ሳተላይት መገንባትም ማምጠቅም እንችላለን           

ዘ ኢኮኖሚስት በአለማችን የተከበረ በመስኩ አንቱ የተባሉ ምሁራን ሰፊ ትንተና የሚሰጡበት ታዋቂ አለም አቀፍ ሳምንታዊ መጽሄት ነው፡፡ የምእራቡን አለም (የኒዮሊብራሎቹን) ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ ነው፡፡ በአለማችን ፈጣን የሆነው ማሕበረሰባዊ እድገት የአስተሳሰብና የአመለካከት ስርነቀል ለውጥ አምጥቶአል፡፡ የምእራቡ አለም ኢኮኖሚስቶች በራሳቸው ስሌትና ቀመር ሊሆኑ አይችሉም ያሉዋቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጦችና እድገቶች በአለማችን ታይተዋል፤ የቀድሞውን ትንበያ ቀመርና ስሌቱንም ገለባብጠውታል፡፡ በአንድ ሁኔታ ላይ ብቻ የሚረጋ ረግቶም የሚኖር የኢኮኖሚ ቀመር የለም፡፡ ፈጣንና ስርነቀል የሆነው ሕብረተሰባዊ ለውጥ ይዞአቸው የሚመጣቸው ያልተጠበቁ ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ ግን ደግሞ ሆነው የተገኙ ለውጦች አሉ፡፡

ቻይናም ሆነች ሩሲያ፤ ሰሜን ኮርያ እንዲሁም የኤሽያ ታይገርስ ተብለው ይጠሩ የነበሩት ሀገራት በየራሳቸው የኢኮኖሚ ቀመር በመመራት ነው ታላላቅ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ያስመዘገቡት፡፡

ከዛሬ 50 አመታት በፊት ቻይና እንዲህ ዛሬ የደረሰችበት የኢኮኖሚ ታላቅነትና ተአምር ትሰራለች፤ እዚህም ትደርሳለች ብሎ የገመተ የምእራቡ አለም ኢኮኖሚስት አልነበረም፡፡ ቻይና የአለማችን ግዙፍ፣ 1 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር ነች፡፡ ሕዝቦችዋን በበቂ ሁኔታ ከማኖርም አልፋ ዛሬ የአለም ሁለተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመሆን የበቃችው በራስዋ የኢኮኖሚ ቀመርና ስሌት በመመራት ነው ታላቅ የተባለ እመርታዊ እድገት የጨበጠችው፡፡ እንደምናየውም ለሌላውም አለም እየተረፈች ትገኛለች፡፡

ከዛሬ 65 አመታት በፊት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በተባበሩት መግስታት የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመወጣት ኮርያ ሲዘምቱ የያኔዋ ኮርያ እጅግ በጣም ድሀ ሀገር ነበረች፡፡ ዛሬ የአለማችን 8ንተኛ ኢኮኖሚ ለመሆን በቅታለች፡፡ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነትና ለነጻነትዋ ያደረጉትን ታላቅ ተጋድሎ ባለመርሳት በኢትዮጵያም በብዙ መልኩ እገዛና እርዳታ እያደረገች ነው፡፡

አንድ ሀገር ተግታና ጠንካራ የራስዋን አዋጪ የኢኮኖሚ ቀመርና የስራ ፈጠራ ከፍታና ሀገራዊ የህዝብ ተሳትፎ ይዛ እስከሰራች ድረስ ከድሕነት የማትወጣበት፣ ወደላቀ የእድገት ምእራፍ የማትሸጋገርበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ዋናው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲውና ቀመሩ የሚነደፍበት የልማት ስትራቴጂ ነው፡፡

