የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ሂደቱ ይቀጥላል

በአገር አቀፍ ደረጃ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ 22 ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፉት ሁለት ወራት ድርድርና ክርክር ለማድረግ የሚያስችላቸው አካሄድ ላይ ሲወያዩ መቆየታቸው ይታወቃል። የድርድርና ክርክሩን ጥሪ ያቀረበው ኢሕአዴግ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እስከ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ሰባት ውይይቶችን አካሂደዋል።

በመጀመሪያው የውይይት መድረክ ላይ በአገር ጉዳይ ላይ መወያየት፣ መከራከርና መደራደር አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም? ኢሕአዴግ በተነሳሽነት የጠራው ውይይት አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ነበር የመከሩት። በዚህም ኢሕአዴግ በጠራውና በአገር ጉዳይ ላይ በሚያተኩር አጀንዳ ላይ መደራደር፣ መከራከርና መወያየት አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተማምነዋል። በመቀጠል በአራት ነጥቦች ላይ ውይይት ተደርጓል። እነዚህም የስብሰባ ሥነ ሥርዓቱ ምን መሆን አለበት፣  የመድረክ መሪነት እንዴት መካሄድ አለበት፣ ጋዜጣዊ መግለጫ  አሰጣጥ እንዴት መከናወን ይገባዋል፣ እንዲሁም የውይይት ታዛቢ ማን መሆን አለበት የሚሉ አጀንዳዎች ነበሩ።

ፓርቲዎቹ በዚህ መነሻነት በመካከላቸው የሚካሄደው ድርድር፣ ክርክርና ውይይት የሚመራበት መመሪያ ደንብ ለማዘጋጀት ተስማሙ። ይህንንም የሚያስፈጽም ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ ለማዋቀር በቅተዋል። በዚህ ሂደት ወደዋናው ድርድር ይሸጋገራሉ በሚል ተስፋ ወፌ ቆመች ስንል ብንሰነብትም፣ ገና ከጅምሩ መንገዱ አባጣና ጎርባጣ በዝቶበታል። ፓርቲዎቹ በአንድ ወገን ድርድር፣ ክርክርና ውይይት ለማካሄድ የሚያስችላቸውን የሥነ ሥርዓት ደንብ ለማዘጋጀት እየተስማሙ፣ በሌላ በኩል ከመካከላቸው ሁለት ሦስት የሚሆኑት ቅድመ ሁኔታዎችን የማስቀመጥ ፍላጎት እንዳላቸው በተለይ ውጭ አገር በሚገኙ ሚዲያዎች ሲገልጹ ቆየተዋል። ሲገልጿቸው የነበሩት ቅድመ ሁኔታዎች፤ የፖለቲካ እሥረኞች ይፈቱ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ ወዘተ…የሚሉ ነበሩ።

ይህ ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ አካሄድ በሰጥቶ መቀበል መንፈስ መካሄድ ያለበትን ድርድር፣ ክርክርና ውይይት ሊያሰናክል ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሮ ነበር። በተለይ ከድርድሩና ክርክሩ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ሊያሰፋ የሚችል ትንሽም ብትሆን ውጤት ይጠብቁ በነበሩ ዜጎች ዘንድ።

ያም ሆነ ይህ ካሁን አሁን ወደዋናው ድርድር፣ ክርክርና ውይይት ተሸጋገሩ ተብሎ በጉጉት ሲጠበቅ፣ የተወሰኑ ፓርቲዎች በውይይቱ ሂደት የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው ማሳወቅ ጀመሩ። ይህ ዝንባሌ የታየባቸው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና ለውይይቱ ዓላማ የተሰባሰቡ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች (ኢዴፓ፣ መኢአድ፣ ሰማያዊ፣ ኢራፓ፣ መኢዴፓ፣ መኢብአፓ) የያዘ ቡድን ናቸው።

