መንግስት ለወጣቶች በብሔራዊ ደረጃ የመደበው የ10 ቢሊዮን ብር ፈንድ ለክልሎች በቀመር ተከፋፍሎአል፡፡ ይህ የገንዘብ ምደባ የወጣቱን ብዛትና የክልሉን ስፋት ከግንዛቤ ያስገባ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ገንዘቡ በፍጥነት ለወጣቱ ተደራሽ ሆኖ ወደስራ የተገባበት ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀመረ ሲሆን የመዘግየት ሁኔታ የታየባቸውም አሉ፡፡
በሁሉም የሐገሪቱ ክልሎች በስራአጥነት ተመዝግቦ የሚገኘውን ወጣት ወደስራ ፈጥኖ ማስገባት፤ የራሱን መነሻ ካገኘ በቀጣይ ስራውን እንዲያሰፋና እንዲያሳድግ ማገዝ፤ በቸገረውና በጎደለው የባለሙያዎችን ምክርና እገዛ እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ ወጣቱን ወደ ስራ ለማሰማራት ክልሎች የየራሳቸው አካሄድና የአደረጃጀት ስልት ይኖራቸዋል፡፡ የወጣቶቻችን አዲስ ተስፋ የተሰጣቸውን ወርቃማ እድል በመጠቀም ስራን አክብረው መስራት፤ ሰርተውም መለወጥና ለራሳቸውም ለሕብረተሰቡም መጥቀም መቻል ነው፡፡
በዋናነት ከየክልሉ የተፈጥሮ ሀብትና እምቅ አቅም ጋር በተያያዘ ነው የስራ ድልድሉና ፈጠራው ሊያተኩር የሚገባው፡፡ ወጣቱ በተሠጠው ሰፊ እድል ያለውን አቅም ተጠቅሞ ለማደግና ለመለወጥ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ እንደነዚህ አይነት እድሎች መልሰውና መላልሰው የሚገኙ የሚመጡም አይደሉም፡፡
ዛሬ ከሀገራችን ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣቱ ነው፡፡ እንዲህ አይነት የገዘፈ የወጣቶች ቁጥር በሀገሪትዋ ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፤ ይህ ባልተጠበቀ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር የሚያሳይ ነው፡፡ ከድህነት ለመውጣት ሰፊ ትግል በማድረግ ላይ ባለች ሀገር ውስጥ የወጣቱ ጉልበትና እውቀት በወሳኝነት አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡
የግዴታ ይህንን ችግር ሊፈታና ሊሸከም የሚችል ኢኮኖሚም መገንባት ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌም ብንወስድ በንጉሱ ዘመን አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ኤርትራን ጨምሮ 25 ሚሊዮን ነበር፡፡ በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 50 ሚሊዮን ደርሶ ነበር ፡፡ዛሬ በኢሕአዴግ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 103 ሚሊዮን ደርሶአል፡፡ የሕዝብ ቁጥሩ ይህን በመሰለ መልኩ በስፋት ማደግና መጨመር ኢኮኖሚው ሊሸከመው ካልቻለ በስተቀር ራሱን የቻለ ችግር ነው የሚሆነው፡፡ የሕዝብ ቁጥር አደገ ማለት ኢኮኖሚው አደገ ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም የአደገውን ኢኮኖሚ ሊያቀጭጨው ይችላል፡፡
ችግሩን በመንግስት ላይ ብቻ መደፍደፉ ስራ አልፈጠረም፤ ስራ የለም ምን እንስራ ማለቱ ራሱን ችሎ የሚያመጣው መፍትሄ የለም፡፡ የስነሕዝብ ፖሊሲያችን በስፋት መጤን ይገባዋል፡፡ አሁን የምናነሳው ዛሬ ስላለው የሕዝብ እድገት መጠን ነው፡፡ በዚህ የሕዝብ ቁጥር ፈጣን እድገት ከቀጠልን ወዴት እንደርሳለን ብሎ እንደ ሀገር ማሰብም ተገቢ ነው፡፡
ኢኮኖሚስቶች አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በቀጣዮቹ አስርና ሀያ አመታት ከ200 ሚሊዮን ሊዘል እንደሚችል ይተነብያሉ፡፡ ይሄንን የሕዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶቹን አሟልቶ፤ የተወለዱ ልጆች ሳይቸገሩ፤ በስርአቱ በልተው ጠጥተው ተምረው ለስራ የሚበቁበትን፤ የጤና ዋስትና የሚያገኙበትን ሁኔታዎች የማመቻቸትና የመፈጸም ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የመንግስት ኃላፊነት ቢሆንም፤ ቁጥሩ ከፍተኛ ከሆነ ለመንግስትም ከፍተኛ ችግር ይፈጥራል፡፡
የሕዝብ ቁጥር እድገት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በስፋት እስካላደገ ድረስ ለሀገርም ለመንግስትም የሚያስከትላቸው ሰፊ ችግሮች አሉ፤ የብዙ ሀገራት ልምድና ተሞክሮም ይሄንኑ ያሳያል፡፡
