የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ተነፍጎ የኖረ ህዝብ ነው። መሠረታዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ከማጣት በተጨማሪ የህይወት ፍላጎቶቹን በወጉ ማሟላት በማይችልበት አስከፊ ድህነት ውስጥ ነው የኖረው። ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ቅንጦት አይደሉም። የተሻለና ዋስትና ያለው ህይወት የመኖር ማረጋገጫ መሣሪያዎች ናቸው። በመሆኑም ለኢትዮጵያ ህዝብ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ፣ የህልውናው ጉዳይ ነበር። ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የነፈጉትን አምባገነን የመንግሥት ሥርዓቶች የተዋጋው ለዚህ ነው። በዘውዳዊና ወታደራዊ ደርግ የመንግሥት ሥርዓቶች እነዚህን መብቶቹን በሠላማዊ መንገድ ማስከበር የሚያስችለው ዴሞክራሲ ባለመኖሩ ከኃይል ትግል ውጭ አማራጭ አልነበረውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት የጠየቀ ትግል አካሂዶ የወታደራዊውን ደርግ አምባገነን ሥርዓት ማስወገድ ያስፈለገው ለዚህ ነው።
ወታደራዊው ደርግ ከተወገደ በኋላ አዲሲቱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ተመሥርታለች። አዲሲቱን ኢትዮጵያ ልዩ የሚያደርጋት መሠረታዊ ነገር ህገ መንግሥቷ ከላይ ከገዥዎች የተሰጠ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዊያን ራሳቸው መክረው በመከባበርና በእኩልነት የህዝቦች አንድነት ያላት አገር መሥርተው ለመኖር ተስማምተው ባፀደቁት ህገ መንግሥት (የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት) የምትመራ መሆኗ ነው።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ብሄራዊ ማንነታቸው በህግ እውቅና ተነፍጎት የኖሩ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የወሰን ሳይሆን የህዝብ አንድነት መሥርተው ለመኖር የተስማሙበት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በአገሪቱ ዘመናዊ የመንግሥት ሥርዓት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የብሄር ብዝሃነትን የተቀበለ ህገ መንግሥት ነው። ህገ መንግሥቱ የብሄር ብዝሃነትን ብቻ አይደለም የተቀበለው። የአመለካከትና የኃይማኖት ወዘተ…ብዝሃነትንም ተቀብሏል። የብሄርና የአመለካከት ብዝሃነት ባለበት አገር ዴሞክራሲን ችላ ማለት የማይታሰብ ነው። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያረጋገጠው ለዚህ ነው። ህገ መንግሥቱ ሰብዓዊ መብቶችንም አረጋግጧል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከአንቀጽ 13 እስከ አንቀጽ 44 የሚገኙት አንቀጾቹ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚመለከቱ ናቸው። የህገ መንግሥቱ አንድ ሦስተኛ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚመለከቱ አንቀጾች ናቸው።
በዚህ ጽሁፍ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚመለከቱ የህገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች እመለከታለሁ። በህገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል ሁለት “ዴሞክራሲያዊ መብቶች” በሚል ርዕስ ሥር ከአንቀጽ 29 እስከ 44 የተለያዩ መብቶችንና ነጻነቶችን አስፍሯል። እነዚህም፤ የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ፣ የመደራጀት፣ የመዘዋወር ነጻነት፣ የዜግነት፣ የጋብቻ፣ የግልና የቤተሰብ፣ የሴቶች፣ የህጻናት፣ ፍትህ የማግኘት፣ የመምረጥና የመመረጥ፣ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች፣ የንብረት፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል፣ የሠራተኞች፣ የልማት፣ የአካባቢ ደህንነት መብቶች ናቸው።
እነዚህን በህገ መንግሥቱ ላይ የሰፈሩ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶችን ይዘትና አፈጻፀም በአንድ አጭር ጽሁፍ መመልከት ስለማይቻል፣ በዚህ ጽሁፍ በአንቀጽ 29 ላይ የሰፈረውን የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ ነጻነት ለመመልከት እሞክራለሁ።
