አልላቀቀን ያለው ስደት

ድሮ ድሮ ሀገርን ለቆ መሰደድ በባሕላችን እንደ ነውር ይቆጠራል፤ ኢትዮጵያዊያንን በውጭ ሀገራት  በስደት ማግኘትም እጅግ በጣም ብርቅ ነበር፡፡ በንጉሱ ዘመን ውስን ስደተኞች ነበሩ፡፡ ስደት የባሰውና ገዝፎ የወጣው ግን በደርግ ዘመን ነው፡፡ ፖለቲካውን በመፍራት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሱዳን፣ በኬንያ፣ በጅቡቲና የመን አድርገው ወደተለያዩ የአለም ሀገራት ተሰደዋል፡፡

ጥያቄው ከመኖርና ካለመኖር ጋር የተያያዘ ስለሆነ የስደት ሕይወትን መረጡ፡፡ ከዚያን ግዜ የጀመረው የኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለቀው የመሰደድ ጉዳይ በኢህአዴግ ዘመንም ብሶበት ጭራሹንም ከጣራ በላይ ወጣ፡፡ አልፎም ሄደ፡፡ ዛሬ በመላው አለም ከአፍሪካ አስከ ኤሽያ አውስትራሊያና አውሮፓ ድረስ መገመትና ማመን በማይቻልበት መልኩ ኢትዮጵያውያን የሌሉበት ሀገር የለም፡፡ እንደሚታወቀው አሜሪካ ሁለተኛ ሀገራቸው ናት፤ እስከ 1ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ የሚሉ ግምቶች አሉ፡፡ 

በአረቡ አለም የተለያዩ ሀገራት ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ መንገድ ገብተው እየሰሩ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ስራ ፍለጋ የሄዱ ሰርተን አግኝተን የራሳችንንና የቤተሰባችንን ሕይወት እንለውጣለን ብለው ከፊት ለፊታቸው አፍጥጦ የመጣውን ሞት ሁሉ ተጋፍጠው በማለፍ የሰው ሀገር ድንበር አልፈው ማስረጃ ሳይኖራቸው የገቡ ናቸው፡፡ በመንገድ ላይ በአውሬ ተበልተው የቀሩትን፣ በባሕር ሰምጠው የሞቱ ዜጎቻችንን ቁጥር ቤቱ ይቁጠረው ማለቱ ይቀላል፡፡

አንዱና የሕገወት ስደት ዋናው ተዋንያን በሕገወጥ የሰው ዝውውር ስራ ላይ ተሰማርተው የከበሩና የደለቡ እንደ ባርያ ንግድ ዘመን የራሳቸውን ዜጎች ለውጭ ሰው-በላ ነጋዴዎችና አዘዋዋሪዎች እየሸጡ ያሉ ሰዎች በብዛት መንሰራፋትና መደበኛ ሕይወታቸው አድርገው የመቁጠራቸው ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ሕገወጥ ስራ በዘረጉት ሕገወጥ መዋቅርና ሰንሰለት ከከተማ እስከ ገጠር ወኪሎቻቸውን በመመደብ በተለይ ወጣቱን በባዶ ተስፋ በመሸንግል ከፍተኛ ገንዘብም በመቀበል ለስደት ሲያበረታቱት፤ በብዛት አገሩን ለቆ እንዲፈልስ ሲያደርጉት ኖረዋል፡፡ ቀደም ብሎ በተወሰኑት ላይ እርምጃ ቢወሰድም ዛሬም በስውር መስራታቸውን ቀጥለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ስደተኞች ዋና አላማ የትም ሀገር ቢሆን ድንበርን በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት አልፎ በመሄድ የሚመጣውንም እስከ ሞት የሚደርስ መከራ በመቀበል ሰርቶ መኖር፣ ማግኘትና መለወጥ ነው፡፡ በተቃራኒው፣ ያለሙት ቀርቶ በተለያዩ ሀገራት ዛሬም የሰውን ሀገር ድንበር በሕገወጥ መንገድ ጥሰው በመግባታቸው ተይዘው በእስርቤት ውስጥ የሚገኙ በርካቶች ናቸው፡፡

