በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄና የመንግሥት ጉዳይ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ህዝብ በመልካም አስተዳደር መጓደልና የመልካም አስተዳደር አንዱ መገለጫ በሆነው ኪራይ ሰብሳቢነት መማረሩንና መሰላቸቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ ቆይቷል። በሌላ በኩል ከመልካም አስተዳደር መጓደልና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ብቸኛ ተጠያቂ የሆነው መንግሥት ችግሩን አልሸሸገም። የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር እንዳለበት፣ የችግሩ ደረጃ አስከፊና ለሥርዓቱ ህልውናም አደገኛ መሆኑን ጭምር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አምስተኛውን ዙር የመንግሥት ሥልጣን ዘመን በይፋ ከመረከቡ ከወራት አስቀድሞ ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤ፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የድርጅቱም የመንግሥትም የህልውና ጉዳይ መሆኑን በአቋም መግለጫው አመልክቷል። ህዝቡ ለኢሕአዴግ ሥልጣን በውክልና የሰጠው የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር እንዳለበት እያወቀ፣ ችግሩን ያስተካክላል በሚል እምነት መሆኑን ኢሕአዴግ በይፋ ሲገልጽ መቆየቱም ይታወቃል። አንድ በህዝብ ውክልና ሥልጣን የተረከበ ድርጅት፣ ችግሩን በዚህ ደረጃ ተረድቶ በይፋ ማሳወቁ በራሱ ወደመፍትሄ ለመሄድ እንደሚያስችል ትልቅ ርምጃ ሊወሰድ ይችላል። ችግርን መረዳትና በይፋ መናገር ግን ብቻውን ውጤት አያስገኝም፤ ነጥረው የታወቁትን ችግሮች መፍታት የሚያስችል ርምጃ መውሰድ የግድ ነው። ርምጃ በመውሰድ ማስተካከል ካልተቻለ ደግሞ ችግሩ ለምቶበት ማንነቱ ሆኗልና አማራጩ ሌላ ነው።
ያም ሆነ ይህ፤ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ በአገሪቱ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር መኖሩ ላይ በቂ ሊባል የሚችል ግንዛቤ ይዘው ነበር አምስተኛው ዙር የሥልጣን ዘመን የተጀመረው። መንግሥት ሥራ እንደጀመረ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም አማካይነት ምናልባት በአገሪቱ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ከነፈርሱ ያሳየ ሊባል የሚችል ጥናት አካሂዶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት መድረክ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል። ይህ ውይይት የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርን ለመዋጋት የህዝባዊ ንቅናቄ ማቀጣጣያ መድረክ እንደሆነ ተነገረ። ተመሳሳይ መድረኮች በፌዴራልና ክልላዊ መንግሥታት በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች መካሄድ ጀመሩ።
ይሁን እንጂ ሁላችንም እንደምናስታውሰው አምስተኛው ዙር የመንግሥት የሥልጣን ዘመን ተጀምሮ ሦስት ወራት እንኳን ሳይሞላው መልካም አስተዳደር የማስፈኑና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግራችንን የማራገፉ ሠላማዊ እንቅስቃሴ በወጉ ሳይጀመር፣ ችግሩ የፈጠረው ቅሬታ በድንገት በተቃውሞ መልክ እንዲፈነዳ የሚያደርግ አጋጣሚ ተፈጠረ። እናም መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ችግራቸውን እያወቁት፣ ችግሩ የሥርዓቱ አደጋ መሆኑን እየተናገሩ፣ ሲነገር የነበረው አደጋ በተጨባጭ ታየ። እርግጥ ተቃውሞውን ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ የሚንቀሳቀሱ የተለያየ ፅንፍ ላይ ያሉ ቡድኖች ሊጠቀሙበት መሞከራቸው አይካድም። ተቃውሞው መልኩን ቀይሮ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ ያነሳውን ህዝብ በሚጎዳ አውዳሚ አኳኋን መገለጹ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። ይህ ጉዳይ ከዚህ ጽሁፍ ትኩረት ውጭ ስለሆነ በዚሁ ልተወው።
