ስደት ይገታ

በአለማችን የስደት ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ጦርነት፣ ግጭት፣ በፖለቲካ ሀሳብ ባለመስማማት የሚደረግ ስደት፣ የኢኮኖሚ ሰደት . . . እያሉ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በየትኛውም መልክ ቢሆን ስደት ከሀገርና ከቤተሰብ ርቆ ወደማያውቁት ሀገር በባህል፣ በስነልቡና፣ በቋንቋም ጭምር ፍጹም እንግዳ ወደሚሆኑበት ምድር በተገኘው ሕገወጥ መንገድ የራስን ሕይወት ለሚከተለውና ለሚመጣው አደጋ ሁሉ ተጋላጭ አድርጎ ከሀገር መውጣትን ያመለክታል፡፡ ስደት አስከፊ በፈተና፣ መከራና ስቃይ የተሞላ ሕይወትም ነው፡፡

 

በእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት በአለማችን የሚኖሩ የበርካታ ሀገራት ዜጎች ወደማያውቁት ሀገር ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ተሰደዋል፡፡ የከፋ እልቂትና ውድመት የሚካሄድባቸው ሶርያ፣ ሊቢያ፣ የመንና የመሳሰሉት በጦርነት አውድማነታቸውና በእልቂት  በአለም እውቅና ያገኙ ሀገራት ዜጎችን ስደት ለማስተናገድ አለም የሚቻለውን ሁሉ አድርጎአል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ ሀገራት ለተከሰተው ሕዝባዊ ነውጥና የዜጎቻቸው መከፋት አንዱና መሰረታዊ ምክንያት እስከመሆን የደረሰው በስደተኞች ተጥለቀለቅን፤ ባሕላችንና ማንነታችን ተዋጠ፤ ስደተኞችን አንቀበልም፤ ወደመጡበት ይመለሱ የሚሉ አወዛጋቢና አከራካሪ ጉዳዮች ናቸው፡፡

 

በእርግጥም አውሮፓ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ በስደተኞች ተጨናንቃለች፡፡ በአሜሪካን ብቻ ሕጋዊነት የሌላቸው ከ12ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ይገኛሉ፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን አሳሳቢ የአለም አደጋ ሁኖ ከተደቀነው አክራሪነት ጋር በተያያዘ  በገፍ ወደአውሮፓ የሚፈልሱትን ስደተኞች አምኖ ለመቀበል ሀገራት ታላቅ ስጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡

 

ከጦርነት ጋር በተያያዘ ሕይወትን ለማትረፍ የሚደረገው ስደት በብዙ መልኩ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም ከዚህ ውጭ ለቀው በሚሰደዱና ሕገወጥ በሆነ ሁኔታ ለስራና የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ሀገራቸውን ለቀው የሌላ ሀገር ድንበር አቋርጠው በሚገቡና በሚያዙ ስደተኞች ላይ የሚፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊትና አያያዝ የሰውን መሰረታዊ ክብር የሚነካና በውርደት የተሞላ ነው፡፡

 

ስለዚህም ሰላምና መረጋጋት ባለባቸው ሀገራት በሕገወጥ መንገድ የተሰደዱ ስደተኞችን ወደየሀገራቸው ለመመለስ የአውሮፓ ሀገራት በየራሳቸው መንገድ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ይሄንን ሀሳብ የሚደግፉ የሚቃወሙም የየሀገራቱ ዜጎች አሉ፡፡ ጉዳዩን አብዛኞቹ ሀገራት ከብሔራዊ የደህንነት ስጋት ጋር ያያይዙታል፡፡ በተለይም እየተስፋፋ ከመጣው አክራሪነትና አሸባሪነት ጋር፡፡

 