የአረቡ አለም ደግሞ የባሰ ይሁን እንጂ በሊቢያ የሚገኙም አሉ፡፡ እንዴት አድርገው እዛ ደረሱ የሚለው በራሱ በጣም አስጨናቂ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ድንበር አልፎ እያቆራረጡ ሊቢያ መድረስ ተአምር ነው፡፡ በሌሎች ሀገራትም እንዲሁ፡፡ በአረቡ አለም ለስራ ፍለጋ በሕገወጥ መንገድ ከሀገራቸው ወጥተው የሚኖሩ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ወንዶችም ሴቶችም፡፡ አግብተው የወለዱም አሉ፡፡

በሕጋዊ መንገድ ከሀገራቸው ስላልወጡ የሚደርስባቸው ፈተናና መከራ እንግልት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ መሆኑን እራሳቸው በተለያዩ ግዜያት በሚዲያ ተናግረውታል፡፡ ሆን ተብሎ በአሰሪዎቻቸው ከፎቅ እየተወረወሩ የሞቱ፤ አካለ ጎደሎ የሆኑ፤ ሕይወታቸው በድብደባና በስለት ያለፈ እህቶችና ወንድሞች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ ዛሬም በአረቡ አለም እስርቤቶች በርካታ ኢትጵያውያን ይገኛሉ፡፡

ጥያቄው ለዚህ አሳሳቢ ለሆነ ብሔራዊ ክብርን ለሚነካ ችግር እንዴት አይነት መፍትሔ ሊገኝለት ይችላል የሚለው ነው፡፡ መንግስት በተደጋጋሚ እንደገለጸው ዜጎች ስራ ፈልገው ከሀገር ሲወጡ በሕጋዊነት መታወቂያና ፓስፖርታቸውን ይዘው ቢወጡ ለሚደርስባቸው ኢሰብአዊ ድርጊትና ክብረ ነክ ጉዳዮች መከላከል ይቻላል፡፡ መንግስት ከመንግስት ጋር ይነጋገራል፡፡ መፍትሄም ይኖረዋል፡፡ በሕጋዊነት ተመዝግበው  ካልሄዱ ግን ምን እንደደረሰባቸው፣ የት እንዳሉ፣ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ አይቻልም፡፡ ይህ ጉዳዩን አስቸጋሪና ውስብስብ ያደርገዋል፡፡

አሁንም የሚመከረው መንግስት አውቆት ሕጋዊ ሁነው ለስራ ከሀገር ቢወጡ ነው ባሉበት ደህንነታቸውን መከታተልና ማስጠበቅ የሚቻለው፡፡ በሕገወጥ መንገድ ከሀገራቸው ከወጡ በኋላ ያለው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ለማንኛውም አደጋ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ምንም አይነት የሕይወት ዋስትና የላቸውም፡፡ አልፎ ተርፎ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሴቶች እህቶቻችንን በሕገወጥ የሰው ዝውውር የተሰማሩት ሰዎች ለወሲብ ንግድ ይሸጡዋቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ከራሳቸውም አልፎ ብሔራዊ ክብርንና ማንነትነን በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ይሄን ቸግር በአንድ ግዜ ማስቀረት ባይቻልም በየደረጃው መፍትሄዎችን ማስቀመጥ ግን ይቻላል፡፡

አንዱና ዋነኛው ሰራ መሆን ያለበት ያለማሰለስ የስደትን አስከፊነት ስደተኞች የሚደርስባቸውን ግፍና በደል ጭቆና ኢሰብአዊ ድርጊት በሚዲያ አማካኝነት በሰፊው ለሕዝቡ ማሳወቅና ማስተማር ነው፡፡ ሌሎች ዜጎች እንዲጠነቀቁና አደጋውን አስቀድመው እንዲረዱ ያደርጋል፡፡ ሌላው በአሁኑ ሰአት ሀገራችን የተሻለ የስራ እድል ለዜጎችዋ መፍጠር የምትችልበት ሁኔታ ስላለ በየአካባቢያቸው በመረጡት የስራ መስክ ለመሰማራት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጸው ከመንግስት ብድር መጠየቅ፣ ማግኘትና ወደስራ መግባትም ይችላሉ፡፡

