ስደት ዴሞክራሲያዊ መብትን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ክብርንም ይገፋል!

ስደት አዲስ ክስተት አይደለም። የሰው ልጆች በዚህ ምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሰዎች ስደት አብሯቸው የኖረ ክስተት ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ እያስተዋልን ያለነው የስደት አይነት እጅግ አስፈሪ ነው። ህይወትን ሊያሳጣ አካልን ሊያጎድል የሚችል የሰደት ዓይነቶችን እየተመለከትን ነው። በህይወት ቁማር የለም።

ሰዎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አስገዳጅ ምክንያቶች አልያም በፍላጎት  ከተወለዱበት ወይም ከሚኖሩበትን አካባቢ ወይም አገር ለቀው ድንበር አቋርጠው ወደ ሌሎች አካበቢዎች ወይም አገራት በመሄድ መኖር ሲጀምሩ ተሰደዱ ይባላል፡፡  ስደት በሁሉም የዓለማችን ክፍል የሚታይ ይሁን እንጂ በታዳጊ ሀገሮች በተለይ ደግሞ በአፍሪካ  ችግሩ ገዝፎ ይታያል። 

ሰዎች በህጋዊም ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ከሚያደርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ጦርነት፣ ድህነት ወይም ርሀብ፣ የስራ ዕድል አለመኖር፣ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ፣ የዴሞክራሲ ዕጦት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት (የትራንስፖርቴሽን መስፋፋት)፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የሰዎች ፍላጎት ማደግ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የአገራችን አብዛኛዎቹ ስደተኞች መዳረሻ አውሮፓና እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ሲሆን የስደተኞች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው  230 ሚሊዮን ስደተኞች በመላው ዓለም እንደሚገኙ ይገልፃል፡፡ ከእነዚህም መካከል 59 በመቶው የሚሆኑት ስደተኞች በአደጉት ሀገሮች የሚገኙ ሲሆን በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ቀሪውን 41 በመቶው በማስተናገድ ላይ እንደሚገኙ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

 

አገራችን ከሰሃራ መለስ ካሉ አገራት ከፍተኛውን የስደተኛ ቁጥር የምታስተናግድ አገር ለመሆን በቅታለች። በቅርቡ በተደረገ ጥናት አገራችን ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ኤርትራ ብቻ በርካታ መቶ ሺህ  የሚቆጠሩ  ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።  ይህን ያህል ቁጥር ያለውን ስደተኛ ማስተናገድ እንደኢትዮጵያ ካሉ  ውሱን ሃብት ያላቸው አገሮች ኢኮኖሚ  ላይ የሚፈጥረው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አውሮፓዎች ለስደተኞች በራቸውን ከርችመዋል። እንደኢትዮጵያ ያሉታዳጊ አገራት ደግሞ ካላቸው ሃብት ቀንሰው እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን  ስደተኛን እየተቀበሉ ነው።

 

ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን መቀበል ብቻ ሳይሆን ባላት አቅም ለስደተኞች ምቹ  የተባለች አገር ለመሆን በቅታለች። የኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን አካፍሎ የመብላት ልምድ ያለው ህዝብ  ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም የህብረተሰቡ ነጸብራቅ ነውና በስደት አገራችን ለገቡ የየትኛውም አገር ስደተኞች የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ ሊያስመሰግነው የሚገባ ተግባር ነው።  

የኢፌዴሪ መንግስት በአገራችን ለሚገኙ ስደተኞች የትምህት ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በርካታ ስደተኛ ወጣቶች በተሰጣቸው የትምህርት ዕድል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የመማር ዕድል አገኝተዋል። ከዚህ ባሻገር በርካታ ስደተኞች በአገራችን በስራ ተሰማርተው ኑሯቸውን በሰላም እየገፉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በዚህ ድርጊቷ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ምስጋ የተቸራት አገር ለመሆን በቅታለች። ይህ ለሁላችንም የሚያኮራ ተግባር ነው። 

በሌላ በኩል  በርካታ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች በተለያየ ምክንያት ወደተለያዩ አገራት በመሰደድ ላይ ይገኛሉ። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በአሁኑ ጊዜ  በአገራችን ክፍያው ቢያንስም ስራ አለ። የክፍያው እንደመካከለኛው ምስራቅ ወይም እንደምዕራባዊያኑ ላይሆን ይችላል እንጂ መስራት ለሚፈልግ ስራ ለማይንቅ ሰርቶ መብላት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥርል።

በአገር ሰርቶም መለወጥ እንደሚቻልም በርካቶች በተግባር አሳይተዋል። በማሳየትም ላይ ናቸው። በስደት ኑሮ ዕድለኛ ከተሆነ ገንዘብ ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ስደት ዴሞክራሲያዊ መብትን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ክብርን ይገፋል። በተለይ አንዳንድ አገሮች ለስደተኛ የሚሰጡት ክብርና ስደተኛን የሚይዙበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው። በመሆኑም በአገር ሰርቶ መኖር ከዚያም አልፎ መበልጸግ እየተቻለ ህይወትን፣ አካልንና ስብዕናን በሚጎዳ መልኩ መሰደድ ተገቢ አይደለም።

