ረገድም የማይተካ ሚና አለው። በመሆኑም ህዝቡ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም የጠየቀውን ያህል የማያስፈልግበት ነባራዊ የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ እንዲፈጠር በውስጡ የተሸሸጉትን የሰላም ቀበኞች አጋልጦ መስጠት ይኖርበታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅታዊ መፍትሄ እንጂ ዘላቂ የሰላም መፍትሄ አይደለም። እርግጥ ለዘላቂ ሰላም አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ዘላቂና ዋስትና ያለው ሠላም፤ የሠላሙ ባለቤትና የሠላም መጥፋት ቀዳሚ ተጎጂ በሚሆነው ህዝብ እጅ ነው ያለው። እናም ዋስትና ላለው ሠላምና መረጋጋት ህዝቡ ዘብ ይቁም።