በኢትዮጵያ መንግሥትና በመላ ህዝቧ ገንዘብና አቅም እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት ስድስተኛ ዓመት ከሰሞኑ ተከብሯል። የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቡ ሲጠናቀቅ 6450 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል። ይህ ግድብ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር በኢኮኖሚ ያስተሳስራል። ከኢትዮጵያም አልፎ የሱዳንና የግብጽን ህዝቦች ተጠቃሚ ያደርጋል። አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪም በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል። በቅርቡ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የግድቡ ግንባታ ክንውን በአሁኑ ወቅት 57 በመቶ ደርሷል።
የግድቡ ሥራ እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ብዙ ፈተናዎች ታልፈዋል። የብድር አገልግሎት እንዳይገኝ ብዙ ተጥሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች በዚህ ትልቅ ፕሮጀክት ዙሪያ የተለያዩ አፍራሽ ርምጃዎችን ከመውሰድ አልተቆጠቡም። "የግድቡ ግንባታ ደረጃውን ላይጠብቅ ስለሚችል ቢደረመስ ግብጽንና ሱዳንን ለጎርፍ አደጋ ይዳርጋል፤ ግንባታው የግብጻዊያንን የውኃ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል" የሚሉና ሌሎች አፍራሽ ሃሳቦችን በማራመድ ጭምር የኢትዮጵያ ህዝብ የተያያዘውን ልማት ለማደናቀፍ ያልተቆፈረ ጉድጓድ የለም። ብዙ ተራውጠዋል፤ ሴራም ጎንጉነዋል።
ሌላው ደግሞ ይህች አገር በዚህ አኳኋን ዕድገቷ ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ውስጥ መበልፀጓ አይቀሬ ነውና በሚል ሥጋት በኢትዮጵያ ህዝብ ስም እየለመኑ ለግል ድሎትና ቅንጦት ያውሉት የነበረው የዕርዳታ ምንጭ እንደሚደርቅ በመገንዘብ ልማቱን መቃወም የእለት ተእለት ሥራቸው አድረገው ተራውጠዋል። ኢትዮጵያ ከዕርዳታ ሰጪዎችና ከምዕራባዊያን ፍላጎትና ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ትላቀቃለች የሚል ሌላ ሥጋት ስላደረባቸውም የቻሉትን ያህል ተንቀሳቅሰዋል።
ግድቡን ለመሥራት ብድርና ዕርዳታ እንዳይገኝ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። የግድቡን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበር ወይም ፈቃደኛ የሚሆን አገር ማግኘትም ሌላው ፈተና ነበር። በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ተስፋውን የጣለው ይህ ፕሮጀክት በራስ አቅም ላይ ብቻ ተማምኖ ግንባታውን "ሀ" ብሎ ጀምሮ ዛሬ ላይ ተገኝቷል። ሆኖም የኢፌዴሪ መንግሥት በግድቡ ግንባታ ሥፍራ ላይ የመሠረት ድንጋይ ካኖረበት ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ጀምሮ ሁሉም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስኬታማነቱን እውን ለማድረግና በራስ ተነሳሽነት ተገቢውን ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ከዳር እስከ ዳር እጆቻቸውን አስተሳስረው ተነሳስተዋል።
የሁሉም የአገራችን ህዝቦች የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የአባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት ከጫፍ ለማድረስ በአዲስ ምዕራፍ ተንቀሳቅሰዋል። የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዬን ዩሮ በላይ ወይም ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቅ ሆኗል። በመሆኑም ወጪውን እኛው ዜጎች ለመሸፈን የምንገደድበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናልና ከዳር ለማድረስ ቃል ኪዳን እንደገባነው ሁሉ ከፍጻሜም ለማብቃት ቃል ኪዳናችን ይታደሳል።
ዛሬ ላይ በህዝቦች የማይነጥፍ ሙሉ ተሳትፎ እየተገነባ ያለውና የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራስ ገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀት ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ቢባል ማጋነን አይደለም። ዜጎች ከዕለት ገቢያቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ ነውና ታሪካዊነቱም የዚያኑ ያህል ከፍ ያለ ነው።
ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ሲቆጩበት የኖሩት የአባይ ወንዝን ጥቅም ላይ የማዋል ራዕያቸውን እንደሚያሳኩ የተመለከቱ ፅንፍ የያዙ ሟርተኞች ቢቆዝሙም ፕሮጀክቱ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ አንድ መንፈስና ሃሳብ አምጥቷል። ይህ የአንድነት መንፈስ ለሌሎች ትላልቅ ልማቶች ተሞክሮ ስለሚሆን የአገሪቱ የዕድገት ጉዞ እውን መሆኑን የሚያመላክት ተምሣሌት ሆኖ ተገኝቷል።
የኢትዮጵያ ማደግና የህዝቦቿ መበልፀግ ለሚያማቸው ቡድኖች ግን እንቅልፋቸውን አጥተው ሥልታቸውን በመቀያየር ልማቱን መቃወማቸውን ቀጥለውበታል። ታዲያም ይህ የማይጨበጥ ባዶ ተስፋቸውና፣ የማይደመጥ የቁራ ጨኸታቸው የተያያዝነውን የልማት ጉዞ ወደ ኋላ የማይቀለብስ አሊያም የማይጎትት መሆኑን ቢረዱ መልካም በሆነ ነበር።
ዳሩ ምን ይደረግ! ከቻሉ የአገሪቱን የልማት ጎዞ የኋሊት ለመቀልበስ ካልሆነላቸው ደግሞ ሂደቱን ለማደናቀፍና ለማጓተት ያስችላል ያሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በአሉባልታ ፈረስ ላይ ሆነው ያንንም ይህንንም ከመደስኮር አልፎ በልማት ፕሮጀክቶቻችን ላይ የጥቃት ዒላማ ለማድረስ ይራወጣሉ። ይህ አልበቃ ብሎም በሚከተሉት ስትራቴጂያቸው በአገሪቱ በመካሄድ ላይ በሚገኙ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ መሠረት የለሽ ዘገባዎችን በአፈ ቀላጤዎቻቸው በኩል በማቅረብ የዓለምን ኅብረተሰብ ለማሳሳት ታች ላይ ይላሉ።
በዚህም በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተዛባ አመለካከት ይዘው ልማቱን እንዳይደግፉ፤ በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎችም እርስ በርስ ተከፋፍለው ለልማቱ መሳካት የሚያደርጉት ድጋፍ እንዲቀዛቀዝ ይውተረተራሉ። በተለይ በዋነኛ መሣሪያነት "ሂዩማን ራይትስ ዎች"ን ከጎናቸው በማሰለፍ ሲቅበዘበዙ አይተን ታዝበናቸዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ያለመታከት ቀን ከሌት መሠረት የለሽ ዘገባዎችን በማሰራጨት የአገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ እየሰራ የሚገኝ "የሰብዓዊ መብት ተሟጋች" ነኝ ባይ ተቋም ነው። በቀደሙት ዓመታት በአገሪቱ በመገንባት ላይ የነበረውንና አሁን የተጠናቀቀውን የጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ላይ ዘመቻ ከፍቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የቅርብ ጊዜው ትውስታችን ነው።
ይህ "የሰብዓዊ መብት ተሟጋች" ነኝ ባይ ድርጅት በኢትዮጵያና በኬንያ ህዝቦች መካከል መቃቃርን ለመፍጠር ያልወጣው ዳገት አልነበረም። የጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ "የቱርካና ሐይቅ የውኃ መጠንን እንዲቀንስ ያደርጋል፣ በቱርክና ሐይቅ ላይ ህይወታቸው የተመሠረተው የአካባቢው ህዝቦች አደጋ ላይ ይወድቃሉ" የሚሉ ሐሰተኛ የማደናገሪያ ዘመቻዎችን ከፍተው ላይ ታች ሮጠዋል – ሐሳብ ምኞታቸው እንደ ጉም በንኖ ቢጠፋም።
አሁንም ምን ያደርጋል! ይህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተብየው ድርጅት የኢትዮጵያ ህዝብ በገዛ የራሱ የተፈጥሮ ሐብት እንዳይጠቀም ከመሞገት አልፎ ከቱርክና ሐይቅ ጋር አያይዞ ያነሳው ጉዳይ በሁለቱም አገራት ህዝቦች ዘንድ ግጭትን የመቀስቀስ ዓላማው ተቀባይነት አጥቶ ጥረቱ አልተሳካለትም። ኢትዮጵያና ኬንያ ልማቱ ሁለቱንም አገራት የሚጠቅም መሆኑን የጋራ ግንዛቤ በመያዛቸው ጆሯቸውን ነፍገውታል – አልሰሙትም።
መላ ኢትዮጵያዊያን ከገቢያቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚጠብቁት ይህ ግድብ አሁን ላይ ወደከፍታው ማማ ያሸጋግረናል ብለው ተስፋ ጥለውበታል። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት ስኬታማነቱን እውን ለማድረግና በራሳቸው ተነሳሽነት ማናቸውንም ጉዳዮች ለመከወን ቃል ገብተዋል፡፡ በህዝቦች ቆራጥነትና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባውና የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ "እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን" ከሚለው የጋራ ቃል አልፎ "እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን" ወደሚል ሌላ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
በዚህም ሁሉም የአገራችን ህዝብ የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አንድነቱን አፅንቶ እየሰራ ይገኛል። እነርሱ ያውሩ እኛ ሥራ ላይ ነን።