ከወርሐ ነሐሴ 2008ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ደረጃዎች ሲካሄድ የነበረውን የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ የደረሰበትን ደረጃና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ በስፋት የገመገመው የኢህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ማጠናቀቁን የግንባሩ ምክር ቤት ፅሕፈት ቤት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ እንደገና በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረኮች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት መፈፀማቸውን ገምግሟል፡፡ የተሃድሶ ንቅናቄው በአመራሩ፣ በአባሉ፣ በሲቪል ሰርቫንቱና በመላው ህዝብ ሰፊና ተከታታይ ውይይት መደረጉንና በዚህም በመሰረታዊ አጀንዳዎቹ ላይ የጋራ መግባባት መፈጠሩንም ተመልክቷል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ወኪል ሆኑት የትምክህትና ጠባብነት አመለካከትና ተግባራት ሀገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም አስገድደዋት እንደነበር የገመገመው ምክር ቤቱ በተቀጣጣለው የተሃድሶ ንቅናቄ አስከፊውን ሁኔታ በመቀልበስ የተጀመረውን ሀገራዊ የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ በአመራርና በአባላት ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት፤ በሲቪል ሰርቫንቱና በህዝቡ ዘንድም የተነሱ ችግሮች ይፈታሉ የሚል ተስፋ አሳድሯል ብሏል፡፡
በአጠቃላይ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው ባለፉት 15 የተሃድሶ ዓመታት በልማት፣ በሰላም እና በዴሞክራሲ መስኮች የተመዘገቡ አንጸባራቂ ድሎች ላይ ህዝቡ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረውም የጋራ መግባባት ተፈጥሮበታል፡፡ በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት ወኪል የሆኑት የትምክህትና ጠባብነት አመለካከቶችና ተግባራት የፌዴራላዊ ዴምክራሲያዊ ስርዓታችን ዋነኛ አደጋ መሆናቸውን የጋራ መግባባት ተደርሰባቸዋል፡፡ በቀጣይ ትግል የህዳሴ ጉዞውን ማደናቀፍ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ በማድረስ ሀገራዊ ህዳሴውን እውን ለማድረግ ድርጅት፣ ሲቪል ሰርቫንቱ እና ህዝቡ ለለውጥ መነሳሳታቸውን ምክር ቤቱ መገምገሙንም መገለጫው አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ባደረጉት መራራ ትግል፤ በከፈሉት ውድ መስዋዕትነት ጭቆናና አድሎአዊ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ በመገርሰስ አዲስ በመፈቃቀድ፣ በመከባበር፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተና ከአድልዎ የጸዳ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስርተዋል፤ በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በየአካባቢያቸው ተፈጥሮ ያደላቸውን ጸጋ፣ መሬት፣ ጉልበታቸውን እውቀታቸውን በማስተባበር በየአካበባቢያቸው በነጻ የመልማት እድል ተጎናጽፈዋል፤ ከዛም በላይ በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው የሚወሱንበት የራስን በራስ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብትም ተጎንጽፈዋል፡፡
በጋራ ጉዳዮቻቸውም ላይ በፍትሃዊና በእኩልነት መርህ የሚወስኑባቸው ተቋማትን በገዛ ፈቃዳቸው መስርተዋል፡፡ ሐቁ ይህ ሆኖ ሳሉ ስርዓቱ አድላአዊ እንደሆነ በማስመሰል በትምክህትና በጠባብ ኃይሎች ዘንድ አንዱን የበላይ ሌላኛው የበታች በማስመሰል የሚቀርበው ፕሮፓጋንዳ መሰረተ ቢስ ከመሆኑም በላይ በህዝቦች ትግል የተመሰረተውን ፌዴራላዊ ስርዓቱን ለማጥቃት ያለመ መሆኑን በመገንዝብ በኃላ ቀር አመለካከቶቹና ተግባራቱ ምህረት የለሽ ትግል መደረግ እንደሚገባም ምክር ቤቱ ገምግሟል፡፡
የኢህአዴግ ምክር ቤት በጥልቅ ተሃድሶው ከተቀመጡት አቅጣጫዎች አንዱ ድርጅትና መንግስትን መልሶ ማደራጀት ነበር፡፡ ከዚህ አኳያም መልሶ የማደራጀቱ ተግባር ከላይ እስከ ታች ባሉ የድርጅትና የመንግስት መዋቅሮችን ቁርጠኝነቱና ተነሳሽነቱ ባላቸው አመራሮች መልሶ የማደራጀት ስራው መከናወኑን የገመገመው ምክር ቤቱ በአመራር ስምሪቱ ላይ ህዝቡ ቀጥተኛና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን ባረጋገጠ አኳሃን አመራሮችን እየተቸ ያገለግሉኛል የሚላቸውን ይሁንታ እየሰጠ አያገለግሉኝም የሚላቸው ደግሞ በአመራርነት እንዳይቀጥሉ ያደረገበት ሁኔታም ህዝቡ የስልጣን ባለቤትነቱን ያረጋገጠበት ከመሆኑም በላይ ለቀጣይም ይኸው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክር ቤቱ አስምሮበታል፡፡
