የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ግንባታችን

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን ዋነኛ ግብ ሀገራችንን በ15 አመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ጋር እንድትቀላቀል ማድረግ ነው። የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂያችን የሚጨምረው ነገር የመካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ የመገንባት ራእያችንን የጥራት ደረጃ ከፍ ማድረግ ነው። በዚህም መሰረት የምንገነባው የመካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ አረንጓዴ ነው። ይህም የሚሆነው የኢኮኖሚያችን መጠንና መዋቅር ወደ መካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ በምንቀይርበት ወቅት ስትራቴጂያችን በወጣበት አመት የነበረውን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መጠን ባለበት እንዲቆይ በማድረግ መሆኑን የዘርፉ ልሂቃን ይጠቅሳሉ። በወቅቱ ሀገራችን በየአመቱ የምትለቀው አማቂ ጋዞች መጠን 150 ሜጋ ቶን (በካርቦን ዳይኦክሳይድ ሲለካ) ነበር። መንግስት የአረንጓዴ ልማት አማራጭን ባይከተል ኖሮ ይኖር የነበረው አመታዊ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መጠን 400 ሜጋ ቶን ይደርስ እንደነበር ነው መረጃዎች የሚጠቅሱት።  

ስለሆነም በ15 አመታት ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሀገሮች ለመቀላቀል እንደሚሰራ መንግስት በ2003 አስታውቋል። ለዚህ ራእይ መሳካት የሚረዳውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂንም በዚሁ ወቅት ይፋ አድርጓል። በአሁኑ ወቅት በየሴክተሩ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን (ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሴክተርን) መገንባት የሚያስችልን ሰትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። በግብርና ሴክተራችን ስትራቴጂው በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን በሌሎች ሴክተሮች ደግሞ ስራው እየተፋጠነ ነው።  

በሁለተኛው ዙር የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት አማራጭ የለሽ ጉዳይ መሆኑ ተመልክቷል። ሰነዱ ጥናቶችን ጠቅሶ እንዳሰፈረው አስፈላጊ እርምጃዎች ከወዲሁ እስካልተወሰዱ ድረስ እ.ኤ.አ እስከ 2050 ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ የሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 7 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እስከ 2 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊያድግ እንደሚችል ተገምቷል። ይህ የሙቀት መጠን የምግብ ዋስትና እንዳይረጋገጥ፣ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዲከሰቱ፣ የመሬት መጎሳቆልና የመሠረተ ልማት ውድመት እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል። ይህንን አደጋ ለመቀነስ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተፋሰስ ልማት በህዝባዊ ንቅናቄ ሰፊ ጥረት የተደረገና አጥጋቢ ውጤት እየተመዘገበበት ሲሆን በሁለተኛው የእቅዱ ዘመን ይህ መልካም ጀምር በተለየ ትኩረት ተጠናክሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ሰነዱ ይጠቅሳል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የተፈጥሮ ልማትና ሃብት አስተዳደርን ማጠናከር፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መጣጣም (Adaptation to climate change) እና የከባቢ አየር ሙቀት ሳቢ ጋዞች ልቀት ሥርየት (Mitigation of Greenhouse Gases) ዋነኛ ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑም በእቅድ ሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂ መሠረታዊ መነሻ የከባቢ ሙቀት ሳቢ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። ለአርሶ እና  አርብቶ አደሩ ገቢ መሻሻል በሚረዳ ሁኔታ የሰብልና የእንስሳት ምርትን ማሻሻል ነው። ስለሆነም የካርቦን ልቀትን ለመቀነስና ለኢኮኖሚና ሥነምህድራዊ አገልግሎት ለማዋል ካለው ፋይዳ አኳያ ደንን መጠበቅና ማልማት አስፈላጊ ይሆናል።  ከታዳሽ ኃይል ምንጭ የኤሌክትሪክ ኃይል በሰፊው በማመንጨት ለአገር ውስጥና ለተጠናው ገበያ ማቅረብ እንዲሁም ከዘመናዊ ኢነርጂ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በትራንስፖርት ኢንዱስትሪና በሕንጻ ኮንስትራክሽን ዘርፎች በመጠቀም እምርታዊ ለውጥ ማምጣት የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።   