በኢኮኖሚ ያደጉና የበለጸጉ ሀገራት የሕዝብ ቁጥራቸውን የመጠኑት የተንዛዛ ችግርና ድሕነት እንዳይሰፍን አስቀድመው በማስላት ነው፡፡ ልጅ እንደፈለገው ይወለድ በእድሉ ያድጋል የሚባልበት የጥንቱ ዘመን ዛሬ ላይ አይሰራም፡፡ ምን እመግበዋለሁ፤ መጠለያስ አለኝ ወይ፤ ለትምህርት ቤቱስ፤ ለልብሱ፤ ለሕክምናው ምን የተዘጋጀ ነገር አለ? ብሎ ማሰብንም ይጠይቃል፡፡ እንዲያውም በሰለጠኑትና በአደጉት ሀገራት የቤተሰብ ቁጥር እጅግ የተወሰነ ነው፡፡ መውለድ አቅቶአቸው አይደለም፡፡ በቤተሰብም ሆነ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን ጫና አስቀድመው ማጤን በመቻላቸው ነው፡፡
የሕዝብ ብዛትና ቁጥር መጨመር ብሔራዊ የኢኮኖሚ አቅምንም ይፈትናል፡፡ መንግስት ይሄን ጉዳይ በውል አላጤነውም ባይባልም፤ የቤተሰብ ምጣኔ ግን ለሀገርም ይበጃል፡፡
አንዱ የስደት ምክንያት የወጣቱ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ነው፡፡ በሀገሬ ውስጥ ሰርቼ ለመኖር እድል የለኝም የሚለው ስሜትም ከዚሁ ይመነጫል። ለሁሉም አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛውን ቁጥር ያያዘውመን፣ 70 በመቶ የሚሆነውን ወጣት ጥያቄ ለመመለስ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ለወጣቱ የተመደበው ፈንድ በኢትዮጵያ ላሉ ወጣቶች ሁሉ ይዳረሳል የሚል ተራ እሳቤ መቸውንም አይኖርም፡፡ ያለው እምነትና ግምት የስራ እድል እንዲያገኙ የተመቻቸላቸው ወጣቶች ስራ ፈጣሪ በመሆን ማንኛውንም ስራ በመስራት አዲስ የስራ እድሎችን ለዜጎች የመፍጠር ስራውን የማስፋት ስራ እንዲሰሩ ማስቻል በሂደትም አቅማቸውን እያጎለበቱ ሰፊ የስራ እድሎችን ለሌሎች ዜጎች እንዲፈጥሩ ማብቃት ነው፡፡
ደጋግመን እንዳልነው፣ ወጣቱ በቀድሞ ዘመናት የነበረውን ከመንግስት ብቻ ስራ የመጠበቅ አስተሳሰብን ከአእምሮው ማውጣት አለበት፡፡ በነጻ ኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ ብዙ ስራዎችና የስራ እድሎች የሚጠበቁት በኢኮኖሚው ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ ካላቸው የግል ባለሀብቶች ነው፡፡ የመንግስት ተሳትፎ በብዙ መልኩ ውስን ነው፡፡ ስራን መፍጠርም ሆነ ማስፋፋት የግል ባለሀብቶችና የኢንተርፕሬነሮች ድርሻ ስለሆነ ወጣቱ የራሱን ስራ የሚፈጥርበትን ስራን አክብሮ ሳይንቅ ማንኛውንም ስራ የሚሰራበትን ሁኔታ መፍጠርና ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡
በሀገራችን አሁን መንግስት ለመነሻ የመደበውን የወጣቶች ፈንድ ብንወስድ ገንዘቡ ወጣቱ በስራው ስኬታማና ውጤታማ እየሆነ ሲመጣ ወደ መንግስት ካዝና የሚመልሰው የሕዝብና የመንግስት ገንዘብ መሆኑን ማጤን ይገባዋል፡፡ ስራ ሰርተው እራሳቸውን እንዲችሉበት ከስራ አጥነት እንዲወጡ የስራ ባለቤት እንዲሆኑ ሰርተውም እንዲመልሱ በብድር መልኩ የተሰጠ እንጂ ስጦታ አይደለም፡፡ ይሄንን ገንዘብ ሰርቶ ለመመለስ ብዙ መልፋትና መስራት ከወጣቱ ይጠበቃል፡፡
የየክልሎቹ የተፈጥሮ አቅም ወጣቱን ብዙ ስራ ሊያሰራው የሚችል ነው፡፡ በግብርናው፤ በከብት እርባታ፤ በንብ ማነብ፤ በከብት ማድለብ፣ በወተት ተዋጽኦ ሽያጭ፣ ለተለያዩ ካምፓኒዎች ወኪል አከፋፋይ በመሆን፣ በማእድን ዘርፍ፣ መዋእለ ሕጻናትና መለስተኛ ትምሕርት ቤቶችን በመክፈት፣ በአሳ እርባታ፣ መዝናኛ ስፋራዎችን ተቀናጅተው በመክፈት፣ ለወጣቱ የሚሆኑ ፊልም ቤቶችን፣ ቤተመጻህፍት ቤቶችን፣ መጻሕፍት ሽያጭን፣ የእንጨት ስራዎችን፣ የብረት ብየዳ ስራዎችን፣ ሽክላዎችና ጡቦችን በማምረት፣ አሸዋና ሲሚንቶ በማከፋፈል፣ በአነስተኛና መካከለኛ ምግብ ቤቶች ስራ ወዘተ ወዘተ ተዘርዝረው የማያልቁ ሰፊ ስራዎች በሀገራችን ውስጥ አሉ፡፡
ወጣቶች የመንግስት ስራተኛ ከመሆን በበለጠ ለግላቸው እየሰሩ ማደግ መበልጸግ የሚችሉበት ሰፊ እድል አላቸው፡፡ ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀምም አለባቸው፡፡ ቀደም ባሉ አመታት በሀገራችን ወጣቱን የስራ ባለቤት ለማድረግ በአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት በማደራጀት ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ውጤታማ የሆኑ አልፈውም ሰፊ የስራ መስክ ለወገኖቻቸው የከፈቱ ደረጃቸውም ከፍ ብሎ ኢንተርፕሬነር ለመሆን የበቁ አሉ፡፡