የቢሮክሲው ውጣ ውረድ እንዳይበዛ መንግስት ይሄንን በተመለከተ ራሱን የቻለ በከፍተኛ አመራር ክትትል የሚደረግበትና ፈጣን ውሳኔ የሚሰጥበት ከስደት ተመላሽ ዜጎች የገንዘብ ብድርና ቦታ አግኝተው ወደስራ የሚገቡበትን ሁኔታ የሚመራና የሚቆጣጠር አካል መፈጠር አለበት፡፡ በአብዛኛው  ችግሩ የሚፈጠረው በላይኛው አካል አይደለም፡፡ ትልቁን ማነቆና እንግልት የሚፈጥሩት በታችኛው አመራር ውስጥ የሚገኙ  አካላት ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ ግዜ በአሰልቺ መልኩ ታይቷል፡፡ አንዱ መፍትሔ ሊሆን የሚችለውም ይሄንን ማስወገድ ነው፡፡

ሌላው ከስደት በፊት ዜጎች እየተደራጁ ስራ መስራት የሚችሉበት ወይንም ስራ ራሳቸው የሚፈጥሩበትና በመንግስት የሚታገዙበት የንግድ ትስስር መረብ የሚፈጥሩበት ሁኔታ በሰፊው መጠናት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ባለፉት አመታት ከሳኡዲ አረቢያ ተመላሽ ዜጎችን በስፋት ተቀብሎ ወደስራ ሊሰማሩ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ስልጠና ተሰጥቶ ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገበት ሁኔታ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ከፊሎቹ ሌላ መንገድና ዘዴ ተጠቅመው ተመልሰው ወደስደት እንደሄዱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሀገራቸው ሁነው ውጤታማ የሆነ ስራ በመስራት ላይ የሚገኙም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የሕገወጥ ስደተኞች ችግር ዳግም አገርሽቶበት ሳኡዲ አረቢያ ማስረጃና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ሕገወጥ ስደተኞች በአስቸኳይ ተመዝግበው በ90 ቀናት ውስጥ በራሳቸው ትራንስፖርት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዋጅ አስነግራለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር የኢትዮጵያውያን እንደሚሆን ይገመታል፡፡

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ዜጎቻችን እንግልት ሳይደርስባቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ቃል አቀባዩ ለመገናኛ ብዙሀን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ሳኡዲ ድረስ በመሄድ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር የተነጋገሩ ሲሆን ከውይይቱ በኋላ ዜጎች በቀላሉ መውጫ ቪዛ እንዲያገኙ በሳዑዲ መንግስት በኩል ተንቀሳቃሽ ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ መደረጋቸውም ታውቆአል፡፡ በሪያድና በጂዳ የሚገኙ ሚሲዮኖች የጉዞ ሰነድ አሰጣጥ የተቀላጠፈ እንዲሆን፤ ሊያጋጥሙ በሚችሉ ቸግሮችም ዙሪያ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በሳዑዲ ከሚኖሩ የኮሚዩኒቲ ማሕበራትና የተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር ውይይት ተደርጎአል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ 4ሺህ ሕገ ወጥ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ ወስደው 200 የሚሆኑት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ችለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ እንደገለፁት ይህ ቁጥር መግባት ከሚገባው አሃዝ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም፣ መገናኛ ብዙሐን የአዋጁን ምንነት በማሳየት በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ለመቅረፍ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የገቡ ስደተኞች፣ ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው በመዘዋወር በሕገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ ስደተኞች፣ የስራ  የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የውጭ ሐገራት ነዋሪዎች፤ የስራ ፍቃድ ኖሯቸው የመኖሪያ ፍቃድ መታወቂያ ካርድ የሌላቸው፣ ለዑምራና ሐጂ ሄደው በዚያው የቀሩ ወይም የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ነዋሪዎች፣ ያለ ሐጂ ፍቃድ የተጓዙ አማኞች በሳዑዲ መንግስት ሕገወጥ ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አሁን አሳሳቢው የስደት ቸግር እንዴት ለዘለቄታው ይገታ የሚለው ነው፡፡ የመንግስት ድርሻ እንዳለ ሆኖ፣ በሰፊው ከሕብረተሰቡ ጋር መወያየት የመፍትሔ ሀሳቦችንም ማመንጨት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