በአፍሪካ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ተከታታይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ለአሥር ተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ያም ሆኖ ግን የስደተኞች ቁጥር ጨምሯል እንጂ አልቀነሰም፡፡ ይኼ ሊሆን የቻለበት ምክንያት በአብዛኛው ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያያዥ መሆኑን የአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ድረ ገጽ ያመለክታል። በአንድ በኩል ዕድገቱ በተለይ ለወጣቱ የሥራ ዕድል የሚፈጥር አልሆነም፡፡ እንዲሁም ደግሞ ወጣቶቹ አስፈላጊውን ክህሎትና ሥልጠና እንዲያኙ አልተደረገም፡፡ ለምሳሌ በቂ የሰው ኃይል የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት አለመቻል አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡
ስደት ጠቅላል ተደርጎ ሲታይ ሁለት ገጽታ ነው ያለው፡፡ አንደኛው በአፍሪካ ቀንድ በጣም ብዙ ሰዎች መኖር ባለመቻላቸው የሚደረግ ስደት ነው፡፡ ይኼ በአብዛኛው በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የሚከናወን ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከቀጣናው ወደ አውሮፓና መካከለኛ ምሥራቅ የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን) እንዲሁም ደግሞ አጠቃላይ በአፍሪካ አኅጉር ችግሩ በጣም ከባድ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ብዙ ሰዎች ስደት ሲባል የሚያነሱት በተለይ ወደ አውሮፓ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው፡፡ ብዙ የተማሩ ወጣቶች ወደ እነዚህ የዓለም ክፍሎች በዚህ ሁኔታ ይሰደዳሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግን ሰዎች የዕለት ገቢያቸው በጨመረ ቁጥር ወደ አውሮፓ የመሰደድ ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡ ወደዚህ አካባቢ የሚደረገው ጉዞ በድህነት ምክንያት ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ዋናውና ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ድህነት አይደለም፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች መካከል ከአንዱ ጎረቤት ወደ ሌላው ጎረቤት የሚደረገው ስደት አለ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ እንዲሁም ከኤርትራ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አስጠልላለች፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብዙ ስደተኞች በማስጠለል ቁጥር አንድ መሆኗም በተለያዩ አግባቦች እየተረጋገጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካላት ውሱን ሃብት ላይ በመቀነስ ለስደተኞች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድም በመንግስታቱ ድርጅት መዝገብ የመጀመሪያው ገጽ ላይ ሰፍራለች። ለአብነት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም የተለያዩ የስራ እድል እንዲያገኙ በማድረጓ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ምስጋና የተቸራት አገር ለመሆን መብቃቷ የቀጠናውን በችግር ውስጥ መሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለዜጎቿ የሚሆን አቅም መገንባቷን የሚያሳይ ነው።
ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ወጣቶች በህገ ወጥ ደላሎች እየተታለሉ የተሻለ ገቢ እናገኛለን በሚል ወደተለያዩ አገራት በተለይ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በህገወጥ መንገድ በመጓዝ ህይወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ነው። የአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ግንዛቤ የመፍጠር ጉዳይ ካልሆነ በኢትዮጵያ ያለው ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን የተመቸ እንደሆነ ይናገራል።
በኢትዮጵየያ ህገመንግስት ዜጎች ወደፈለጉት አገር ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል።ስለሆነም ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደፈለጉት አገር መሄድና መስራት እየቻሉ ለህገወጥ ደላሎች እየተጋለጡ ከሆነ ጉዳዩ ከግንዛቤ ጋር የተያያዘ ብቻ ነው የሚሆነው። በኢትዮጵያ አንዳንድ ወጣቶች በህጋዊ መንገድ ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ ህይወትን ለአደጋ በማጋለጥ በአጭር ጊዜ ለመክበር የሚያደርጉት ጥረት ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን የሚገልጸው ኢንስቲትዩት ፤በርካታ ወጣቶች ግን ከላይ የተመለከተውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በአጭር ጊዜ ውስጥ መለወጣቸውን ያብራራል። የኢንስቲትዩቱ ማብራሪያ ሲቀጥል በኢትዮጵያ ሁኔታ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል እና ግን ደግሞ ስኬታማ ለመሆን የመጀመሪያው ነገር ቁርጠኛ መሆን፣ ወድቆ ተነስቶ መስራትንና መጣርን የሚጠይቅ መሆኑን ነው።
