የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ተራማጅ ነው። ይህ ተራማጅ ህገ መንግስት የዜጎችን ሰብዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከመደንገግ ባለፈ፤ የዜጎችን መሰረታዊ ጥቅሞች በማስከበር ረገድ ወደር የማይገኝለት ነው። በዚህ ህገ መንግስት የሀገራችን ዜጎች የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመቃወም፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመፃፍ…ወዘተ. ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተረጋግጧል። በተግባርም ላለፉት 22 ህገ መንግስታዊ ዓመታት እንዲከናወኑ ተደርጓል። ማንኛውም ዜጋ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቃወም የሚችልበትን አሰራር በመዘርጋትም ተራማጅነቱን ያረጋገጠ ሞዴል ህገ መንግስት ነው።
በዚህ ህገ መንግስት መሰረት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኃይማኖቶችን ተገን ያደረጉና ከእምነቶቹ መርህ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በቀሰቀሷቸው ግጭቶች ምክንያት የወደሙ የኃይማኖት ተቋማትን በጋራ ገንብተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ የኃይማኖቶች የመቻቻል፣የመከባበርና የመደጋገፍ ተምሣሌት ተደርጋ የምትወሰድ ሀገር ነች፡፡
በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከተደነገጉ የሕዝቦች መብቶች አንዱ የኃይማኖት እኩልነት ነው፡፡ መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን፤ ሁሉም ሰዎች በመካከላቸው የዘር፣ የብሔር፣ የብሔረሰብ፣ የጾታ፣ የኃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው፣ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊናና የኃይማኖት ነጻነት፣ የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት ለብቻው ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን የማምለክ፣ የማስተማርና የመግለጽ መብት እንዳለው ህገ መንግሥቱ ደንግጓል፡፡
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ለእነዚህ ድንጋጌዎች ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው የኃይማኖቶች እኩልነትና የእምነት ነጻነት ሳይረጋገጥ ያለፈውን የተዛባ ግንኙነት ማስተካከል አይቻልም ከሚል መሠረታዊ አስተሳሰብ በመነሳት ነው፡፡ አዲስ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የመገንባት ጉዳይም ከእነዚህ መብቶች ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነውና፡፡ ሌላው ነጥብ ለሕዝብ የሚገደብ መብት መኖር የለበትም የሚል መሠረታዊ እምነት ስላለ ጭምር ነው፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ ብዝኃነት አገሪቱ በዓለም ያላትን ገፅታ ቀይሯል፡፡ አንዳንዶች በብሔርና በጎሣ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ቢገልፁም የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ የሚያሳየው ግን የተለየውን ሆኗል፡፡
ብዝኃነትን ዕድል ማድረግ የሚቻለው ማንነቶች የሀገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ አሳይቷል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ሠላም የሰፈነባት የተረጋጋች ሀገር መሆኗን ብዙዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በብዝኃነት የተመሠረተ አንድነት ተከታታይና ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የብዝኃነት አያያዝ ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ምርጥ ትምህርት የሚሰጥ ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ ከላይ የጠቃቀስናቸው ሁሉም ስኬቶች ሊመዘገቡ የቻሉት ባለፉት መንግሥታት ዘመን ማንነቶች ያነሷቸው የነበሩት መብቶች በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መልስ በማግኘታቸውና በተግባር ተፈፃሚ በመሆናቸው ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት መጠናከር ወሣኝ ፋይዳ ያለው ጉዳይ በሥርዓቱ መሠረታዊ አስተሳሰቦች፣ መርሆዎችና አፈፃፀማቸው ላይ የተሟላ ግንዛቤ መኖር ነው፡፡ በማንነቶች መካከል የተፈጠረውን የመከባበርና የመደጋገፍ ባህል ጥልቀት እንዲኖረው፣ የሚጋሯቸውን እሴቶች ማድመቅና አዲሱ የኢትዮጵያዊነት ማንነት እየተጠናከረ እንዲሄድ ማድረግ ይጠይቃል፡፡
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችና የመንግሥት ሥልጣን ምንጮች መሆናቸው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጐ ይገኛል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የኃይማኖትና መንግሥትን መለያየት መርህ በማስቀመጥ መንግሥት ለሁሉም እምነቶች እኩል የማገልገል ግዴታን ጥሎበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት የመከተል መብቱ የተረጋገጠ መሆኑም እንዲሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት መጠናከር ወሣኝ ፋይዳ ያለው ጉዳይ በሥርዓቱ መሠረታዊ አስተሳሰቦች፣ መርሆዎችና አፈፃፀማቸው ላይ የተሟላ ግንዛቤ መኖር ነው፡፡ በማንነቶች መካከል የተፈጠረውን የመከባበርና የመደጋገፍ ባህል ጥልቀት እንዲኖረው፣ የሚጋሯቸውን እሴቶች ማድመቅና አዲሱ የኢትዮጵያዊነት ማንነት እየተጠናከረ እንዲሄድ ማድረግ ይጠይቃል፡፡