የኢህአዴግ ምክር ቤት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጠናከር ለማድረግ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚንቀሰቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ አካላት ጋር ነጻ ሀሳብ እንዲሸራሸር ውይይቶችና ድርድሮች እንዲካሄዱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የመድብለ ፓርቲ ዴሞከራሲያዊ ስርዓቱ ለማጎልበት በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይቶች መጀመራቸውን ገምግሟል፡፡
እስከአሁኑ በተደረጉ ውይይቶችም ለድርድሩ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር ገንቢ ሚና እየተጨዋቱ እንደሚገኙና ሂደቱም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክር ቤቱ አስምሮበታል፡፡
ከመልካም አስተዳደር፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ተግባራት የገመገመው ምክር ቤቱ ከጥልቅ ተሃድሶው ጋር ተያይዞ በዚህ ረገድ እየተከናወኑ ያሉትን ስራዎች ይበልጥ መስፋትና መጠናከር እንደሚገባቸውም አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡
የወሰን ማካለል ጉዳይን በአፋጣኝ ዕልባት ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው የኢህአዴግ ምክር ቤት የገመገመ ሲሆን ቀሪ ተግባራት በፍጥነት እንዲከናወኑ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጉዳይ የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ቁልፍ ስራ ነው ያለው ምክር ቤቱ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ በተመለከተም ነባሩን የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅ የነበሩበትን ክፍተቶች በማረም የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በመሰረታዊነቱ እንዲመልስ ሆኖ ተዘጋጅቷል ብሏል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ወጣቶችን የማሰልጠን፣ የማደራጀት፣ ብድር የማመቻትና በተወሰኑ ቦታዎችም ወደ ስራ የማስገባት ተግባራት መከናወናቸውም ገምግሟል፡፡ በቀጣይ በተሟላ አግባብ ወጣቱን ወደ ስራ ለማስገባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰረት አንደሚገባው ምክር ቤቱ አጽኦት ሰጥቶበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚም መላ የሀገራችን ወጣቶች ላሳዩት ትጋት ምክር ቤቱ አድናቆቱን ገልጻል፡፡
ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት በተመለከተም ምክር ቤቱ የማክሮ ኢኮኖሚዊ ጉዳዮችና እና የኢኮኖሚዊና ማሕበራዊ ዘርፎች፣ ባለፉት ዓመታት እየተመዘገበ የመጣው ፈጣን እና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በያዝነው ዓመትም ቀጥሏል ብሏል፡፡
በመስኖና በበልግ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ርብርብ ከተደረገ በያዝነው ዓመት የመኸር ግብርና እድገት በአማካይ 12 በመቶ ማስመዝገብ እንደሚቻልም ትንበያዎች ያመላክታሉ ብሏል የኢህአዴግ ምክር ቤት ፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ህዝቡ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በተፋሰስ ልማት በስፋት በማሳተፍ የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ በመገምገም በቀጣይም ስራዎቹ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥቶበታል፡፡
በሀገራችን ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በተፈጠረው የዝናብ አገባብ፣ መጠንና ስርጭት መዛባት ምክንያት በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በተወሰኑ የኦሮሚያ እና ደቡብ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱንና የድርቁን አደጋ ለመቀልበስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም ውጤታማ እንደሆኑ ምክር ቤቱ አይቷል፡፡ መንግስት ለጉዳዩ ቅዲሚያ ሰጥቶ የድርቁን አደጋ ለመቀነስ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን በዝርዝር የገመገመው ምክር ቤቱ በተለይ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲሁም በእንስሳት ላይ ሚደርሰው ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል አቅጣጫ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስምሮበታል፡፡
የኢንዱስትሪ ዕድገት በተመለከተም በ2008 በጀት ዓመት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ በመግባታቸው ምክንያት የማምረቻ ኢንዱስትሪው የተሻለ እድገት ማስመዝገቡን የገለፀው ምክር ቤቱ በዘርፉ ለተመዘገበው ፈጣን ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው ብሏል፡፡ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማት በማፋጠን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን የተመለከተ ምክር ቤቱ 13 የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ስራ በተሻለ አፈፃፀም እየተከናወን መሆኑን አይቷል፡፡
ከእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል በየቦሌ ለሚ ምዕራፍ አንድ 20 የሚሆኑ የፋብሪካ ሼዶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ወደ ምርት ስራ የተሸጋገሩ ሲሆን ፓርኩ በአሁኑ ጊዜ 10 ሽህ ለሚደርሱ ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክም በመጀመሪያ ዙር ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው ከተጠናቀቁ 37 የፋብሪካ ሼዶች መካከል 11 ሼዶች የምርት ስራ መጀመራቸውን ገምግሟል፡፡ የሌሎች ኢንዳስትሪያል ፓርኮች ግንባታ በተመለከተም በተለያየ ደረጃ እንዳሚገኙ ተመልክቷል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የዋጋ ንረቱን በነጠላ አሃዝ ገድቦ ለመያዝ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑንም የተመለከተው ምክር ቤቱ ይህም የብር የመግዛት ዓቅም ጠብቆ ለማቆየት፣ ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ የገቢ ክፍፍልንና የሃብት ድልድልን ሚዛዊ ለማድረግና የማሕበራዊና ኢከኖሚያዊ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ስራዎች አማካይነት የተገኘ ውጤት እንደሆነ አስምሮበታል፡፡
የመሰረተ-ልማት አቅርቦት ማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ሜጋ ፕሮጄክቶች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም የኢህአዴግ ምክር ቤት አረጋግጧል፡፡
በማሕበራዊ ልማት ዘርፍ የአንደኛ ትምህርት ለሁሉም ለማዳረስና የሁለተኛ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማስፋፋት አኳያ በዕቅዱ ግማሽ ዓመት የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸው የተመለከተው ምክር ቤቱ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተከናወኑ ስራዎችም መልካም ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን እንደተጠበቀ ሆነ በቀጣይ የትምህርት ጥራት ለማሻሻል በተለይም የመዋዕለ ህፃናትና የአንደኛ ደረጃ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሻ ተመልክቷል፡፡ የአንደኛ ደረጃ መጠነ ማቋረጥ ለማስቀረት መረባረብ እንደሚገባ የጠቆመው ምክር ቤቱ የጎልማሶች ትምህርትም ለህዳሴ ጉዞው ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር በመመዘን በቀሪ ጊዜ ውጤታማ ስራ ለማከናወን መረባረብ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በጤና መስክም በተለይ የእናቶችና የህፃናት ሞት በመቀነስ ስኬታማ ስራዎች እንደተከናወነ ገልጿል፡፡ ይሁንና የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓቱና የኤክስቴንሽን ሙያተኞች የሚያጋጥሟቸውን የማሕበራዊና የሙያ ማነቆዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት እንደሚገባ በመጠቆም በዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት መጓደል ችግር ለመፍታትም ቀጣይ ትኩረት እንደሚሹ አስምሮበታል፡፡
በአጠቃላይ የተሃድሶው ንቅናቄና የሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም አበረታች ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን በመጠቆም ከተሃድሶ አኳያ የኪራይ ሰብሳብነት አመለካከትና ተግባር ወኪል የሆኑትን ትምክህትና ጠባብነት ቀጣይ ትግል ሊደረግባቸው እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥቶበታል፡፡
የሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሁለተኛው ዓመት አጋማሽ በገጠር የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በከተማ ደግሞ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ሚና በማጎልበት በአንድ በኩል የተጀመረውን ፈጣንና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስቀጠል በሌላ በኩል ያጋጠመንን ድርቅ በሰው ህይወት ላይ ሞት በእንስሳት ላይ ደግሞ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በራስ አቅም ለመቋቋም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ እና የህዝቡን ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የመስጠት ጉዳይ በልዩ ትኩረት መከናወን እንዳለበት አቅጣጫ በማስቀመጥ “እየታደስን እንሰራለን እየሰራን እንታደሳለን!” በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባውን አጠናቅቋል፡፡
የኢህአዴግ ምክር ቤት