የቀንዱን ሌሎች ሃገራት በተመለከተ ግን ወጣቶቻቸውን የሚሸከም አቅም እንደሌለ ገልጾ፤ በሂደት እንደኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ኢኮኖሚ የስደተኞቹ ሰለባ እንዳይሆን መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን የጥናት ግኝቶች ያስቀምጣል። ለምሳሌ አንድ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው አፍሪካውያን ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በነፃ እንዲዛወሩ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ነው፡፡ አፍሪካውያን ከአንድ የአፍሪካ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ለምን ቪዛ ያስፈልጋል? ኬንያ ውስጥ የሚኖሩ አፍሪካውያን ወደ ሌላ አፍሪካ አገር ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ለምን ቪዛ ያስፈልጋቸዋል? ይኼ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ያሉትም ሆነ በኬንያ የተጠለሉት ስደተኞች ይህንን መብት አግኝተው ቢሆን፣ ስደተኛ ሆነው በካምፕ ተቀምጠው የለጋሾች እጅ የሚጠብቁበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ በነፃ ተዘዋውረው ሠርተው ይኖሩ ነበር፡፡ ይህ ቢደረግ ሁለት ነገሮችን መቀነስ ይቻላል ።አፍሪካውያን ወጣቶች ትኩስ ጉልበት ይዘው ወደ አውሮፓና ሌላ አኅጉር ሄደው ስደተኛ የሚሆኑበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለወጣቶች በቤታቸው የሥራ ዕድል ተፈጠረላቸው ማለት ነው፡፡ በዚህም የአፍሪካውያን ስደት በአውሮፓ የመነጋገሪያ ጉዳይ መሆኑ ይቀርራል። እንዲህ ቢሆን አፍሪካውያን በሜዲትራኒያን ባህር የዓሳ ዕራት ከመሆን ይድናሉ። አውሮፓውያንም አንድ አፍሪካዊ ሠራተኛ የሚወስዱት ፈልገውና ከእነ ሙሉ ክብሩ ይሆናል፡፡ የስደተኛና የሕገወጥ ዝውውር ሁኔታ ቀርቶ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ይተካል፡፡ ይህ ደግሞ መረጋጋትን ይፈጥራል፡፡
ይኼ ደግሞ በአንድ መንግሥት ወይም በተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥረት የሚመጣ አይደለም፡፡ ጉዳዩን የጋራ አድርጎ በመቀበል በተባበረ ክንድ ነው መፍታት የሚቻለው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተር በሱዳን ገንዘቡን አፍስሶ ቢሠራ የሚጠቀመው ሥራ ፈጣሪ ኢንቨስተሩ ብቻ አይደለም፡፡ የሱዳን ወጣቶች ናቸው ተቀጥረው የሚሠሩበት፡፡ከአኅጉሩ ወደ ውጭ የሚወጣ ሀብታም አይኖርም ማለት ነው፡፡
የኢትዮጵያን የስደት ቅነሳ ፖሊሲና ትግበራ ሌሎቹም የቀጠናው ሃገራት እስካልተጠቀሙበት ድረስ ዞሮ ዞሮ ጫናው ወደፊት የማይችሉት እንደሚሆን አያጠያይቅም። ከላይ የተመለከተው ጥናትና የመፍትሄ ሃሳብ አንድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ቁምነገርን ይዟል። ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሌላው እየመጣባቸው መሆኑን ስለምን ብለው ሊጠይቁ እና የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ሊጠቀሙበት የሚገባ መሆኑን የተመለከተ ቁም ነገር።
የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ እንደ አገራችን ባሉ ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት በመናድ በምትኩ የልማታዊነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን መገንባት ተሳቢ ያደረገ መሆኑ የመጀመሪያው ነው። ይህ ስትራቴጂ በአገሪቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችልና ህዝቡ ከልማቱ በላቀ ደረጃ ሊጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው። ከዚህም ባለፈ በከተሞች ለዴሞክራሲ ማበብ የሚበጅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነ ተግባራዊ በሆነው ውጤቱ ታይቷል። በሃገሪቱ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ በመደረጉ ገበያው በፍላጎትና በአቅርቦት እንዲመራ ተደርጓል። የሸቀጦች ዝውውርና የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴም በካፒታል ጣሪያ ስለዚሁ ጉዳይ እንዳይገደብ ተደርጓል። ልዩ ትኩረት የማይሹ የመንግስት የልማት ድርጀቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዞር እና ሀገራዊ ጥቅምን ባስከበረ መልኩ እንዲመሩ የተደረገውም ስለዚህ ነው። ኢኮኖሚያችንን ከዓለም ኢከኖሚ ጋር ለማስተሳሰር የተወሰዱ እርምጃዎች ጨምሮ ኋላ ቀር አሠራሮችን በማሻሻል የተቀላጠፈና ውጤታማ አገልግሎት አሠጣጥ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ በማድረግ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን የማስቻሏ እውነታ ለወሰዱ ከሚገባቸው ተሞክሮዎች እና ወጣቶቻችን ሊያጤኗቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ወሳኞቹ ናቸው።
የግሉ ዘርፍ የኦኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሃገራዊ ባለሃብቶች እንዲፈሩ ተደርጓል፡፡ በዓለም የገበያ ውድድር ውስጥ ጠንካራ የመወዳደር አቅም እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያላቸው ድጋፎች በመደረጋቸው በርካታ አስመጪዎችና ላኪዎች ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ሀብት እንዲያፈሩ እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ ለልማቱ የሚያስፈልገውን ሀብት በማመንጨት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማበርከት የመቻላቸውም እውነታ ሊጤንና ሊወሰድ የሚገባው ተሞክሮ ነው፡፡