አንዳንድ ወጣቶች ህይወትና አካላችሁን ለህገወጥ ደላሎች ኪስ ማደለሚያነት አሳልፋችሁ እየሰጣችሁ መሆኑን ልትገነዘቡት ይገባል። ህገወጥ ደላሎች ከህብረተሰቡ የተሸሸጉ፣ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡሮች አይደሉም። ስለዚህ እነዚህን ሰውን የሚሸጡ  አካላት ለህግ አሳልፎ መስጠት ይገባል። የመንግስት መመሪያና ደንቦች ውጤታማ የሚሆኑት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲታጀቡ ብቻ ነው። አገራችን በሰላም ማስጠበቁም ሆነ በኢኮኖሚው ዕድገት ውጤታማ የሆነችው የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በጎላ የህብረተሰብ ተሳትፎ በመታጀባቸው ብቻ ነው። ህገወጥ ስደትንም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ማቆም ይቻላል። ወጣቶቻችንን በሌለ ተስፋ እያማለሉ ወደ ሞት እያመሩብን ያሉ በሰው ደም የሚነግዱ ደላሎችን ህብረተሰቡ ለህግ አሳልፎ  በመስጠት ለፈጸሙት በደል ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል።    

በአገራችን ህገመንግስት ዜጎች ወደፈለጉት አገር ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደፈለጉት አገር መሄድና መስራት እየቻሉ  ለህገወጥ ደላሎች  ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ህይወታቸውንና አካላቸውን ለአደጋ ማጋለጣቸው  አግባብነት የጎደለው ነገሮችን ሰከን ብሎ ካለማሰብ ነው። ህገወጥ ደላሎች የሌለ አለም እየፈጠሩ የሚነግሩንን ተረት መፈተሽ ይገባል።  

በህጋዊ መንገድ ሰርቶ መለወጥ እየተቻለ በአቋራጭ ለመክበር የሚደረግ ሙከራ የጤነኝነት አይደለም። በህገወጥ ደላሎች የፈጠራ ወሬ ተደናብረው ስደትን የተከተሉ በርካታ እህትና ወንድሞቻችን በየበረሃውና በየባህሩ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ጠፍቷል፤ አካላቸው ጎድሏል። ይህ አገራችንም ገጽታም የሚበጅ አይደለም። በመሆኑም ወጣቶች ውሳኔቸውን መልሰው መላልሰው ማሰብ ይኖርባቸዋል። ከፍተኛ ገንዘብ ለህገወጥ ደላሎች  በመክፈል ለአደጋ ከመጋለጥ ይልቅ ያንን ገንዘብ በአገር ውስጥ መነሻ በማድረግ መስራትና መለወጥ ይቻላል። በአሁኑ ሰዓት አገራችን ማንም በአነስተኛ ገንዘብ መነሻ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በሌላ በኩል ወጣቶች መረዳት ያለባቸው ጉዳይ አገራችንን ተባብረን ማሳደግ የሁላችንም ሃላፊነት መሆን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ዛሬ የምንሰደድባቸው አገሮች እኩ በዜጎቻቸው ጥረት እንደተለወጡ ሁሉ እኛም ተባብረን አገራችንን መለወጥና ማገልጸግ እንችላለን። አሁን ላይ አገራችን በፍጥነት በመለወጥ ላይ ትገኛለች። ይህን ዕድገት ማስቀጠል ከቻልን በጥቂት አመታት እኛም አገራችንን ወደከፍታ እናወጣታለን።  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን እንኳን ለዜጎቿ ለጎረቤት አገር ዜጎች ጭምር  ምቹ ሁኔዎችን በመፍጠር ላይ ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ  በአብዛኛው ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተሰደዱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች። አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር  ላይ ነች። ይህም ድርጊቷ በተባባሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጭምር ሙገሳን ተችሯታል።

በቅርቡ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የሁሉንም አገር ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላችው ስደተኞችን ወደየ ሀገራቸው ለመመለስ  የ90 ቀን የማስጠንቀቂያ ቀን መስጠቱ ይታወሳል። የኢፌዴሪ መንግስት ከመመለከታቸው የሳዑዲ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በመነጋገገር ዜጎች ያለእንግልት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በጥረት ላይ የገኛል። በ2014 ሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች ከአገሯ ስታስወጣ ወደትውልድ አገራቸው የተመለሱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መንግስት ባመቻቸላቸው ሁኔታ በጥቃቅንና አነስተኛ  ተደራጅተው  በርካቶቹ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ አሁንም መንግስት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ዜጎቹ እንግልት እንዳይደርስባቸው ከሚመለከታቸው አካላቶች ጋር በመነጋገገር ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ ህገ-ወጥ ስደት ሰብአዊ መብትን የሚረግጥና የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመሆኑ የችግሩ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነውን የህገ-ወጥ ደላሎችን ምሽግ ለማፈራረስ መንግስትና ህዝብ በቅርበት መስራት ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከቤተሰብ  ልጆቻቸውን መምከር አለባቸው። መንግስትም  ወጣቶች በአካባቢያቸው የስራ ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ጥረቱን ማጠናከር ይኖርበታል።