የኢፌዴሪ መንግስት ከሰላም ማስከበር አኳያ ዓለም አቀፋዊና አፍሪካዊ አስተዋጽኦውንና ኃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል፤ ዛሬም ድረስ እየተወጣ ነው። በዚህም የቀጣናው ኩራት መሆን ችሏል። በተለይም በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሠላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንድትሆን አስችሏል። እርግጥ እ.ኤ.አ. አዲሱ ሚሌኒየም ሲጀመር በቡሩንዲ ሁቱና ቱትሲ የተባሉ ጎሳዎቿ ግጭት ውስጥ ነበሩ።
ዘር ለይቶ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በአፋጣኝ ሠላም አስከባሪ ኃይላቸውን እንዲልኩ ከተደረጉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሀገር ነበረች። በዚህም ታሪካዊ አስተዋፅኦዋን አበርክታለች። በላይቤሪያም እንዲሁ። ላይቤሪያ ባለፈው የአውሮፓውያን አስርት ዓመታት መጨረሻ ላይ በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች። ሀገሪቱን ወደ ሠላምና መረጋጋት ጎዳና ለመመለስ በተደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ተሳትፎ ወደር አልነበረውም። በሀገሪቱ ሠላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግም ሚናውን ተጫውቷል።
በሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሠላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ መሆኗም ይታወቃል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም ብቻውን የተሰማራ ሠላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በማሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባር እያከናወነች ነው።
ሀገራችን በሁለቱም ሀገሮች መንግሥታትና ሕዝቦች ያላት አክብሮትም ከፍተኛ ነው። ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሠላም፣ ጸጥታና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ባለችው ሚና በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት አልባነትና አክራሪነት በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች።
በተለይም የአፍሪካ ህበረትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚሰጣት ማናቸውም የኃላፊነት ቦታዎች በገለልተኝነት ተግባሯን በመወጣት አንቱታን ማትረፍ ችላለች። ለዚህም በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ (አሚሶም) ጥላ ስር በመሆን የዓለም አቀፍ አሸባሪው አልቃዒዳ ክንፍ የሆነውን አልሸባብን ትርጉም ወደሌለው ደረጃ እንዲወርድ በማድረግ ቀጣናውን ከስጋት የመታደግ ስራዋን መጥቀስ ይቻላል።
በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታትም ሀገራችን በአደራዳሪነትና ሰላም የሚያስጠብቁ ኃይሎቿን ጭምር በመላክ ወንድም የሆነውን የዚያች ሀገርን ህዝብ ሰቆቃ ለማስወገድ ችላለች፤ ስደተኞችን በመቀበል ጭምር። ተግባሯን በገለልተኝነት በመከወኗም በአፍሪካውያንም ይሁን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተቀባይነቷን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገች መጥታለች።
እርግጥ ሠላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለፀገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመሥራት ላይ ትገኛለች። በሞሮኮና በአልጄሪያ፣ ናይጄሪያ ውስጥ የቢያፍራ የመገንጠል እንቅስቃሴን እንዲሁም በሱዳን የቤኛኛ እንቅስቃሴ ከማዕከላዊ መንግሥታት ጋር የነበራቸውን ግጭት በመፍታት ታሪካዊ አስተዋጽኦ ማበርከቷም የሚዘነጋ ሃቅ አይደለም።
ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን እያስመዘገበችው ያለው ልማታዊ እመርታ ተጠቃሽ ነው። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና የማዕከላዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ ትስሰር የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ ነው።
በመሠረተ-ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት ታደርጋለች። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች። ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጋር የመንገድ ግንኙነት በመፍጠር ለጋራ ጥቅም በመትጋት ላይ ትገኛለች። ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መሥመር ግንባታው ተጠናቅቆ ተመርቋል፤ ከኬንያ ጋር የሚያገናኘው መሥመርም ዝርጋታው እየተከናወነ ነው። ኢትዮጵያ ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያንም በተመሳሳይ ሁኔታ እንድትጠቀም በመጣር ላይ ትገኛለች።
ሀገራችን በምትከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መርህም ተቀባይነት ያላት ናት። በዚህ አስተሳሰቧም የአባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም አስፈላጊነቱን አምናም እየሰራች ነው። አብዛኛዎቹ የናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች ወደ ጋራ መግባባት እንዲመጡ አድርጋለች። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት 6 ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ሜጋ ዋት በማመንጨት ዓላማዋ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ጎረቤት ሀገሮችንም መጥቀም መሆኑን የማሳመን ስራዎችን እያከናወነች ነው።
በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን የተያዘውን ጥረትም በአፍሪካ እርስ በርስ መገማገሚያ ስልት (ኔፓድ) በንቃት ተሳታፊ ናት። በታላቁ መሪያችን በአቶ መለስ ዜናዊ ወቅትም ይሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወቅት ኔፓድ ውስጥ ወሳኝ ተሳታፊ ሆናለች።
የአህጉሪቱ ርዕሰ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የዓለም- አቀፍ ዲፕሎማሲ መናኸሪያ እንድትሆን ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች። ይህም ለአፍሪካውያን ታላቅ ኩራት ይመስለኛል። አፍሪካ ውስጥ አንድ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ መፍጠር ችላለች። ይህ ሁሉ ሀገራችን የምትከተለው የሰላም መርህ ውጤት መሆኑ አይካድም።
እናም የኢትዮጵያ የሰላም ፍላጎት በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተመሰከረለት ነው፤ ቀጣናውን በማወክ ተግባር ላይ ከተሰማራው የኤርትራ መንግስት በስተቀር። ሰላምን ያነገበ ማንኛውም ሀገር ሁሌም በሌሎች መወደሱና የችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሆኑ አይቀርም። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያን ሰላም ወዳድነት የሚያውቁ መንግስታት ሀገራችን እያደረገች ያለችውን ተግባር ሲያደንቁና ለመደገፍም ዝግጁ መሆናቸውን ሲገልፁ መስማት የተለመደ ነው።
ያም ሆኖ ኢትዮጵያ የራሷን ሰላም ከማስጠበቅ አልፋ ዛሬ ላይ ለቀጣናው መፍትሔ ሰጪ እየሆነች ነው። እንደህ ዓይነቱ በብቃት የታጀበ ተቀባይነት ደግሞ ዝም ብሎ የሚገኝ አይደለም። ጠንካራ ስራንና ስለ ሰላም ሲሉ ሁሉንም መስዕዋትነቶችን መክፈል ይጠይቃል። ከዚህ አኳያ ሀገራችን ለሰላም ስትል ብዙ ርቀት ተጉዛለች። በውጤቱም በቀጠናው ላይ አንዣበው የነበሩ የጦርነት ስጋቶችን አስወግዳለች። ለማስወገድም እየሰራች ነው።
ለሰላም መስራት ትሩፋቱ ብዙ ነው። የሌሎችን በተለይም የጎረቤቶችን ሰላም ማስጠበ መልሶ ራስን የሚከፍል ነው። ጎረቤት ሀገሮች ሰላም ከሆኑ ግጭት አይኖርም። ግጭት ከሌ ደግሞ ስደት አይፈጠርም። ስደት ካልተፈጠረ የሁሉም ሀገር ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ በሰላም በመኖር ምስራቅ አፍሪካን ወደ ልማት ጎዳና ያራምዳሉ። የእነዚህ ውጤቶች መገለጫም በሀገራችን ላይ ሊያርፍ ይችላል። እናም ሰላምን በመርህነት መከተል መልሶ የሚከፍል ተግባር በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ያሉት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ለሁሉም ሰላም!