በእርግጥ እና ከላይ በተመለከተው አግባብ  የ2002 የኢትዮጵያ አመታዊ የሙቀትአማቂ ጋዞች የልቀት መጠን 150 ሜጋ ቶን ነው። በዚህ መሰረት ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ ያለባት ተጠያቂነት ከቁጥር የማይገባ ነው። ኢኮኖሚያችን ለብዙ አመታት በተከታታይ እድገት ካስመዘገበ በኋላም እንኳ ያለው አመታዊ የነፍስ ወከፍ ልቀት መጠን ሁለት ቶን ነው። ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም ትንሽ ነው። ለምሳሌ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ አማካኙ የነፍስ ወከፍ ልቀት አስር ቶን ሲሆን በአሜሪካና አውስትራሊያ ደግሞ ሃያ ቶን መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ ። ስለሆነም የኢትዮጵያ አመታዊ የልቀት መጠን ከአለም አመታዊ የልቀት መጠን ጋር ሲነጻጸር 0.3 ከመቶ ነው።

በግብርናዉ ሴክተር የከብት እርባታና የሰብል ምርት በቅደም ተከተል ዋነኞቹ የሙቀት-አማቂ ጋዞች ልቀት ምንጭ ናቸው። ሃገራችን በአሁኑ ወቅት ያላት የቀንድ ከብት መጠን ከ50 ሚሊዮን ተሻግሯል። እንዲሁም 100 ሚሊዮን የሚጠጉ የቀንድ-ያልሆኑ የቁም ከብቶች በሃገሪቱ እንዳለ ይታመናል። የቁም ከብቶች ሚቴን የተባለውን ሙቀትአማቂ ጋዝ ከምግብ ማብላላት-ስርአታቸው ጋር በተያያዘ ይለቃሉ። እንዲሁም ናይትረስ ኦክሳይድ የተባለ ሙቀትአማቂ ጋዝ ከቁም ከብቶች እበት ጋር ተያይዞ ወደ ከባቢው አየር ይለቀቃል። ከሀገራችን አመታዊ ሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ዉስጥ 40 ከመቶ የሚሆነው (65 ሜጋ ቶን) ከቁም ከብት ጋር የሚያያዝ ነው። የሰብል ምርት የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ምንጭ የሆነበት ምክንያት ማዳበሪያ ስለምንጠቀምና የሰብል ቅሪቶች ሲበሰብሱ ሙቀት አማቂ ጋዝ ስለሚፈጥሩ ነዉ።

ከደን ሀብታችን ጋር ተያይዞ የሚመጣዉ የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን 55 ሜጋ ቶን ነዉ። ከዚህ ውስጥ 50 ከመቶዉ የሚሆነው ለእርሻ ተብሎ ከሚካሄደው የደን ምንጠራ ምክንያት መሆኑን የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት እንዲሁም የአካባቢ እና ደን ሚንስትር መረጃዎች ያረጋግጣሉ። የተቀረው ደግሞ የማገዶና ጣውላ ፍላጎትን ለማሟላት  በሚደረግ ህጋዊና ሕገወጥ የዛፍ ቆረጣ ጋር ይያያዛል። በትራንስፖርት ሴክተር 75 ከመቶ የሚሆነዉ ልቀት የሚመነጨዉ ከየብስ ትራንስፖርት ሲሆን በዋናነት ከሸቀጦች ማጓጓዣና ኮንስትራክሽን መኪኖች ጋር ይያያዛል። 23 ከመቶ የሚሆነዉ ከአየር ትራንስፖርት የተነሳ ነዉ።

የሀይል ሴክተሩ ድርሻ ትንሽ የሆነበት ምክንያት የሀይል ምንጫችን ታዳሽ በመሆኑ ነዉ። 90 ከመቶ የሚሆነው የሀይል ምንጭ የሀይድሮ-ኤሌክትሪክ ነው። በሀይል ምርት የተነሳ ሀገሪቱ የምትለቀው አመታዊ የጋዝ መጠን ከ5 ሜጋ ቶን ያነሰ ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ሀገር አመታዊ የልቀት መጠን በአማካኝ 25 ከመቶ የሚሆነው የሚመነጨው ከሀይል ምርት ጋር በተያያዘ ነዉ።

