ሰላማዊ ተቃውሞ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው!

ህገ መንግስቱ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የመሰላቸውን አቋም የመያዝ፣ ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ የመግለፅና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቋውሟቸውን ማሰማት እንደሚችሉ ደንግጓል። እርግጥ ይህ ድንጋጌ የሚሰራው በህግ ካተገደበ ነው። በተለይም ሰላማዊ ተቃውሞ ሲደረግ ህገ መንግስቱን ተመርኩዞ በተቀመጡ መብትና ግዴታዎች ታጅቦ ነው። ያም ሆኖ ግን የህግ ድንጋጌው ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ማናቸውንም ተቃውሞዎች ማቅረብ እንደሚችሉ መብት ይሰጣል።

ህገ መንግስቱ ለሰላማዊ ተቃውሞ መብት ይሰጣል ሲባል፤ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ የሚደረጉ ማናቸውም ፍላጎቶች አይፈቀዱም ማለት ነው። እናም ህገ መንግስቱ ለሰላማዊ ተቃውሞ መብት የሚሰጠውን ያህል ህግና ስርዓትን ለሚጥስ ማናቸውም ተግባር ምንም ዓይነት ዕውቅና የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ፣ የህግ የበላይነትን መፃረር በመሆኑ በወንጀል ተጠያቂነት ያለበትም ነው።

እንደሚታወቀው በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ እንደሚሆንበት ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል።

ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው። ይህም የህገ መንግስቱን አንቀፅ 56 የሚመለከት ነው። በዚህ አንቀፅ መሰረት በምክር ቤተ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅት የፌዴራሉን መንግስት የህግ አስፈፃሚ አካል እንደሚያደራጁና እንደሚመሩ ተገልጿል።

ይህም የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ህገ ወጥ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ከህገ መንግስቱ አኳያ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉ ማናቸውም የፖለቲካ አሊያም የሽብር ድርጅቶች ህገ ወጥ ናቸው። ከእነርሱም ጋር የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት ወይም የእነርሱን አጀንዳ በማራመድ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች የህግ የበላይነትን መፃረር እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባ ይመስለኛል።

ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ውስጥ በአሸባሪነት የተሰየሙትን ኦነግንና ግንቦት ሰባት የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን ከደገፈ ወይም የእነርሱን ዓላማ ለማሳካት በተለያዩ መንገዶች ከተንቀሳቀሰ ከህግ የበላይነት ጋር እየተጋጨ መሆኑን ግንዛቤ ሊይዝ ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ የሽብር ቡድኖች ህገ መንግስቱን ተፃርረው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው ነው። እናም እነርሱን አለመደገፍ የህግ የበላይነትን ማክበር ሲሆን፣ የእነርሱን ህገ ወጥ ዓላማ በማናቸውም መንገድ መደገፍ ደግሞ የህግ የበላይነትን መፃረር መሆኑን መረዳት ይገባል።

የህግ የበላይነት ልዕልና ሊጠበቅ ይገባል። የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል። ይህም ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። በመሆኑም ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር በሀግ አስፈፃሚው አካል በሚፈፀምበት ወቅት የተለየ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም።

ለዚህ ፅሑፍ አንባቢያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ከሰሞኑ ክስተት አንድ ዕውነታን ላንሳ። ይኸውም በህገ መንግስቱ መሰረት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው። እንደሚታወቀው አዋጁ ተፈፃሚ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ክልከላዎቹን ጥሰው በሚገኙ ሰዎችና ድርጅቶች ላይ ተገቢውን የአስቸኳይ ጊዜ ርምጃ መውሰድ ተገቢ መሆኑ ተገልጿል። ይህም የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ በማሰብ የተደረገ ነው። ይሁንና አዋጁ ለሁሉም የሚሰራ መሆኑ ተዘንግቶ አንዳንድ ወገኖች አዋጁን የተላለፉ እንደ ዶክተር መረራ ጉዲና ዓይነት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሆን ተብሎ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት የተደረገ ሲያስመስሉ ይስተዋላሉ።

ነገር ግን ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በአንድ ሀገር ውስጥ የሚወጣ ማንኛውም አዋጅ ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት መሆኑ ነው። ለነገሩ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ አዋጁን በመተላለፍ ዶክተር መራራ ጉዲና በህግ ጥላ ስር ዋሉ እንጂ፤ ሌላ ሰው ቢታሰር ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ ነገር አይነሳም ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን አዋጁ ለሁሉም የወጣ ከመሆኑም በላይ የህግ የበላይነትን ልዕልናን ለማስከበር ሲባል አዋጁን የተላለፉ ግለሰቦችን በህግ አግባብ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢና ትክክል ይመስለኛል።

እናም ማንኛውም ወገን በህገ መንግስቱ መሰረት ተግባሩን በህግ አግባብ መከወን ይኖርበታል። በተለይም ተቃውሞ የአንድ ዴሞክራሲያዊ ሀገር መገለጫ እንደመሆኑ መጠን በሰከነ መንገድ መፈፀም አለበት። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የሚመጣበት ምክንያትም፤ የመራጩ ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁ በጊዜ ሂደት እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድ በመሆኑ ነው፡፡ አንድ በጅምር ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ዕድሜ አስቆጠር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችል ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው ዴሞክራሲ በአንዴ የሚገነባ ሳይሆን አብሮ በጊዜ ሂደት ከህዝቡ አስተሳሰብ እያደረ የሚራመድ ነው የሚባለው፡፡

ከዚህ አኳያ የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ገና ለጋ በመሆኑ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት ባይቻልም፤ ከዕድሜ አኳያ ስንመለከተው ግን አሁን ያለንበት ደረጃ የመራጩ ህዝብ አስተሳሰብ እያደገና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም እየሰፋ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይህም በቀጣይነት የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታን ይበልጥ ለማጎልበት ከወዲሁ ተስፋ መኖሩን አመላካች ነው። እናም በተቃዋሚነት የተሰለፉ ወገኖች ይህን ዕውነታ ማወቅ ይኖርቸዋል።

በተቃውሞ ጎራ ተሰልፈው ችግሮችን በጥላቻ መንፈስ ለመፍታት ከተሞከረ ሰላማዊነትን አያመላክትም። በመሆኑም ሰላማዊ ለመሆን የሁሉም ወገኖች መቻቻልና ለዴሞክራሲ መጎልበት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም ዴሞክራሲን በማጎልበት የህግ የበላይነትን አስጠብቆ ለመቀጠል ማንኛውም ተቃሞ በህግና በስርዓት እንዲሁም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ሊመራ ይገባዋል እላለሁ።