በሀገራችን ብዙ ዜጎቻችን ስራና የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በሚል በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ድለላ በባዶ ተስፋ እየተሞሉ ወደማያውቁት ሀገር እንዲሰደዱ፤ ከባድ መከራና ፈተና ውስጥ እንዲወድቁ፤ የሕይወት መስዋእትነትም እንዲከፍሉ ተደርገዋል፡፡ ከቤታቸው እንደወጡ፣ የት እንደደረሱ እንኳን የማይታወቁትን፣ ቤተሰብ በይመለሳሉ ባዶ ተስፋ የሚጠብቃቸውን፣ በባህር ላይ የቀሩትንና በአውሬ የተበሉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡

 

የዚህ ሁሉ መነሻው እንደባሪያ ፍንገላ ዘመን በሰው ሕገወጥ ንግድና ደላላነት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በስፋት መኖርና ኑሮአቸውን በዚሁ ላይ መተዳደሪያ አድርገው መመስረታቸው ነው፡፡ መንግስት ከሕብረተሰቡ በሚደርሰው መረጃና ጥቆማ መሰረት በዚህ ጸያፍ ተግባር  ተሰማርተው የነበሩ በርካታ ግለሰቦችን በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጎአል፡፡ ችግሩን የበለጠ ለመቅረፍም በነዚህ ግለሰቦች ድለላና ማታለል ከፍተኛ ገንዘብ እየተቀበሉ ወጣቶችን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩ ሕገወጥ ሰዎችን በስፋት ማጋለጥና አደጋውን መከላከል ቅድሚያ ትኩረት ይሻል፡፡

 

ከኢትዮጵያ በተለያየ ሕገወጥ መንገድ በመውጣት ወደ የመን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን በመውጣት ወደተለያዩ የአፍሪካና የአረብ ሀገራት በስደት የፈለሱት እልፍ ናቸው፡፡  የመስጠም አደጋን ማለፍ ከቻሉ ባሕርና ውቅያኖስ አቋርጠው ወደ አውሮፓ የተሻገሩ ለመሻገር ሲሉም ሰምጠው የሞቱ ወጣት ዜጎቻችን ቁጥር ስፍር የለውም፡፡ እነዚህ ወጣቶች በሀገራቸው ላይ የተገኘውን ስራ በመስራት መኖር መለወጥ ማደግ ይችሉ የነበሩ ናቸው፡፡

 

ምንም ሆነ ምን ስደት አይበረታታም፡፡ የኢኮኖሚ ስደተኝነት ሰርቶ አግኝቶ ሕይወትን ከመለወጥ ጋር የተያያዘ ሲሆን ከሀገር በሕገወጥ መንገድ ለመውጣት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ብሮችን ለደላሎቹ መክፍል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ገንዘቡ የሚገኘው ቤተሰብ ተጨንቆ በሌለው አቅሙ ተበድሮ በወለድ በሚታሰብ ከአራጣ አበዳሪዎች ከሚያገኘው ገንዘብ ነው፡፡

 

በአረቡአለም ለስራና እንጀራ ፍለጋ በሄዱ እህቶቻችን ላይ ሲሰራ የኖረውንና የተፈጸመውን ግፍና በደል አይተናል፡፡ ስንቶች በአሰሪዎቻቸው ከፎቅ ተወርውረው እንደሞቱ ዛሬም ስንትና ስንት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተለያዩ ሀገራት ውስጥ በእስር ቤቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

ዛሬ ሀገራችን ስራን አክብረው ለሚሰሩና ማደግ ለሚፈልጉ ወጣቶች ከትላንት የተሻለ የተለያዩ የስራ እድሎች ያሉባት ሀገር ናት፡፡ የሕዝባችን ቁጥር ከሚጠበቀው በላይ መጨመሩ በሀገራዊ ኢኮኖሚውና በስራ እድሎች እንዲሁም በኑሮው ላይ የሚያሳድረው ጫና እንዳለ ሆኖም መንግስት ከሀገሪቱ ዜጎች 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት መሆኑን በተደጋጋሚ ይፋ በማድረግ የስራ እድልን ለወጣቱ በማስፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በሰፊው እየሰራ ይገኛል፡፡

