ታሪካዊው የአባይ ወንዝ አነጋጋሪ፣ አከራካሪ፣ አነታራኪና አወዛጋቢ ሁኖ የኖረ፤ አሁንም በዚሁ የቀጠለ የተፈጥሮ ወንዝ ነው፡፡ ግብጾች አባይን “አባታችን” ከማለትም አልፈው እንደአምላክ ያመልኩታል፡፡ ስለአባይ ለብዙ ሺህ ዘመናት በግብጾች አእምሮ ውስጥ የተቀረጸው የተዛባ አስተሳሰብ ነው አሁንም ፈተና የሆነባቸው፡፡ በግዜ ሂደትና በዘመናት ፍርርቅ እውነት ብለው ራሳቸውን ያሳመኑት በሚገርም ሁኔታ “አባይ የእኛና የእኛ ብቻ ነው” በሚለው ነው፡፡ ይሄ ቅዠትም እብደትም መሆኑ ነው፡፡ አባቱ አባይ . . . እናቱ ጣና . . . የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና!! የሚለው የድምፃዊው ስንኝ ለአባይ የኢትዮጵያዊ ማንነቱ ማረጋገጫ ነው፡
ግብፆች፣ መሪዎቹ ማለት ነው፤ ሲያሻቸው ልዩ ታሪካዊ መብት አለን ብለው ደፍረው በአደባባይ ይናገራሉ፤ በል ሲላቸው ደግሞ እስኪ ንክች . . . በማለት ሊያስፈራሩን ይሞክራሉ። ከየት የመጣ ታሪካዊ መብት፤ ማን ሰጣችሁ? ሲባሉ የፈረደበትን የቅኝ ግዛት ውል፣ እንግሊዝ ኢትዮጵያ በሌለችበት ለግብጽና ለሱዳን ያከፋፈለችውን የውኃ መጠንና ድርሻ ይጠቅሳሉ፡፡ እኛ በቅኝ ግዛት ሕግ፣ በቅኝ ገዢዎችም ስር ተገዝተን ተዳድረን አናውቅም፡፡ በባርነትና በገባርነት ስር ያልኖርን ነጻ ሀገርና ነጻ ሕዝቦች ነን፡፡ ይሄ ይጠፋቸዋል ብለን ደግሞ አናምንም፡፡
ግበጾች የሚጽፉት በቅጥፈትና በውሸት የተሞላ ታሪክ ነው፡፡ ታሪካዊ ትንተና የሚሉትን ያቀርባሉ፡፡ ኢትዮጵያ የአባይ፣ የሶባት፣ የአትባራ፣ የተከዜና ሌሎችም በርካታ ወንዞች መፍለቂያ ማሕጸን መሆንዋን አያውቁም እንዳይባል አሳምረው ያውቃሉ፡፡ 85 በመቶ የአባይ ውኃ ምንጭና ባለቤት ኢትዮጵያ ጭምር፡፡
እነሱ ለዘመናት አባይ እያጋዘ ከሚወስደው ጥቁር አፈራችን ለምነትና ከውሀችንም ሲጠቀሙ ኖረዋል፤ በልፅገውበታልም፡፡ ታላላቅ እርሻዎችን ከፍተውበታል፡፡ አስዋን ግድብን፣ ናስር ሀይቅን የመሳሰሉ ሰርተዋል፡፡ በአባይ ውሀ ትሩፋትና በመስኖ ልማት የአሳ እርባታ፣ የአትክልት እርሻ፣ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ሁሉ ሰርተው ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ አውሮፓ ድረስ እያሻገሩ የሚነግዱት ምርጥ ብርቱካንና ሙዝ የአባይን ውሀ ጠግቦ እየጠጣ ያደገ ነው፡፡ ለሙ አፈርም ከእኛው የሄደ ነው፡፡ ባጭሩ የግብጽ በረሀ ንዳዱ የሚተነፍሰው በአባይ ሲሆን የህይወታቸው የመኖር ሚስጢርም አባይ ውሀ ነው፡፡
አባይን ግብጾች አባታችን እናታችን አምላካችን ቢሉት ምንም ስህተት የለበትም፡፡ አባትም ሆነ እናት ከዚህ በላይ የሚያደርጉት የለምና፡፡ ጥንትም ዛሬም የእኛው አባይ ውሀ ማርና ወተት ሁኖ የእስከዛሬ ግብጻውያን ትውልዶችን መግቦ ያኖረ ነው፡፡ አሁን የእኛ የኢትዮጵያውያን ጥያቄ እኛስ? የሚል ነው። እኛስ? ማነው ማደግ መበልፀግ አይወድላችሁም ያለን??