ይሄን መንደርደሪያ ማንሳት የተፈለገው በቅርቡ አፕሪል 5 ዘ ኢኮኖሚስት “Reaching for the sky: Why Ethiopia is building a space programme” በሚል ርእስ ያወጣው ኢትዮጵያን የተመለከተ ዘገባ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የራስዋን የሕዋ ፕሮግራም ለምን ትገነባለች? የሚል ጥያቄን አንስቶ ይበዛባታል፤ በትንሹ ብትሰራ ተጠቃሚ ነች፡፡ 5.6 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ በሚያስፈልገው ሰአት የሕዋ ግንባታ ማድረጉ ግራ ያጋባል ሲል አስነብቧል፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው፤ ኢትዮጵያ ድሀ ሀገር ናትና የጠፈር የሕዋ ምርምር ማእከል መገነባቷ፣ ሳተላይት ማምጠቋ ይበዛባታል እያለ ነው ዘ ኢኮኖሚስት፤ የሚገርመውም ይሀው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጥንታዊና ቀደምት መንግስትነት በአለም ታሪክ ሁሉ ተመዝግቦ የሚገኝ ነው፡፡ በእርስ በእርስ ጦርነት የተነሳ የነበራት ቀደምት ስልጣኔ አዘቅዝቆ ወደድህነትና ችግር ምእራፍ ተምዘግዝጎ ወረደ እንጂ ቀደምትና ገናና ስልጣኔ የነበራት ዛሬም ወደቀድሞው ገናና ታሪክዋ ለመመለስ ታሪክ እየሰራች የምትገኝ ሀገር ናት፡፡

በአክሱም ስልጣኔ ዘመን ብዙው የአለማችን ክፍል አይኑን ባልገለጠበት ሰአት ባሕር ኃይልና ተከፋይ መደበኛ ሰራዊት፤ የወርቅ መገበያያ ሳንቲም የነበራት፤ እደጥበብን ያስፋፋች፤ አዱሊስን የመሰለ ታላቅ ወደብ የነበራት ከቀይ ባህር እስከ ኤደን ባሕረሰላጤ አልፋም እስከ ፖርት ዘይላና በርበራ ማዶ ተሻግራ እስከ የመንና ሱአዲ አረቢያ ድረስ ትመራና ታስተዳድር የነበረች ሀገር ስለመሆንዋ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

ኢትዮጵያ የራስዋ ፊደል፤ የዘመን አቆጣጠር ጥንትም የነበራት ሀገር ነች፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ በገነነበት ዘመን አቻዎችዋ የነበሩት መንግስታት የባይዛንታይን ሮማ ኢምፓየር፤ እነእንግለዝ፤ ጀርመን፤ ፈረንሳይ፤ ጃፓን፤ ስፔን፤ ፖርቹጋልን የመሳሰሉት ነበሩ፡፡ ይሄንን ማንሳት የተፈለገው ዘ ኢኮኖሚስት የኢትዮጵያን የቀደመ ማንነት ባለመረዳት በአሁኑ ሰአት ሳተላይት ወደሕዋ ማምጠቅ ለምን ያስፈልጋታል የሚለውን ሀሳብ በመሰንዘሩ ነው። ዛሬ የሕዋ ቴክኒዮሎጂ ለኢትዮጵያ ከምንም በላይ ያስፈልጋታል፡፡ ለምን ቢሉ፣ ግዙፍ በሆነ ሁኔታ ኢኮኖሚዋ  እያደገና እየጎለበተች የመጣች ሀገር ነችና ነው፡፡

በውጭ የሳተላይት ኮሚኒኬሽን ጥገኛ ከመሆን ይልቅ ራስን መቻልና ሀገራዊ እድገትን ማቀላጠፍ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ሲያጠቃን የኖረውን ድርቅና የአየር ንብረት መዛባት አስቀድሞ ከመከሰቱ በፊት ለማወቅና ለመከላከል እንዲቻል የሳተላይት መረጃዎች ከምንም በላይ አስፈላጊ ናቸው፡፡

