ኢትዮጵያን በሰፊ ድንበር ከሚያዋስኗት የምስራቅ አፍሪካ አጎራባች ሀገራት መካከል ሪፐብሊክ ሱዳን አንዷ መሆኗ የሚታወቅ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ የኢትዮ-ሱዳን ዘመናትን ያስቆጠረ ጉርብትና ፤ ሰሞኑን ኢትዮጵያን ጎብኝተው የተመለሱት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ፊልድ ማርሻል ኦማር ሐሰን አልበሽር ከመጡበት ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ጋር በሚያያዙ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን መሰረተ ሃሳብ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
የኢትዮ-ሱዳን መንግስታት አጠቃላይ ግንኙነት የሚገለፅበትን እውነታ ሁለቱ ሀገራት፣ ለመላው ምስራቅ አፍሪካ አርአያ የሚሆን የህዝብ ለህዝብ ጠንካራ ትስስርን መስረት ያደረገ መልካም ጉርብትና እንደገነቡ የሚያመለክት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ሀሳቤ ማጠናከሪያ የኢትዮ- ሱዳን ህዝቦችና መንግስታት ተጨባጭ እውነታዎች መካከል አንዳንዶቹን ብንመለከት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በኢትዮ- ሱዳን ህዝቦች መካከል ስር የሰደደ የአፍሪካዊ ወንድማማችነት ስሜት መኖሩን ከሚያሳዩን የመልካም ጉርብትና መገለጫዎች ቀዳሚ ስፍራ የሚይዝ ሆኖ በተለይም የሁለቱ ሀገራት ሙዚቃ በእጅጉ የሚወራረሳቸው የጋራ ባህሪያት ያለው መሆኑ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ የሚስተዋለውን የኢትዮጵያና የሱዳን ሙዚቃ የቅኝት መወራረስ ጉዳይ ለዘርፉ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች በመተው ፣ ለሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር መፈጠር ምክንያት ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉትን አንኳር ነጥቦች መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ የኢትዮ-ሱዳን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ታሪካዊ ዳራ ለመዳሰስ ሲሞከር አሁንም የተሻለ ማሳያ ሊሆነኝ የሚችለው፤የሁለቱ ተጎራባች ሀገራት የሙዚቃ ጥበብ ባለሙያዎች የቋንቋ ድንበር ሳይገድባቸው፤ አንዱ የሌላውን ዜማ በማቀንቀን (በመዝፈን) የባህል ልውውጥ ትርጉም ባለው መልኩ እየዳበረ እንዲመጣ እያደረገ ይገኛል፡፡
ለአብነት ያህልም ታዋቂዎቹ የሱዳን ድምፃዊያን እነ መሐመድ ዋርዲ፣እነ ሰኢድ ከሊፋና ከሴቶች ደግሞ እነ ሀናን ቡልቡላ ያዜሟቸውን ተወዳጅ የሱዳን ዘፋኞች እየተለማመዱ ያቀነቀኗቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች መኖራቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡ እንዲሁም ሱዳኖቹም የኛ ሀገር አንጋፍና ተወዳጅ ድምፃዊያን ካዜሟቸው የአማርኛ ዘፈኖች መካከል ጥቂት የማይባሉትን በተመሳሳይ መንገድ እያጠኑ ያቀነቀኑበት ሁኔታ እንዳለ የሚታወቀው ነው፡፡
ሌላው በከፍተኛ ድምቀት ያከበርነውን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም በዓል ድምቀት ለመስጠት ሲባል ሱዳናውያኑ ታላላቅ ድምፃዊያን አዲስ አበባ መጥተው እንደነበርና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ከባለቤታቸው ጋር መድረክ ላይ ወጥተው ሲደንሱ የታዩትም በሱዳኖቹ ተወዳጅ ዜማ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ማለትም ደግሞ የኢትዮ -ሱዳንን የህዝብ ለህዝብ ትስስር በፅኑ መስረት ላይ እንዲገነባ ከማድረግ አኳያ፤ በተለይም ተወራራሽ ቅኝት እንዳለው የሚነገርለት የሁለቱ ሀገራት ሙዚቃ የማይስተባበል አወንታዊ ሚና ስለመጫወቱ የሚያመላክት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