የአመለካከትና ሃሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብት በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ነው። ይህ መብት የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መገለጫ ከሆኑት ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በአንቀጽ 29 የአመለካካት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመገለጽ መብት በሚል ርዕስ ሥር የሚከተለው ተደንግጓል።
- ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል።
- ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት አለው። ይህ ነጻነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሁፍ ወይም በህትመት፣ በሥነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሃሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል።
- የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነጻነት ተረጋግጧል። የፕሬስ ነጻነት በተለይ የሚከተሉትን መብቶች ያጠቃልላል፤
ሀ. የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣
ለ. የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን፣
- ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሃሳቦችና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋጋጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነጻነትና የተለያዩ አስተያያቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ ይደረግለታል።
- በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ የመገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል።
- እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሃሳብና መረጃ የማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመሥርተው በሚወጡ ህጎች ብቻ ይሆናል። የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ህጋዊ ገደቦች በእነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ። የጦር ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህግ የሚከለከሉ ይሆናል።
- ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በህግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል።
እንግዲህ፣ የመጨረሻው አምባገነን መንግሥት ከመወገዱ በፊት በወታደራዊው ደርግና በዘውዳዊው የመንግሥት ሥርዓት ዘመኖች፣ ሃሳብን የመግለጽ መብት የሚባል ነገር አልነበረም። የግል ጋዜጣ ወይም መጽሄት ማሳተም፣ ማሰራጨት ወዘተ…በህግ የተከለከለ ነበር። ራዲዮ ጣቢያ ማቋቋም ደግሞ ጭራሽ የማይታሰብ ነበር። በራዲዮ መናገር የሚችለው መንግሥት ብቻ ነበር። በአጠቃላይ የግል ወይም ነጻ ፕሬስ የህልም እንጀራ ነበር። አሁን እንደ ዋዛ ገዝተን የምናነባቸው መጽሄትና ጋዜጦች በዘውዳዊውና ወታደራዊው ሥርዓት ዘመን ከሰማይ የራቀ ነበር። በተለይ በወታደራዊው ደርግ የሥልጣን ዘመን፣ መጽሄትና ጋዜጣ በአገር ውስጥ አሣትሞ ማሰራጨት ቀርቶ፣ በውጭ አገራት የታተሙ መጽሄቶች ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም አይቻልም ነበር። ይዞ መገኘትም ያስጠይቃል።
በእነዚህ ሥርዓቶች ሃሳብን ከመግለጽ ነጻነት ጋር በተያያዘ ሊጠቀስ የሚችሉት ልብ ወለድ መጻህፍትና ዘፈኖችን ማሣተም ነበር። እነዚህም ቢሆኑ ግን እንደ ዋዛ የሚከናወኑ አልነበሩም። የልብ ወለድ መጽሃፍት ወይም የዘፈን ግጥሞች ደራሲ ወይም አሣታሚ የፈጠራ ሥራቸውን ለህትመት ከማብቃታቸው አስቀድመው ወደማስታወቂያና መርሐ ብሄር ሚኒስቴር የሣንሱር መምሪያ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። የሣንሱር ኃላፊው ሥርዓቱን ይቃወማል፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ክብር ያዋርዳል ወዘተ…ብሎ የገመተውን ማንኛውንም ሃሳብ ከፈጠራ ሥራው ውስጥ ተቆርጦ እንዲወጣ ያደርጋል። ተቆርጦ ሊጣል የማይችል ከሆነ ደግሞ የፈጠራ ሥራው ሙሉ በሙሉ ይታገዳል። እንደ አጋጣሚ ከሣንሱር ሾልከው ለመታተም ከበቁ በደራሲው፣ በአታሚው፣ በሻጩ ምናልባትም ባነበቡና ባዳመጡ ዜጎች ላይ የዘፈቀደ እሥርና እስከሞት የሚደርስ ቅጣት ያስከትላል።