የአየር ትንበያው ለቅድመ መከላከሉ ትልቅ ግብአት ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያ የምታመጥቀው ሳተላይት ዘ ኢኮኖሚስት እንዳለው ለስለላ ስራ አይደለም፡፡ ይሄም ቢሆን አንዲት ሉአላዊት ሀገር ራስዋን ከቅርብና ሩቅ ጠላቶችዋ ለመከላከል የግዴታ የምድርና የአየር ክልልዋን በሳተላይት መረጃዎች የመጠበቅ ግዴታ አለባት፡፡ ብዙዎቹ ታላላቅ ሀገራትም የሚያደርጉትም ይሄንኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ  አቅሟ እያደገ እስከመጣ ድረስ ይሄንኑ ከማድረግ የሚያግዳት ምንም ነገር የለም፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያን አቅም አሳንሶ መገመት ይሄን ብታደርግ ይሻላት ነበር የሚለው አስተያየት ልኬታ ውስጥ መግባት ከዘ ኢኮኖሚስት  አይጠበቅም፡፡

ቀላሉ ምሳሌ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ በራስዋ ገንዘብ ይሄንን በአለም 7ተኛ፤ በአፍሪካ 1 የሆነ ግድብ ትገነባለች ብሎ ያሰበም ሆነ የገመተ አልነበረም፡፡ ግን ሆነ፡፡ በመሆኑም ሊያደንቀው ይገባው ነበር፡፡ ይሄን ለማድረግ የበቃች ሀገርና ሕዝብዋ  ሳተላይት ቀርቶ ሌላም ብዙ ነገር ሊሰሩ እንደሚችሉ መጠራጠር አይቻልም፡፡

5.6 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እየጠበቀ ኢትዮጵያ ለሳተላይት ማምጠቅ የሰጠችው ቅድሚያ ግራ ያጋባል ሲል ዘ ኢኮኖሚስት የገለጸውም ነጥብ በራሱ መስመሩን የለቀቀ ነው፡፡ የሳተላይት ግንባታና ማምጠቁ ጉዳይ ድርቁ ከመከሰቱ በፊት የተያዘ እቅድና ፕሮግራም ሲሆን ድርቁን ኢትዮጵያ በራስዋ አቅምና ኢኮኖሚ ለመመከት ያደረገችው ከፍተኛ ርብርብ ከቀድሞዎቹ ዘመናት ሁሉ ይለያል፡፡ ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጣን በሆነ  ሁኔታ ብሔራዊ የአስቸኳይ እርዳታ ግዜ ስራዎችን በመተግበር ዜጎች ለከፋ አደጋ እንዳይጋለጡ የተደረገው ርብርብ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ በለጋሾች ጭምር አድናቆትና እውቅና አግኝቶአል፡፡

አንዱ ድርቁንና የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎችን አስቀድሞ ለማወቅና ለመከላከል መረጃ በመስጠት ረገድ የሚጠቅመው የራስ ሳተላይቶች መኖር ነው፡፡ ይህም ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ቢያንስ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግና መከላከሉን ለማዘጋጀት ይረዳል፡፡ ኢትዮጵያ የራስዋን ሳተላይት ወደ ሕዋ የማምጠቅ አቅምም መብትም አላት፡፡ ቅድሚያ ለምን ጉዳይ መሰጠት እንዳለበትም አሳምራ ታውቃለች፡፡

አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በራስ አቅም የመድረስ ሰፊ ስራ ከፌደራል ጀምሮ በሁሉም ክልሎች በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ በመሆኑ ለውጥ ተገኝቶአል፡፡ በዚህም ድርቁን ለመመከት ተችሎአል፡፡ ዛሬ የበለጠ እየተሰራ ያለው ስራ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከልና ለመመከት ብቻ ሳይሆን ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር በመላው ሀገሪቱ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡

በተራቆቱ መሬቶች ላይ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል በደን እንዲሸፈኑ የማድረግ፤ የመሬት መሸርሸርን ለመግታት የአፈርና ውሀ እቀባ ስራ፤ የተጎዱ መሬቶችን እንዲያገግሙ የማከም፤ በከባድ ዝናብ ወቅት የሚፈሰው ከፍተኛ ውሀ በተለያዩ ዘዴዎች ወደመሬት ውስጥ ሰርጎ እንዲገባና እርጥበት እንዲፈጥር የማድረግ፤ ትላልቅ ጉድጓዶችን በተለያዩ ቦታዎች በማዘጋጀት ውሀውን የማቆርና ለመስኖ ማለትም ለአትክልት ልማት የማዋል፤ ችግኞችን ለማፍላት የመጠቀም፤ ለከብቶች መኖ የሚውል ሳር እንዲበቅል ማጠጫ በማድረግና በመሳሰሉት ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