እንግዲህ ለአብነት ያህል የተዋሱት የኢትዮ-ሱዳን ተጎራባች ሀገራት ህዝቦች የግንኙነት መስመር መገለጫ ነጥቦች የሚያመለክቱት ጉዳይ ቢኖር፤ የእስከዛሬው ትስስራችን እምብዛም የሚታይ ኢኮኖሚያዊ ገፅታ አልነበረውም ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም የሁለቱን የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ትርጉም ባለው የኢኮኖሚ ትስስር ሳይደገፍ የቆየ መልካም ጉርብትና ይበልጥ መልካም ገፅታ እንዲላበስና ወደላቀ የአፍሪካዊ ወንድማማችነት ሊያሸጋግረው የሚችል አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እየተከፈተ እንደሆነ በግልፅ የሚያመላክት ወቅት ላይ መድረሳችን ይሰማኛል፡፡
ምንም እንኳን ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የኢትዮ-ሱዳንን ጉርብትና “መልካም” የሚባል ዓይነት ሆኖ እንዲቆይ ያደረገ የሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች ባህላዊ ዝምድና የታከለበት ማህበራዊ ግንኙነት ዛሬ የተጀመረ አለመሆኑ ቢታመንም ትርጉም ወዳለው ኢኮኖሚ ትስስር ሳይሸጋገር በመቆየቱ ምክንያት ይስተዋል የነበረውን ክፍተት ለመድፈን የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ የተከፈተው በተለይም የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ መገንባት ከጀመረ ወዲህ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ የውሃ ሀብቷ የመጠቀም መብቷን የሚያረጋግጥ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት መነሳቷን ያሳወቀችበትን ዜና ተከትሎ፤ ሱዳናዊያኑ ወንድሞቻችን ጉዳዮን ያለ አንዳች ማቅማማት እንደሚደገግፉት የገለፁበትን ሁኔታ ማስታወስ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡
በእርግጥ ሱዳን፤ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ላለው የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ገና ከመነሻው ጀምሮ ልባዊ ድጋፍዋን ስትገልፅ የተስተዋለችበት ዋነኛ ምክንያት፤ ጉዳዩ እርሷንም የሚጠቅም ሆኖ ስላገኘችው እንደሆነ ይገባኛል፡፡ በተለይም ደግሞ የዓባይ ወንዝ ውሃ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ቁልቁል መንጎድ በሚጀምርባቸው የክረምት ወራት ውስጥ፤ የታችኞቹን የተፋሰሱ ሀገራት ያጋጥማቸው የነበረው በድንገተኛ ደራሽ የጎርፍ አደጋ የመጥለቅለቅና ለፈርጀ ብዙ ጉዳት የመዳረግ ተፈጥሯዊ ክስተት፤ በግድቡ ግንባታ ምክንያት ሰው ሰራሽ መፍትሔ እንደሚበጅለት ሲታሰብ፤ ሱዳኖች ያሳዩት ድጋፍ የሚጠበቅ እንጂ የሚያስገርም አይደለም ማለት ይቻላል፡፡
የመረጃ ምንጮች እንደሚያመለክቱት፤ በተለይ የዓባይ ወንዝ ውሃ መሀል ለመሀል ከሁለት ከፍሏት እንደሚያልፍ የሚነገርለት የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም፤ ለበርካታ ጊዜ በጎርፍ የመጥለቅለቅ እድል ገጥሟታል፡፡ እንደዚህ አይነቱ አደጋ ከሚያስከትለው ኪሳራ ጋር በተያያዘ መልኩ ህይወታቸው የሚመሰቃቀል የመዲናዋ ነዋሪዎች ቁጥር ጥቂት እንዳልነበረና የሱዳን መንግስት ችግሩን ለመቋቋም ሲል እጅግ በርካታ ገንዘብ በየአመቱ ያወጣ እንደነበር ምንጮቹ ያስረዳሉ፡፡
ስለዚህ፤ የጎረቤት ሱዳን ህዝብና መንግስት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግዙፉን የህዳሴ ሃይል ማመንጫ ግድብ እንደምትገነባ ይፋ ማድረጓን ተከትሎ፤ ከመደናገጥ ይልቅ የድጋፍ ስሜት ባዘለ አወንታዊ አቋም ከጎናችን ሲቆሙ መስተዋላቸውም ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ይልቅስ የተፋሰሱን የውኃ ሀብት በፍትሀዊ ክፍፍል ለጋራ ጥቅም የማዋል ጉዳይ፤ በየትኛውም መልኩ ቢታይ የሚደገፍ እንጂ የሚያሳስብ ጎን ሊኖረው እንደማይችል አበክረው ለመገንዘብ አይቸገሩምና ነው ፡፡ ክረምት በገባ ቁጥር የካርቱም እምብርት ተደርጎ የሚወሰደውን አንዱርማን የምትባለው የከተማዋ ነዋሪዎች ሱዳናውያን በድንገተኛ ደራሽ የጎርፍ አደጋ እንጥለቀለቅ ይሆናል ከሚል ስጋት ጋር እየተፋጠጡ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩበት ጉዳይ ያበቃለት መሆን እረፍት የሚሰጣቸው ነው ፡፡