 

ይህን ግዙፍ መስራትና መለወጥ የሚችል የወጣት ኃይል አቅሙና ዝንባሌው በሚፈቅደው የስራ መስክ ለማሰማራት መንግስት 10 ቢሊዮን ብር መድቦ በሁሉም ክልሎች ለወጣቱ አዳዲስ የስራእድሎች እንዲከፈቱ አድርጎአል፡፡ ለዚሁ ማስፈፀሚያም ክልሎች የተመደበላቸውን በጀት ወስደው ወደስራ ገብተዋል፡፡ ይህ እድል ወጣቱን የራሱ የስራ ባለቤት የሚያደርገው ከመሆኑም በላይ ስኬታማ በመሆን ሌላ የስራ እድል ለዜጎች እንዲፈጥር የሚያስቸለው ነው፡፡ ወጣቱም ራሱንና ቤተሰቡን መለወጥና ማሳደግ የሚችልበት እድል ተፈጥሯል፡፡

 

ወጣቱ ራሱን አላስፈላጊ ለሆነ አደጋ አጋልጦ ለስደት በመውጣት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ሊረዳው ይገባል፡፡ በሕገወጥ ስደት ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ሀገር ዘለቄታዊ ጥቅም አያገኙም፡፡ በሀገር  እየኖሩ እየሰሩ ለሀገር ልማትና እድገት የበኩልን ድርሻ እየተወጡ የራስን ስራ በመክፈት፣ በማስፋትና በማሳደግ መለወጥና ማደግ ይቻላል፡፡ በስደት ቢወጡም ብዙዎች በተሳሳተ ግንዛቤ እንደሚያስቡት አልጋ በአልጋ የሆነ ሕይወትና ኑሮ የለም፡፡ አለም አቀፍ ሕግ ከሚፈቅደው የስራ ሰአት ውጪ አንድ ሰው በቀን ሊሰራው ከሚገባው ሰአት በላይ በባርነት ለቀጣሪዎች መስራት፤ እረፍትና እንቅልፍ በማጣት ሰውነትና ጉልበትን መገበር፤ ክብር ማጣትና መዋረድ፤ ምንም አይነት ነጻነት  እንደሌለው ሰው ጌቶቹ ያሻቸውን እንደሚያደርጉት የድሮ ዘመን ባሪያ መቆጠር ያህል ነው ስደት። ለሀገርም ለህዝብም ውርደት ነው፡፡

 

በስደት የሄደና ነጻነት የሌለው ሰው ሰብአዊ መብቱን የተገፈፈና በአሰሪዎቹ በጎ ፈቃድና ቸርነት የሚኖር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በነጻነት የኖርን፣ ባርነትንና ቅኝ ተገዢነትን የማናውቅ፣ ለነጻነታችን ባለን ቀናኢነት ለሌሎችም የጥቁር አለም ሕዝቦች በነጻነት ተምሳሌትነት የምንጠቀስ ሀገር ልጆች የመሆናችንን ታላቅ ክብር በዚህ ዘመን ያዋረደ፤ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባ ድርጊት ነው፡፡

 

ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ ስደት እከሌ የሚባል ሀገር ገብተው ተያዙ . . . ድንበር ሊያቋርጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ …. ፍርድቤት ቀረቡ … ተገደሉ . . . ባሕር ውስጥ ሰምጠው ሞተው ተገኙ . . . በአሸባሪዎች ታረዱ . . . ወዘተ በየወቅቱ የምንሰማቸው፤ ሕሊናን የሚያደሙ፤ እንደዜጋም ቁጭት ውስጥ የሚከቱ፤ ከልብ የሚያሳዝኑ መሪር ዜናዎች ናቸው፡፡

 