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችና የመንግሥት ሥልጣን ምንጮች መሆናቸው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጐ ይገኛል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የኃይማኖትና መንግሥትን መለያየት መርህ በማስቀመጥ መንግሥት ለሁሉም እምነቶች እኩል የማገልገል ግዴታን ጥሎበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት የመከተል መብቱ የተረጋገጠ መሆኑም እንዲሁ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠለ መብታቸው መጠበቁን፣ እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንድ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት የተረጋገጠለት መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ከዚህም ጋር ሴቶች በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ መስኮች ከወንዶች ጋር እኩል መሆናቸውንና ከዚህ በፊት በነበረው ልዩነት ምክንያት የተፈጠረባቸውን ጫና ለመቅረፍ ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተደንግጓል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መሬት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት መሆኑን ደንግጓል፡፡
እነዚህ ማንነቶች ራሳቸውን የማልማትና በማያቋርጥ ሁኔታ ኑሯቸውን የማሻሻል መብት እንዳላቸው እንዲሁም አባል የሆኑበትን ማኅበረሰብ በሚመለከቱ የመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ሀሳብ የመስጠት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ እንዲሁም አናሣ ብሔረሰቦች ያለምርጫ በልዩ ሁኔታ የሚወከሉበት ከሃያ የማያንስ መቀመጫዎች በተወካዮች ምክር ቤት እንዲኖራቸው መደንገጉ ድምፃቸው ከፍ ብሎ እንዲሰማ ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ከኃይማኖትና እምነት ጋር በተያያዘ የሕዝብን ደህንነት፣ ሰላም፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የሞራል ሁኔታ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች እና የመንግሥትና ኃይማኖት መለያየት ለማስጠበቅ በሚወጡ ሕጎች ኃይማኖትና እምነትን የመግለፅ መብት እንደሚገደብ ነው፡፡ እንዲሁም ትምህርት ከኃይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከትና ከባህላዊ ተፅዕኖዎች ነፃ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ኃይማኖቶች ለሠላም፣ ለጤና፣ ለትምህርትና ለሌሎች ደሞክራሲያዊ መብቶች አደጋ እንደማይሆኑ ይታወቃል።
እነዚህ ድንጋጌዎች ተፈላጊ የሆኑበት ምክንያት ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የእምነት ነፃነትና እኩልነት የሚፃረሩ እንቅስቃሴዎች ስለሚታዩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የእምነት ነፃነትና የኃይማኖት እኩልነት የሚፃረር እንቅስቃሴ በቀጥታ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ስለሚፃረር ነው፡፡ ይህ ፀረ ዴሞክራሲ እንቅስቃሴ ለሕዝብ የሚገደብ መብት አይኖርም የሚለውን የሕዝብ ልዕልና መሠረታዊ አስተሳሰብ ስለሚፃረር ጭምር ነው፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች የምንገነዘባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡
አንደኛው የሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር ማንነቶችን መሠረት ያደረገ መሆኑን ነው፡፡ እያንዳንዱ ማንነት የራስ አስተዳደርን የመመሥረት መብት ተጎናፅፏል፡፡ የማንነት መገለጫ የሆኑት ሁሉም ቋንቋዎች እኩል እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ከሌሎች በርካታ ፌዴሬሽኖች የሚለየው ጉዳይ አወቃቀሩ በማንነቶች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ማንነቶችን የሚመለከቱ መብቶች ከጅምሩ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዲያገኙ ማስቻሉ ነው፡፡ ማስቻል ብቻ ሳይሆን በሁሉም አካባቢዎች ዕውን እየሆነ ነው።
እርግጥ በአሁኑ ወቅት የህገ-መንግስቱ መርሆዎች በተጨባጭ እየተተገበሩ ለመሆናቸው ከላይ የጠቀስኳቸው አንኳር ጉዳዩች ማሳያዎች ናቸው። እናም ዛሬም ከ22 ህገ መንግስታዊ ዓመታት በኋላ፤ የህገ መንግስቱን ቱሩፋቶቹን እያጣጣመ ያለው የሀገራችን ህዝብ ለህገ-መንግስቱ ገቢራዊነት ይበልጥ መትጋት ይኖርበታል። በዚህ ተራማጅ ህገ መንግስት ተመርቶ ያገኘውን ለውጥ ከእርሱ በላይ የሚገነዘብ ባለመኖሩም፤ ይህን ተራማጅ ህገ መንግስት እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል እላለሁ።