አሁን በተያዘው ሰፊ ስራ በመግፋት በእርግጠኝነት ድርቅን ከመከላከል አልፈን ድርቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለፈ ታሪክ የሚሆንበት ዘመን ላይ እንደርሳለን፡፡ በሌላም በኩል ሀገሪቱ አጠንክራ በመስራትዋ ከዚህ ቀደም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ላይ መገኘትዋ በአለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረለት እውነት ነው፡፡

ሰፊ መሰረተ ልማቶች ተዘርግተዋል፡፡ የሀገሪቱ ዘመናዊ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አድጎአል፡፡ የከተማና የረዥም ርቀት የባቡር መስመር ገንብታለች፡፡ ዘርግታለች፡፡ በአፍሪካ ቀደምትና ተወዳዳሪ የሌለው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አየር መንገድና ዘመኑ የፈቀደውን ድሪም ኤየር ላይነሮችና ኤየር ባሶች ቦይንግ ጀቶች ያላት ሀገር ነች፡፡

አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ታላላቅ ሆቴሎች ያላት ለቱሪስቶች ተመራጭ የሆነች፣ ጥንታዊ፣ በዩኔስኮ አመካይነት በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ባሕሎች እንዲሁም ታሪካዊ ቦታዎች፣ ገዳማትና መስጊዶች የሚገኙባት፤ አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች በብዛት ገብተው በተለያየ መስክ ኢንቨስት ያደረጉባትና ትላልቅ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚካሄዱባት፣ በስርነቀል ኢኮኖሚያዊ ለውጥና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡

የአፍሪካ ሕብረት መስራችና ዋና ጽ/ቤት፤ ለአውሮፓ ሕብረት ከኒውዮርክና ከቤልጂየም ቀጥሎ አዲስ አበባ ሶስተኛ ከተማ የሆነችበት፤ ታላላቅ አለምአቀፍ ኮንፈረንሶችና ስብሰባዎች የሚካሄዱባት፤ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የአለምም የፖለቲካ መዲና እስከመሆን የደረሰች ታላቅ ሀገር ነች ኢትዮጵያ፡፡ ይሄ እንደ ዜጋ በአያሌው ያኮራናል፡፡

ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከእነዚህ አጠቃላይ እውነቶች ስንነሳ ኢትዮጵያ ለግዜው በውጭ ጣቢያ ተጠቅማ የራስዋን ሳተላይት ወደ ሕዋ ለማምጠቅ ዝግጁ ብትሆንም በእርግጠኝነት የራስዋን የሳተላይት ግዙፍ ጣቢያ ትገነባለች፡፡ የራስዋንም ብዙ ሳተላይቶች በሕዋ ላይ ትለቃለች፡፡ በውጭ የኮምኒኬሽን ጣቢያዎች ጥገኛ የምትሆንበት ሁኔታም ያበቃል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች ዛሬ ላይ በሀገር ቤት በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም ወደፊት ከፍተኛ ቁጥር ይኖራቸዋል፡፡ ዛሬም በስደት ወደ ተለያዩ ሀገራት ሄደው አውሮፓና አሜሪካ በተለያዩ የምርምር ጣቢያዎች የሚሰሩ ከፍተኛ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች እንዳሉ ልንረሳውም አይገባም፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን በየግዜው እየመጡ ለወንድምና እህቶቻቸው ስልጠና ሊሰጡ በምርምር ጣቢያው ሊሰሩ ሊያሳድጉትና ሊያሰፉትም ይችላሉ፡፡ እንጦጦ የተገነባው የኢትዮጵያ የሕዋ ምርምር ጣቢያ መነሻ እንጂ መድረሻችን አለመሆኑም ሊታወቅ ይገባል።

