ሀገራችን ስለ ልማት በሚያወሩ ተቋማትና ሀገራት ዘንድ አፍሪካዊቷ “ታይገር” የሚለውን ስያሜ ተጎናፅፋለች። ይህን ስያሜ ያገኘችው ያለ ምክንያት አይደለም። በተለይ ላለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት ባስመዘገበችው የዕድገት ውጤት መሆኑ አይካድም። ይህ ኢትዮጵያ በዕድገት መስክ ያስመዘገበችው ድል የሁሉም አፍሪካዊ ወንድሞቻችን መኩሪያና መመኪያ ነው ማለት ይቻላል።
ለማንኛውም የአፍሪካዊቷን የኢኮኖሚ “ታይገር” እመርታዎችን መጥቀስ ይገባል። እንደሚታወቀው ሀገራችን ላለፉት 15 ዓመታት በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች። ይህም ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ያላት ሀገር እንድትሆን አስችሏታል። የአፍሪካ መነሳሳት ተጠቃሽ ምሳሌ እንድትሆንም ያደረጋት መሆኑም እንዲሁ። ይህ ደግሞ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤት መሆኑ አይካድም። እንደሚታወቀው የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘው ዕቅድ ያለፉት አስር ዓመታት አፈጻጸም ሲቃኝ አበረታች እንደነበር በተለያየ አጋጣሚ ተገልጿል፡፡ ያለፉት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ዕድገት እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ አበረታች እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በግብርናው ዘርፍ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች የታዩትን መልካም ተሞክሮዎች በማስፋት አርሶ አደሩን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተሰርቷል። ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ አርሶ አደሩን ለማገዝ ጥረት ተደርጓል።
እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የመሳሰሉ ግብዓቶች በማቅረብ ረገድም ቀላል የማይባል ሥራ ተከናውኗል። ከዚህ አንጻር የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ያስቻለ እንቅስቃሴ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ። ምርጥ ዘርን የማራባትና ለአርሶ አደሩ የማከፋፈል ተግባር አንዱ እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ በማዕከል ደረጃ ካለው የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት በተጨማሪ ክልሎች እንደየአስፈላጊነቱ የምርጥ ዘር ማዕከላትን በማቋቋም አርሶ አደሩን በቅርብ እያገዙ ይገኛሉ።
ከኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቱ ያለውን የዘር ፍላጎት ለማሟላት በየጊዜው በሺህዎች በሚቆጠሩ ሄክታር መሬት ላይ ዘር የማባዛቱ ሥራ ይከናወናል፡፡ በየዓመቱም በአማካይ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ያህል የምርጥ ዘር ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተለያዩ ወቅቶች የተካሄዱ ግምገማዎች ውጤት እንደሚያሳየው የአገሪቱ የልማት ተግባራት በአበረታች ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ነው። በገጠርና በከተማ የሚኖረውን ኅብረተሰብ በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት በተያዘላቸው እቅድ መሠረት እየተከናወኑ ናቸው፡፡ ይህ የግብርና ምርትን የማሳደግ ሥራ በተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ለመምጣቱ ምስክር አያሻውም።
መንግስት የተለያዩ ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ፈቅዷል፡፡ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት የግብር የእፎይታ ጊዜን ሰጥቷል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ማደግ ሌላው ገጽታ የመሠረተ ልማት ግንባታ ነው፡፡ የቴሌኮም፣ የመብራት፣ የመጠጥ ውኃ እና የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ለአንድ አገር ምጣኔ ሀብት እድገት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው። በአገሪቱ ከሀያ ዓመታት በፊት የነበረው የመሠረተ ልማት ግንባታ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡
እንደ መንገድ፡ ቴሌኮምና መብራት የመሳሰሉት ዋና ዋና የመሠረተ ልማት አውታሮች በከተሞች ብቻ የተወሰኑ ነበሩ፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት መሠረተ ልማትን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት ተችሏል።
በማህበራዊ ልማት ዘርፍም በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉንና በወላጅ፣ በመምህራንና በተማሪዎች የተደራጀ ጥረት አመርቂ ውጤት መታየቱን አረጋግጧል፡፡ ቀደም ሲል በመላ አገሪቱ የትምህርት ማዕድ ተቋዳሽ መሆን ከሚገባቸው ዜጎች መካከል 19 በመቶ ወንዶች እና 16 በመቶ ሴቶች ብቻ ነበሩ የዕድሉ ተቋዳሾች፡፡
በቀደሙት ሥርዓቶች ለትምህርት ተቋማት መስፋፋትና ለፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት የተሰጠ ትኩረት አልነበረም፡፡ ከታች እስከ ላይ ድረስ የነበሩት የትምህርት ተቋማት ውስን ከመሆናቸውም በላይ የተቋቋሙት በከተሞች ብቻ ነበር፤ በአገሪቱ አንድም የግል ዩኒቨርስቲ ሆነ ኮሌጅ አልነበረም፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት ትምህርት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቷል፡፡ በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል፡፡ እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህጻን ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋንም ሰፍቷል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የሚታደሙበት ማዕድ ሆኗል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ተስፋፍተዋል፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርትን አስፈላጊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ህጻናት የምገባ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ምገባው ህጻናት በምግብ አቅርቦት ማነስ ምክንያት ከትምህርታቸው እንዳይሰናከሉ ማገዝ ችሏል፡፡
ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት ቤቶች ሥርጭት ኢ ፍትሃዊነትን ለማስወገድ በአገሪቱ እያደገ የመጣው የትምህርት ቤቶች ቁጥር ሥርጭት ፍትሃዊነቱን እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አንጻር ቀደም የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡
በትምህርት ሥርጭት ላይ የነበረው ኢፍትሃዊነት በክልሎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ኢፍትሃዊ ሥርጭት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተመጣጣነ ሁኔታ ማደግ አለመቻላቸውንና የልማት ተጠቃሚነታቸውም ላይ ልዩነት መፍጠሩ አልቀረም፡፡
በአገራችን ባለፉት ሃያ ዓመታት ከተሰሩት ተግባራት አንዱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የትምህርት ሥርጭት እንዲኖር መደረጉ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው የትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
በአገሪቱ የነበሩት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲታደሱና የማስፋፊያ ግንባታ ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ሺህ በላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በልዩ ትኩረት እንዲስፋፉ በመደረጉ የተቋማቱ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ታይቷል፡፡ ተማሪዎች ሥራ ፈጣሪ እንጂ ክፍት ሥራ ፈላጊ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ተግባር እየፈፀሙ ነው- የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት ወጣቶች ሥራ ፈጣሪና ባለሙያ ሆነው የሚሰለጥኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በአገሪቱ ሥራ ፈጣሪና በራሱ የሚተማመን ወጣት ማፍራት የሚችሉ ከአምስት መቶ በላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተቋቁመው የሥልጠና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአንድ አገር ለውጥ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ባለፉት 26 ዓመታት በአገሪቱ የነበሩት ሁለት ዩኒቨርስቲዎች እንዲስፋፉና ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው በመደረጉ የቅበላ አቅማቸው አድጓል፡፡
የወጣቱን የትምህርት እድል ለማስፋት የግል የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ተደርጓል። ይህ አገሪቱ ለልማት የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የግል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ የተማረና ብቃት ያለው ባለሙያ በሌለበት አገር ዘላቂ ልማት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያሳየችው ውጤትም አገሪቱ እያስመዘገበች ላለው የምጣኔ ሀብት እድገት መሠረት ነው፡፡
በአገራችን ለተመዘገበው ሁለንተናዊ ለውጥ ሌላው መገለጫ በጤናው ዘርፍ የተገኘው ስኬት ነው፡፡ ጤናማ ትውልድ መገንባት ዋነኛው የልማት አካል ነው፡፡ እንበለ ጤናማ አምራች ዜጋ ዘላቂ ልማት አይታሰብም፡፡ ከዚህ አኳያ አገራችን የነበረችበትና አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን ማየት ለተሟላ ግንዛቤ ይረዳል፡፡
በኢትዮጵያ የዛሬ 26 ዓመት በፊት የነበረው የጤና ሽፋን ከ38 በመቶ በታች ነበር፡፡ ሽፋኑ በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች ብቻ የተወሰነ ስለነበር በገጠር የሚኖሩ እናቶች ለከፋ የጤና ችግር ይጋለጡ ነበር- ህጻናትና እናቶች በአቅራቢያቸው የህክምና አገልግሎት ባለማግኘታቸው የተነሳ፡፡ በዚህ ምክንያት ለህልፈተ ህይወት ይዳረጉ የነበሩ እናቶች ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት የተደረገው ጥረት ገጠርና ከተማን ሳይለይ ሁሉም ኅብረተሰብ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል፡፡ በአገሪቱ ያለው የጤና ሽፋን በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል፡፡ በከተሞች ብቻ የነበረው የጤና አገልግሎትም ወደ ገጠር ዘልቆ ገብቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጤና ጣቢያ አለያም የጤና ኬላ የሌለበት የገጠር ቀበሌ የለም፡፡
የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና የጤና ተቋማት መስፋፋት፤ የጤና አገልግሎት ከከተማው አልፎ የገጠር ቀበሌዎችን ማዳረስ፤ ወባንና ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከልና ሥርጭቱን በመግታት፤ በጤናው ዘርፍ የግል ባለሃብቶች በሰፊው እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ ባለፉት 26 ዓመታት በርካታ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በአጠቃላይ የከተማውንም ይሁን የገጠሩን ነዋሪ ህይወት ለማሻሻል በሁሉም መስኮች የተከናወኑት ተግባራት ሀገራችንን አፍሪካዊቷ “ታይገር” አሰኝቷታል። ይህም የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተላቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምን ያህል ትክክል መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። እናም ሀገራችን በዚህ ከቀጠለች ነገ ትልቅ የዕድገት ማማ ላይ ወጥታ ሌላ ስያሜ ልታገኝ የምትችልበት እድል ከፍተኛ ነው።