እርግጥ ነው፣ ለብዙ ሺህ ዘመናት የሞቀ፣ ቅስቅስ የማይል እንቅልፍ ተኝተን፣ ደብቶን ስናንኮራፋ ኖረናል፡፡ ታላቅ አዚም ውስጥ ተደፍቀን መላወስ አቅቶን በእርስ በእርስ ሽኩቻ መናቆር፣ መባላት፣ መጣረስ ውስጥ ገብተን የጅል ጨዋታ እንድንጫወት እያደረጉ እነሱ ከኋላ ሆነው ጃስ እያሉ ሲያናክሱን ሲያፋጁን ሲያጫርሱን ኖሩ፡፡ ኢትዮጵያ ደካማ አቅም የሌላት ተረጂና ተመጽዋች እንድትሆን፣ ጉልበት አግኝታ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሰራ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ ኖሩ፡፡
ከእያንዳንዱ ጸረ ኢትዮጵያ ሴራ ጀርባ ከድሮ እስከ ዘንድሮ ግብጽ የምትባል ሀገር ነበረች፡፡ ዛሬም አለች፡፡ እንግዲያው ድንበርተኛ አይደለን፣ ወሰን አልተላለፍን፣ መሬት አልተወሳሰድን፤ ከሩቅ መጥታ ደርሶ ጠላት የሆነችን በዚሁ በአባይ ወንዝ የተነሳ ነው፡፡ በኤርትራ ውስጥ ጀብሀ የሚባል እስላማዊ ፓርቲ እንዲመሰረት ያደረገችው ግብጽ ነበረች፡፡
ኤርትራ አረባዊት ናት ያለች ግብጽ፤ የመገንጠል ጥያቄ እንዲያነሱ መልምላ ሀገርዋ ወስዳ ያስተማረች፣ ያሰለጠነች፣ ያስታጠቀች፣ ያሰማራች ግብጽ፤ ስትወጋን የኖረችው ግብጽ፤ የሶማሊያው መሪ የነበረው ጀነራል ዚያድ ባሬ አስከ አፍጢሙ ዘመናዊ መሳሪያ እስከ ጦር ጀት ድረስ ሰራዊቱን አስታጥቆ የኢትዮጵያን ድንበር 700 ኪሎ ሜትር ድረስ ሰብሮ እንዲገባ የጦር እቅድና ፕላን አውጪዋ ግብጽና ጀነራሎችዋ፤ በምስራቅ ኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ የነበረውን እስላሚያ ኦሮሚያ የጃራ ቡድን ትረዳ ነበረችው ግብጽ ነበረች፡፡ ለዚህ ሁሉ የከፋ ጠላትነት መነሻው የአባይ ወንዝ ውሀ ነው፡፡
ኦጋዴንን ለመገንጠል የሚንቀሳቀሰው ኦብነግ የሚረዳው በግብጽ፤የሶማሌው እስላማዊ ምክርቤት በኮሎኔል ዳሂር አዌይስ ይመራ የነበረውና በኃላ ወደ አልሻባብነት የተቀየረውን ኃይል ሙሉ በሙሉ ትረዳ የነበረችው ግብጽ፤ኦነግን ካይሮ አስቀምጣ ለስልጣን አበቃሀለሁ ያለችው ግብጽ፤ዘንድሮ በእሬቻ በአል ላይ የተከሰተው ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የዜጎች ሞትና እልቂት እንዲፈጠር ከጀርባ ሁና ወኪሎች መልምላ በማሰመራት የመራችው ግብጽ ነች፡፡
በባድመ ጦርነት ከሻእቢያ ጀርባ ሁና የወጋችን ግብጽ፤ በደቡብ ሱዳን በኩል አድርጋ ሰላዮችና ታጣቂዎች በማሰማራት ወደ ሕዳሴው ግድብ ለመላክና ጥፋት ለማድረስ የተንቀሳቀሰችው ግብጽ ናት፡፡ ብዙ ብዙ ተነግረውና ተዘርዝረው የማያልቁ ጸረ-ኢትዮጵያ ሴራዎችን ጥንትም የሰራች፣ ዛሬም በመስራት ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ አልፋ ሄዳ ግብጽን የነካችበት አንድም የተመዘገበ ታሪክ የለም፡፡
ዛሬም በሶማሊያ፣ በየመን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በጅቡቲ ቋሚ የጦር ካምፕ ለመመስረት ጥያቄ ያቀረበች፤ በዚህም ኢትዮጵያን በአራቱም ማእዘናት እከባለሁ፣ አምሳለሁ፣ ሲያስፈልግም በተለያየ አቅጣጫ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብላ ስትራቴጂካዊ እቅድ አውጥታ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘው ሀገር ግብጽ ነች፡፡ ይሄንን የግብጾች ሴራና ተንኮል የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ብቻ ሳየሆን ድፍን አለም ያውቀዋል፡፡ ዛሬም ከዚሁ ከጥንት ጀምሮ አብሮአቸው ከኖረውና ከዘለቀው ኢትዮጵያን ለማጥፋት፣ ለመከፋፈልና ለመበታተን ከሚጠነስሱት ሴራቸው አልታቀቡም፡፡ ከዚህ ባሻገር የዲፕሎማሲ ዘመቻም በስፋት ሲያካሂዱብን መቆየታቸው ከዚሁ ጋረ አበሮ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ነው። ይህን ሁሉ ያድርጉ እንጂ፣ ግዜውም አለምም አልተቀበላቸውም፡፡ አይናቸው እያየ ሴራቸው እንደጉም በኖ ሲጠፋ፤ ሲከሽፍ ተመልክተዋል፡፡
የራሳቸው የግብጾች አንድ የጥንት አባባል አለ፡፡ “አባይን የተቆጣጠረ ግብጽን ተቆጣጠረ” የሚል፡፡ ፍርሀታቸውም፣ ስጋታቸውም ከዚሁ የመነጨ ነው፡፡ እንግዲህ እንዴት ይደረግ? አባይን የምንቆጣጠረው እኛ ባለቤቶቹ እንጂ መቸም በሰው ሀገርና መሬት ገብተው አባይን እንቆጣጠር ሊሉ አይችሉም፡፡ ደሞስ በጋራ እንጠቀም ተባለ እንጂ መቆጣጠርን ምን አመጣው??