በቅድሚያ መድረክ 22 የፖለቲካ ፓርዎች በሚወከሉበት ድርድር፣ ክርክርና ውይይት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው፣ ከዚህ ይልቅ ሌሎቹን ፓርቲዎች ወክሎ በአውራ ተደራዳሪነት ብቻውን ከኢሕአዴግ ጋር የመደራደር ሃሳብ አቀረበ። ከዚሁ ጋር አያይዞ ድርድሩ፣ ክርክሩና ውይይቱ በገለልተኛ ሦስተኛ ወገን ይመራ የሚል ሃሳብ አቀረበ። በተመሳሳይ የስድስት ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው ቡድንም፣ ገለልተኛ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ይኑር የሚል አቋም ያዘ። የምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡን በፊርማቸው ያፀደቁና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የመሠረቱ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በመጀመሪያ ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል የሚል አቋም ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ይህን አቋማቸውን ቀይረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑት ፓርቲዎች፤ ሠላማዊ በሆነች አገር፣ በሠላማዊ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ድርድር፣ ሠላምን ባጡ አገራት እንደሚደረገው ዓይነት በሦስተኛ ወገን የሚደረግ ድርድር አያስፈልግም፤ ማንም ሰው ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነፃ እና ገለልተኛ ይሆናል ብለን ስለማናስብ ገለልተኛ እና ነፃ አደራዳሪ የሚለውን አንቀበለውም፤ አደራዳሪው መድረክ ከመምራት ባሻገር ሌላ ሚና ስለማይኖረው አያስፈልገንም የሚል ምክንያት አቅርበዋል።

ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ፤ ነፃ እና ገለልተኛ ስንል የፓርቲ አባል ያልሆኑ ግለሰቦች ማለታችን ነው፤ ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ሊያደራድሩን ይገባል፤ ኢሕአዴግን ስለማናምነው ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ወገን እንዲኖር እንፈልጋለን የሚል ምክንያት አቅርበዋል።

ኢሕአዴግ በበኩሉ፣ ከአሁን ቀደም ያለ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ በፓርቲዎች ብቻ በተደረጉ ድርድሮች የምርጫ ህጎች መሻሻላቸውን አስታውሶ፣ አንድ ግለሰብ የፓርቲ አባል አይደለም ማለት የአንድ ወይም የሌላ አስተሳሰብ ደጋፊ አለመሆኑን ስለማያረጋግጥ ገለልተኛ እና ነጻ አደራዳሪ የሚለውን ሀሳብ አልቀበልም ብሏል።

ያም ሆነ ይህ፣ በዚህ የሦስተኛ ወገን የአደራዳሪ ጉዳይ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል የተፈጠረው ልዩነት አስመልክቶ፣ ፓርቲዎቹ የመጨረሻ አቋማቸውን ለማሳወቅ ለሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ነበር። ይሁን እንጂ ጥቂት ፓርቲዎች ራሳቸውን ከድርድሩ መውጣታቸውን አሳውቀዋል። ራሳቸውን ከድርድሩ ለማስወጣት የወሰኑት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ናቸው። መድረክ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መገለጫ የሰጠ ሲሆን ሰማያዊ ፓርቲ ግን ውጭ አገር በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን አማካይነት ነው ያሳወቀው።

መድረክ ድርድሩን አቋርጦ መውጣቱን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ድርድሩ ላይ ለመሳተፍ፣ በድርድሩ ላይ ፓርቲያችንን በመወከል ግንባር ቀደም ተደራዳሪ ሆነው ሊቀርቡ የሚገባቸውን ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ሌሎች የድርጀቱ አመራር የሆኑ ፖለቲከኞች ይፈቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ የሚል አቋም እንዳለው አሳውቋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋም ድርድሩ ላይ ለመሳተፍ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ይኑር ከሚለው በተጨማሪ የፖለቲካ እሥረኞች ይፈቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ የሚል ቅድመ ሁኔታን አስቀምጠዋል።

እነዚህ ራሳቸውን ከድርድሩ ማስወጣታቸውን ያሳወቁ ፓርቲዎች፣ ከድርድሩ የሚጠበቀውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያጎለብት ውጤት ታሳቢ በማድረግ ወደ ድርድሩ ሊመለሱ የሚችሉበት እድል መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ከድርድሩ ለመውጣት በምክንያትነት ያቀረቡትን አቋም እንመለከት።

ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ይኑር ከሚለው እንጀምር። በቅድሚያ አንድ አደራዳሪ ሆኖ የሚቀርብ ግለሰብ ወይም የቡድን ተወካይ፣ ድርድሩ ላይ በየተራ እንዲናገሩ ከማድረግ ያለፈ ድርሻ እንዲኖረው አይጠበቅም። የሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ድርሻ ይህ ከሆነ፣ አደራዳሪ ካልተገኘ ድርድሩን አልፈልግም የሚል አቋም ላይ ሙጭጭ ማለት ድርድሩ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ጥርጣሬ ላይ ይጥላል። ምናልባትም፣ ከድርደሩ ሊገኝ የሚችለውን ፋይዳ አለመገንዘብ ሊሆን ይችላል።