ኢትዮጵያ ብዙ ታላላቅ ተራራዎች ያላት ሀገር ናት፡፡ ራስ ዳሽንም ሌሎችም ላይ ግዙፍ የጠፈር መመልከቻ መሳሪያ መትከል ይቻላል፡፡ በርግጥ፣ ዘ ኢኮኖሚስት ለምን አቅማችንን አሳንሶ ገመተን ነው እንጂ ያልነው የኢትዮጵያውንን ሕልም አልካደም፡፡

 

ዘ ኢኮኖሚስት ጥንታዊው ቅዱሱ የላሊበላ ከተማ በኢትዮጵያ ሰሜን ተራሮች ከባህር ወለል በላይ በ2ሺ 500 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ከዋክብት ተመልካቾች በላሊበላ አካባቢ ያሉ ተራራዎች አንድ ቀን አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መመልከቻ ማማ ኖሮት ትላልቆቹን በቺሌና በሐዋይ የሚገኙትን ግዙፍ የሕዋ መመልከቻ ማማዎችን የሚቀናቀን፣ የሚፎካከር ይሆናል ብለው ሕልም ያልማሉ፡፡ በወቅቱም ኢትዮጵያ ከዋክብቶችን በሰማይ አትኩሮ ከመመልከት በላይ የበለጠ ስራ ለመስራት ተስፋ ታደርጋለች፡፡ የራስዋን ሳተላይት ማምጠቅም ትሻለች ብሎአል፡፡  .

ዘ ኢኮኖሚስት በጥር ወር የኢትዮጵያ መንግስት በቻይና የተሰራ የሲቪል ሳተላይት በውጭ ከሚገኝ የሮኬት ጣቢያ ጋር ተደርቦ በቀጣዮቹ አምስት አመታት የሚያስወነጭፍ መሆኑን ገልጾአል፡፡ የሮኬቱ ንድፍና ጥበብ ኢትዮጵያዊ በሆኑ መስፈርቶች አሰራርና ቅርጽ ነው የሚሰራው፡፡ ሰብሎችን የአየር ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር ጥርጥር በሌለው ሁኔታ ጎረቤቶችንም ለመሰለል ይውላል፡፡ መንግስት የራሱን የኮሚኒኬሽን ሳተላይት በማወንጨፍ በውጭ ቴሌኮሞች ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ ይፈልጋል ብሎአል፡፡ ይሄም ትልቅ ዜና ነው፡፡

የራስዋን ሳተላይት በምሕዋርዋ ላይ በማዋል ኢትዮጵያ ቀደም ብለው ይህን ያደረጉትን የአፍሪካ ሀገራት ምርጥ ቡድኖች ትቀላቀላለች፡፡ ናይጀሪያ ከ2003 ጀምሮ አምስት ሳተላይቶችን ወደሕዋ ለማስወንጨፍ ከፍላለች፡፡ ናይጀሪያ ከሳተላይቶቹ ጥቂቶቹ አሸባሪነትን ለመዋጋት እንደጠቀሙዋት ትናገራለች፡፡ ደቡብ አፍሪካም በርካታ ሀገር ውስጥ የተሰሩ ሳተላይቶችን በሕዋ ላይ አስቀምጣለች ሲል ዘ ኢኮኖሚስት ጽፎአል፡፡

ግብጽ 2ለት የመሬት መመልከቻ ሳተላይት ያመጠቀች ሲሆን ሁለቱም አልተሳካላቸውም፡፡ ወድቀዋል፡፡የግል ካምፓኒ የሆነው ናይልሳት ኮምኒኬሽን በተሳካ ሁኔታ ይንቀሳቀሳል፡፡ ኬንያ አንጎላና ጋና ለመቀላቀል ሀሳብ ያላቸው መሆኑንም መጽሄቱ ገልጾአል፡፡