ይህን ተከትሎ መልካም አስተዳደር የማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የማስወገድ ህዝባዊ ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት የፈነዳውን የህዝብ ተቃውሞ የማርገብ ጉዳይ ዋና ሥራ ሆነ። ከዚሁ ጋር አሁንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል የተባለ ተመሳሳይ ንቅናቄ፣ "በጥልቀት መታደስ" በሚል ሥያሜ እንደገና መጣ። በጥልቀት መታደስ የሚለው እንቅስቃሴ በይዘት ኢሕአዴግ አምስተኛውን ዙር የመንግሥት ሥልጣን ከመረከቡ በፊት ባካሄደው ጉባዔ ላይ ይዞት ከተነሳው አይለይም። ይሁን እንጂ አዲሱ በጥልቀት መታደስ የሚለው እንቅስቃሴ የመልካም አስተዳደር መጓደልና ኪራይ ሰብሳቢነት በተጨባጭ ካስከተለው የህዝብ የተቃውሞ ንቅናቄ ጋር ተዳምሮ ጠንከር ያለ የትግል ተነሳሽነት መንፈስ መፍጠሩ አይካድም። ያም ሆነ ይህ መንግሥት ችግሩን ለማቃለል ያለው ቁርጠኝነትና ጥረት የሚደነቅ ነው። የህዝብ ቁጣ ናዳ እንዳይቀድመው እንጂ ጉልህ መሻሻል ማምጣቱ አይቀሬ መሆኑንም መገመት ይቻላል።
እንግዲህ አሁን በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ዘመን ውስጥ እንገኛለን። በዚሀ መልካም አስተዳደርን የማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የማጥራት የተሃድሶ ንቅናቄ በርካታ ተጨባጭ ርምጃዎች ተወስደዋል። በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ከከፍተኛ እስከየበታች እርከን ያሉ አስፈጻሚዎችን የማንሳትና በአዲስ የመተካት ርምጃ ተወስዷል። በክልሎች በዞንና በወረዳ ደረጃ የተሾሙ የአስፈጻሚ ኃላፊዎች ህዝብ ፊት ቀርበው እንዲገመገሙ መደረጉ ያልተለመደና በጥልቀት የመታደስ እንቅሰቃሴው ውጤት በመሆኑ በመልካም ርምጃነት የሚጠቀስና ይበል የሚያሰኝ ነው።
ይሁን እንጂ በተለይ ከመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ተያይዞ ለህዝብ ጥቅም የተጀመሩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጻም ላይ የሚታየው መጓተትና፣ ግማሸ ድረስ ሄደው ሥራቸው የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ጉዳይ አሁንም መፍትሄ አላገኘም ማለት ይቻላል። በዚህ ችግር ዙሪያ ያለውን መረጃ አንድ ሁለት ብሎ ቆጥሮ በዚህ ጽሁፍ ላይ ማቅረብ የማይቻል ቢሆንም፣ በተለይ የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ሥርጭትን የተመለከተ ምን ያህል ችግር እንዳለ መረዳት ይችላል። ከፕሮጀክት መቋረጥ፣ ተጠናቀቁ የሚባሉትም ከመመረቅ ያለፈ አገልግሎት መስጠት አለመቻል ወዘተ…ጋር ተያይዞ ህዝብን ተስፋ ያስቆረጡና ያስኮረፉ ችግሮች በየእለቱ ይቀርባሉ። በአማራ ክልል ቴሌቪዥንም ተመሳሳይ መረጃዎች የሚሰራጩ ይመስለኛል። እነዚህን ችግሮች በየእለቱ የሚሰማ ሰው በጥልቀት የመታደሱ ርምጃ ውጤቱ የት አለ ብሎ መጠየቁ አይቀርም። አሁንም በህዝቡ ዘንድ መንግሥት ላይ እምነት የማጣት፣ የተስፋ የመቁረጥ ስሜቶች በገሃድ ይታያሉ። በዚህ አጋጣሚ በእነዚህ የክልል ሚዲያዎች ዘንድ የሚታየው የህዝብን ድምጽ የማሰማት ጥረት እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በአጠቃላይ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማቃለል እየተካሄደ ያለው ንቅናቄ የሚያበረታታ ቢሆንም፣ አሁንም እጅግ ብዙና መሠረታዊ ሥራዎች ይቀራሉ። በቅርቡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ይፋ ያደረገውና በባለድርሻ አካላት ውይይት የተካሄደበት ጥናት ይህን ያረጋግጧል። "መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር የሕዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስዔዎችና የመፍትሔ ሀሳቦች" በሚል የተካሄደው ጥናት፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የአስፈጻሚ አካላት ጣልቃ ገብነት ዋነኛ ማነቆ መሆኑን አመልክቷል። መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ፣ የሕዝብ ምክር ቤቶችና ማኅበራትም ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዳይሆኑ የአስፈጻሚ አካላት የሚያሳድሩት ጫና ዋነኛ ማነቆ መሆኑን ነው ጥናቱ ያረጋገጠው።
ይህ በአስፈጻሚው ዘንድ የሚታየው ችግር፣ የሕዝብ ውክልና ያላቸው በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች፣ መገናኛ ብዙሃንና ሕዝባዊ ማኅበራት እንዳይጠናከሩ ምክንያት መሆኑም በጥናቱ ተጠቁሟል። የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በየደረጃው ለሚገኙ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣ የሙያ እንዲሁም የሴቶችና የወጣቶች ማህበራት ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑ የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ደንብና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ሂደት የመሳተፍ እድል እንደሚነፍጓቸው ተመልክቷል። ይህም ህዝቡን በተገቢው መልኩ አለማሳተፍ መሆኑ ተገልጿል።
