እንደትላንቱ ሁሉ ነገም የሰላሙ ባለቤት ህብረተሰቡ ነው

 

 

ከዛሬ 25 ዓመታት አስቀድሞ ለሃገራችን ሰላምና መረጋገት እንቅፋት የነበረው በዋናነት የደርግ የአፈና መዋቅር መሆኑ ይታወሳል። በተለይም ከአፈና መዋቅሩ ጋር አብሮ የተበተነው በርካታ የጦር መሣሪያ ዝውውርና ዘረፋ፣ ያልተረጋጋ ኢኮኖሚና ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የህዝቡ ኑሮ ለአገራዊ ሰላምና መረጋጋት እጅግ ፈታኝ የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ ይታወሳል፡፡

ከሃገራዊ ሰላምና መረጋጋት አንጻር ይህንኑ ፈታኝ ዘመንና የአፈና መዋቅር ታሳቢ ያደረገው የሽግግር መንግስት ስራውን የጀመረው በአገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ የተለያየ አመለካከትና አስተሳሰብ ያላቸው ወገኖች (በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚል ሁሉ) ሃሳቡንና አማራጭ አመለካከቱን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲያሰበስብ የሚያደርግ ቻርተር በማርቀቅ፣ ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ በማድረግ ነው።

በዚህ ጊዜ ታዲያ የሽግግር መንግስቱ ሠራዊት በቻርተሩ የተቀመጠውን የሽግግር መንግስት ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በአግባቡ መጠበቅ ሲቀጥል የኦነግ ሠራዊት ግን ቻርተሩን በመጣስና የኢትዮጵያን ህዝብ በመክዳት እጅግ ጭካኔ በተሞላበትና በሚዘገንን ግድያና ጭፍጨፋ ሲሰማራ የሽግግር ዘመኑን ሰላምና ደህንነት ፈታኝ አድርጎት የነበረ መሆኑም ይታወሳል፡፡ አሁንም በየምክንያቱ እና ኮሽታ ባለበት የማይጠፉት የጠባብና የትምክህት ሃይሎችም በበርካታ የአገራችን አካባቢዎች ተፈልፍለው የሽግግር መንግስቱ የሰላምና መረጋጋት ተልዕኮ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሃይሎች በተለይ አገር በቀል ከሆኑና ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች ጋር በማበር የህዝቡን በሠላም የመኖር ዋስትና በተደጋጋሚ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ከፍተኛ ሙከራ አድርገዋል፤ አሁንም አልተቆጠቡም፡፡

እነዚህን ፈተናዎች በማለፍ ዓይነተኛ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ለማድረግ የሽግግር መንግስቱ በዋናነት የሰላም ምንጭም ባለቤትም ህዝቡ እንዲሆን የሚያደርግ የማይነቃነቅ ስርአት ዘርግቷል። ይህም ህብረተሰቡ በየአካባቢው የራሱን ሰላም የሚጠብቅበት ሁኔታና አደረጃጀት /ሠላምና መረጋጋት/ ፈጥሮ በመንቀሳቀሱ በየጊዜው ዓይነተኛ ሰላም እንዲመጣና መረጋጋት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

ይህንኑ መነሻ ያደረገው ስርአት በጊዜ ሂደት ውስጥ ስር የያዘ ሲሆን የህዝቡን የሰላም ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ሥራ በተለይ እና በተከታታይነት ከህዝቡ ጋር በመሰራቱለሰላምና ደህንነት ጠንቅ የሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎች ዛሬ ላይ በአስተማማኝ መልኩ እንዲቀየሩ አስችሏል ፡፡

የሃገሪቱ የውጭ ግንኙነት ሥራዎችም በዋናነት በሰላም አብሮ በመኖርና የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገና ዋንኛ ትኩረቱንም የውስጥ ተጋላጭነታችንን እንዴት መቀየር እንችላለን የሚሉ ጉዳዮችን ላይ መሆኑ በአገር ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአስተማማኝ መልኩ የተረጋገጠው ሰላምና መረጋጋት ከጐሮቤት አገሮችም ተመሳሳይ ለውጥና ስኬት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡

ያም ሆኖ ግን፣ ትምክህትና ጥበት አሁንም የሰላማችን ጠንቅ እየሆኑ በተደጋጋሚ  መከሰታቸውን ቀጥለዋል። የትምክህት ሃይሉ ሲመቸው እየተሰባሰበ፣ ሳይመቸው ደግሞ በብሄሩ ጥላ ስር ተከልሎ የተጠቃንና ተጎዳን አስተሳሰቡን በአግባቡ አሰናድቶ በማሰራጨት አማላይ ቃላትና ስስ የማህበረሰቡ ፍላጎቶችን በመነካካት የአገራችን ህዝቦች እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ ብሎም ወደመተላለቅ እንድሄዱ ያለማቋረጥ መስራቱን እንደቀጠለ ነው። ይህ ትምክህተኛ ሃይል ስለዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ሲነሳበት ሃሳቡን በሃሳብ ታግሎ ከማሸነፍ ይልቅ /ቀድሞም የተሸነፈ አስተሳሰብ በመያዙ ምክንያት/ ወንበር የመቁጠር፣ በተጨባጭ በአርሶ አደሩ ኑሮና ህይወት ውስጥ የመጣውን ለውጥ ከማየት ይልቅ አውራው እኔ ስለሆንኩ በልዩ ሁኔታ መስተናገድ አለብኝ የሚል ቅኝቱን አጥብቆ በመያዝ ይገለጣል።