ከዚህ ሁሉ ሩቅ ሀገር ናፍቆትና ስደት ይልቅ በአለ አቅም በሀገርና በወገን መሀል ሁኖ በመስራት መለወጥና ማደግ ይቻላል፡፡ ስራን ሳይንቁ በመስራት ሕይወትን መለወጥ የሚያስችሉ ሰፊ እድሎች አሉ፡፡ ስደት ተሂዶም እኮ ማንኛውንም አይነት የተገኘ ስራ ነው የሚሰሩት፡፡ ይሄንን የስራ ፍቅር በሀገራቸው መሬት ላይ ቢያደርጉት ብዙ አደጋዎችን መቀነስም በተቻለ ነበር፡፡

 

የቀደሙት አባቶቻችንና አያቶቻችን የትኛውንም ያህል ድሕነት ቢኖር በሀገራቸው ክብርና በነጻነታቸው የማይደራደሩ፤ ክብራቸውንም አሳልፈው የማይሰጡ ነበሩ፡፡ ይህ በአለም ታሪክ ውስጥ የተመዘገበ ነው፡፡ ዛሬ ስደት እንደክብር የሚቆጠርበት፤ ሰው ሀገር ሄዶ መውለድና ዜግነት ማግኘት እንደ ታላቅ አዋቂነትና የባለጸጋነት መገለጫ ተደርጎ በብዙ ዜጎቻችን የሚቆጠርበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ የዚህ ሁሉ መንስኤው ሀገራችን ድሐ ናት፤ እኛም ድሀ ነን የሚል ከድህነት አስተሳሰብ የመነጨ ውጤት ነው፡፡

የየትኛውም የአለማችን ሀገራት ሕዝቦች ድህነትን ያሸነፉት በሀገራቸው ላይ ሁነው ጠንክረው በትጋት በመስራትና በማደግ ነው፡፡ ሀገርን ለቆ በመሰደድ ለሰው ሀገር ጉልበትና እውቀትን በመሸጥ በባርነት በማገልገል አይደለም፡፡ ይህ አይነቱ ደካማ አስተሳሰብ በተለይ ሀገራችን ለፍታና ደክማ በሌለ አቅምዋ ያስተማረቻቸው፤ ግን ደግሞ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ለባእድ ሀገር በመሸጥ በፈረደበት ማሳበቢያ የፖለቲካ ስደት ስም በተለያየ ሀገራት በመስራት ከብረው ተንደላቀው የሚኖሩ ምሁራንንም ይመለከታል፡፡

 

ሀገሬ ወገኔ ብለው የሚያስቡ ብዙዎች የመኖራቸውን ያህል ስለሀገራቸው ለማሰብ ለመርዳት ስሜቱና ፍላጎቱ የሌላቸው ምሁራን ከቀድሞ መንግስታት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሰፊው በስደቱ አለም ውስጥ ተንሰራፍተው ሲኖሩ አይተናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ያስተማራቸውን ወገናቸውንና ለታላቅነት ያበቃቻቸውን ሀገራቸውን ለማስታወስ አለመብቃታቸው ደግሞ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ የዛኑም ያህል በስደትም ሁነው ለሀገራቸውና ለቤተሰባቸው ብዙ የሚያደርጉ ልባቸው ሀገራቸው ላይ የሆነ እልፍ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መኖራቸውን ስናስታውስ  ተሰፋችን ዳግም ይለመልማል፡፡

 

አሜሪካንን አሜሪካ ያሰኙዋት ሌሎቹንም ታላላቅ ሀገራት የገነቡትና ያሳደጉት፤ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃም እንዲደርሱ ያደረጋቸው የስደተኞች እውቀትና ጉልበት ነው፡፡ አሜሪካ ራስዋ ስደተኞች የመሰረቱዋት ሀገር ነች፡፡ እነዚህ ስደተኞች ያንን ልፋትና ድካም እውቀት ለሀገራቸው ቢያውሉት ኖሮ ዛሬ ድሀ የሚባሉ ሀገሮቻቸው ወደ ታላቅ የእድገት ምእራፍ ባመሩና በገሰገሱም ነበር፡፡