ልማታዊ አስተሳሰብ መያዝ ከተፈለገ የህዝብን አስተሳሰብና ፍላጎት ማወቅ ወሣኝና አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ፣ የአመራር ምደባ ላይ ማንኛውም የአስፈጻሚ አካል ቦታዎች እውቀቱ ባላቸው ሰዎች እንዲያዙ ማድረግ፣ ኅብረተሰቡ አዲስ በሚመደቡ አስፈጻሚዎች ላይ አስተያየት መስጠት የሚችልበትን የተሳትፎ መድረክ ማዘጋጀት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን፣ የህዝብ ምክር ቤቶችና የሙያ ማኅበራት ሚና ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግን እንደመፍትሄ አስቀምጧል።
ጥናታዊ ጽሁፉ በቀረበበት መድረክ ላይ የተገኙት በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሐዬ መንግሥት ከዚህ ቀደም በልማት፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሕዝቡን በስፋት ሲያሳትፍ መቆየቱን አስታውሰዋል። የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በሕዝባዊ ማኅበራት፣ በመገናኛ ብዙኃንና በሕዝብ ምክር ቤቶች ላይ በሚያሳድሩት አሉታዊ ጫና የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ አያገኙም ነበር ብለዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣ መገናኛ ብዙሃንና የሕዝብ ማኅበራት መብቶቻቸውን በተቀመጡ ህጎችና በህገ መንግሥቱ መሠረት የመጠየቅና ፊት ለፊት መጋፈጥ ላይ ክፍተቶች መኖራቸው መረጋገጡንም አስታውቀዋል። አስፈጻሚ አካላት የህዝቡን ሚናና ኃያልነት ያለመገንዘብ ችግር እንዳለባቸው መረጋገጡንም ገልፀዋል።
ከላይ የተመለከተው ጥናታዊ ጽሁፍና በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሐዬ የሰጡት ገለጻ፣ መንግሥት በየደረጃው ያስቀመጣቸው አስፈጻሚዎች የመልካም አስተዳደር ዋና መገለጫ የሆኑትን የህዝብ ተሳትፎና የግልጽነት መርሆች የደፈጠጡ መሆኑን ያመለክታል። በተግባርም እንደምናየው በተለይ ለህዝቡ ቅርብ የሆኑ በቀበሌ፣ ወረዳና ክፍለ ከተማ ደረጃ ያሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አስፈጻሚዎችን የሚቆጣጠሩ ሳይሆኑ፣ አስፈጻሚው የሚመራቸው ነው የሚመስለው። አነዚህ ምክር ቤቶች አስፈጻሚው የሚያቀርብላቸውን ሪፖርት አዳምጠው ከመሄድ ባለፈ ችግሮችን የሚጠይቁ አይደሉም። አስፈጻሚው ለእነርሱ ተጠያቂ መሆኑን የሚያውቁ አይመስሉም። ይህ የአሳታፊነት የመልካም አስተዳደር መርህ የተደፈጠጠ መሆኑን የሚያሳይ አስረጂ ነው። በየአካባቢው የምናያቸው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለማት ፕሮጀክቶች መጓተትና ከተጠናቀቁም በኋላ አገልግሎት መስጠት አለመቻል ችግር ምንጭ ይህ የአካባቢ አስፈጻሚዎች በአካባቢያዊ ምክር ቤቶች ተጠያቂ አለመሆንና አለማሳተፍ ነው። ይህ አቶ አባይ ፀሐዬ እንደገለጹት የህዝብን የበላይነት መዘንጋት ነው።
የመገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ፣ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት በክልል ሚዲያዎች አካባቢ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማጋለጥ ረገድ አበረታች ሥራዎች ቢታዩም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚሰሩ የህዝብ ሚዲያዎች ዘንድ አሁንም የአስፈጻሚ አወዳሸነት ይታያል። አስፈጻሚው ሚዲያዎቹን የመንግሥትን ችግር እንደሚሸፋፍኑ እንጂ፣ ችግሩን ለህዝብ እንደሚያጋልጡ ተቋማት አይመለከቷቸውም። ሚዲያዎቹም የመንግሥትን ችግር ማጋለጥ ነውር ነው የሚመስላቸው። የመንግሥትን ችግር ለማቅረብ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢገጥማቸው እንኳን፣ ይህን በሚያካክስ ግዙፍ ውዳሴና ሙገሳ ታጅቦ ነው የሚቀርበው። በዚህ አኳኋን ሚዲያዎቹና አስፈጻሚዎቹ አንዱ ሌላውን የመንከባከብ ጋብቻ ፈጽመዋል።
በዚህ መካከል አስፈጻሚውም፣ ሚዲያዎቹም ብቸኛ የመንግሥት ሥልጣን ባለቤትና ምንጭ የሆነውን ኃያሉን ህዝብ ዘንግተውታል። እናም ህዝቡን ማስታወስ አለባቸው። ህዝብን፣ የህዝብ ተወካዮችንና ማህበራትን እንዲሁም ሚዲያን ያላሳተፈ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጥረት ከወሬ አልፎ የትም እንደማይደርስ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከምንም በላይ የህዝብን ኃያልነት መዘንጋት ከህገ መንግሥታዊ መርህ አኳያ ተገቢ ያልሆነ፣ ከፖለቲካ ሥነ ምግባርም አኳያ ፀያፍ መሆኑ ሁሌም መታወስ አለበት። ህዝብ ኃያል ነው። ከተቀመጡበት የሥልጣን ወንበር የማንሳት ባለመብት ነውና።