ሰፊውን ህብረተሰብ ለማሳተፍና ተጠቃሚ ለማድረግ ይልቁንም ወጣቱን ሃይል በሞላ በስራ ላይ ማሰማራት እንዲቻል የአገራችንን ኢንዱስትሪ ዘርፍ በፍጥነት ማሳደግ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ በማስመዝገብ ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ሽግግር መፍጠር የእድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ ሁኔታ ነው። ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን የሚደረገው ሽግግር ምኞት ሆኖ እንዳይቀር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች የተሰሩ እና፤ እየተሰሩ ቢሆንም የሰለጠነ የሰው ሃይል በበቂ ማልማትና ማቅረብ እንዲሁም በባላሃብቱ ውስጥ የሚስተዋለውን የአመለካከት ውስንነት ማስወገድ አለመቻሉ ግን አሁንም ስለሃገራችን ወጣቶች ሊጤን እና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ልማታዊ ባለሃብቱን በስፋትና ከበቂ ድጋፍ ጋር ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቆርጦ እንዲገባ በማድረግ ረገድ አመራሩ ጋር የሚታየው የያዝ ለቀቅ አካሄድ መቀየር አለበት። በዘርፉ ለሚሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚደረገው መንግስታዊ ድጋፍ ከለላ በማድረግ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠውን አመራርም መቆንጠጥ ተገቢ ነው።
ወጣቶች እንኳንስ መስራት ለሚችሉባቸው በርካታ አማራጮች ቀርቶ በአገሪቱ የሃምሳ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውና ሰፊ አካባቢ ያካለለውን የድርቅ አደጋ፣ ለዜጎች በየቀያቸው ዕርዳታ በወቅቱ በማቅረብ ምንም ዓይነት የህይወት አደጋ ሳያስከትል መቋቋም መቻሉ በአገሪቱ የእየተገነባ ያለውን የኢኮኖሚ የአመራርና የአፈፃፀም ዕድገት በሚገባ አመላክቷል፡፡ በቀሪዎቹ ጊዜያት ይህንን አቅም ሙሉ በሙሉ በልማት ተግባር ላይ በማዋል ዕቅዱን የማሳካት ዕድል ሰፊ መሆኑንም ያረጋግጣል፡፡
እስካሁንና በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተገነቡት መሰረተ ልማቶች፣ ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማነት ትልቅ አቅም መሆናቸው ሌላው ተፈፃሚነቱን ከወዲሁ የሚያመላክቱና የሃገራችን ወጣቶች ለህገ ወጥ ስደት ምክንያት የሌላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ሁነኛ አስረጅ ነው፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአገሪቱን የኢኮኖሚ አውታር በማስፋት፣ ኢንዱስትሪ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት በማድረግና የወጪ ንግድን በማሳደግ፣ የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በማሳለጥ ስደተኝነት ነውር የሚሆንበት ደረጃ ላይ ማድረስ ነው፡፡
ወጣቱ ትውልድ በገጠርና በከተማ ልማት በማሰማራት የስራ ዕድል ከመፍጠር ጎን ለጎን የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሃይል ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ የገጠሩን አጠቃላይ ገፅታ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለውጠው ታምኖ እየተተጋ ነው፡፡ የመስኖ ግብርና፣ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንደዚሁም የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ስራ በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋትን ትኩረት ያደረገው ዕቅድ፣ ግብርናው በዕቅድ ዘመኑ ለልማቱና ለፈጣን ዕድገቱ የማይተካ አስተዋፅኦ ከማድረግ ባሻገር የዘመናዊ አምራች ዘርፍ ዕድገት ዋና ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያስችለው ይጠበቃልና ለህገ ወጥ ስደት አሳማኝ ምክንያት አይኖርም ፡፡
የገጠር ኢንዱስትሪ ማዕከላት በሂደት እየተፈጠሩ ከተሞቻችንም በዛው መጠን እያደጉ ሲሄዱ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እየተቀየረ፣ የከተማና የገጠር ትስስር እየጠበቀ፣ ያደገ ህብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችለን አቅም እየተፈጠረ መሄዱ አይቀሬ እና ሂደቱም እያሳየን ነው፡፡ በዚሁ ላይ ደግሞ ለወጣቶቻችን የሚበጅ አዲስ የተዘዋዋሪ ፈንድ ተዘርግቷልና ለህገወጥ ስደት የሚሆኑ ምክንያቶች ሁሉ አብቅቶላቸዋል ባይባልም እየተሸረሸረ መሄዱ የግድ ነው። ከወጣቶቻችን የሚጠበቀው ዋናው ጉዳይ የተዘረጋውን ስርአት በአግባቡ የመጠቀምና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ብቻ ነው።
መንግስት ለወጣቱ የሰጠው ትኩረት የቁርጠኝነቱና የህዝባዊነቱ ማሳያ ነው። ስለሆነም ወጣቶች የስራና የቁጠባ ባህላቸውን በማሻሻል፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል የአመለካከት ለውጥ ሊያመጡ ይገባል። ይህን ደግሞ የተመደበላቸውን ገንዘብና የተሰጣቸውን ዕድል በሃላፊነት ስሜት በመጠቀም ሊያረጋግጡ ይገባል።