ግብጾች ኢትዮጵያ ይህን ታላቅና ግዙፍ ግድብ የገነባቸው በአካባቢው ያለውን የፖለቲካ የኃይል ሚዛን ለመቆጣጠርና ልእለ ኃያልነትዋን ዳግም ለማረጋገጥ ነው፤ ብዙ ወንዞች እያሉዋት የአባይን ውሀ በብዛት ማከማቸትዋ ግብጽን ለመቆጣጠር ነው ብለዋል፡፡ ግድብ የተሰራበት ቦታ እጅግ አደገኛ ስለሆነ ግድቡ ቢፈርስ ውሀው ሱዳንንና ግብጽን ከነስልጣኔያችን አጥለቅልቆ ያጠፋዋል፡፡ ከተሞቻችንም፣ የተገነቡ ግድቦቻችንም አይተርፉም በማለትም በጋዜጣቸው፣ በአል አህራም ላይ ጽፈዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሀ እስኪሞላ ድረስ ግብጽ ውሀ አታገኝም የሚል ውሃ የማይቋጥር መከራከሪያም ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ አባይ ወንዝ ተፈጥሮ በጋራ እንድንጠቀምበት የሰጠችን ስለሆነ ለሁላችንም ይበቃል፤ የውሀ ድርሻችሁ አይቀንስም ብላ በተደጋጋሚ ብትናገርም እነሱ ሊሰሙ አልቻሉም፡፡
እኛ በድርቅ፣ በረሀብ፣ በቸነፈር ስንመታ የአባይን ልጅ ውሀ ጠማው ታሪክ እውነት ሆኖ ዜጎቻችን በድርቁ መንስኤነት ውሀ እያጡ ሲያልቁ ግብጽ በአባይ ውሀ ሰፋፊ መስኖ እያለማች ግድቦች እየሰራች አንድም ድርቅና ረሀብ የሚባል ነገር በታሪክዋ አይታ ሳታውቅ ኖራለች፡፡ እንደውም ድሆችና ረሀብተኞች ተረጂዎች ናቸው በማለት ሲሳለቁብን ነበር፡፡
ግብጾች በአባይ ጉዳይ አለም አቀፍ ተሰሚነትንና ተቀባይነትን ለማግኘት ሁሉንም አይነት ሚዲያ ይጠቀማሉ፡፡ ምሁራኖቻቻው የሚጽፉትን ሁሉ በፊስቡክ፤ በሁዋትስ አፕ፤ በትዊተር፤ በያሁ፤ በጎግል በሁሉም ዘዴና መንገድ ለአለም እንዲደርስ አድርገው ያሰራጫሉ፡፡ የእኛስ ምሁራን በአብዛኛው ተገቢውን የዜግነት ድርሻና ኃላፊነት ተወጥተዋል ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ሊወጡ ይገባቸዋል፡፡
መንግስት ይመጣል መንግስት ይሄዳል፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው፡፡ ሀገርና ትውልድ በየፈረቃው እየተቀባበሉ ይቀጥላሉ፡፡ በአንድ የታሪክ ወቅት በስልጣን ላይ ያለን መንግስት መቃወምና መደገፍ መብት ነው፡፡ ሀገርን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ግን መቃወም ከቶውንም አይሞከርም፡፡ አባቱ አባይ . . . እናቱ ጣና . . . የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና!! እንደገና አዲስ ታሪክ ይሰራል!!