ዜጎች ሃሳባቸውን በይፋ መግለጽ ብቻ አልነበረም የተከለከሉት። በማንኛውም ሥፍራ፤ በሥራና በመዝናኛ ቦታዎች፣ በመኖሪያ ቤታቸው ጭምር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሥርዓቱንና ባለሥልጣናቱን የሚቃወሙ ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን ተናግረው ይህም የሥርዓቱ ነጭ ለባሾች ጆሮ ከደረሰ ድርጊቱ ሊያሳስር፣ አካል እስኪጎድል ሊያስደበድብ፣ ምናልባትም ህይወት ሊያሳጣ ይችላል። መንግሥት ህዝብ እንዳያውቅ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች አዳምጦ ወይም አንብቦ መገኘትም የሚያስቀጣበት ሁኔታ ነበር።
የመጨረሻው አሃዳዊ አምባገነን መንግሥት የነበረው ወታደራዊ ደርግ ከተወገደ በኋላ መረጃ የማግኘት መብትና ነጻነት ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ በአዋጅ ተነሳ – በ1984 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በሽግግር መንግሥቱ በታወጀው የፕሬስ ነጻነት አዋጅ። በኋላም ይኸው መብት ቀደም ሲል በጠቀስነው የህገ መንግሥቱ ድንጋጌ ተረጋገጠ።
ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት በህገ መንግሥት መረጋገጡን ተከትሎ ለቁጥር የሚያታክቱ የግል መጽሄቶችና ጋዜጦች ታትመው ይሰራጩ ጀመር። እርግጥ ይህ የጀመረው በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ነበር። ታትመው የሚሰራጩት መጽሄቶቹና ጋዜጦቹች በህገ መንግሥቱ መሠረት ቅድመ ምርመራ አይደረግባቸውም። እንደየአሣታሚዎቹ ዝንባሌ ከፖለቲካዊ እስከ ወሲባዊ እና የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ። ህዝቡም ለዘመናት የተከማቸውን የንባብ ረሃቡን ያህል ያገኘውን ሁሉ በነጻነት አነበበ። እያደረ ግን የመረጃ የማግኘት የንባብ ጥማቱ እየረካ ሲሄድ ክፉውን ከደግ፣ የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው እየለየ ማንበብ ጀመረ። ብዙዎቹን በ1984/85 ላይ ወደሥርጭት የገቡት መጽሄትና ጋዜጦች ከገበያ ውጭ የሆኑት ህዝብ ከሥነ ምግባር አኳያ ፀያፍ በመሆናቸው፣ የተቀሩት ደግሞ የማይታመኑና የረባ መረጃ የሌላቸው ሆነው ስላገኛቸው አንጓሎ ጥሏቸው ነው። በአሁኑ ጊዜ የተቃውሞ የፖለቲካ ሃሳቦችና አቋሞች በየእለቱ ታትመው በሚሰራጩ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ይፋ እየወጡ ነው። ልሂቃንና ሌሎችም ዜጎች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የመሰላቸውን አስተያየቶች እያቀረቡ ይገኛሉ።
ከጋዜጦችና መጽሄቶች በተጨማሪ መጻህፍት ያለምንም ገደብና ቅድመ ምርመራ ታትመው እየተሰራጩ ነው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ቢያንስ በሣምንት አንድ የልብ ወለድ፣ የታሪክ፣ የሙያ፣ ፖለቲካዊ ወዘተ…ይዘት ያላቸው መጻህፍት ታትመው ይሰራጫሉ። ውጭ አገር የታተሙ መጻህፍት ወደ አገር ውስጥ ገብተው በድጋሚ እዚሁ እየታተሙ ይሰራጫሉ። በወታደራዊው ደርግ ሥርዓት በዓመት አንድ መጽሃፍ መመልከት ብርቅ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ታትመው ከሚሰራጩት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መጻህፍት መካከል አብዛኞቹ በህዝብ ውክልና ሥልጣን የተረከበውን ፓርቲና በአጠቃላይ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚቃወሙ ናቸው። ይህ የሆነው ሃሳብን የመግለጽ መብት በህገ መንግሥቱ በመረጋገጡ ነው። ከመጽሃፍት በተጨማሪ ዘፈኖች፣ ፊልሞች፣ የመድረክ ቲያትሮች ያለምንም ቅድመ ምርመራ ተዘጋጅተው ለህዝብ ይቀርባሉ። ይህም በህገ መንግሥቱ የተረጋገጠው የአመለካከትና ሃሳብን የመግለጽ መብት ውጤት ነው።
በአጠቃላይ ሃሳብን የመግለጽ መብት መገለጫ የሆነው የፕሬስ ነጻነት ዓላማ ዴሞክራሲን ማጎበት፣ ሠላምን ማስፈንና ልማትን ማቀላጠፍ እንዲሁም ማዝናናት ነው። ፕሬስ ከዚህ ውጭ ዓላማ የለውም። የፕሬስ ነጻነት በህዝቦች መካከል ግጭት የመፍጠር፣ በሐሰተኛ መረጃ መንግሥትና ህዝብን የማራራቅ፣ ጦርነት የመቀስቀስና ሽብርተኝነትን የማበረታታት፣ የግለሰቦችንና ህጋዊ ሰውነት ያላቸውን ተቋማት መልካም ስምና ዝና በሐሰት የማጥፋት መብትን አያጠቃልልም። ይህን ማድረግ በህግም በሙያው ሥነ ምግባርም የተከለከለ ወንጀልና ፀያፍ ነው። የፕሬስ ነጻነት ገደቦች እነዚህ የህዝብና የግለሰብ መብቶችና ነጻነቶች ብቻ ናቸው። ከዚህ ውጭ ያለው ገደብ ሰማይ ብቻ ነው።