የትምክህት አስተሳሰቡን ለማረመድ የሚያስችለውን ህበረተሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ ቅሬታዎችን፣ አመራሩ አካባቢ የሚፈጠሩ የአመራር ጉድለቶችንና የመንግስት  መዋቅር ውጤታማ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለቅሞ በመቀመር ለሁከትና ለአመፃ ይጠቀምባቸዋል። የረካ አርሶ አደር መፈጠሩን ተከትሎ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ቢቀበልም፣ በዚህ ስርአት ተወልደው ያደጉና ተምረው ስራ ያላገኙ የአርሶ አደሩን ልጆች በመያዝ ገና በማለዳው በህገ-መንግስቱ ላይ የተመለሰውን የማንነት ጥያቄ አወገርግሮ በማቅረብና በማዛባትም ይገለጣል።

በተለያየ ምክንያት ከአመራር የተወገዱ ሰዎችን በአስረጅነት በማቅረብ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን የአፈፃፀም ክፍተቶች ከኒዮ ሊብራሊዝም አስተምህሮ በመነሳት በወጣቶቹ ላይ ሰፋ ያለ የማነሳሳትና የመቀስቀስ ስራ በመስራት ቁጥሩ ቀላል ያልሆነን የወጣት ሃይል ለአመፃና ለሁከት ሲጠቀም ተስተውሏል። በዚህም ምክንያት በማህረሰቡ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲነግስ፣ ጥላቻ እንዲዘራ፣ በፀጥታ ሃይሎችና በህግ አስከባሪ አካላት ላይ እምነት እንዳያድር ከማድረግ አንስቶ የትምክህት ሃይሉ አንዳንድ ቦታ እንደተስተዋለው በመሳሪያ እስከመፋለም ደርሷል።

ሀገር ውስጥ የሚገኘው የትምክህት ሃይል በውጪ ከሚገኘው የዚህ ሃሳብ አቀንቃኝ ጋር በመዛመድ ገንዘብና ክሂሎቱን በማጣመር ሁሉንም የግኑኝነት አማራጮች በተሰላ መንገድ በመጠቀም የሞት ሽረት ትግል እያካሄደ ነው። ሲመቸው ከጥበት ሃይሉ ጋር ጋብቻ እየፈፀመ፣ ሳይመቸው ደግሞ ከዚህ ሃይልም ጋር እየተናቆረ ያለው ይህ ሃይል ሁሉንም የመንግስት ክፍተቶች የሱ ምቹ ሜዳ አድርጎ በመውሰድ እና ክፍተቶቹን በማባዛት፣ በማድመቅና በማጉላት እድሎቹን ሁሉ ለመጠቀም እየሞከረም ነው።

ብዝሃነትን አለመቀበል ዋንኛው የትምክህት ሃይሉ መለያ ባህሪ ነው። ሆኖም ግን ለሁከትና ብጥብጥ ስትራቴጂው ከጠቀመው ከማንኛውም የጥበትና የአክራሪ ሃይል ጋር ግንባር ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ አያመነታም። ይህ ባህሪው ደግሞ በተለየ ባሳለፍነው አመት በኦሮሚያና የአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተነስቶ በነበረው ሁከት በሚገባ የታየና ጎልቶ የወጣ ነው።   

የጥበት ሃይሉ በአገራችን ፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም የረባ ለውጥ ሳያመጣ አሳቻ ጊዜና አመቺ ሁኔታ ሲፈጠር ብቅ እያለ መኖሩን የሚያሳውቅ፣ ሁከትን፣ ብጥብጥንና ትርምስን በመፍጠር የፈረሰች አገር ለመፍጠር እየሰራ ያለ ሃይል ነው። ይህ ሃይል በዋናነት መነጠልን የሚያቀነቅን ሲሆን፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የጋራ አገር ስለመፍጠር ፍላጎቱም ሆነ አስተሳሰቡ የለውም። በጋራ በመስራትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እምነት የለውም። እሱም እንደ ትምክህት ሃይሉ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ያጥወለውለዋል። የአገራችን የፌዴራሊዝም ስርአት በፍፁም አይዋጥለትም።

የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለጋራ ልማትና አገር ግንባታ የሚያደርጉት ርብርብ ስለማይመቸው በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህን ለማደናቀፍ የሚሰራ መሆኑም በተመሳሳይ ባሳለፍነው አመት ገጥሞን በነበረው ሁከት ላይ ታይቷል። በአስተሳሰቡ ዙሪያ ሰዎችን በማሰባሰብ፣ በማሰልጠንና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በመደለል ሁከትና ብጥብጥ ለመፈጠር ሰርቷል። የአገራችንን ሰላም በማደፍረስ፣ በልማታዊ መንገድ ሠርተው ለመበልፀግ የሚጥሩ ዜጎችን ሃብት ንብረት አውድሟል። ብሄር ላይ ያነጣጠር የጥላቻ ዘር በመዝራት ሰዎች እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ እንዳይተማመኑና ከልማት ግስጋሴያቸው እንዲገቱ ባለ በሌለ ሃይሉ ተሯርጧል። እየተሯሯጠም ነው። የጥበት ሃይሉ በሚኖርበት አካባቢና አስተሳሰቡን በተሳሳተ መንገድ በሚሸምቱ  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የዘራው ጥላቻና የጥፋት አመለካከት ውድምትን ከማስከተል አልፎ ማህበረሰባዊ ቅራኔዎችንና ጥርጣሬዎችን እስከመፍጠር ደርሷል።

ይህ ሩጫ ሃገሪቱን በ25 አመታት ታሪኳ፤ ይልቁንም በሽግግር ዘመኑ ወቅት ያልገጠማት ፈተና እንዲገጥማት በማድረግ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አብቅቷታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በራሱ በእርግጥም ሰላማችን እንዲመለስ አላደረገልንም። በዋናነት ሰላማችን እንዲመለስ ያደረገው ህዝቡ ነው። ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት እስከሆነ ድረስ የትኛውም ሃይል ምንም ማድረግ እንደማይቻለው ስለታየም አንዳንዶቹ የአዋጁ ድንጋጌዎች ተሽረዋል። የሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ያለው በህዝቡ እጅ ላይ እንደሆነም ባሳለፍነው አመት ገጥሞን የነበረው ፈተናና ፈተናውን የተቋቋምንበት ሂደት በሚገባ አሳይቶናል። ስለሆነም መጠናከር ካለበት ይኸው ህዝብን ባለቤት ያደረገ የሰላምና የጸጥታ ስራ ነው።

በመንግስት  በኩል መደፈን ያለባቸው ቀዳዳዎች እየተደፈኑ ነው። በተለይ፣ ከላይ በተመለከተው አግባብ ወጣቱን ለአመጻ ተግባር የሚቀሰቅሰው የትምክህትና የጥበት ሃይሉ የሚጠቀምበት የወጣቶች ተጠቃሚነትን የተመለከተው ክፍተት እየተዘጋ ነው ።

ወጣቶች የስራና የቁጠባ ባህላቸውን በማሻሻል፣ ነገን የተሻለ የሚያደርጉበት እድል እየተመቻቸ ነው። ወጣቶች ስራ ፈጣሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ለስራ ያላቸውን ክብር እና የስራ ባህላቸውን በመቀየር  ተምሳሌት የሚሆኑበት ስርአትም እየተዘረጋ ነው። የፌዴራል መንግስት ካለው ውሱን ሃብት ላይ ቀንሶ ለወጣቶች የስራ ፈጠራ መነሻ የሚሆነውን ገንዘብ የመደበው ስለዚሁ ሲል ነው። የፌዴራል መንግስት ከመደበው በጀት  ባሻገር የክልል መንግስታትም እንደየአቅማቸው ለወጣቶች የስራ መነሻ የሚሆን ተዘዋዋሪ ፈንድ (Revolving fund) መድበዋል።  ስለሆነም በፍጥነት የተረጋጋችው አገራችን አሁንም የነበሩ ክፍተቶችን የበለጠ በመድፈን  ከህዝቡ የሰላሙ ባለቤት መሆን ጋር ተደምሮ ሃገራችንን ወደ በለጠና ዘላቂ ወደሆነ ሰላምና መረጋጋት ያሸጋግራታል።

እንደትላንቱ ሁሉ ነገም  የሰላሙ ባለቤት ህብረተሰቡ ነው፤ ምክንያቱም የአገራችንን ሰላም አስተማማኝ ያደረገው  ህዝብና መንግስት በቅርበት መስራት በመቻላቸው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጤታማ የሆነው ህብረተሰቡ ለሰላም መስፈን ባለው ጠንካራ አቋምም ስለሆነ ነው።

የሰላምን ዋጋ  እንደኢትዮጵያ ህዝብ  የሚረዳ እንደሌለ ተረጋግጧልና ትምክህትና ጥበት መድረሻ ቢስ መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ጉዳይ ነው የሚሆነው። አንዳንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጾች እንዲነሱ የተደረገው  መንግስት  ህብረተሰቡ ለአካባቢው ለሰላም መጠበቅ ያለውን ጽኑ  ፍላጎት እና ተግባር በመረዳቱ መሆኑም ሌላኛውና ተጨማሪው ጉዳይ ነው።