በሌላ በኩል ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ የመሰየም ጉዳይ፣ አንድ መሠረታዊ ጥያቄን ማስከተሉ አይቀርም። ይህም ገለልተኛ ማነው? የሚለው ነው። ከርዕዮተ ዓለምና ከአቋም ውጭ የሆነ ግለሰብ ወይም ቡድን ማፈላለግ ጭው ባለ በረሃ ውኃ ከመፈለግ አይለይም። ሰዎች ከአንድ ርዕዮተ ዓለም ወይም አቋም ጋር ያላቸው ግንኙነት በመደገፍ ወይም በማራመድ ወዘተ… ደረጃ የተለያየ ሊሆን ይችል እንደሆነ እንጂ፣ ፍጹም ነጻና ገለልተኛ ሊሆኑ አይችሉም፤ በተለይ ምሁራን።

በመሆኑም ሦስተኛ ወገን መሰየም ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ምናልባት አይቻልም። የኃይማኖት አባቶች በፖለቲካ ድርድሩ ውስጥ እንዲገቡ መጠየቅ፣ ፖለቲካና ኃይማኖትን ማደባለቅ እንዳይሆን ያስፈራል። የውጭ አገር አደራዳሪ መጠየቅ ደግሞ፣ የኢትዮጵያውያን ጉዳይ ብቻ በሆነው የአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው የውጭ አገራት ቡድኖች ገብተው እንዲያቦኩ ከመፍቀድ የሚለይ አይደለም። ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ካልኖረ የሚለውን አቋም ከእነዚህ ነጥቦች አኳያ ስንመዝነው መሠረተ ቢስ ነው። መድረክ ያቀረበው አውራ ተደራዳሪ ልሁን የሚል ጥያቄ፣ በሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀባይነት ያጣ በመሆኑ ይህን ጉዳይ ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ አላገኘሁትም።

የፖለቲካ እሥረኞች ይፈቱና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ የሚለውን እንመልከት። በቅድሚያ፤ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ የለም። የፖለቲካ እሥረኛ ማለት አንድ ግለሰብ በያዘው፣ በሠላማዊ መንገድ በሚያራምደው፣ በሚደግፈውና በሚገልፀው አቋሙ በቁጥጥር ሥር የዋለ ማለት ነው። በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአመለካከት ነጻነት፣ አመለካከትን በግልና ከሌሎች ጋር ተደራጅቶ የማራመድ፣ በይፋ የመግለጽ፣ በአመለካካት ለፖለቲካ ሥልጣን የመፎካከርና በህዝብ ድምጽ በሚገኝ ውክልና ሥልጣን የመረከብ መብት ተረጋግጧል። መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ የተቋቋሙት፣ አቋማቸውን በይፋ የሚያራምዱትና የሚገልጹት፣ ለምርጫ የሚፎካከሩት በዚህ ህገ መንግሥታዊ መብታቸው ተጠቅመው ነው። ሰዎች በአቋማቸውና በአመለካከታቸው የሚታሰሩ ቢሆንማ፣ የመድረክ መሪ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ ባልኖሩ ነበር።

በፖለቲከኝነት የሚታወቁ በፍርድ ቤት ቅጣት ተወስኖባቸው፤ የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ እሥረኞች ግን አሉ። እነዚህ ግለሰቦች በፍርድ ቤት ክስ የተመሠረተባቸውና በጥፋተኝነት የተፈረደባቸው ግን በፖለቲካ ሥራቸው በያዙትና ባራመዱት አቋም አይደለም። ከዚህ ይልቅ በወንጀል ህጉ ወይም በልዩ ባህሪያቸው ምክንያት በተለየ ህግ የተደነገጉ የወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም ተጠርጥረውና ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ ተረጋግጦ ነው። እነዚህ ደግሞ የፖለቲካ እሥረኞች አይደሉም። የወንጀል ተጠርጣሪዎችና ጥፋተኛ ወንጀለኞች እንጂ።