ኮሚኒኬሽንን ለማስፋት መቻል ወይንም ፎቶዎችን ከሕዋ ላይ ማንሳት ጥቂት የኢኮኖሚ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪትዋን በካርታ ማስፈር በመሬት ላይ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት ይረዳል፤ የግብርና ምርታማነትን ለማስፋፋትና ከተሞችንም በበለጠ ደረጃ ለማቀድ ያግዛል፤ በሕዋና በሳይንስ ላይ ኢንቨስት ማድረግ የኢንዱስትሪ እድገትን ያፋጥናል የሚል እምነት አለው ሲልም ዘ ኢኮኖሚስት ይገልጻል፡፡

ከመነሻው ጀምሮ ልንሄድበት የፈለግነው አከራካሪው የዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ በተለይ በእዚህኛው መስመር ላይ የሰፈረው ነው፡፡እነዚህን ጥቅሞች ለማግኘት ኢትዮጵያን የመሰሉ ሀገሮች የራሳቸው ሳተላይት እንዲኖራቸው መፈለግ፣ መገንባት ወይንም የራሳቸውን ሳተላይት ማምጠቅ አለባቸው ወይ? ሲል ይጠይቃል፡፡

ሳተላይት እንዲኖር መፈለግ፤ መገንባት፤ ማምጠቅ አለባቸው ወይ? የሚለው ጥያቄ በ ኢኮኖሚስት መነሳቱ ያነጋግራል፡፡ ድሆች ስለሆኑ አቅም ስለሌላቸው በስልጣኔ ስላልገፉ ሳተላይት ሊኖራቸው አይገባም ነው ወይንስ ሀገራት የየራሳቸው ሳተላይት ተጠቃሚ ከሆኑ ምእራባውያን የሚያገኙት ጥቅም ስለሚቀርባቸው ሊገነቡ ሊኖራቸውም አይገባም ማለት  ነው?

ምእራባውያን በአጠቃላይ በአለምአቀፍ ደረጃ ያለውን የአየር ንብረት፤ የተፈጥሮ አደጋ፤ የየሀገራቱን ስውርና በከርሰ ምድር ያለሀብት፤ የጦርና የሰራዊት ንቅናቄ ጭምር የሚያጠኑትና የሚከታተሉት ምስጢሩን የሚያገኙት ስለላም የሚያካሂዱት ወደ ሰማይ ባመጠቁዋቸው ፈርጀ ብዙ ስራ ባላቸው ሳተላይቶቻቸው አማካኝነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአፍሪካ ቴሌኮም ሳተላይት ለስልክ ወዘተ በመጠቀሙ በቀደሙት አመታት በአመት ለአውሮፓ ቴሌኮም 500 ሚሊዮን ዶላር ይከፍል ነበር፡፡ የአፍሪካን እዳ በሙሉ በመክፈል አፍሪካ የራስዋ የሳተላይት ቴሌኮም እንዲኖራትና ለአውሮፓ ቴሌኮም የሚከፈለው ገንዘብ እንዲቆም ያደረጉት በዚህም አፍሪካ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስቻሉት የሊቢያው መሪ ኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ ነበሩ፡፡

ወደእኛ እውነት ስንመለስ ኢትዮጵያ የራስዋን የሳተላይት ጣቢያዎች መገንባትና ማምጠቅ ሙሉ በሙሉ ትችላለች፡፡ ለሀገሪቱ ልማትና እድገት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል፤ ድርቅን የአየር ንብረት መዛባትን፤ የመሬት መንቀጥቀጥን፤ ከፍተኛ አውሎ ንፋሶችን፤ ወዘተ ቀድሞ ለማወቅ ያግዛል፡፡ የሰብል ምርቶችን ግብርናውን ለማሳደግ የኢንዱስትሪና የሳይንስ ምርምር እድገትንም ለማፋጠን ለሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ይጠቅመናል፡፡ ባጭሩ፣ ሳተላይት መገንባትም ሆነ ማምጠቁ ይገባናል፤ ያስፈልገናልም። ግልፅ ነው፣ ዘ ኢኮኖሚሰተ??