ልምድና ተሞክሮው ወጣቱ በመንግስት ከታገዘና ከተደገፈ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ያስተማረ በተግባር ያሳየ ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ነው ስፋት ባለው ደረጃ በመላው ሀገሪቱ ወጣቱን ያማከለና ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ ለመስራት ፈንድ ተመድቦ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ያለው፡፡ በሀገራችን ለረዥም ዘመን የተለመደው መንግስት ቤት ተቀጥሮ መስራት ጡረታ ሲወጡም መውጣት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በአብዛኛው የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡ ዛሬ ይህ ሁኔታ ከመሰረቱ ተለውጦአል፡፡
ሀገሪቱ ከምትከተለው የነጻ ገበያ ስርአት አንጻር የሚበረታታው የራስን ስራ መፍጠር ማስፋት በዚህም ራስንና ህብረተሰቡን ሀገርንም ተጠቃሚ ማድረግ መቻል ነው፡፡ ያደጉና የበለጸጉ ሀገራትን ወደላቀ የኢኮኖሚ እድገት ማማ እንዲወጡ ታላቁን አስተዋጽኦ ያደረጉት ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቱ የትኩስ ጉልበትና በፈጠራ ችሎታ የተሞላ አእምሮ ባለቤት በመሆኑ በሀገር ኢኮኖሚያው እድገት ውስጥ የላቀ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በጥናትና ምርምሩ በአዳዲስ ስራ ፈጠራዎችና ግኝቶች በግንባታውና በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በዘመናዊ ግብርናው በከተሞች ግንባታና በመሳሰለው ዘርፍ ወጣቱ ወሳኝ የስራ ኃይል ነው፡፡
ወጣቱን ያላሳተፈና ያላቀፈ የሕብረተሰብ እድገትና ለውጥ መቼም አይኖርም፡፡ ይሄንን በውል በመገንዘብ ነው ለወጣቱ የተለየ ትኩረት የተሰጠው፡፡ እድሉን አስፍቶ በሚበጀው መልኩ መጠቀም የሚጠበቀው ከወጣቱ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች የተዘዋዋሪው የወጣቶች ፈንድ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቆአል፡፡
በከተሞች በሕገወጥ መንገድ የታየዙ ሼዶች፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች ላይ ማጣራት ማድረግ የተጀመረ ሲሆን እስካሁን በተደረገ ክትትል 824 ሼዶች በሕገ ወጥ መንገድ መያዛቸዉ ስለተረጋገጠ ሼዶቹን ተመላሽ በማድረግ ከ429 በላይ ሼዶች በሕዝብ ፊት ለስራ አጥ የገጠር እና የከተማ ወጣቶች በእጣ እንዲተላለፉ ተደርገዋል፡፡ 395 ሼዶች ደግሞ ለወጣቶች በመተላለፍ ሂደት ላይ መሆናቸው ተገልጾአል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የማዕድን ቦታዎችን በተመለከተ ያለአግባብ የተያዙ 14ሺ 301 ነጥብ 3 ሔክታር የማዕድን ማዉጫ ቦታዎችን ከሕገ ወጦች በማስመለስ ለወጣቶች የማስተላለፍ ስራ ተስርቷል፡፡ በማዕድን ዘርፍ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ በ1978 ማሕበራት ለተደራጁ 44ሺ 869 ለሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸው አበረታች እርምጃ ነው፡፡
ለወጣቶቹ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር አስተማማኝና ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር በክልሉ ከሚገኙ ትላልቅ የሲሚንቶ አምራች ኩባንያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚህም መሰረት ደርባ ሜድሮክ እና ዳንጎቴ ከተደራጁ ወጣቶች የሲሚንቶ ግብአት ማዕድናትን ለመግዛት ቀደም ሲል ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ኢስት ሲሜንት፣ ናሽናል ሲሜንት እና ሙገር በቅርቡ ከወጣቶቹ ጋር ውል እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፡፡ በዚህ መልኩ ወጣቱን የስራ እድል ባለቤት ለማድረግ የሚሰራው የተቀናጀ ስራ በሌሎችም ክልሎች በምሳሌነቱ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