ወደ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስንመለስ፣ ማንኛውም ሠላም ወዳድና ለአገሩ ዘላቂ ሠላምና ልማት የሚያስብ ዜጋ እንደሚረዳው፣ መነሻው ምንም ይሁን ምን ባለፈው ዓመትና በያዝነው ዓመት መግቢያ ላይ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ግልጽና ደራሽ አደጋ አጋጥሞ ነበር። መንግሥት ይህን አደጋ የመከላከል ህገ መንግሥታዊ ግዴታ ያለበት መሆኑም ይታወቃል። በተለይ ሁከቱ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ስትራቴጂ ነድፈው የሚንቀሳቀሱ የአገሪቱ ጠላቶች ከጀርባ ሆነው የሚመሩት መሆኑ እጅግ አሳሳቢ አድርጎት ነበር።

ይህን በፍጥነት እየተዛመተ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ሲያደርስ የነበረ የአገሪቱ ጠላቶች ጭምር እጃቸውን ያስገቡበት አደገኛ ሁከት በተለመደው የህግ ማስከበር ሥራ መቆጣጣር አልተቻለም። ይህን እውነታ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲም ጠንቅቀው ያውቁታል። ምናልባት በግርግር የፖለቲካ ትርፍ ሊያስገኘን ይችላል የሚል ግምት ሊኖራቸው ግን ይችል ይሆናል። እንግዲህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገው በአገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች ይመራ የነበረውን ሁከት መክቶ የአገሪቱን ሠላምና መረጋጋት ወደነበረበት ለመመለስ ብቻ ነው። አዋጁ የአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ወደነበረበት እስኪመለስ ብቻ ሥራ ላይ የሚቆይ ነው። አዋጁ በፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴም ላይ ሆነ በሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ክንውኖች ላይ ምንም ተጽዕኖ አላሳደረም። ይህ በተጨባጭ የታየና ቀና ህሊና ያላቸው በሙሉ ሊመሰክሩለት የሚችሉት እውነት ነው። አዋጁ ተልዕኮውን ሳያሳካ ይነሳ የሚለውን አጀንዳ በድርድር ቅድመ ሁኔታነት ማስቀመጥ ውይይቱንና ድርድሩን ካለመፈለግ፣ ወይም ለማደናቀፍ ካለ ፍላጎት ለይቶ ማየትተ ስህተት ይመስለኛል።

በአጠቃላይ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን መሠረተ ቢስ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠው ራሳቸውን ከድርድሩ ውጭ ለማድረግ መወሰናቸው ተገቢ እርምጃ አይደለም። ፓርቲዎቹ በድርድሩ ሊገኙ የሚችሉ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ሊያሰፉ ለሚችሉ ውጤቶች ዋጋ ያልሰጡ መሆናቸውን ያመለክታል። በዚህ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ያገኙትን እድል እየገፉ መሆኑም መታወቅ አለበት። ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ርምጃ በውጭ አገር ለሚንቀሳቀሱ በተለይ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል የማፍረስ ህልም ያላቸው ቡድኖች የአገሪቱን ሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ችግር ያለበት አስመስለው በማቅረብ የአካሄዳቸውን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፍጆታነት ከማዋል ያለፈ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም።

ራሳቸውን ከድርድሩ ያገለሉት ፓርቲዎች ሊያውቁት የሚገባው ሌላው እውነታ፣ የእነርሱ በድርድሩ ላይ አለመሳተፍ ድርድሩን የማያቆመው መሆኑን ነው። አብዛኞቹ ፓርቲዎች እስካሁን ባለው ሂደት በድርድሩ ላይ የመሳተፍ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል። ልክ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡ ላይ ድርድር የተካሄደ ጊዜ የመድረክ ድርድሩን ረግጦ መውጣት በድርድሩና ባስገኘው ወጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላሳደረው ሁሉ፣ አሁንም ምንም የሚያሳድረው ተጽዕኖ የለም። እናም ራሳቸውን ከድርድሩ ለማውጣት የወሰኑ ፓርቲዎች ወሣኔያቸውን ቢያጥፉ ለራሳቸውም ለህዝቡም መልካም ይመስለኛል። እነርሱ ቢኖሩም ባይኖሩም፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሳተፈ ድርድር፣ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ የማስፋት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ስለሆነ ሂደቱ ይቀጥላል።