ያም ሆኖ ግን ሀገራችን በምትከተለዉ ታላቅ የእድገት ጎዳና እና ከሚጠበቀው የሕዝብ ቁጥር እድገት ጋር ተያይዞ  የሃገራችን የልቀት መጠን ካለበት አመታዊ 150 ሜጋ ቶን ወደ 400 ሜጋ ቶን ያድጋል ተብሎ ይገመታል። የነፍስ-ወከፍ ልቀታችን ደግሞ ከ1.8 ወደ 3 ቶን ከፍ ይላል። ይህ የሚሆነው ግን ልቀትን ለመቀነስ ምንም ሙከራ ካልተደረገና እስከ አሁን የተጓዝንበትን ጎዳና ይዘን ከቀጠልን ነው።

 

ስለሆነም በሰብል ምርትና እና እንስሳት እርባታ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማስፈን፤ የአርሶአደሩን ገቢ መጨመርና፤ ልቀትን መቀነስ ያስፈልጋል።  ሃገራችን እስከዛሬ በተከተለችው የልማት አማራጭ መንገድ መቀጠልም ይገባል። ነገር ግን እንደወትሮው የሚደረገው የግብርና አሰራርና እድገት የሚያመጣቸውን መዘዞች ልብ ማለት ይገባል። ከመዘዞቹ አንዱ ከፍተኛ የሆነ የግብርና መሬት መስፋፋት ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ አሁን ያሉንን ደኖች በመመንጠር ነው።  

የአረንጓዴ ኤኮኖሚ የልማት አማራጭን የምንከተል ከሆነ  የግብርናውን ክፍለ-ኢኮኖሚ እድገት ሳንገታ እላይ የተጠቀሱትን መዘዞች ማስወገድ ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው፤ የግብርና መሬትን ከማስፋፋትና የከብትን ቁጥርን ከመጨመር ይልቅ፤ የከብትና የሰብልን ምርታማነት በመጨመር ነው።  

የተሻሻሉ ግብአቶችን በመጠቀምና ተረፈ-ምርትን በአግባቡ በማስተዳደር የግብርና መሬት መስፋፋትን መቀነስ፤ደኖችን መንጥሮ አዲስ የእርሻ መሬት ከመፍጠር ይልቅ የተራቆቱ አካባቢዎችን በማከምና አነስተኛ፤ መካከለኛ፤ እና ከፍተኛ መስኖዎችን በመጠቀም ተጨማሪ የእርሻ መሬት መፍጠር፤ ዝቅተኛ-ልቀት ያላቸዉን የግብርና ቴክኒኮችን (ለምሳሌ፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ፤ ካርቦን እና ናይትሮጅን ማመቅ የሚችሉ ተክሎች) ማስተዋወቅ፤ የእንሰሳት እርባታ ክፍለ-ኢኮኖሚዉን ውጤታማነትና አዋጪነት በማሳደግ ምርታማነትን መጨመር፤ የተሻለ የህክምና እና የገበያ አገልግሎቶችን በማቅረብ በእያንዳንዱ የቁም ከብት የሚገኘውን ምርት ማሳደግ፤ አንድ ከብት ከትውልድ እስከእርድ የሚቆይበትን ጊዜ ማሳጠር፤ዝቅተኛ ልቀት ያላቸውን የፕሮቲን ምንጮች (ለምሳሌ ዶሮ) ማስተዋወቅ፤ በስጋ ፍጆታችን የዶሮ ስጋን ድርሻ ሰላሳ በመቶ በመጨመር ከፍተኛ የሆነ ልቀት መቀነስ ይቻላል፤የእርሻ አሰራርን መካናይዝ ማድረግ፤ ለማረስና ለመውቃት ከከብት ይልቅ ማሽንን መጠቀም፣የግጦሽ መሬትን በአግባቡ በመጠቀም ምርትን እና በአፈር ውስጥ ታምቆ ያለውን የካርቦን መጠን መጨመር፣ የሙቀት-አማቂ ጋዞችን ከመቀነስ አልፈዉ የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ ያሳድጋሉ። የምግብ ዋስትናን ያረጋግጣሉ። እንዲሁም የግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚዉን ዘላቂነት ባለው መልኩ ያሳድጋሉ።