በግልፅ አነጋገር፣ የተፋሰሱ ሀገራት የሚያጥለቀልቅ የጎርፍ አደጋ ያስከትል የነበረው የዓባይ ወንዝ ውሃ፤ የግንባታ ሂደቱ እየተገባደደ ባለው የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ውስጥ ገብቶ፤ በሰው ሰራሽ ጥበብ እየተመጠነ የሚለቀቅ እንጂ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ በበጋው ወራት የሚዳከምና በክረምት ደግሞ ወደ ዱብ ዕዳነት የሚቀየር አይሆንም ተብሎ ይታመናልና ነው፡፡ ስለሆነም የዚህ መጣጥፍ ትኩረት የኢትዮ ሱዳን መንግስታት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደመሆኑ መጠን፤ ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለይም ለሱዳኖች ስለሚሰጠው ተጨባጭ ጥቅም ሲነሳ፤ ከላይ እንደተጠቆመው በክረምት ወራት ይከሰት የነበረውን በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋ ለመከላከል ሲሉ የሚያወጡትን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስቀርላቸው ተደርጎ መወሰዱ፤ ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው ቁልፍ ነጥብ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የእኛን ለም አፈር ጠራርጎ እየወሰደ የታችኞቹን ሀገራት ልዩ ልዩ የውሃ ግድቦች በደለል እንዲሞሉ ያደርግ የነበረው የጎርፍ አደጋ፤ ከእንግዲህ በከፍተኛ ደረጃ መጠኑ ይቀንሳል ተብሎ ስለሚታመንም፤ ደለሉን ለመጥረግ ተግባር ይውል የነበረውን ገንዘብ ለሌላ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሊያውሉት እንደሚችሉ ይነገራል፡፡ ሱዳናዊያኑ ምናልባት ገንዘቡን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሚያመነጨው 6ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ላይ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ለመግዛት ይጠቅማቸው ይሆናል ፡፡ ደግሞስ ፕሬዝዳንታቸው ኦማር ሐሰን አልበሽር አሁን ላይ ሀገረ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡበት ምክንያት ሌላ ምን እንዲሆን ይጠብቃል?
ለማንኛውም ግን፤ አልበሽር በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢፌዴሪ ጠቅላላ ሚኒስቴር ከአቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝና ጋር ተገናኝተው በሁለቱ አገራት የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ መክረዋል፡፡ ታዲያ የሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መንግስታት እጅጉን እየተጠናከረ የመጣ አጠቃላይ የግንኙነት መስመር አኳያ፤ ኢትዮጵያና ሱዳን አፍሪካን በኢኮኖሚያዊ አውታሮች ለማስተሳሰር የሚደረገውን አህጉር አቀፍ ጥረት የሚያሳይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምረዋል ብለን ብናምን ስህተት ተደርጎ ይወሰድብን ይሆን? ለማንኛውም ግን፤ ዛሬ በህይወት የሌለው ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ ፅፎት፣ ድምፃዊ አበበ ተካ ካዜመው የዘፈን ግጥም ላይ ጥቂት ስንኞችን ቀንጭቤ ለወቅቱ እንግዳችን ለፕሬዘዳንት አልበሽር መጋበዝ እፈልጋለሁ፡፡
ያ ሱዳን ሱዳኒ፤
የ አኒ የ አኒ፤
ሱዳን እንዱርማኒ፤
ካገሬ ወጥቼ፤ ያኔ በዚያን ጊዜ ዘመን
እንኳን ክሽን ዶሮ፤ ባይኔ ሲዞር ጎመን
ማን ነበር እንዳንቺ፤ ለነፍስ የሚታመን፡፡
ለፍቅር የሚታመን፡፡
ያ ሱዳን ሱዳኒ፤
ያ ሱዳን ፈናኒ፤
የ አኒ አኒ የ አኒ…