የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉባቸው፣ በአገሪቱ ያለውን የድህነት ሁኔታ ለመቅረፍ የጎላ ፋይዳ ያላቸው የልማት ተግባራት በሁሉም ማዕዘናት እየተገነቡ ይገኛሉ። የኃይል ማመንጫዎች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታዎች፣ የመንገድ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የትምህርት፣ የጤናና የመስኖ ልማት ግድብ ግንባታዎች ተጠቃሾች ናቸው።
በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ያሉት ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ፣ የሕዝብ ተሳትፎን ለማቀዛቀዝ፣ ህዝቡ የራሱን ልማትና ብልፅግናና የአገሩን ዕድገት እንዲቃወም ያስችላል የሚሏቸውን ስትራቴጂ ነድፈው ሲራወጡም ይስተዋላሉ። በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ እነዚህን ሜጋ ፕሮጀክቶች ማጣጣልና የልማቱ ተሳታፊ የሆኑ የማኅበረሰቡን ክፍሎች ተሳትፎ ማቀዝቀዝ ላይ ያነጣጠሩ ተግባራትን በመፈፀም ላይ ይገኛሉ።
የአንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች የእስካሁን ጉዞና ተግባራቸው እንደሚያሳየው ለሕዝብ የሚጠቅም አጀንዳ ያልያዙ መሆናቸውን ነው። ይህ ነው የሚባል በኢትዮጵያ ፖለቲካ የጎላ ሚና ያለው ተሳትፎ ሲያደርጉ አይስተዋሉም። ይልቁን በአገሪቱ ወቅታዊ የሆኑ ችግሮች ናቸው ብለው ያመኑባቸውን አጀንዳዎች እየመዘዙ የማባባስና ህዝብን የማደናገር ሥራን ሲከውኑ ይስተዋላል።
በግልፅ በአደባባይ የአገሪቱን የሕግ ሥርዓት የማደፍረስ፣ በየጊዜው ዓላማቸውንና ሃሳባቸውን በመቀያየር፣ ወቅታዊ ሁነቶችን እየተከተሉና ብሶት አለባቸው ብለው የሚያምኑባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን እያሰባሰቡ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረሱ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ራሳቸው ተደናግረው ሌሎችን የሚያደናግሩ ሥልቶችን ያራምዳሉ። መንግሥት በአገሪቱ እየጎለበተ የመጣው የዴሞክራሲ ሥርዓት የበለጠ እንዲጠናከርና የሕዝቡን የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት እንዳይሸራረፍ ብርቱ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ከዚሁ ጋር በተጎዳኝም በህዝብ ላይ ያነጣጠረ የሁከትና የጥፋት እንቅስቃሴ መገታት እንዳለበት በእምነት ይዞ እየሰራ ይገኛል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከመግለጽም አልተቆጠበም። የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በጣሰ መንገድ ሕዝብን የማተራመስና የማወክ መርዝ ለመርጨት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችንም ‘ተው’ ማለቱን ሳይዘነጋ።
በአፍሪካ እየተጠናከረ የመጣውን የአክራሪነትና የፅንፈኝነት እንቅስቃሴን እንደ መልካም የፖለቲካ አጋጣሚ በመውሰድ የፓርቲያቸው የፖለቲካ ማራመጃ መሣሪያ አድርጎ መንቀሳቀስን የመረጡም አሉ። በሽብር ድርጊታቸው የህግ እሥረኛ ለሆኑ ግለሰቦች ዋስ ጠበቃ መስሎ መቅረብ፤ በሕገ መንግሥቱ የተጎናፀፉትን መብት መልሰው ራሳቸው በመካድ ‘አማራጭ ሕገ መንግሥት አርቅቀናል’ በሚል አንድ ሰሞን ለፕሮፖጋንዳ ሥራቸው ይበጀናል ብለው ሲራወጡ ታይተዋል። ይህ የሚያሳየውም ፓርቲዎቹ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ታማኝ አለመሆናቸውንና በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ ሁለት የተለያዩ ሕገ መንግሥቶች ኖረው እንደማያውቁ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ሕገ መንግሥትን ማርቀቅ ውጤት አልባ ከመሆኑም በላይ፤ በወንጀል ሕጉ "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማፍረስ ወንጀል" እንደሆነ ነው። አንዳንዶቹ የፓርቲ መሪዎች ዓይኖቻቸውን በጨው ታጥበው ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ይልቅ የግዛት አንድነትን ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለው ሲደሰኩሩም ይደመጣሉ።
በዚህ መሠረት የመሬት ባለቤትነትን ለግለሰቦች የሚሰጥ ሥርዓትን እንመሰርታለን ብለውም ይከራከራሉ። የተለየ ሃሳብ ማንሸራሸር ሆነ በሠላማዊ መንገድ አቋም ይዞ መከራከር ባልከፋ ነበር። ግና እነዚህን ተግባራት ለመፈፀም ሆነ የፖለቲካ አጀንዳ እድርጎ መታገል ከተፈለገ የፖለቲካ መስመሮቻቸውን ለህዝብ አቅርበው የህዝብን ይሁንታ በማግኘት ሊሆን ይገባቸው ነበር። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሁሉም ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወያይተውበትና አገሪቱንም ወደ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማራመድ እንደሚያግዝ አምነውበት የፀደቀ እንደሆነም መለስ ብለው ቢገነዘቡ ይበጃቸው ነበር።
ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላም ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ተተግብሯል። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና እኩልነትም ተረጋግጧል፤ በመላ አገሪቱ ሠላም በአስተማማኝ ሁኔታ ሰፍኗል። በሁሉም ዘርፎች ሁለንተናዊ የዕድገት ለውጥ ተመዝግቧል። ዜጎች ሕገ መንግሥቱ በሰጣቸው የመደራጀት መብት ተጠቃሚ ሆነዋል። ከዚህ ባፈነገጠ ሁኔታ ግን ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ያስችለናል የሚሉት አካሄድ ተመራጭም አዋጭም አለመሆኑን ቆም ብሎ ማስተዋል የሚበጅ ይሆናል።
በአገሪቱ ሕዳሴውን ለማረጋገጥ ከሚከናወኑት በርካታ የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን መንግሥት ለዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር መጎልበት የበኩሉን የመሪነት ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይህ በሆነበት በዚህ ወቅት ኃይማኖትና ሌሎች አጀንዳዎችን ሽፋን በማድረግ የሚንቀሳቀሱ አካላት በአገሪቱ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እየተመዘገበ ያለውን ውጤት የመጎተት ዓላማ አንግበው እየሰሩ ስለመሆናቸው በግልፅ የሚታይ ነው።
በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ሁነቶች በመከተልና አጀንዳቸውንም ከችግሮቹ ጋር በማቆራኘት በአገሪቱ ሁከትን ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። በሽብር ተግባር ተከሰው በአገሪቱ ሕግ ሥርዓት መሠረት በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ይፈቱ በሚል የሽብር መፈክር ይዘው በመውጣት ግለሰቦችን በመሣሪያነት ለመጠቀም የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉም በዚያን ሰሞን ታዝበን አልፈናል። አገሪቱ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እያደረገች ያለውን ጥረት ለማደናቀፍም የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ይነሳ በማለት ሲቀሰቅሱም ያኔ አድምጠናቸዋል። በሽብር ተግባራት ከተሰማሩ ቡድኖች ጋርም ቁርኝት ፈጥረው ላይ ታች ሲሉም አስተውለናቸዋል።
ኢትዮጵያ ከነበረችበት አስከፊ ድህነት ወጥታ በልማት ጎዳና መጓዝ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። መንግሥት የህዝቡን ኑሮ በመሠረታዊነት ለመቀየርና የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን የሚያስችል የልማት ስትራቴጂ ነድፎ በመተግበር ድህነትን ታሪክ የማድረግ እንቅስቃሴ እየተገበረ ይገኛል። የልማት እንቅስቃሴው ከተስፋ ሰጪነት አልፎ የበርካታ ዜጎችን ህይወት በተጨባጭ መቀየር አስችሏል። በግብርናው ዘርፍ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሚሊዬነር አርሶ አደሮች ተፈጥረዋል። በከተማም በአነስተኛ ጥቃቅን ተደራጅተው ዛሬ የኢንዱስትሪ ባለቤት ለመሆን የበቁ ዜጎች ተበራክተዋል። ይህንን የልማት ጉዞ ምሉዕ ለማድረግና መላውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥም ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በመንደፍ ትግበራው በመልካም አፈጻፀም ላይ ይገኛል።
በአጠቃላይ አገሪቱ መገለጫዋ ከነበረው የከፋ ድህነትና ሰቆቃ በመላቀቅ ቀጣይነት ያለውን ልማት በማረጋገጥ ላይ ትገኛለች። ከዚህ ቀደም ትታወቅባቸው የነበሩት የረሃብና የሰቆቃ ገጽታዎች መቀየር ይዘዋል። በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት ተርታም መሰለፍ ችላለች። በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማፋጠንና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። አገሪቱም ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት መሠረት ይጥላሉ ተብለው የሚገመቱ በርካታ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ተነድፈው በግንባታ ላይ ይገኛሉ። ይህም አገራችን በህዳሴ ጎዳናዋ ላይ እንደምትገኝ የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ይሆን ዘንድም ሁሉም ዜጋ ፀረ-ህዳሴ ኃይሎችን በሁሉም መስኮች ሊታገላቸው ይገባል።